Sunday, 10 May 2015 15:36

የፋሺስት ኢጣልያ ግፍ በአዲስ አበባ

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(6 votes)

ያ ሁሉ ግፍ ለምን?

   ከሠባ ሥምንት ዓመታት በፊት፤ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በቅዱሥ ሚካኤል በዕለተ ቀኑ ረፋድ ላይ የኢጣሊያዊቷን ልዕልት ልደት ምክንያት በማድረግ፤ የአዲስ አበባና የአካባቢው የፋሺስት ኢጣሊያ ገዢ ጄኔራል ግራዚያኒ፡- መኖሪያና መብል የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ምንዱባን በቤተ መንግሥት ሠብሥቦ እየመገበ ሣለ ነው ድንገት በተከታታይ ሠባት ቦንቦች ወደ ጄኔራል ግራዚያኒ የተወረወሩት፡፡ ግራዚያኒ ጠረጴዛ ሥር ገባ፡፡ በአካባቢው ከባድ ድንጋጤ ሠፈነ፡፡ ለተወሰኑ ቅፅበቶች አካባቢው በጭሥ ታፈነ፡፡
ቦንቦቹን የወረወሩት፡- ይሄንን ግዳጅ ለመወጣት ለበርካታ ቀናት ምሥጢራዊ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩት፤ በትውልድ ኤርትራዊ መሠረት ያላቸው በነፍሥና በመንፈሣቸው ልባቸው በኢትዮጵያዊነት የአገር ፍቅር የተሞላና የነደደ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አብርሃም ደቦጭ እና ሞገሥ አሥገዶም ናቸው፡፡ አብርሃም ደቦጭና ሞገሥ አሥገዶም ቦንቦቹን ከወረወሩ በኋላ በፍጥነት ከአዲስ አበባ ከተማ በመውጣት ወደ ሠሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ማምለጣቸውን ጳውሎስ ኞኞ፡- “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በተሰኘ መጽሐፉ ላይ ፅፎአል፡፡ በጣም የሚያሣዝነው፡- በመጨረሻ አብርሃም ደቦጭና ሞገሥ አሥገዶም ጐጃም ውስጥ መገደላቸውን ጳውሎስ ኞኞ በመፅሐፉ ላይ ጨምሮ ፅፎልናል፡፡
በእብሪት ያበጠውና በቦንብ ፍንጣሪ የቆሠለው ጄኔራል ግራዚያኒ፤ በቁጣ ነድዶ ለወታደሮቹ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሁሉ በጥይት ቁሉት አላቸው፡፡ “ፍጁት!...ያገኘኸውን ሁሉ ግደል!”
የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች፡- የጠመንጃ ቃታ የሣቡበት ጣታቸው እስኪዝል ድረስ በመላው አዲስ አበባ ዳር እስከ ዳር ተኩስ በመክፈት ያልታጠቀውን የከተማዋን ነዋሪ ህፃን ሽማግሌ፤ ነፍሰ ጡር አሮጊት ሣይሉ ኢትዮጵያዊ የሆነውን የአገሬውን ሰው ሁሉ በጅምላ በጥይት የቆሉት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ጠመንጃ ያልታጠቁት የፋሺስት ወታደሮች በቆንጨራ፣ በገጀራ፣ በአካፋ፣ በመጥረቢያ ከፊታቸው ያዩትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጭካኔ ጨፈጨፉት፡፡ በወቅቱ ብዙዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች የሣርና የገለባ (የምርቅ) ክፍክፋት ደረባ ጣሪያ ያላቸው ጐጆ ቤቶች በመሆናቸው ጣሊያኖች ከእልቂት ከፍጅቱ ሸሽቶ ወደቤቱ በሚገባው ኢትዮጵያዊ ላይ ሁሉ እሣት ለቀቁበት፡፡ በውስጣቸው የተሸሸጉ ኢትዮጵያውያን የሞሉባቸውን ጐጆ ቤቶች ሁሉ በእሣት አነደዷቸው፡፡ ከሚነድደው ጐጆ ውስጥ ወጥቶ ለማምለጥ የሚሞክረውን በጥይት ለቀሙት፡፡
አዲስ አበባ በነዋሪዎቿ ኢትዮጵያውያን የደም ጐርፍ ተጥለቀለቀች፡፡ በእሣት ላንቃ ተላፈች፡፡ በአዲስ አበባ ሠማይ ሥር ሞትና ጭስ ሠፈኑ፡፡ የሞት ጥላ በአዲስ አበባ አናት ላይ ተደፋ፡፡ ፍጅትና እልቂቱ፤ ጭፍጨፋና ቃጠሎው ረፋድ ላይ የጀመረ ሌሊቱን ሙሉ ዘለቀ። ጄኔራል ግራዚያኒ በተከፈተ መስኮት ለማየት የሚችለውንና የሚደረገውን የህዝብ የጅምላ ግድያና የኢትዮጵያዊ ትውልድ እልቂት እያየ ከት ብሎ ይስቃል፡፡
ለኢትዮጵያውያን በጣም አስጨናቂ የሆነው የሞት፣ የፍጅትና የእልቂት ጊዜ… ረዘመ እንጂ ከቶውንም ሊያጥር አልቻለም፡፡ ጅምላ ግድያውና ጭፍጨፋው ቃጠሎውና ሠቆቃው የካቲት አሥራ ሁለት የጀመረ ከሶስት እስከ አሥር ለሚደርሱ ተከታታይና ተጨማሪ ቀናት መቀጠሉን የታሪክ ተመራማሪና ተርጓሚ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በተለያዩ ጥናታዊ መፃሕፍቱ ላይ ጽፎአል፡፡ እንዲሁም ሌሎች ገናና ኢትዮጵያውያን የታሪክ ተመራማሪዎች፤ እና ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የውጪ አገር የታሪክ ምሁራን በተለያዩ መጽሐፎቻቸው ላይ በታሪክ ውስጥ የሞት ምዕራፍ፤ የሞት ፋይል ሊሠኝ የሚችለውን ይሄን ክንውን አሣምረው ጽፈውታል፡፡
ማናቸውም የበዛና የከበደ ሀዘን ልብን ይሠብራል፡፡ ነፃነት የሌለበት፤ ብሔራዊ ክብርና ልዕልና የተደፈረበት፤ ሠብአዊ ፀጋ ተፈጥሮአዊ ውበትና በጐነት የተዋረደበት፤ የበዛና የከበደ ሀዘን ደግሞ የበለጠ ይሠብራል ልንል ከምንችለው በላይ ብዙ ርቀት ይሄዳል፡፡
ሁሉም ባገር ነው፡- ሲሉ፤ በነፃነት ለማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር የሚያምረው በነፃነት ክብር በምትኖርባት የትውልድ አገርህ ላይ ነው ለማለት፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች ከሠላሣ ሺህ እስከ ሠማንያ ሺህ የሚደርሱ ያልታጠቁ ንፁህ ኢትዮጵያውያንን በግፍ በገፍ ፈጁ፤ ገደሉ፡፡ አዲስ አበባን በእሣት አቃጠሉ፤ አወደሙ፡፡ በወቅቱ በ1879 ዓ.ም መቆርቆር የጀመረችውና ከተመሠረተች ሃምሣ ዓመት የሆናት የአገራችን ርዕሠ መዲና አዲስ አበባ፤ በጅምላ እልቂትና ፍጅት በበረታ ከባድ የሀዘን መንፈስ ጣዕርና ጭንቅ በሞላበት የሞት ላንቃ በንፁሀን የደም ጐርፍና የደም ጩኸት ክፉኛ ተመታች። ሰሚ የሌለው ያልታጠቁ ንፁህ ኢትዮጵያውያን የደም ጩኸት ወይንም የንፁሀን የደም ጐርፍ ጩኸት!...
የጣሊያን ዜግነት የሌላቸው፤ የፋሺስት ኢጣሊያ የተለያዩ የቅኝ ግዛት አገር ወታደሮች፡- ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ካራባኔሪ ይባላሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የቅኝ ግዛት አገር ኤርትራ ተወላጆች የሆኑ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ካራባኔሪዎች አሉ፡፡ የጄኔራል ግራዚያኒ በቁጣ የነደደ ትዕዛዝ እንደተላለፈ፡- እነዚህ ባለጥቁር ሸሚዝ ካራባኔሪ የኤርትራ ተወላጆች፣ የጦር መሣሪያ ባልታጠቁ ንፁሀን ዜጐች ላይ አንተኩስም አሻፈረኝ በማለታቸው፤ የጣሊያን ዜግነት ባላቸው የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች እንዲረሸኑ ተደረገ፡፡ ትጥቃቸውን ፈትተው መደዳውን ሆነው በጠመንጃ አረር ተረሸኑ፡፡ በዚህ ውሣኔያቸው ጀግናም ሠማዕትም ናቸው። ባልታጠቁ ንፁሃን ሰዎች ላይ አንተኩስም በማለታቸው ጀግኖች ሲሆኑ፤ በዚህ ውሣኔያቸው ምክንያት በመረሸን በመገደላቸው ደግሞ ሠማዕት ናቸው፡፡
ይህ የፋሺስት ኢጣሊያ አረመኔነት የተመላበት አሠቃቂ የገፍና የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ሀዘንና ለበዛ ሰብአዊና ቁሣዊ ጉዳት መዳረግ ብቻ ሣይሆን፤ የኢትዮጵያውያንን የኢትዮጵያዊነትና የፍትሀዊነት፣ የአገር ፍቅርና የነፃነት መንፈስ እጅጉን አስቆጣ፡፡ ዱር ቤቴ ላለው አርበኛም ሆነ በዱር በገደሉ ላልከተተው ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ነፃነት የመጋደልና የመዋደቅ ብርቱ ጉልበት ሠጠ፡፡
አገራችንን በግፍ የወረሩ የፋሺስት ኢጣሊያ ኃይሎች ከእልቂትና ከፍጅት የተረፈውን ኢትዮጵያዊ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሣይሆን ከመላው ኢትዮጵያ አካባቢዎች እያደኑ በተለያዩ እፍግፍግ ያሉ እሥር ቤቶች ውስጥ አጐሩት፡፡
ጥቂት ቆይተው ኢትዮጵያውያኑን ከተጨናነቁበትና ከተፋፈጉበት እሥር ቤቶች እያወጡ ወደ ኢጣሊያ አዚናራ፣ ወደ ቀይ ባህር ናኩራ ደሴቶች፣ ሶማሊያ ደናኔ የግዞት እሥር ቤቶች አጋዙዋቸው፡፡ ወደ ሶማሊያ ደናኔ እና ወደ ቀይ ባህር ናኩራ የግዞት እሥር ቤቶች የተጋዙት ኢትዮጵያውያን ግዞተኞች የተጫኑት በካሚዮኖች ሲሆን፤ በሚፈፀምባቸው ጭካኔ የተመላበት አስከፊ ግፍ ምክንያት በጉዞ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ያለፈው ጥቂት አይደሉም፡፡ በግዞት እሥር ቤቶቹም ሠውነታቸውን በምላጭ እስከመተልተል የሚደርስ ጭካኔ የተመላበት ኢሠብአዊ ድርጊትና ተፈጥሮአዊ ጥፋት ተፈጽሞባቸዋል።
*   *   *
ግን ለምን?  
ከሠባ ስምንት ዓመታት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የጦር መሣሪያ ያልታጠቁ ንፁሀን ኢትዮጵያውያንን እንዲያ በገፍና በግፍ የፈጁ የጨፈጨፉት ለምንድነው? ይሄ ሁሉ ጭካኔና ግፍ ለምን አስፈለገ? ይሄ መጠነ ሠፊ የትውልድ እልቂት እንዲፈፀም በቁጣ የነደደ ትዕዛዝ ላስተላለፈው ጄኔራል ግራዚያኒ መታሠቢያ ሀውልት እንዲሠራ የሚል ሃሳብ የሚመነጨው እንደምን ካለ ህሊና ነው? እንደምን ካለ አእምሮ?
*   *   *
በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ ይህ እስከዚህ የተወሳው በገፍ የተፈፀመ ግፍ ግድያ፣ ፍጅትና እልቂት ከተከወነ ሰባ ስምንት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት በተደረገ ፀረ ፋሺስት ተጋድሎ በመጨረሻ ፋሺስት ኢጣሊያን እኛ አሸንፈን፤ ከመላው ኢትዮጵያ ምድረ ገጽ ረግጠንና ጠራርገን በማስወጣት ባለፈው ማክሰኞ ሠባ አራተኛ ዓመቱን የድል ቀኑን ባከበርነው ዕለት፤ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የድል ሠንደቃችን ከተጣለበት አንስተን፣ በክብር በማውለብለብ የኢትዮጵያን ድልና ነፃነት ለዓለም ሁሉ አውጀናል፡፡
ለጀግኖች አባቶቻችን፣ ለጀግኖች ወላጆቻችንና ለእኒያ ሠማዕታት ክብር ይሁን! የጀግኖች ሠማዕታትን የመስዋዕትነት ፍሬዎችንና የአባቶቻችን ርስት አንሰጥም፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
ሠላምዎ ይብዛ በፍቅር!
Soli Deo Gloria!

Read 2686 times