Sunday, 10 May 2015 15:34

አስገራሚው የተፈጥሮ ዋሻ

Written by  ፕርስፎራ ዘዋሸራ
Rate this item
(11 votes)

 የሀገራችን ልዩ ልዩ ቅርሶችና የታሪክ ማስረጃዎች ዋሻ ውስጥ ጭምር መገኘታቸው እሙን ነው። ከዚህም ባሻገር ዋሻዎች የቤተክርስቲያን መልክ እንዲይዙ ተደርገውና ተፈልፍለው በመቅደስነት፣ በቅድስትነትና በቅኔ ማህሌትነት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ርእሰ ጉዳይ መሠረት አድርጌ ላስነብባችሁ የፈለግሁትም የታላቁ ገዳም የዲማ ጊዮርጊስ ጽላተ ሕግ ስለሚኖርበት የተፈጥሮ ዋሻ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሚያዚያ 23 ቀን በየዓመቱ የዓለም ወዝ አደሮች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት ዕለት ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በአለበት ሁሉ ዓመታዊ የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጉስ በዓለ ንግሥ በምዕመናን ዘንድ ታስቦ እንደሚውል የታወቀ ነውና እኔም ወደ ታላቁ ገዳም ዲማ ጊዮርጊስ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ውቃቢ የሸሻቸው፣ ሰይጣን ያበላሻቸውና በእስልምና እምነት ሽፋን የሚንቀሳቀሱት እስማኤላውያንና አማሌቃውያን የአይኤስ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በቅርቡ የንጹሐን ኢትዮጵያውያንን አንገት ቀልተው እንደፈጇቸው ሁሉ የቀድሞ የግብር አባታቸው የፋርሱ ንጉሥ ዱድያኖስም ነውርና ኃጢአት የሌለበትን የቅዱስ ጊዮርጊስን አንገት በሰይፍ ቀልቶ የገደለው በሚያዚያ ወር ላይ ስለሆነ ድርጊቱ የኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያመሳስል ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የክብር አክሊል ይጠብቃቸዋል፡፡
የልዳው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚከበሩት ሰማዕታት አንዱ በመሆኑ ዘንድሮም ዲማ ውስጥ በዓለ ንግሡ ሲከበር ልዩ ድምቀት ነበረው፡፡ የዲማ ጊዮርጊስ ሥርዓተ ማህሌት ጥንታዊ ወጉንና ከብሩን የጠበቀ ነው፡፡ ወረቡ ድፋቱ፣ አብቸቦው፣ የከበሮ መረግዱና ዝማሜው ልብ ይመስጣል። በዋዜማው ላይ የሚወርደው ቅኔ ምሥጢር ያማልላል። ስለቤተክርስቲያኑ ውስጣዊ ውበት፣ በባህላዊ መንገድ ስለተሣሉት ሥዕላት፣ ወጥ ስለሆኑት ረጃጅም የእንጨት በሮች፣ መቃኖችና መስኮቶች፤ ስለነጋሪቶች፣ ከበሮዎች፣ እምቢልታዎች፣ በቅዳሴ ጊዜ ካህናትና ዲያቆናት ስለሚያደርጓቸው ወርቅና የብር አክሊሎች በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል፡፡ የቀድሞ ነገሥታት ያበረከቷቸው ዘውዶች፣ የወርቅ ጫማዎች፣ ልዩ ልዩ አልባሳት በገዳሙ ይገኛሉ። የቀድሞው ንጉሥ ከነባለቤታቸው፣ ያበረከቱት የሥጋጃ ስዕልም በቅርስነት ተቀምጧል፡፡ የጻድቃንና ሰማዕታት ተጋድሎ በየሥዕላቱ ሥር በአጫጭር የግዕዝ ቋንቋ ተጽፎ ይታያል፡፡ እያንዳንዱ ሥዕል የራሱ የሆነ መግለጫ አለው፡፡ ጣራው ላይ ያለው የመላእክት ሥዕል ታይቶ አይጠገብም፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ረጅም ጣሪያ ላይ መላእክቱ ተስለው ቁልቁል ሲመለከቷቸው በቅጽበት ወደ መሬት የሚወርዱ ይመስላሉ፡፡ ይህንኑ ያስተዋለ አንድ ደብር ወርቅ ደብተራ በመላእክቱ ሥዕል አዝኖ ዲማዎችን በራሳቸው ቅኔ ማህሌት ቆሞ በቅኔ እንዲህ ብሎ ሰደባቸው ይባላል፡-
“እም አይሁድ አይሁደ
እመ ይትሌዓሉ
“መላእክት በሰማይ ሰቀሉ፡፡ ዲሞች ከአይሁድ ይልቅ አይሁዶች ስለሆኑ መላእክትን በጠፈር ላይ ሰቀሉዋቸው። አይሁድ ግን ክርስቶስን የሰቀሉት በመሬት ላይ ነው፡፡” እንደማለት ነው፡፡  ገዳሙም የሴትና የወንድ ተብሎ በሚገባ የተደራጀ ነው። የንባብ ቤቱ፣ ዜማ ቤቱ፣ የቅኔና የሐዲሳት ማስመስከሪያ እንዲሁ በወግ በወጉ ተደራጅቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ገዳሙ ዘመናዊ ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የገዳሙ መስራች ሾዔው አባ ተክለ አልፋ ናቸው፡፡ ክብረበዓላቸው ታህሳሥ 8 ይታሰባል፡፡
በገዳሙ ውስጥ የበርካታ ጻድቃንና ሰማዕታት ስሞች የተቀረጸባቸው ታቦታት ሲኖሩ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላተ ክብር ግን በአስገራሚው የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ መኖሩ አስደናቂ ነው፡፡
የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦተ ሕግ በዚያ አስፈሪና ግርማዊ በሆነ የተፈጥሮ ዋሻ ውስጥ ከመቼ አንስቶ መኖር እንደጀመረ ያስረዳኝ ባይኖርም ዋሻውን ከዲማ ጊዮርጊስ በስተግራ በኩል በግምት 1 ኪ.ሜ ከተጓዙ በኋላ ጸበሉ በአለበት የገደል አፋፍ ላይ ሆኖ ማየት ይቻላል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላተ ክብር የሚኖርበት ዋሻ በዲማና በግርኛ ማርያም ቤተክርስቲያናት መካከል በሁለተኛው የገደል እርከን ስር ይገኛል፡፡ ታቦቱ ከዋሻው ውስጥ ከመውጣቱ በፊት በእምብርክክ የሚያስኬደውን መንገድ ቁልቁል መውረድና ሽቅብ መውጣት ይጠይቃል። አባ ተከስተብርሃን የተባሉ አባት ታሪክም በገዳሙ ውስጥ በሰፊው ይተረካል። አባ ከሰተብርሃን በዲማ ጊዮርጊስ ገዳም የኖሩና የትሩፋት ሥራ ሰርተው ያለፉ የበቁ አባት ናቸው፡፡ እኒህ አባት ፆም በቀኖና በብህትውና በዋሻው ውስጥ ሲኖሩ ከትውልድ ቦታቸው አንዲት አህያ የሽንብራ ስንቃቸውን ጭና አድርሳላቸው ወደ አገሯ ትመለስ ነበር ይባላል፡፡ የትሩፋት ሥራ በመሥራት ላይ እንዳሉ ሥራቸውን ሳይጨርሱ፣ ፀሐይ ከምዕራብ የመግቢያ መስኮትዋ ላይ ደረሰች፡፡ በዚያ ወቅት “ሥራየን ሳልፈጽም አትጥለቂ” ብለው ሲገዝቷት ጨለማው ብርሃን በብርሃን ይሆናል፤ ከዚህም የተነሳ ነው ስማቸው አባ ተከስተ ብርሃን የተባለው፡፡
አባ ተከስተ በጾምና በቀኖና ላይ እንዳሉ በዋሻው ውስጥ ያርፋሉ፡፡ የዲማ ካህናትና መነኮሳትም ዋሻ ውስጥ በሕይወት ያሉ መስሎዋቸው ሲኖሩ በትራቸው ከዋሻ ተነሥታ ወደ ዲማ በመሄድ ሞታቸውን አስረድታለች፡፡ በትራቸውም በአሁኑ ሰዓት ዲማ ውስጥ አለች ይባላል፡፡
ዋሻው በእጅጉ የሚያስፈራ ሲሆን በዕለቱ በግርኛ ማርያምና በዲግ በኩል ባለው መግቢያ ሰው በገደሉ ላይ እየተንሸራተተ ወርዶ፣ ወደ ዋሻው አናት ላይ ሲወጣ ሲታይ በየገደሉ እየተንጠላጠለ ቅጠል የሚያሳድድ የፍየል መንጋ ይመስላል፡፡ ከዋሻው ጫፍ እስከ ጫፍ ለመድረስ ሁለት ጧፍ ይጨርሳል፡፡ ዋሻው ውስጥ ሲገባ ጧፍ እየተበራ ነው፡፡ ከዋሻ ውስጥ በጸበልነት የሚያገለግል ትልቅ ባሕር አለ፡፡ የጸበሉ መልክ ጥቁር ቡና ይመስላል፡፡
የጊዮርጊስ የንግሥ በዓል ሲቃረብ የበቁና ቅድስና ያላቸው አባቶች ወደ ዋሻ ውስጥ ይገቡና ለ7 ቀን እፍኝ ሽምብራ እየተመገቡ ሱባኤ ይገባሉ። ሲያስታኩቱና ቦታውንም ሲያጥኑ፣ ፈጣሪን ሲያመሰግኑ ይሰነብታሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን ታቦቱ ለንግሥ ይወጣና በመጀመሪያ ከገደሉ እርከን ሥር በተተከለለት ድንኳን ይገባል፡፡ ከዚያም ወደ ሜዳ ታጅቦ ከወጣ በኋላ በእልልታ፣ በሆታ፣ በጭብጨባ፣ በከበሮ ድምጽ እየታጀበ ሄዶ ዲማ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይገባል፡፡ በራሱ ጊዜም ተመልሶ ወደ ዋሻው ይገባል፡፡
የፍጡነ ረድኤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ከመንበረ ክብሩ ሲወጣና ወደ መንበረ ክብሩ ሲመለስ በአውሎ ነፋስ ይታጀባል ይላሉ አባቶች። አንድ አባት እንዳወጉኝ፤ አንድ የበቁ ጻድቅ ታቦተ ሕጉን ከዋሻ ውስጥ ለማውጣት ጧፍ እያበሩ ወደ ዋሻው ሲገቡ፣ አንዲት የሌት ወፍ የሚበራውን ጧፍ በክንፍዋ መትታ ታጠፋባቸዋለች፡፡
ጻድቁ ተስፋ ሳይቆርጡ በዳበሳ ታቦተ ሕጉ ወደ አለበት ቦታ ደርሰው ታቦቱን በጨለማ ሲነኩት አምስቱም ጣቶቻቸው እንደጧፍ ያበራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጽላቱ አንደበት አውጥቶ “አባ ተጠነቋቆልን” አላቸው ይባላል፡፡
ከዋሻው አቅጣጫ ከሜዳው ላይ ከገደሉ አፋፍ ደግሞ ሌላ ትንግርት አለ፡፡ አንድ ወቅት በዚያ አለታማ መንገድ አንዲት መነኩሴ ስትሄድ አንድ የጠገበ ጐረምሳ ክንዷን ይዞ ሊጥላት ሲል፤ “አቤት አቤት ፍጡነ ረድኤቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድረስልኝ” ብላ ትጮሃለች፡፡ ወዲያው ፍጡነ ረድኤቱ ያንን አለት ሰንጥቆ ይደርስላትና ያንን ባለጌ ወጣት ቀሰፈው ይባላል፡፡ እናም አሁን ድረስ የፈረሱ ኮቴ፣ ጦሩ ያረፈበት ድንጋይ ይታያል፡፡ በደማሚት የማይፈርሰው ጥቁር አለትም እስከ ታች ድረስ ክፍት ሆኖ ሰው ይሾልክበታል፡፡  

Read 6653 times