Saturday, 25 April 2015 10:41

የአዲግራቱ የምሽት ፓርቲ ያስከተለው ጣጣ!

Written by  ከዘሥሩግ ከጫናዱግ)
Rate this item
(2 votes)

    አዲግራት በቀድሞ አጠራሩ የዐጋመ አውራጃ፣ በአሁኑ ደግሞ የምሥራቅ ትግራይ ዞን ዋና ከተማ ናት፡፡ አዲግራት ከተራራ ሥር የተመሠረተችና እንደወርቅና ዕንቁ የምታበራ ከተማ ናት፡፡ አዲ ግራት ማለት የእርሻ ቦታ እንደማለት ነው፡፡ ነዋሪዎችም ከሁሉም ሰው ጋር በቀላሉ የሚግባቡ፣ ፈጣኖችና እንግዳ አክባሪዎች፣ ለእውነትና ለሀቅ የሚሞቱ ናቸው፡፡
ለሁልጊዜም ከልቤ የማትጠፋውንና ስሟ ሲጠራ በፍቅርዋና በውበትዋ የምትማርከኝን ይህችን ነፋሻማና ለኑሮ ተስማሚ የሆነችውን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት በ1973 ዓ.ም ነው፡፡ ሞቅና ደመቅ ወደአለችው ወደ አዲግራት ከተማ የገባሁት በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን አዲግራት በገባሁ በሦስተኛው ቀን የጫናዱግን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛና 12ኛ ክፍል መምህር ሆኜ እንዳስተምር ተነገረኝና ሥራዬን ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ የነበረው የቀበሌ አመራርም የምኖርበት የቁጠባ ቤት ሰጠኝ፡፡ የእኔ ቤት በርካታ የቁጠባ ቤቶችና ነዋሪዎች በሚኖሩበት አንድ ግቢ ውስጥ ሲሆን ምንም ዓይነት አጥር በሌለው ግቢ ውስጥ ልብስ ታጥቦና ውጭ ተሰጥቶ ቢውል ቢያድርና ወር ሙሉ ቢቀመጥ የሚሰርቀው ምንም ዓይነት ሌባ አለመኖሩ ሁልጊዜ ሲደንቀኝ ይኖራል፡፡
የከተማዋን ኑሮ ስለማመድ “ባላምባራስ” የሚለው ቃል እየተደጋገመ ሲጠራ ሰማሁ፡፡ ሕዝቡ ባላምባራስ ሐድጉ፣ ባላምባራስ ሥዩም፣ ባላምባራስ አሰፋ፣ ባላምባራስ ዋሴ… እያለ ሲናገር አንዱን የአዲግራት ተወላጅ መምህር፤ “አዲግራት የባላምባራሶች ሀገር ናት እንዴ? ባላምባራሶች ለምን በዙ? አልኩት”
እርሱም፤
“እንዴ አዲግራትኮ የራሶችና የደጃዝማቾችም ሀገር ናት፤ እነራስ ስብሐት እነ …” እያለ ይደረድርልኝ ጀመር፡፡ ቀጠለና፤ እንዳልከው ባላምባራሶች ብዙ ናቸው አንድ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ አሥመራ ሲሄዱ አዲግራት አርፈው ነበር፡፡ ያገሩ ባላባት ወዲ ሰባ ጋዲስ ይባላል፡፡ በአጠራሩም ገንታ አፈሹም ይባላል እናም ንጉሡ አዲግራት እንደደረሱ ለበርካታ ሰዎች የባለምባራስነት ማዕረግ ሰጥተዋል” አለኝ፡፡ ያ ጓደኛየ ቀጠለና፤ “ባላምባራስ ዋሴ ግን የአዲግራት ተወላጅ ሳይሆኑ ጎጃሜ ናቸው” አለ፡፡
“ጎጃሜው እንዴት እዚህ አገር መጥተው ኖሩ? እንዴትስ ባላምባራስ ተባሉ?” አልኩት
“አዲግራትኮ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገር ናት” አለ፡፡
ሁለት ወር እንደሞላኝ የገና በዓል ደረሰ፡፡ እኔ ደግሞ በልማዴ የገና በዓልን የማከብረው ሌሊት ቤተክርስቲያን አድሬ በማስቀደስና ከቤቴ ውስጥ በመዝናናት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ወደ እንዳ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ሄጄ ለማደር ሐሳቡ ነበረኝ፡፡ ከመኻል የጫናዱግ ሁለተኛ ደረጃ የስፖርት መምህር ክንፈ አበራ፤ “ዘሥሩግ! የተወሰንን ሰዎች ፓርቲ አዘጋጅተን የገናን በዓል በኢትዮጵያ ሆቴል ተሰባስበን ለማክበር ስለአሰብን አንተንም ጋብዘንሃል” ይለኛል፡፡
“እኔ እንኳን እንደ ቂርቆስ ሄጄ ለማደር ነው የፈለግሁት” ስለው
“ቦታው ላንተ ይርቅሃል ደግሞ ገና እንግዳ ስለሆንክ አይመችም፡፡ ከእኛ ጋር ስትጫወት ብታድር ይሻላል፡፡ መዋጮው 50 ብር ነው፡፡ ብሩን እኔ ከፍየልሃለው” አለኝ፡፡
“የምሽት ፓርቲ አዘጋጅተናል ነው የምትለኝ?” እኔኮ ዳንስ አልችልም? አልኩት፡፡
“እንዴ? እንዴት የአዲስ አበባ ልጅ ሆነህ ዳንስ አልችልም ትላለህ?” አለና ቀለደብኝ፡፡ በፓርቲ ምሽቱ ላይ የጫናዱግ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ መምህር ኩምሳ፣ የባንክ ቤት ሠራተኛው ወንድወሰን፣ የግብርና ሠራተኛው ሐሰንና የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት ፀሐየ እንዳሉበት ነገረኝ፡፡ በአጠቃላይ በፓርቲ ምሽቱ ላይ 6 ሰዎች እንደምንሳተፍ ነገረኝና በገና ዋዜማ ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በከፍተኛ የሙዚቃ ቅንብር ፓርቲው ተጀመረ፡፡ ስድስታችንም በቦታው ተገኘን፡፡ መጠጥ እየቀማመስን ለራት ስንዘጋጅ በአካል የማላውቃቸውና በአገር ባህል አለባበስ ያሸበረቁ 6 ልጃገረዶች ወደ ፓርቲው አዳራሽ ገቡ፡፡ ከእኔ በስተቀር ሌሎቹ ለካ የሴት ጓደኞቻቸውን አዘጋጅተው ጠርተው ኖረዋል፡፡ እያንዳንዱ ከአዘጋጀው የሴት ጓደኛው ጋር እየተነሳ ራት ወደተዘጋጀበት ቦታ ሲሄድ፣ ክንፈ ቀልጠፍ አለና የአንዷን ልጃገረድ እጅ ይዞ ወደእኔ መጣና “ተዋወቃት፤ የዛሬ የገና ስጦታህ ይህች ናት” አለኝ፡፡ ልጅቱ አጠር ከማለቷ በስተቀር በጣም ታምራለች፤ የጠይም ቆንጆ ናት፡፡
“እቴማንች እባላለሁ” ብላ ተዋወቀችኝ፡፡ እቴማንች በጣም ዓይናፋር ናት፡፡ በሐሰን የሴት ጓደኛ በለምለም ብትመረጥልኝም፣ እኔ በውበትዋና በፍቅርዋ ልማረክ አልቻልኩም፡፡ እንዲሁ ለስሜቴ እህቴ መሰለችኝ፡፡ ከበላን በኋላ አብረን ተቃቅፈን ብንደንስም ስሜቴን አልማረከችውም፡፡ ይልቁንም ልቤ በጊዜው ከተዋወቅኋት ከርግበ ጋር ስለነበር እቴማንችን አቅፌ ርግበ ነበረች ትዝ የምትለኝ፡፡
“ያገመ ኮረዳ ያፈሹም የገንታ፣
የምታስደነግጥ በዓይን ብሌን ገብታ፡፡
ዓይኗ ተወርዋሪ፣
ዓይኗ ተናጋሪ፣
ጽጌረዳ ከንፈር
የጣዝማ ንጣሪ …” እያልኩ
ከአደነቅኋትና በጊዜው ከአፈቀርኳት ከርግበ ጋር ሌሊቱን ባሳልፈው እመኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ኃይለኛ የሆነ የቤተሰብ ቁጥጥር ስለነበረባት አዳር ቀርቶ ቀን ከእርሷ ጋር ለመገናኘት በጣም ከባድ ነበር፡፡ አንድ ዕለት ግሪክ ከመሰለችውና ዓይኗ እንደ ኮከብ ከሚያበራው ከርግበ ጋር ተገናኝተን ሽንቅጥ ወገቧን እቅፍ አድርጌ፣ ጡቷ ደረቴን እየወጋው ስደባብሳት “ግደፍንዶ” ስትል ልክ ትግርኛው እንዳልገባኝ “እኔምኮ ለመግደፍ ነው አጥብቄ የምዳብስ” ስላት ሳቀችብኝ፡፡
አንደበቷ ማር ማር እንዳለኝ፣ የጥርስዋ ውበት ልቤ ላይ እንደተሰካ፣ ፈገግታዋ የደስታ ሽቱ በሰውነቴ ላይ እንደረጨ፣ ትንፋሽዋ ነዶ እሳት ሆኖ አካሌን እንዳቀጣጠለው በዓይኗ ዕይታ ህይወቴ እንደተማረከ ተለያየን፡፡
እናም እቴማንችን አቅፌ በትዝታ ከርግበ ጋር ስንደንስ ሌሎች ጓደኞቼም እየተቃቀፉ ብልጭ ድርግም በሚለው መብራት በመሽከርከር ላይ እንዳሉ መሬት የሚያናውጥ ተኩስ ተከፈተ፡፡ ተቃቅፎ ይደንስ የነበረው ሁሉ ተለያየ፡፡ በተኩሱ ያለንበት ኢትዮጵያ ሆቴል ብቻ ሳይሆን ከተማዋ ተናወጠች፡፡ ተደናግጠን ስንረበሽ በበሩ በኩል “እጅ ወደ ላይ እጅ ወደ ላይ” የሚል ኃይለኛ ድምጽ ሰማን። ነገሩ ግራ የሚያጋባ ሆነ፡፡ መሳሪያ የያዙ ፖሊሶችና የአብዮት ጥበቃዎች እኛ ወዳለንበት አራስ ነብር መስለው ሲገቡ፣ አቶ ሞላ የተባሉት የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር በቀኝ እጃቸው ማካሮቭ ሽጉጣቸውን ይዘው ወደ እኛ ቀረቡና፤
“አብዮታዊ ሠራዊት በየጦር ግንባሩ በሚፋለምበት በአሁኑ ሰዓት እናንተ እዚህ ጆሊ ጃኪዝም ታካሂዳላችሁ፡፡ ባርቲ መስርታችሁ አገር ታምሳላችሁ፡፡ እኛ ከኢሰፓኮ ሌላ ባርቲ አናውቅም። ፈሽፋሻ ሁላ፡፡ እነዚህ የሠው ህዝብ ልጆች የሆኑት ልጃገረዶች የእናንተ መጫወቻዎች ናቸው እንዴ? ቅደም? ወደፊት? አሉ፡፡ የአዲራት ከተማ የአብዮት ጥበቃ አባላትና ፖሊሶች እያጣደፉ ወስደው ከሌሊቱ በ7 ሰዓት ጨለማ በዋጠው እስር ቤት ወስደው ወረወሩን፡፡ ልጃገረዶችም እኛ ከታሠርንበት ቀጥሎ ባለ ክፍል ታሰሩ፡፡ እስራቱ ለሶስት ቀን ያህል ቀጠለ፡፡ በኋላ እንደተረዳሁት፤ እነ ክንፈ አበራ ፓርቲ ሲደግሱ ቀበሌውን ማስፈቀድ ነበረባቸው፡፡ ታስረን በሀሳብ ስንንገላታ በእኛና በሴቶች እስር ቤት መሃል ባለ ቀዳዳ በኩል አንዲት ወረቀት ወደ እኛ ተወረወረች፡፡
“የአውራጃ አስተዳዳሪውና የፖሊስ አዛዡ ባሉበት ለምርመራ ልንቀርብ ስለሆነ ቃላችሁ አንድ እንዲሆን፡፡ ይኸውም መምህር ኩምሳና ምጽላል ትኩ ለመጋባት ቃል ኪዳን ስለገቡ ይህንኑ ምክንያት አድርገው ራት ስለጋበዙን ነው በምሽቱ ግብዣ ላይ የተገኘነው በሉ” ትላለች ወረቀቲቱ፡፡ ምጽላል የመምህር ኩምሳ የሴት ጓደኛ ስትሆን የወታደር ልጅ ናት፡፡ እናም ዘዴው በአባቷ በኩል የመጣ ይመስለኛል፡፡
እንደተባለው አወራጃ አስተዳዳሪውና የፖሊስ አዛዡ በተገኙበት ለምርመራ ተጠራን፡፡ የአሥራ ሁለታችንም ቃል አንድ ሆነ፡፡ በወቅቱ ስለ ጆሊጃኪዝም አስከፊነት በስፋት በመገናኛ ብዙኀን ይነገር ነበርና በተለይ አውራጃ አስተዳዳሪው
“ፀሐይ ያየቺውን ሰው ሳያየው አይቀርም” የሚባል የትግሪኛ ተረት አለ፡፡ “እናንተ ኢትዮጵያ ሆቴል የተሰባሰባችሁት ኩምሳና ምጽላል ቃል ኪዳን ስለተገባቡ ሳይሆን የሰፊውን ህዝብ ልጆች ለማማገጥ ነው፡፡ ለዚህ እኛ ትዕግሥት የለንም፤ እስከ 6 ወር እና እስከ አንድ ዓመት ልናሳስራችሁ እንችላለን፡፡ ግን የተወሰናችሁት መማህራን/መምህራን ለማለት/ ስለሆናችሁ የመማር ማስተማሩ ሂደት ይጎዳል። ወደፊት ሆቴል ውስጥ ሆነ በሌላ ቦታ ከሴት ጋር ብትገኙ እርምጃችን የከበደ ይሆናል፡፡ ለዚሁ በቂ ዋስ እየጠራችሁ ልትፈቱ ትችላላችሁ” አለ፡፡
በወቅቱ ሁሉም ዋስ እያቀረቡ ሲፈቱ እኔ እንግዳ ስለሆንኩና ሰውም ገና ስለአላወቅሁ ዋስ አጣሁኝና ተለይቼ ስቀር ምንም የማላውቀውና የአሰፋ ክንደያ ወንድም የማነ የተባለ የአዲግራት ተወላጅ ዋስ ሆኖ አስፈታኝ፡፡ የሰው አገር ሰው ለምን ተለይቶና ታስሮ ቀረ ብለው ከየማነ ጋር የነበሩት ሰዎች በመፈታቱ ተደስተው ይዘውኝ ወደ ቤቴ ስንሄድ፣ በመንገድ ላይ አንድ አውራ ደሮ ተንደረደረና ከአንዲቱ ደሮ ላይ ወጣባት፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ፤ “ኧረ አንተ አውራ ዶሮ! ጆሊጃኪዝም አካሄደ ተብለህ እንዳትታሰር!” ስል ሰዎቹ በጣም ሳቁ፡፡ በሌላ ጊዜ አዲግራቶች “አንተ አውራ ዶሮ ተው እንዳትታሰር አለ ዘሥሩግ” እያሉ እንደተረት ያወሩ ጀመር፡፡
በኋላ ላይ እንደተረዳሁት ከእስራት በቶሎ እንድፈታ አውራጃ አስተዳዳሪውንና የፖሊስ አዛዡን ያግባባልን አሁን አሜሪካ ውስጥ የሚኖረውና የቀበሌው ሊቀመንበር የነበረው አቶ ታፈረ ኃይለሥላሴ ነው፡፡

Read 6274 times