Monday, 20 April 2015 15:27

የፋና ሬዲዮ “ሞጋቹ” ሲሞገት

Written by  በቢኒያም ም.
Rate this item
(10 votes)

ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ፡፡ ቅዳሜ ዕለት ነው፡፡ በቀጣዩ ወር የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከሚቀርቡ “ክርክርና ቅስቀሳ” ቢጤዎች ባሻገር እዚህም እዚያም ከሚዘጋጁ መድረኮች በአንዱ ተገኝቻለሁ፡፡ ጉዳዩን ክርክር ቢጤ ያልኩት የምርጫ ክርክር ማለት ምን ማለት እና እንዴት  እንደሆነ በቅርቡ በአፍሪካ በዴሞክራሲው ሰፈር አንቱታን ባተረፈችው ናጄሪያ የተካሄደውን ምርጫ ሲያቀብጠኝ ተከታትዬ ነው። መቼም ምኞት አይከለከል ለሃገሬም ተመኘሁት፡፡
በቅርቡ ለንባብ በበቃ አንድ ጋዜጣ ላይ የገዢው ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ፤ “ከኢሕአዴግ ጋር አይደለም ሊፎካከር አጠገቡ የመቆም አቅም ያለው ተፎካካሪ ፓርቲ የለም” ማለታቸው ይህንን ምኞቴን ከንቱ ያደርገዋል፡፡ እኔን ግርም የሚለኝ ኢሕአዴግ አጠገብ ድርሽ የሚል ተፎካካሪ ከሌለ  ምርጫ እየተባለ የሌለ የሀገርና የህዝብ ሃብት ለምን በከንቱ እንደሚባክን ነው፡፡ ስንት መስኖ፣  ስንት ት/ቤት፣  ስንት ጤና ጣቢያ በተሰራበት ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን የኮንዶሚኒየም እጣ ደርሷቸው  የሚከፍሉት በማጣት በጭንቀት ለህምም ተዳርገዋል ለተባሉት የአዲሳቤ ነዋሪዎች በድጎማ መልክ ቢከፋፈል እንኳ ትልቅ ነገር ነው፡፡
እኔን እስከሚገባኝ ምርጫ የሚካሄደው አማራጮች ሲኖሩ ነው፡፡ መቼም አንድ አይነት ዳቦ ብቻ በቀረበበት ገበታ ላይ “መርጠህ ያማረህን ብላ” አይባል ነገር፡፡ ከተባለም ማላገጥ ነው የሚሆን ነው። የኢሕአዴጉ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ባሉት ነገር ላይ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ፓርቲያቸው የሚፎካከረው ቀርቶ አጠገቡ የሚደርስ ፓርቲ እንዳይኖር በትጋት መስራቱ ለዚህ ውጤታማ አፈጻጸም አብቅቶት ይሆን? ይህን ድንቅ የዴሞክራሲ ተሞክሮውን ለሌሎች አገራት በተለይም ለእንግሊዝና አሜሪካ ቢያጋራው የአለማችን ዴሞክራሲ ምንኛ በተመነደገ ነበር!
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ፡፡ የተገኘሁበትን መድረክ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሚኒኬሽን ት/ቤት መሆኑን የጥሪው ካርድ ይናገራል፡፡ “በምርጫ የሚዲያ ሚና፣  የኢትዮጵያ  ተሞክሮና በቀጣዩ ምርጫ ላይ ያለው አንደምታ” ለምክክር የተመረጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የሚዲያ ባለሙያ ወይም የምርጫው አስመራጭም ተመራጭም አይደለሁም፡፡ በሌላ የትምህርት ክፍል የምማር የዩኒቨርሲቲው እጩ ተመራቂ ብቻ ነኝ፡፡ እንደተለመደው ፕሮግራሙ ዘግይቶ ተጀመረ፡፡
የክብር እንግዳው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ናቸው፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ሳይመጡ ቀሩ፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ ግን ዘግይተውም ቢሆን መጥተዋል፡፡ በረፋዱ ክፍለ ጊዜ ሁለት የመወያያ ጥናቶች  ቀረቡ። አንደኛው በት/ቤቱ ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይ የቀረበ ነበር፡፡ በምርጫ ወቅት የሚዲያ ሚና ምን መሆን እንዳለበት አለም አቀፍ የሙያውን  መሰረታዊ መርሆዎች በአማረ ሁኔታ የዳሰሰ አስተማሪ ጽሁፍ ነው፡፡ የEBC እና የFBC (ፋና)  አለቆች ቢኖሩ ብዬ ተመኘሁ፡፡ በድርጅት ስብሰባ ላይ እንጂ እንዲህ አይነቱ እውቀት  በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ አዘውትረው ቢገኙማ  ተቋሞቻቸው እንዲህ ህዝብ የሚታዘባቸው ባልሆኑ ነበር ብዬ አሰብኩ። የEBC የካሜራ ባለሙያዎች ግን ነበሩ፡፡ የዶክተሩ ሃሳብ በቤቱ የተወደደና የተጨበጨበለት ሆኖ ተጠናቀቀ። “የተማረ ይግደለኝ” የሚለው የከረመ አባባላችን ከዘመኑ ጋር መታደስ ያለበት ይመስለኛል። ለአስተሳሰብም ህዳሴ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን አሁን ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ዲግሪ ለመጫን ቀልድ ሆኗል፡፡ በዚሁም ልክ በጫነውና ባልጫነው መካከል ያለው የልዩነት መስመርም ደብዝዟል፡፡ ስለዚህ “የተማረና የሚያነብ ይግደለኝ” በሚል ቢስተካከልስ፡፡
በቤቱ አነጋጋሪ የነበረው ቀጥሎ የቀረበው ጽሁፍ ነው፡፡ አቅራቢው ደግሞ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመስል ነበሩ፡፡ በአንድ ልቤ የፋናው አለቃ በመገኘታቸው ደስ አለኝ፡፡ ጽሁፉ ጥናታዊ እንደሆነ በፕሮግራሙ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም አቅራቢው ጥናታዊ እንዳልሆነ አስቀድመው ተናገሩ፡፡ ከዶክተሩ የተጨበጨበለት ምሁራዊ ትንተና አንጻር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስገምት አቅራቢው አሳዘኑኝ፡፡ የእርሳቸው ርዕሰ ጉዳይ በሀገራችን በ1997 እና በ2002 በተካሄዱት ምርጫዎች በተለይም የብሮድካስት  ሚዲያው ሚና ምን ነበር የሚል ነው። በተለይም ምርጫ 97ን ሊነካኩት መሆኑ ሲገባኝ ደስታም ቅሬታም ተፈራረቁብኝ። ኢሕአዴግም በአቶ በረከት “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ላይ እንዳመነው፣ ይህ ወቅት የሀገራችን ዲሞክራሲ ህዝብን በሙሉ ፍላጎት ያሳተፈ ነበር፡፡ ከታሪካዊ አመጣጡ ጀምሮ የገዢው ፓርቲ ፍላጎትና ርዕዮት ይጫነዋል የሚባለው የዚያኔው ሬዲዮ ፋና ደግሞ ትልቅ ሚና ነበረው። ሚናው ለዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ግንባታ ጠቀመ ወይስ ጎዳ? የሚለው ጉዳይ ግን መጤን ያለበት ይመስለኛል፡፡ እናም የዚህን አነጋጋሪ ጣቢያ እይታ ለዚያውም ከዋናው ሰውዬ ልሰማ መሆኑን ሳስብ ነው ደስ ያለኝ፡፡ ቅሬታዬ ግን አቅራቢው እንዳሉት ይህን ጉዳይ ያውም ያለምንም የተደራጀና ጥልቀት የሌለው ጥናት መነካካቱ የሚቀርበውን ነገር ከእውቀት የፀዳና ስሜታዊነት ያጠቃው እንዳይሆን አስግቶኝ ነበር። አቶ ወልዱ የሚያቀርቡት ነገር ጥናት ያልሆነበት ምክንያት ያዘጋጁት ነገር ስለጠፋባቸው ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በተሰጣቸው ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ወዲህና ወዲያ እየተላጉም ቢሆን ለማለት የፈለጉትን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
ሃሳባቸው ሲጠቃለል በምርጫ 97 በተለይ የብሮድካስት ሚዲያው /ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ማለታቸው ነው/ ምርጫው ህዝብ በንቃት የተሳተፈበትና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ በሌሎች በዴሞክራሲ በዳበሩት አገራት እንኳን ባልታየ መልኩ ምርጫው ሊከናወን መንፈቅ ሲቀረው ጀምሮ የምርጫ ክርክሩና ቅስቀሳው መጀመሩ ነው። ይሄ ደግሞ አቅራቢውን ያስቆጫቸው ይመስላል። ኢሕአዴግም ቆጭቶታል ልበል? ለዚህም ይመስለኛል የዘንድሮው ምርጫ ለመካሄድ ሁለት ወር ያልሞላው ጊዜ ሲቀረው ያውም በተቃዋሚዎች ውትወታ የተጀመረው፡፡ ከስህትት መማር ማለት እንዲህ ነው፡፡
አቅራቢው ሲሆን የነበሩ ነጻ (የግል) የህትመት ውጤቶች ከብሮድካስት ሚዲያው በተቃራኒ ቆመው እንደነበር፡፡ ይህን ኢሕዴግም ሲለው የነበረ ሲሆን አብዝቶም በመጸጸቱ እየተንገታገቱ ካሉት ጥቂት በቀር ሁሉንም የፕሬስ ውጤቶች በአንድ ፈርጆ ድምጥማጣቸውን ያጠፋ በመሆኑ የአቅራቢው ድምዳሜ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ለእኔም ሆነ በኋላ እንደታዘብኩት ለብዙዎቹ የመድረኩ ታዳሚያን የገረመን ሰውየው የሚዲያ ባለሙያ ሆነው ያውም ለ20 አመታት የቆዩና ከዚህም ውስጥ የሚበዛውን ጊዜ በፋና ትልቁ ወንበር ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን ሳገናዝብ ነው፡፡ ድምዳሜያቸው ስህተት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቢያንስ ሁሉንም በአንድ ፈርጆ ከመውቀጥ መለየት እንኳን ይገባቸው ነበር፡፡ የኢሕአዴግን አቋም የማይደግፍና የእሱን የልማት ስራ አጋኖ ሳያቋርጥ የማይዘግብ (ልማታዊ ያልሆነ) ሚዲያ መኖር የለበትም የሚል አቋማቸውን ለማስተጋባትም ተከታዩን ድምዳሜ አቅርበዋል፤ “በተለይ የምርጫ 97 ውጤትን ተከትሎ በሃገሪቱ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ አገሪቱ ልትፈራርስና ወደማያባራ ግጭት ልትገባ በቋፍ ላይ ነበረች። በዚህ ቀውጢ ጊዜ አገርን ለማዳን በተደረገው ርብርብ የብሮድካስት ሚዲያው ትልቁን የማረጋጋት ሚና ተጫውቷል፡፡ የህትመት ሚዲያው ግን ከዚህ በተቃራኒው በመቆም አገሪቱን ወደማያባራ እልቂት ለመጨመር ሲሰራ ነበር፡፡” /እንደወረደ የቀረበ/በ97ቱ ምርጫ ወቅት የብሮድካስት ሚዲያ የመንግስት ቲቪና ሬዲዮ እንዲሁም ፋና ሬዲዮ ብቻ ነበሩ ልብ ይሏል፡፡ አገር አዳኞቹም እነርሱው ነበሩ። ዛሬ ከእልቂት ተርፈው እየተፍጨረጨሩ ያሉት “ሪፖርተር”ና “አዲስ አድማስ” እንኳን አልታያቸውም።
አቶ ወልዱ እንደተናገሩት፤ ከ97 ምርጫ አንጻር  በ2002 ምርጫ የነበረው የሚዲያ ሚና የተሻለ ነበር፡፡ ለዚህም መንግስት አብዛኞቹን በእርሳቸው አገላለጽ፤ “አገር ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የህትመት ተቋማትን እንዲዘጉ በማድረጉ ነው፡፡ ስለሆነም ከ97ቱ የተሻለ ህዝብ በብዛት የተሳተፈበትና ችግር ያልነበረበት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ አቅራቢው የግል ፕሬሱ ድምጥማጡ በመጥፋቱ የተደሰቱ ይመስላሉ። በአንድ በኩል እውነት አላቸው፡፡ በገበያ ውስጥ ያለ ተቋም እንደመምራታቸው መጠን ያለተፎካካሪ የሃሳብ ገበያውን ለመጋለብና ህዝቡን ጋሪ እንደሚጎትት ፈረስ እርሳቸውና ፓርቲያቸው በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ለመምራት ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ግን ደግሞ 20 አመት ያውም የሚበዛውን ጊዜ በሃላፊነት በሚዲያው አለም የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን የግሉም ይሁን ሌላው ሚዲያ እንዲያብብ መመኘት፣ ለዚህም መስራት ይጠበቅባቸው ነበር የሚል እምነት አለኝ። እውን የዴሞክራሲ መስፈን አሳስቧቸው ከሆነ ወደ በረሃ የገቡት ማለቴ ነው፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶ/ር አጋረደች የተባሉ ምሁርም ይህንኑ የሚያጠናክር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ “የግል የህትመት ሚዲያው በመክሰሙ ደስ ያለዎት ይመስላሉ፡፡ ችግር አለባቸው ከተባለ ችግራቸውን በሂደት እያረሙ እንዲኖሩ ማድረጉ ለህዝብና ለዴሞክራሲ ስርአቱ ግንባታ ይበጅ የነበረ አይመስሎትም ወይ?” አሏቸው፡፡
አቶ ወልዱ አጠገባቸው የተቀመጡትንና ቀደም ብለው ወረቀት ያቀረቡትን ዶ/ር አብዲሳን አልሰሟቸውም እንጂ  ይህንን ተናግረው አቧራ ባላስነሱ ነበር፡፡ ዶ/ሩ የቀድሞውን የአሜሪካን ፕሬዝደንት ንግግር ነበር የጠቀሱት፡- “በአጣብቂኝ አማራጭ ውስጥ ገብቼ ፕሬስ አልባ መንግስት ከሚኖርና መንግስት አልባ ፕሬስ ከሚኖር ምረጥ ብባል የኋለኛውን የምመርጥ ይመስለኛል”፡፡ በርግጥ ዶ/ሩ የፕሬዚዳንቱን አባባል በአውዱ /contextually/ መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡- የሁለቱም መኖር ለአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት፡፡ አቶ ወልዱ የሚያቀርቡትን ሲያጠናቅቁ እንደመጀመሪያው አቅራቢ ያልሞቀ ግን ደብዘዝ ያለ የአክብሮት ጭብጨባ አግኝተዋል፡፡
“ሞጋቹ” ሲሞገት
በእኒህ መሰሉ መድረኮች ላይ ስገኝ ሁሌም የሚገርመኝን ነገር በቅድሚያ ላንሳ፡፡ ብዙው የውይይት ጊዜ የሚፈጀው በጥናት አቅራቢዎቹ ነው። ያውም የሚበዙት ጥናት ያልሆኑ ጥናቶች እያቀረቡ፡፡ ምክክር እንዲህ ነው እንዴ?!
እንዲህም ሆኖ ወደ ውይይቱ ተገባ፡፡ ገና እድሉን ለመስጠት አወያዩ ሲያስቡ፣ ብዙ እጆች አየር ላይ ነበሩ፡፡ ያለማጋነን እጁን ያላወጣው ታዳሚ በቁጥር ያንስ ነበር፡፡ ሃሳብና ጥያቄዎች ከግራ ከቀኝ፣  ከግንባር ከደጀን መዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ አብዛኞቹ የጎረፉት ወደ አቶ ወልዱ ነበር፡፡ ካቀረቡት ሃሳብ አንጻር የሚጠበቅ ስለነበረ አልገረመኝም፡፡ ምናልባት እርሳቸው በለመደ ፍረጃቸው ጠያቂዎቹን ሁሉ ምድረ “ኒዮ ሊብራሊስቶች” ወይም “ፀረ ልማቶች” ብለው ፈርጀውን ሊሆን ይችላል፡፡ የሚቻል ቢሆንም ግን ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጣቢያቸው “ሞጋች” የሚባል ፕሮግራም ከፍቶ የተለያዩ ፓርቲዎችን እየጠራ የጣቢያው አወያይም ጭምር ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፎ ጉንጭ አልፋ ክርክር እንደሚያደርግ እኔ በግሌ አውቃለሁ፡፡ ለፋናው አለቃ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በተለይ የዚህ የሞጋች ነገር ቀልቤን ስቦታል። የኔው ቢጤ አንዱ ተማሪ ጉዳዩን እንዲህ በማለት ነበር ያነሳው፤
“ፋና ከየት እንደመጣና አላማው ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከ24 አመታት በኋላም የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ ማለቱን አልተወውም፡፡ ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ሃሳቦች እንዲደመጡ ፍላጎት የለውም። በተለይ በዚህ ሞጋች በምትሉት ፕሮግራም አወያይ ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ሰው ግልጽ የሆነ አምባገነንነትና ጉልበተኝነት ይታይበታል። ለኢህአዴግ መወገኑ በግልጽ ይታወቅበታል። ከሙያውም ስነምግባር በጣም የራቀ ነው፡፡ ሰውዬው ለፋና ሊመጥን ይችላል፡፡ ለሚያዳምጠው ህዝብ ግን አይመጥንም፡፡ ስርአት የለውም፡፡”
ሌላዋ ተወያይ ቀጠሉ፡-
“እኔ የማውቀውና የማስተምረው ጋዜጠኝነት ይህንን አይነቱን ኢ-ስነምግባራዊ የሆነ ድርጊት አይፈቅድም፡፡ ጣቢያችሁ ሚዲያ ሆኖ ሳለ የእናንተ ጋዜጠኛ ግን በተለይ የህትመት ሚዲያውን ሲዘልፍና ሲያብጠለጥል ነው የሚውለው፡፡ ሞጋች እያለ የሚያቀርበውም ፕሮግራም ፍጹም ስነምግባር የጎደለውና የሰውን ክብር የሚነካ ነው። የሚጋብዛቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች የራሳቸው ደጋፊና ተከታይ እንዳላቸውና እነዚህም እንደ ኢህአዴግ ደጋፊዎች ሁሉ የተከበሩ ህዝቦች መሆናቸውን ሊያውቅ ይገባል፡፡ግን ሰውዬው ምንድነው?”
የፋናው አለቃ ይህንና ሌሎችንም ጉዳዮች  በተመለከተ የቀረበባቸውን ትችት መቋቋም እየተሳናቸው ሲመጡ በግልፅ ተስተዋሉ፡፡ ምላሽ እንዲሰጡ እድል ተሰጣቸው፡፡ ምላሻቸውም በአብዛኛው የሚያበሳጭና ዙሪያ ገባውን ያላስተዋለ ነበር፡፡ በተለይ አጠገባቸው የነበሩትን ዶ/ር መዘንጋታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ “ሞጋች” በተባለው ፕሮግራማቸው ላይ የተነሱባቸውን ትችቶች ግን ሙሉ ለሙሉ ተቀብለው ለማስተካከል እንደሚጥሩ በሚያስተዛዝን ድምጸት ተናገሩ፡፡ እኝህ ሰው የድርጅቱ ዋና ሰው ናቸውና ያስተካክሉታል ብዬ ተስፋ አደረግሁ፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ፕሮግራም እጅግ ከሚበሳጩትና እንዲህ አይነት ጋዜጠኝነት በአለም ላይ አለ ወይ ስልም ከሚጠይቁት ወገኖች አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው እንግዲህ ፋና በ97ቱም ሆነ ከዚያ በኋላ በተደረጉትና በቀጣዩም ምርጫ የነበረውና የሚኖረው ሚና መጤን አለበት ማለቴ፡፡
የፋናው ዋና ራስ ስህተት መሆኑን የተቀበሉትንና ይቅርታ የጠየቁበትን ጉዳይ እንዴት እንደሚያስተካክሉት ለመታዘብ እሁድ ረፋድ ላይ ሬዲዮኔን ከፈትኳት፡፡ ያአምባገንነትና ጉልበተኝነት” ይስተዋልበታል የተባለው አወያይ አየሩን እየተገፋተረም እያሸማቀቀም መጣ፡፡ ለውጥ አልታየበትም፡፡ መጨረሻውን ለማየት ማድመጤን ቀጠልኩ፡፡ ሰማያዊ ፣ አንድነትና  ኢህአዴግ ናቸው ለሙግቱ የቀረቡት፡፡ የኢራፓው ተወካይ ተጋብዘው ሳይሆን “ተጠርተው” እንደቀሩ ጋዜጠኛው ደጋግሞ ተናገረ፡፡ እመጣለሁ ብሎ መቅረት ተገቢ ባይሆንም ግን ደግሞ መብት መሆኑን ጋዜጠኛው የዘነጋው ይመስላል፡፡ ካሉበት በአስቸኳይ እንዲመጡም ጮክ ብሎ ተጣርቶ ነበር፡፡ ሳይመጡ ቀሩ እንጂ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲሀ መሃል ላይ ላይ ችግር ተፈጥሮ አየሩ ደም ደም መሽተት የጀመረው፡፡ እኔ እምለው ግን ፋና ስቱዲዮ ውስጥ ያለው የውይይት ጠረጴዛ ነው ወይስ ታንክ? የምሬን እኮ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ሳይሆን ታንክ ከበው የሚነጋገሩ ነው የሚመስሉት፡፡ ነገሩን አደፍርሶ የአወያዩን ቁጣ ጣሪያ ያደረሰው ደግሞ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲው ተወካይ ሃሳብ  ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሰው (አቶ ዮናታን) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የምክክር መድረክ ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ አወያዩ ለዚህ ሰው እንዲናገር እድል ይሰጠዋል ግን አያናግረውም፡፡ አፍ አፉን እያለ አየር ያሳጣዋል። የወጣቱን አልሸነፍ ባይነትና እርጋታ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ ሊያሳድጋቸው የሚገቡት ቀሪ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው፡፡ ይህም ሆኖ “ህዝቡ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን እንታገላለን፡፡ ከካርድም ውጭ ቢሆን፡፡” ማለቱ አወያዩን እስከ ሰማየ ሰማያት ድረስ በሚሰማ መልኩ አስጩሆታል፡፡ በተማሪ አቅሜ የገዛኋትና ሬዲዮ ለማድመጥም የምታገለግልኝ ሞባይል ስልኬ ከመፈንዳት ለጥቂት ተርፋ፣ የሁለቱን ሰዎች ትንቅንቅ ማስደመጧን ቀጠለች፡፡
እኔ የምለው አወያዩ ጋዜጠኛ ይህን ያህል ለኢህአዴግ የሚቆረቆርና የተቃዋሚዎች ሃሳብ ደሙን የሚያፈላው ከሆነ ሌሎቹ የፓርቲው ተወካዮች እዚያ መገኘታቸው ለምን አስፈለገ? ጋዜጠኛው የመጠየቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ እኔም እስማማለሁ፡፡ ኢህአዴግን ወክሎ የመከራከርና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሆን ብሎ ስሜት ውስጥ በመክተት (provoke በማድረግ) ክፉ ማናገር ግን አይገባውም፡፡ ይሄ ፍጹም የሆነ የአወያዩ አምባገነንነትና ማን አለብኝነት በቦታው ለነበሩት የኢህአዴግ ተወካዮችም  ንቀት ከመሆኑ በተጨማሪ ለዴሞክራሲ ስርአቱ ግንባታ ረብ የሌለው፣ የጋዜጠኝነትንም ሙያ የሚያራክስ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ እንዲህ ነው እንዴ?!
እኔ በግሌ የሰማያዊ ፓርቲን ከካርድ ውጭ አገላለፅ በአውዱ የተገነዘብኩትና ተወካዩ ያብራራውም በሌላ መልኩ ነው፡፡ ምርጫ ሲመጣ እየጠበቅን ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ሰልፎችንና ሌሎችንም መንገዶች በመጠቀም ህዝብን እናሳምናለን ነው… ያለው፡፡ ይህ ደግሞ መብትም ትክክልም በመሆኑ ከጣሪያ በላይ የሚያስጮህ አንዳችም  ነገር የለውም፡፡
ጊዜ ለኩሉ?
 አከራካሪው በጊዜ አጠቃቀም ላይ ፍጹም የሆነ አድሏዊነት ይታይበታል፡፡ የኢህአዴጉ ተወካይ አቶ መኩሪያ በአንድ ጊዜ  ከአርባ ላላነሱ ደቂቃዎች ያለማቋረጥ አውርተዋል፡፡ ተቋሚዎቹ ከአስር ደቂቃ በላይ የተናገሩበትን ጊዜ አላስታውስም። ያውም አወያዩ በረባ ባልረባው እያቋረጣቸው። አወያዩ የአየር ጊዜውንም እንደፈለገ የመጠቀም መብት እንዳለውም መታዘብ ይቻላል፡፡ “ስለሰአቱ አትጨነቁ፡፡ የቻላችሁትን ያህል እንገፋለን። እናንተን ካልሰለቻችሁ” ሲል ተደምጧል፡፡ ፅድቁ ቀርቆብኝ በቅጡ በኮነነኝ፡፡ እንኳን ሚዲያን የሚያክል ተቋም ይቅርና ዛሬ የእያንዳንዱ ግለሰብ ዘመናዊነት የሚለካው አንድም በጊዜ አጠቃቀሙ ውጤታማነት መሆኑን የዘነጋው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጋው ሲያዳምጥ ውሎ ሲያዳምጥ ያለማደር መብት አለው፡፡ ሰው አዳምጦ ሊገነዘበው የሚችልበት መጠንም አለው፡፡  ሲለፈለፍ ስለተዋለ ሰው እያዳመጠ ነው ማለት እንደማይቻል መገንዘቡ የኮሙኒኬሽን ሀሁ ይመስለኛል፡፡ የማታ ማታም “የፋና ቴክኒሺያኖች ሰአት የለም አሉ” በሚል ውይይቱ ተጠናቀቀ፡፡ (እድሜ ይስጣችሁ!)
የህዝብ/ የአድማጮች ጥያቄ
ሌላው እኔን ግርም ያለኝ የህዝብ /የአድማጮች ጥያቄ እየተባሉ የሚቀርቡት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ በርግጥ የህዝብ ናቸው ወይ? ህዝቡስ ጥያቄ ያለው ለተቃዋሚዎች ብቻ ነው ወይ? መልስ የሚያስፈልገው የህዝብ ጥያቄ ይመስለኛል። መልሱን ግን ከዚያው ከሞጋቹ ሰው ማግኘት ይቻላል። ጥያቄዎቹ በስልክ የመጡ የህዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን እንደነገረን ረስቶት ራሱ ሲያብራራቸው ይቆይና ትዝ ሲለው ደግሞ ወዲያው መለስ ብሎ “ጠያቂው እንዲህ ለማለት ፈልገው አይመስሎትም ወይ?” ሲል ልባችንን ያደርቀዋል፡፡ በርግጥ ሰውዬው ጥሩ ፖለቲከኛ አይደለም፡፡ ጥሩ ፖለቲከኛ የዋሸውን አይረሳማ፡፡ ህዝቡ እንዲጠይቅ ከተፈለገ ለምን በቀጥታ በስልክ ገብቶ እንዲጠይቅ አይደረግም? ወይም ከኢህአዴግ አንጻር ችግር ይፈጥራል ብሎ ካሰበ /ማሰቡም አይቀር/ ሌሎች የውጭ ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት ቀርጾና የማይፈልገውን አስቀርቶ አያቀርበውም? ህዝቡ ድምጹ ሳይሰማ /መናገር እየቻለ/ ጠየቀ ሲባል ትንሽ አይከብድም? ንቀትስ አይሆንም? ቆይ በዚህ በኛ ሀገር፣ ህዝብ የሚባለው የማይናገር፣  ሃሳብ የሌለው፣  ግኡዝ ነገር ሆኖ አረፈው ማለት ነው? ኧረ በህግ! የሌሎችን አተያዮችን እጠብቃለሁ፡፡ እንወያይበት!!

Read 3098 times