Monday, 20 April 2015 15:24

ኮንዶሚኒየም እውነት ለድሃው ነው?

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“ዕጣው ያልደረሰኝ… ለበጐ ነው”

    የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ላይ 30ሺ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለከተማዋ ነዋሪዎች በዕጣ ማስረከቡን አብስሮናል፡፡ እውነትም የአፍሪካ መዲና የሆነችውና ከ4 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይኖርባታል ተብሎ የሚገመትባት አዲስ አበባ፤ ፈርጀ ብዙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄደባት የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የከተማው አስተዳደር ከአስር ዓመት በፊት የጀመረው የኮንዶሚኒየም የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁን 10ኛ ዙር ላይ ሲሆን 136ሺ ቤቶችም ለነዋሪዎች ተላልፈዋል ተብሏል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በመሰረቱ የድሃውን ህብረተሰብ የመኖሪያ ቤት ችግር ይቀርፋል በሚል ዓላማ የተወጠነ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተጨባጭ ግን በሀገሪቱ በፈጣን ሁኔታ እየገሰገሰ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ፍላጎትና አቅርቦቱን ማጣጣም ባለመቻሉ፣ የመኖሪያ ቤቶቹን እየተጠቀመ ያለው ድሃው የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን መካከለኛ ገቢና ከዚያ በላይ የተሻለ ገቢ የሚያገኘው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ለዚህ መቼም ሳይንሳዊ ትንተና የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በየኮንዶሚኒየሙ የተሰቀሉ የቴሌቪዥን ሳህኖች፤ በየፎቁ ስር ተጨናንቀው የቆሙ መኪናዎችና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ በቂ ምስክሮች ናቸው፡፡
ቤቶቹን ድሆች እጣው ደርሷቸው ያከራዩት… ወይም ባለእድሉ ነዋሪ ራሱ ይኑርበት ዜጎች ወጥተው የሚገቡበት ታዛ መገኘቱ በራሱ እሰየው ያስብላል፡፡
ነገር ግን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እጣ ወጥቶላቸው መኖሪያ ቤታቸውን በአቅም ማነስ ምክንያት መረከብ ያልቻሉ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቁጠባ ባህልን ማዳበር እንዲችል ለማበረታታት የከተማ ቤቶች ልማት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደረሱት ስምምነት መሰረት፣ ባንኩ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንቢያ የሚሆን 1ቢሊዮን ብር ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት በብድር መልክ እንዲሰጥ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት በጥናት ደረስኩበት ባለው መሰረት፤ በተጨባጭ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለበት ድሃው የህብረተሰብ ክፍል እጣው በወጣለት ወቅት የሚጠየቀውን ቅድሚያ ክፍያ ማሟላት አለመቻሉን ታሳቢ በማድረግ፣ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎችን ዳግም በመጥራት እንዲሁም አዲስ ተመዝጋቢዎችን አካቶ በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም ላይ ባካሄደው ምዝገባ፣ ከ900ሺ በላይ ቤት ፈላጊ የከተማዋ ነዋሪዎችን እንደ አቅማቸው በ10/90፤ በ20/80 እና በ40/60 መርሀ ግብር ከፋፍሎ ወደ ቁጠባ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡
ይሄን ተከትሎም 135 ሺህ የሚደርሱ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች፣ የእድሉ ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ከ21 ወራት ቁጠባና ቆይታ በኋላም ባለፈው መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቢያንስ ለ16 ወራት የቆጠቡ ነዋሪዎች በእጣው ተካትተው፣ 35ሺ የሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎችን የቤት ባለ እድል ማድረጉን አስታውቋል፡፡ መቼም እጣው ደርሶት ያልተደሰተ፤ ያልፈነደቀ ያለመኖሩን ያህል፣ 16 ወራት መቆጠብ ባለመቻሉ ከእጣው የተገለለና ቆጥቦ እንኳን ቢሆን እጣው ያልወጣለትና ያላዘነ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ደስታና ሁካታ በብርሃን ፍጥነት ወደ ሀዘንና ተስፋ ማጣት ሲቀየር፣ በአንጻሩ እጣው ያልወጣለት ደግሞ “እሰየው ለበጎ ነው… እጣው የዘለለኝ” ሲል ከሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ብቻ ነው የወሰደበት፡፡
ለምን ይሆን አትሉም?
ምክንያቱማ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ስለቤቶቹ ማስተላለፍ በበተነው ብሮሸር ላይ የተቀመጠው የቤቶቹ ሂሳብ አከፋፈል መመሪያ፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር በወቅቱ ተፈፃሚ ይሆናል ብሎ ቃል ከገባበት መመሪያ ጋር ተጻራሪ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ የከተማ ልማት ሚኒስትሩ በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ መንግስት ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ በ1997 ዓ.ም የጀመረው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ አለመሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ እጣው የወጣላቸው ባለእድለኞች ግን ቤቱን እንዲረከቡ ጥሪ በሚደረግበት ሰዓት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በይበልጥም ድሃው ለቅድምያ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ከባድ ፈተና እንደሆነበት መንግስት መረዳቱን ጠቁመው አዲስ የተዘረጋው በየወሩ የመቆጠብ አሰራር ወርሃዊ ቁጠባውን እንዲያከናውንና እጣው በወጣለት ጊዜም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መኖሪያ ቤቱን እንዲረከብ በማድረግ የአስተማማኝ ኑሮ ዋስትና እንዲያገኝ ያግዛል በማለት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ቃል ሲናገሩ፤ እያንዳንዱ ቤት ፈላጊ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ቢያንስ በየወሩ እንዲቆጥብ የተተመነበትን ሂሳብ በአግባቡ ከቆጠበ፣ እጣው በደረሰው ወቅት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቤቱን ተረክቦ ኑሮውን ይጀምራል ማለታቸው እንደሆነ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ለ10ኛ ዙር ባለ እድለኞች የቀረበላቸው መመሪያ ግን ዱብ እዳ ነገር ነው፡፡ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በቅርቡ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሁን የተገነቡት ቤቶች ዋጋ የልደታ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ግንባታ ሲካሄድ የተፈጠረውን የዋጋ ልዩነት ታሳቢ በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም ቤቶቹን ለመገንባት ይፈጃል የተባለው ተመን የ20 በመቶ የጭማሪ ማሻሻያ እንደተደረገበት አስታውቋል፡፡ ልብ በሉ! እንግዲህ ቤቶቹን የሚገነባው አካል በተፈጠረበት የዋጋ ንረት መሰረት የ20 በመቶ ጭማሪ ሲያደርግ የከተማው ነዋሪውም ከሚያገኘው ገቢ ላይ በንጽጽር የዚያኑ ያህል የዋጋ ንረት ይገጥመዋል ማለት ነው፡፡
ሆኖም የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ከሁለት ዓመት በፊት ሚኒስትሩ የተናገሩትንና ተግባራዊ ይሆናል ብለው ቃል የገቡትን ውሳኔ ወደ ጐን በመተው፣ ስለ እድለኞች የመኖሪያ ቤት ርክክብ በሚያስረዳው መመሪያ ላይ በቀረበው የዋጋ ትመና መሰረት፤ ለ10/90 ቤቶች በካሬ ሜትር 1ሺ 910 ብር፤ ለ20/80 ስቱዲዮ 2ሺ 483 ብር፤ ለ20/80 ባለ አንድ መኝታ ቤት 3ሺ 438 ብር፤ ለ20/80 ባለ ሁለት መኝታ ቤት 4ሺ 394 ብር እና ለ20/80 ባለ ሶስት መኝታ ቤት 4ሺ 776 ብር መጨመሩ ታውቋል፡፡ ከዚህ ሌላ የ10/90 ባለዕድለኞች 10 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ሲጠበቅባቸው፤ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድለኞች ደግሞ የ20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ይኖርባቸዋል ይላል፡፡ እንደ ቤቶቹ አይነትና ስፋት እያንዳንዱ ባለ እድለኛ ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍል የቀረበለት ተመንና ከሁለት ወር የእፎይታ ጊዜያት በኋላ በ15 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የወርሃዊ ክፍያ ተመን ጭንቅላት አስይዞ የሚያስጮህ፤ የሚያስበረግግ ምናልባትም እንደ እብድ በየጎዳናው ላይ ለብቻ እያወሩ እንዲጓዙ የሚያደርግ ነው፡፡ ለዚህ ነው አንዳንዱ ነዋሪ እጣው “እንኳንም አልደረሰኝ!!” ያለው፡፡
እንደ ማሳያ ለማቅረብ ያህል፣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት የደረሰው ባለ እድለኛ አለ እንበል፡፡ አፍ ሞልቶ በእርግጠኝነት ይኖራል ማለት አስቸጋሪ ስለሚሆን ብቻ ዝም ብለን አለ እንበል፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ለባለሁለት መኝታ ቤት የሚከፍለው ጠቅላላ ክፍያ ብር 317068 ይሆናል፡፡ በመመሪያው መሰረት፣ 20 ከመቶ ቅድሚያ ክፍያ መክፈል ስላለበት 21 ወራት እንኳን ቆጥቧል ቢባል (560 ብር x 21 ወራት = 11,760 ብር) ይመጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ባለ እድለኛ 51,653 ብር ገደማ ለቅድሚያ ክፍያ አቅርቦ ከንግድ ባንክ ጋር መዋዋል ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ይሄ ብር ከየት ይመጣል? ኧረ በምን ስሌት ይሆን ከሁለት ወር የእፎይታ ጊዜ በኋላ በየወሩ 2,700 ብር ከፍሎ በ15 ዓመት ውስጥ እዳውን የሚያጠናቅቀው? ምግብ አይበላም? የትራንስፖርት ወጪ የለበትም? ለልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ አይከፍልም? እንደው በደፈናው ቤቱ ይድረሰው እንጂ ከባሌም ከቦሌም ብሎ ይክፈል በሚል የኢኮኖሚክስ መርህን በሚጥስ ስሌት ተዘጋጅቶ የቀረበ መመሪያ ነው የሚመስለው፡፡ ይሄ በእውነቱ “መንግስት አበደ እንዴ?” ያሰኛል፡፡ ግን መንግስት ቢያብድ ምን ይሆን የሚደረገው? መንግስት የኑሮውን ሁኔታና ክብደት መረዳት ይከብደው ይሆን እንዴ? የተማረ ኢኮኖሚስት ጠፍቶ ነው ወይስ የፖለቲካ ደባና ሴራ እየተካሄደ ነው? ለነገሩ ይህቺ ከተማ ለድሆች ፊቷን ካዞረች ሰነባብታለች፡፡
አንዳንዱ ሰው እኮ በአምላክ ተዓምር ካልሆነ በቀር፣ ልጆቹን እንዴት እያሳደገ እንደሆነ ማሰብ ሁሉ ይከብዳል፡፡ በዘመናዊ የሽፍን መኪና የምትመላለሱ የፖለቲካ አመራሮቻችን፤ መንግስት በአነስተኛ ክፍያ ቤት እየሰጣችሁ የምትኖሩ ባለስልጣኖቻችን፤ ልጆቻችሁን የተሻለ ት/ቤት የምታስተምሩ አለቆቻችን… እስኪ ለአንድ ወር እንኳን የእኛን የድሃዎቹን የአኗኗር ዘይቤ ኑና ተቋደሱ!!
መንግስትና አገሪቷን እየመራ ያለው ኢህአዴግ፣ በምርጫ ዋዜማ በእርግጥም ይህን አይነት የፖለቲካ ኪሳራ የሚያከናንብ ድርጊት አምኖበት ይሆን የፈጸመውን? እስኪ እውነት እንነጋገር ከተባለ መንግስት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቤቶች መስሪያ የተበደረውን 1 ቢሊዮን ብር ለማስመለስ ዋስትና ማቅረብ ይሳነዋል? የትኛውስ ኢትዮጵያዊ ነው የባንክ እዳውን መከፈል ሳይችል ቤቱ ውስጥ መኖር የሚችለው? እውነት ንግድ ባንክ እዳቸውን ያልከፈሉ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በሃራጅ ሸጦ ብሩን ማስመለስ ያቅተዋል?
ኢህአዴግ ትላልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን እየመራ፣ እነዚህን ጥቃቅን የሆኑ፣ ነገር ግን ህዝብን የሚያማርሩ ስህተቶችን እንዴት ይፈጽማል?  በአፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የሰለጠኑ አገራት አመራሮች እኮ ስህተት ተፈጽሞ ሲገኝ በይፋ ህዝባቸውን ይቅርታ ጠይቀው የእርምት እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ እኔማ አንዳንዴ መንግስትንና ህዝብን የማቃቃር ተልእኮ ያነገቡ ጸረ ሰላም፤ ጸረ ዲሞክራሲና ፀረ ልማት ሀይሎች በመዋቅሩ ውስጥ እንዳይኖሩ እሰጋለሁ፡፡ ኢህአዴግ ሆይ፤ አሁንም የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አልረፈደም። ኧረ ጎበዝ ልብ እንበል!

Read 3780 times