Tuesday, 14 April 2015 07:56

የቢዝነስ ሰዎችን መወንጀል፤ “ቱባ ባህላችን” ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“መንግስት የሌሎች አገራትን ያህል የነዳጅ ዋጋ የማይቀንሰው ለምንድነው?” ብለን ግን አንጠይቅም
     በያዝነው ሳምንት እና ከዚያም በፊት በኢዜአ የተሰራጩ ሁለት ሦስት ዜናዎችን ተመልከቱ። በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደታየ የገለፁ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ፤ ከዚሁ ጋር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ቅናሽ ግን አልታየም ሲሉ የአገሪቱን ነጋዴዎች እንደወቀሱ አትቷል ኢዜአ - ረቡዕ እለት ባሰራጨው ዜና። አዎ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በግማሽ ያህል መቀነሱ እውነት ነው። የተጣራ ነዳጅ (ለምሳሌ የቤንዚን) ዋጋም እንዲሁ ቀንሷል - በ35 በመቶ ገደማ። በአገራችንስ ምን ያህል እንዲቀንስ ተደረገ? ወደ 15 በመቶ ገደማ ብቻ ነው የቀነሰው። ዋጋውን የሚተምነው ደግሞ የንግድ ሚኒስቴር ነው። በአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል ያልቀነሰው ለምን ይሆን? ኢዜአ ይህን ጥያቄ ለሚኒስትር ዴኤታው አላቀረበም። ነጋዴዎችን መወንጀል ነው ቀላሉ ነገር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ አዱኛ፣ የአገሪቱ የንግድ አሰራር የገበያ  ህግንና ስርዓትን እንደማይከተል ጠቅሰው፤ ነጋዴዎች ግልፅነት በጎደለው አርቴፊሻል የዋጋ ትመና እንደሚሰሩ ተናግረዋል ይላል ኢዜአ። “ይህም በመሆኑ፣ በአለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ በቀነሰበት ወቅት በኢትዮጵያ ሸቀጦች ላይ ግን ቅናሽ ሳይታይ ቀርቷል”በማለት እኚሁ ምሁር ማስረጃ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ለመሆኑ ኢኮኖሚስቱና ኢዜአ የት አገር ነው ያሉት? በአለም ገበያ ከታየው የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ማስተካከያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዳይሆን የተደረገው በንግድ ሚኒስቴር የዋጋ ትመና እንጂ በነጋዴዎች ምርጫ አይደለም። በየወሩ የንግድ ሚኒስቴር የሚያወጣውን የዋጋ ተመን ራሱ ኢዜአ ይዘግባልኮ። ግን፤ ይህችን እውነታ ከማገናዘብ ይልቅ፤ የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የመወንጀል ባህልን ጠብቆ ማቆየትና “ማስቀጠል” ይበልጥብናል መሰለኝ።
የንግድ ሚኒስትር ዴኤታውም እንዲሁ፤ የአገራችን የነዳጅ ዋጋ የሌሎች አገራትን ያህል እንዳይቀንስ የተደረገው በመስሪያ ቤታቸው የዋጋ ትመናና ውሳኔ መሆኑን ይዘነጉታል? ከአለም የነዳጅ ገበያ ጋር በአገራችን የሸቀጦች ዋጋ ያልቀነሰው ነጋዴዎች በሚከተሉት ብልሹ አሰራር ምክንያት እንደሆነ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሚናገሩት። ምን የሚባል ብልሹ አሰራር? ሚኒስትር ዴኤታው አንድ ሁለት እያሉ ይዘረዝራሉ። በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ ዋጋን በስምምነት የመወሰን አሰራር አለ ብለዋል። የተለያዩ ኩባንያዎችን በማዋሃድ ሞኖፖል የመፍጠር አሰራርም አለ ብለዋል።
እስቲ አስቡት። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የኩባንያ ባለአክሲዮኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጣሉ ኩባንያቸውን ለሁለት ለሶስት ሲሰነጥቁ እንጂ፤ ውህደት ሲፈጥሩ አይታችኋል? ወይስ ስለ ሌላ አገር ነው የሚናገሩት? የቢዝነስ ሰዎች የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሲወስኑስ የሚታዩትስ የት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች፣ የሸቀጦችን ዋጋ በስምምነት ሊወስኑ ይቅርና፤ ሰላምታ ለመለዋወጥም ያህል የመቀራረብ ልምድ የላቸውም። የገበያ ውድድርን እንደጠላትነት ነው የሚቆጥሩት። ለነገሩ ሚኒስትር ዴኤታውም ይህንን እውነት አይክዱም። በንግድ ማህበረሰብ ውስጥ፣ ሁልጊዜ በተወዳዳሪነት ለመቀጠል በፅናትና በትጋት የመስራት ባህልን ከማሳደግ ይልቅ፤ አንዱ ተወዳዳሪ ሌላውን ለማጥፋት የመመኘት ባህል እንደሚታይ ገልፀዋል ዴኤታው።
እና እንዲህ አይነት ባህል ይታይባቸዋል የተባሉት ነጋዴዎች፤ በምን ተአምር ነው ከእለት ተእለት የሸቀጦችን ዋጋ በምክክር ለመወሰንና ከዚያም አልፈው ኩባንያዎቻቸውን ለማዋሃድ የሚስማሙት? ግን፤ እንዲህ አይነቶችን ጥያቄዎች እያነሳን ነገሩን መመርመር አንፈልግም - ብዙዎቻችን። በአጠቃላይ ለቢዝነስ ስራዎች አወንታዊ አመለካከት የለንማ። እንዲኖረንም አንፈልግማ። አንዳንዶቻችን ከእውቀት እጥረትና እጦት የተነሳ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን በክፉ አይን እንመለከታለን። በእድሜ ገፋ ያሉት ብዙዎቹ ምሁራን፤ የደርግ አይነት የሶሻሊዝም አባዜ ተጠናውቷቸው “በዝባዥ ከበርቴዎችን” በመፈክር ማውገዝ ይናፍቃቸዋል። አንዳንዶቹ ወጣት ምሁራንም እንዲሁ፤ የቢዝነስ ስራንና የቢዝነስ ሰዎችን የሚያወግዝ የትምህርት ቅኝት ውስጥ ተነክረው ከወጡ በኋላ፤ ዞር ብለው ነገሩን ለመመርመር አይሞክሩም። ያንኑን ቅኝት ሲያስተጋቡ ይኖራሉ። በዚያ ላይ... ብዙዎቻችን በደፈናውና በጭፈን የታቀፍነው ነባሩ ፀረ-ቢዝነስ ቱባ ባህላችን ከጉያችን እንዲርቅ ፈቃደኞች አይደለንም። በማናቸውም ሰበብ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን ማውገዝና መወንጀል ለብዙዎቻችን ሱስ ሆኖብናል ማለት ይቻላል።
እንዲያ ባይሆን ኖሮማ፤ እውነታውን ለማየትና ለማገናዘብ ዳተኛ ባልሆንን ነበር። ከደርግ የሶሻሊዝም ስርዓት ወዲህ፤ መጠነኛ የነፃ ገበያ አሰራር በመፈጠሩ ብቻ፤ የቢዝነስና የንግድ ውድድር እንደተሻሻለ የበርካታ ኢኮኖሚስቶች ጥናት ያረጋግጣል። በየጊዜው የዋጋ ንረት የሚፈጠረውም፤ መንግስት አለቅጥ በሚያሳትመው የብር ኖት ምክንያት እንደሆነ የመንግስት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። በ2000 ዓ.ም፣ ከዚያም እንደገና በ2003 ዓ.ም ጣራ የነካ የዋጋ ንረት የተፈጠረው፤ በሌላ ሰበብ ሳይሆን የብር ኖር በገፍ ስለታተመ ነው። የአገሪቱ ውስጥ የተሰራጨው የብር ኖት በግማሽ አመት ውስጥ በሃምሳ በመቶ ያህል ሲጨምር፤ ብር መርከሱና የዋጋ ንረት መከሰቱ ይገርማል እንዴ? ይሄው ነው በ2003 ዓም የተከሰተው። ራሱ መንግስት ለፓርላማ ያቀረበው ሪፖርት መሆኑንም ልብ በሉ።
እንዲያም ሆኖ፤ ሁሌም በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ላይ ነው የሚሳበበው። ለመሆኑ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት የዋጋ ንረቱ ረገብ ያለው፤ የነጋዴዎችና የቢዝነስ ሰዎች ባሕርይ ስለተለወጠ ይሆን? አይደለም። መንግስት የብር ህትመቱን ረገብ ስላደረገ ነው የዋጋ ንረት የተረጋጋው - ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም። እውነታው የዚህን ያህል ግልፅ ቢሆንም፤ ነጋዴዎችንና የቢዝነስ ሰዎችን በጭፍን የማውገዝ ሱሳችን እንዲቀርብን ስለማንፈልግ፤ እውነታውን አይተን እንዳላየን ማለፍን እንመርጣለን።
እስቲ ተመልከቱ። ከአመት በፊት የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል፣ 110 ዶላር ገደማ ነበር። መቶ ሊትር ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ደግሞ በ100 ዶላር ገደማ እየተገዛ ወጪ ነበር። ያኔ የአንድ ሊትር የችርቻሮ ዋጋ በንግድ ሚኒስቴር ተመን 20 ብር ከ50 ሳንቲም ነበር የምንገዛው። ካለፈው ሰኔ በኋላ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ሲጀምር፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ መቶ ዶላር፤ የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ደግሞ ወደ 95 ዶላር ገደማ ወረደ - በነሐሴ ወር። ነገር ግን፤ የንግድ ሚኒስቴር በወቅቱ የችርቻሮ ዋጋ ለመቀነስ አልፈለገም። በአለም ገበያ ግን የነዳጅ ዋጋ በዚህ አላቆመም።
መስከረምና ጥቅምት ላይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ ዘጠና ብር፣ ከህዳር በኋላ ከሰባ ዶላር በታች ወርዶ ታህሳስ ላይ ነው 60 ቤት የገባው። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ፣ መቶ ሊትር ቤንዚን በአማካይ በ72 ዶላር ወጪ ነው ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ የነበረው። እንግዲህ አስቡት። የመቶ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከመቶ ዶላር ወደ 72 ዶላር ቀንሷል። ከታህሳስ ወዲህ ደግሞ ከ65 ዶላር በታች ሆኗል። በብር ሲመነዘር አንዱ ሊትር ከ13 ብር በታች ይሆናል ማለት ነው። የንግድ ሚኒስቴር ግን፤ የነዳጅ የችርቻሮ የአለም ገበያን በሚመጥን ሁኔታ እንዲቀንስ አላደረገም። 20 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረውን የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ፤ ቢያንስ ቢያንስ ወደ 14 ብር ማውረድ ነበረበት። ግን አላደረገውም። 17 ብር ከ50 ነው ያደረገው።
ለምን? የተለያዩ አጓጉል ምክንያቶች ሲቀርቡ እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። በአለም ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም የቤንዚን ዋጋ ያን ያህልም አልቀነሰም የሚል ሰበብ ቀርቦ ነበር። ይሄ ሃሰት ነው። የአለም ዋጋ ከመቀነሱ በፊት፣ ለበርካታ ወራት እየጨመረ ስለነበረ፣ ብዙም ለውጥ የለውም የሚል ማመካኛም ቀርቦ ነበር። ይሄም ሃሰት ነው። የነዳጅ ዋጋ ካለፈው ሰኔ ወር በፊት ለሁለት አመታት ያህል ብዙ ውጣውረድ አልነበረውም። እና እውነተኛው ምክንያት ምንድነው? ማለቴ የንግድ ሚኒስቴር የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በአግባቡ ያልቀነሰበት ምክንያት ምንድነው? እስቲ በኢዜአ የተሰራጨ ሌላ ዜና ተመልከቱ።     
በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ መንግስት እንደተጠቀመ የገለፀው ኢዜአ፤ በስምንት ወራት ውስጥ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለማዳን ተችሏል ሲል ዘግቧል። 20 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው። ነዳጅ ወደ አገር የሚገባበት ወጪ ከቀነሰ፤ ለምን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዚያው መጠን አልቀነሰም? መንግስት እንዳሰኘው ሊያተርፍብን ፈርልጎ ይሆን? የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ በሰጡት ምላሽ፣ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በተወሰደነ ደረጃ ብቻ እንደቀነሰ ጠቅሰው፤ ሌላው ትርፍ ግን እስካሁን የተከማቸ የውጭ እዳ ለመክፈል እየዋለ መሆኑን ገልፀዋል።


Read 1680 times