Monday, 06 April 2015 09:27

ፌዴሬሽኑ በ9 የወዳጅነት ጨዋታ ዕድሎች አልተጠቀመም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባለፉት ሁለት ወራት ለ9  የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄዎች ቀርበውለት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጠቀማቸው መቅረቱን አስታወቀ። የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ለመገናኛ ብዙሃናት በኢሜል ባሰራጨው መግለጫ የፌደሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በህጋዊ መንገድ ለሚቀርቡ የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ በአፋጣኝ መስጠቱ እንደሚታመንበት ተገልፆ፤ የወዳጅነት ጨዋታዎቹ በሚኖራቸው ጠቀሜታ፤ በሚጠይቁት ወጪ እንዲሁም ከኘሪሚየር ሊግ ውድድሮች ጋር አጣጥሞ ለማካሄድ በሚያስችል የሥራ መመሪያ እንደሚመለከታቸው አስታውቋል፡፡
ለፌዴሬሽኑ ከኮሎምቢያ  የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ እንደቀረበለት  በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆችና በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው ዘገባም ተስተባብሏል። ፌዴሬሽን ጥያቄውን እንዳልተቀበለ ተቆጥሮ የተሰራጩት ትችቶች አንዳችም መሠረት የላቸውም ብሏል መግለጫው፡፡ ጨምሮ አስታውቋል፡፡ በየትኛውም አይነት የመገናኛ ዘዴ ይፋዊ በሆነ መንገድ ከላይ ከተጠቀሰው ሀገር ፌዴሬሽን፣ በፊፋ እውቅና ከተሰጣቸው ወኪሎችም ሆነ ከማንኛውም ኤጀንት ለፌዴሬሽኑ የደረሰው አንዳችም አይነት የጽሑፍም እና የድምጽ መልዕክት የለም ተብሏል፡፡  በየካቲት እና በመጋቢት ወራት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ጨዋታ ለማካሄድ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና በወኪሎች አማካኝነት በርካታ የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄዎች ለፌዴሬሽኑ በኢሜይል አድራሻው እንደተላኩ የሚገለፀው መግለጫ በአጋጣሚዎቹ ለመጠቀም ያልተቻለባቸውን ምክንያቶችም ዘርዝሯል፡፡
የከ23 ዓመታት በታች የወዳጅነት ጨዋታ ከቱኒዚያ ጋር በወኪል አማካኝነት፣ የዋናው ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ከየመን ጋር  በዶሀ ኳታር በየመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት፣ ከሁንደራስና ከኤልሳልቫዶር ጋር በዋሽንግተንና በኒውዮርክ ሲቲ በወኪል አማካኝነት፣ ከቶጐ ብሔራዊ ቡድን ጋር በወኪል አማካኝነት፣ከ2ዐ ዓመት በታች ከጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ጋር በጅቡቲ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠያቂነት፣ ከሴንትራል አፍሪካን ሬፖብሊክ ጋር በወኪል አማካኝነት፣ ከኮትዲቭዋር ብሔራዊ ቡድን ጋር በአቢጃን በፊፉ በወኪል አማካኝነት፣ ከሲሸልስ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሲሸልስ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት፣ ከግብፅ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር በግብፅ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት የተወሰኑ ወጪዎችን በመሸፈን ለፌዴሬሽኑ በኢሜይል አድራሻው የተላኩት ናቸው፡፡
በመጋቢት ወር የፊፋ መርሃግብር መሠረት የወዳጅነት ጨዋታ ያልተካሄደው በከ23 ዓመት በታች የማጣሪያ  ውድድሮች ምክንያት ዋናው ብሔራዊ ቡድን ባለመሰባሰቡ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም በተለያዩ ኘሮግራሞች በመያዙ፣ እንዲሁም በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅትና እና በአህጉራዊ የክለቦች ውድድር ምክንያት የዝግጅት ጊዜው በማጠሩ ምክንያት ነው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የ10 ወራት ግምገማና አጠቃላይ ሪፖርት በወቅቱ ተጠናቅቆ አለመቅረቡም እንደተጨማሪ ምክንያት ይወሰዳል በሚል መግለጫው አመልክቷል፡፡

Read 1209 times