Saturday, 21 March 2015 10:53

ባሬቶ ይቀጥላሉ!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 6 ወጣቶች ለካምፕ ስልጠና ወደ አውሮፓና አሜሪካ  ይላካሉ
ዋልያዎቹ በ56 ሚ. ብር ዋና ስፖንሰር አግኝተዋል
  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መስራት ከጀመሩ 1 ዓመት ሊሞላቸው ወር የቀራቸው ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከሃላፊነቱ እንዲነሱ  ግፊት ቢደረግባቸውም በሃላፊነታቸው ይቀጥላሉ፡፡ አሰልጣኙ ሊባረሩ  እንደሚችሉ አሉባልታዎች እየተነገሩ ቢቆይም ስለጉዳዩ ምንም የተለየ ነገር እንዳልሰሙ፤ በሚቀጥለው ሰሞን ሚዲያውን በጉዳዩ ላይ ከፌደሬሽኑ ጋር ለማወያየት እንደታሰበና እንደ እቅዳቸው መስራት ባይችሉም በኢትዮጵያ እግር  ኳስ ውስጥ ለማሳካት የፈለጉትን ለውጥ መሰረት ለማስያዝ በጀመሯቸው ተግባራት  ትኩረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ባረፉበት ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከስፖርት አድማስ ጋር አጭር  ውይይት ያደረጉት አሰልጣኝ ባሬቶ በሃላፊነታቸው ዙርያ ስለተነሳው አሉባልታ ብዙ እንደማይጨነቁ ተናግረው፤ በዓላማቸው ለመስራት የሚያደርጉትን ጥረት እንደቀጠሉ ገልፀዋል፡፡ ይህን ለማስገንዘብም ሲሉ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙበትንና በጥብቅ ክትትል የመለመሉዋቸውን ስድስት ወጣት ተጨዋቾች ለ1 ወር የካምፕ ስልጠና ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ ለመላክ ማረጋገጫ ማግኘታቸውን አሳውቀዋል፡፡ ከስድስቱ የወደፊት የብሄራዊ ቡድን ተስፋ የሚሆኑ ተጨዋቾች ሁለቱን በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ በሚገኝ ክለብ እንዲሁም  አራቱን በፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ በነፃ 1 ወር የካምፕ  ስልጠና ልምድ እንዲወስዱ  የግል ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ተጨዋቾቹን ለብሄራዊ ቡድን ለማዘጋጀት የፈጠርኩት   እድል ነው ያሉት አሰልጣኙ በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ በሚገኝ ክለብ ለሁለት ወጣት ተጨዋቾች ሁኔታውን ያመቻቹት ለስብሰባና ለስልጠና በሄዱበት ወቅት ባደረጉት ምክክር እንደሆነ ገልፀው፤ የፖርቱጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን አካዳሚ ደግሞ ለ10 ዓመታት በሰጡት ግልጋሎት ላቀረቡት ማመልከቻ ተገቢውን ድጋፍ እንደሰጣቸው ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ ከስድስቱ ተጨዋቾች ሁለቱ በበረኛነት የሚጫወቱ እንደሆነ የጠቆሙት ባሬቶ ሁሉም በካምፕ ቆይታቸው ለ30 ቀናት በፕሮፌሽናል ክለብ በሚሰሩት የስልጠና መርሃ ግብር የማነቃቂያ ልምድ ያገኛሉ ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሄኒከን ኩባንያ ጋር በመመካከር በእረፍት ቀናት በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በርካታ ታዳጊ ቡድኖች የሚሳተፉባቸው ውድድሮችን በየሳምንቱ በማዘጋጀትና በቅርብ ክትትል በመስራት ለዘላቂ ለውጥ መነሻ የሚሆን የእድገት ስትራቴጂ ለመጀመር እየሰሩ መሆናቸውንም አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ “በየእሁዱ 300 ልጆች ወደ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም እንዲመጡ እጠብቃለሁ፡፡ ሜዳውን ለ3 እከፍልና 7ለ7 ሆነው እየተቧደኑ በአንድ አሠልጣኝ እየተመሩ ሲጫወቱ ለማየት ጉጉት አለኝ፡፡ ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች በቶሎ ተመልክቶ ለመሥራት የሚያግዝ የውድድር ዓይነት ነው፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ብዙ የሉም እንጂ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሠራት ያለበት ነው፡፡ ወደፊት በስፋት እንዲሠራበት ማነቃቃት እፈልጋለሁ፡፡ ልጆችን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም እድል መስጠት ለእያንዳንዱ ቡድን ኳስ ለመስጠትና ማሊያና ምግብ ለማቅረብ የበኩሌን ጥረት እያደረኩ ነው፡፡ ከሁሉም ሰው ጋር ግልጽ ግንኙነት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ወደዚህ ስመጣ በወጣቶች እግር ኳስ ልማት ላይ የመሥራት ዋና አላማ ነበረኝ፡፡” ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ሀ-17 ሊግ መጀመሩን አውቃለሁ የሚሉት ማሪያኖ ባሬቶ፤ ቅድምያ ተሰጥቶ መሠራት ያለበት በሀ-21 መሆን እንደነበረበት ገልፀው፤ ወደ ብሔራዊ ቡድን ወጣቶችን ለማሳደግ የሚያመች አሠራር መኖሩ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ ብለዋል፡፡  ሥራዬን በ23 ምክንያቶች መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ እንደምክንያትም የወጣት ተጨዋቾችን ሥም ዘርዝረዋል፡፡ ታሪኩ ፣ ኪብሮም፣ አንዳርጋቸው፣ ናትናኤል፣ ዳዊት፣ ራምኬል፣ አብዱልከሪም…ወዘተ በማለት ለእነሱ ተጨዋቾች የማልታገለው ፈተና የለም በማለት፡፡ ኢትዮጵያውያን በሥራዬ ደስተኛ እንደሆኑ ነው የምረዳው፡፡ ተጨዋቾቼም ደስተኛ ናቸው፡፡ የውጭውን እድል የሚያገኙ ወጣቶችን ምርጫ የማደርገው እራሴው ነኝ፡፡ የማማክረው ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን የማከናወን ፍላጐት አለኝ የሚሉት አሠልጣኙ፤ በተለይ በቅርቡ የቼልሲ ክለብ አካዳሚ ለመጐብኘት ቀጠሮ ይዣለሁ ብለው ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ ከሞውሪንሆ ጋር በጣም ጓደኛሞች መሆናቸው እና በጉብኝታቸው ወቅት በክለቡ አካዳሚ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ያሉትን እድሎች መመልከት እንዳሰቡ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ሔኒከን ቢራ ፋብሪካ ዋልያዎቹን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በዋልያ ቢራ እና ድራፍት ምርቶቹ በዋና ስፖንሰርነት በ56 ሚሊዮን ብር ለመደገፍ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከትናንት በስቲያ ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ ዋልያ ቢራ እና ድራፍት የብሄራዊ ቡድኑ ዋና ስፖንሰር ሆኖ  በየዓመቱ 14 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያበረክት ሲገለፅ የብሄራዊ ቡድኑን ውጤታማነት   እንደሚደግፍም ታውቋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ያገኘው የስፖንሰርሺፕ ገቢ በአሰልጣኙ መነሳት ላይ የተፈጠረውን ግፊት አብርዶታል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃናት ባደረሰው አጭር መግለጫ በማርያኖ ባሬቶ ዙርያ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ የተነጋጋረበት ሁኔታ አለመኖሩን  ገልፆ ነበር፡፡ በዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ጉዳይ ላይ በአፈጻጸም ሪፖርቶችና ሙያዊ ግምገማዎች ላይ በመመስረት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚከተለውን አቅጣጫ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በወቅቱ እንደሚያደርስም በወቅቱ መግለፁ አይዘነጋም፡፡ ይህን ተከትሎ ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝን በተመለከተ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ትናንት ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን በአሰልጣኙ መነሳትና መቀጠል ዙርያ ምን ውሳኔ እንዳሳለፈ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፖርቱጋላዊው የ58 አመት አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ  በ2 አመት ኮንትራት ለማሰራት መፈራረሙ የሚታወስ ነው፡፡  
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኃላፊነት ያስቀመጣቸው የቴክኒክ ዲፓርትመንትና ቴክኒክ ኮሚቴ ከአሠልጣኙ ጋር ግንኙነታቸው የሻከረ መሆኑ  ጫና እንደፈጠረ የሚገለፅ ሲሆን፤ በዋናው ብሄራዊ ቡድን ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ  ባለመቻሉና ከዚያም በኋላ ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በመምራት  ከመላ አፍሪካ ጨዋታዎች  በመቅረታቸው በአንዳንድ ሚዲያዎች እና የስፖርት አፍቃሪዎች ከሃላፊነታቸው ይነሱ የሚለው አጀንዳ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖባቸዋል፡፡  አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ከሶስት ሳምንት በፊት ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ፌደሬሽኑ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በነበሩ እቅዶች መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡  አሰልጣኙ ዋናው ብሄራዊ ቡድኑ በሃላፊነት ለመምራት ሲረከቡ   እቅዳቸው በወጣቶች ላይ መስራት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡   ከ7 በላይ የሚሆኑ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን  በማሳደግ  ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ማርያኖ ባሬቶ በቆይታቸው በነጥብ ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉት አንድ ጨዋታ ብቻ መሆኑ ብሄራዊ ቡድኑ እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኑ በሜዳው ማሸነፍ አለመቻሉም ተተችቷል፡፡ በአጠቃላይ 19 ጨዋታዎች ተጫዉተው በ12ተሸንፈው በ4ቱ አቻ ወጥተው 3ቱን አሸንፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ታሪክ ባለፉት 56 ዓመታት ከ20 በላይ አሰልጣኞች በሃላፊነቱ የተፈራረቁ ሲሆን ከእነሱ መካከል ባሬቶን ጨምሮ ከስምንት አገራት የተውጣጡ 10 የውጭ አገር አሰልጣኞች ሰርተዋል፡፡ የውጭ አገር አሰልጣኝ በአፍሪካ ደረጃ ለሚይዘው ብሄራዊ ቡድኑ በአማካይ እስከ  4 ዓመታት የሚቆይ የስራ ኮንትራት ማስፈለጉ ቢገለፅም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሩት አንዳቸውም በሃላፊነቱ ከሁለት ዓመታት በላይ አልቆዩም፡፡ ከማርያኖ ባሬቶ በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን የቻሉ የውጭ አገር አሰልጣኞች መካከል   በ1959 ለሁለት አመታት የቼኮስላቫኪያው ጂሪ ስታሮስታ ፤ በ1961 እኤአ አንድ አመት ላልሞላ ጊዜ የዩጎስላቪያው ስላቫኮ ሚሎሶቪች፤በ1968 ሃንጋሪያዊው ስዙክስ ፈርኔክ ለ1 ዓመት፤ በ1974 ጀርመናዊው ፒተር ሽትናይገር ለሁለት ዓመት ፤ በ1988  ጀርመናዊ ክላውስ ኢግናሃብሰን ለአንድ አመት ፤ በ2002 ጀርመናዊው ጆሃን ፊገ ለ10 ወራት፤ በ2006 እኤአ ፈረንሳዊው ዲያጎ ጋርዚያቶ ለ14 ወራት፤ በ2010 እኤአ ስኮትላንዳዊው ኢፊ ኦኑራ ለ9 ወራት፤ በ2011 ቤልጅማዊው ቶም ሴንትፌንት ለ6 ወራት ብቻ እንደሰሩ ከብሄራዊ ቡድኑ የታሪክ መዝገብ ለመረዳት ይቻላል፡፡

Read 1539 times