Monday, 16 March 2015 09:36

አሉባልታና የአገራችን ሚዲያ በ”ቴአትረ ቦለቲካ”

Written by  ዮሐንስ ገለታ
Rate this item
(2 votes)

ርዕስ፡ ቴአትረ ቦለቲካ - አሉባልታና የአገራችን የፖለቲካ
        ገመና
ጸሐፊ፡         ልደቱ አያሌው
የታተመበት ዓ.ም.፡     2007
የገጽ ብዛት፡     287
የመጽሐፉ ዋጋ፡     ብር 100

አሉባልታና ሚዲያ
አቶ ልደቱ አያሌው በቅርቡ ያሳተሙትን ሦስተኛ መጽሐፋቸውን አነበብኩት፡፡ ከግል ልምዳቸው ምሳሌዎችን እያጣቀሱ ያቀረቡት ታሪክ ራሳቸውን ንጹህ አድርጎ ከማቅረብም በላይ ማሕበረሰባዊ ትንታኔ የሚሰጥ ሥራ ነው፡፡ መጽሐፉ  በአገራችን የፖለቲካ ስሪት ውስጥ አሉባልታ ምን ያክል ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ በማሳየት የጸሐፊውን ፖለቲካዊ ብስለት ይጠቁማል፡፡
ቴአትረ ቦለቲካ በአገራችን ፖለቲካ (ወይም በመጽሐፉ ርዕስ ላይ ጸሐፊው በገጠር የንግግር ዘዬ እንዳስቀመጡት  “ቦለቲካ”) አሉባልታ ምን ያክል ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በሰፊው ያብራራል፡፡ ለአሉባልታ መስፋፋትም ሆነ ዕውነትን አጣርቶ ለሕዝቡ ባለማቅረብ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ነው። የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ውስጥ በሚዲያ የሚሰራጭ አሉባልታ ለምን ተዓማኒነት እንደሚያገኝ ለመግለጽ “እኔም እንደዚያው ነበርኩ” በማለት የራሳቸውን ልምድ ምሳሌ በማድረግ ያስረዳሉ፡፡ “ትግሉን በተቀላቀልኩበት ወቅት በጋዜጦችና በአንዳንድ የውጭ ሬዲዮ ጣቢያዎች ኢህአዴግንም ሆነ በወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ አባል የነበሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በተመለከተ የሚወራውን አሉባልታ በሙሉ እኔ ራሴ ያለምንም መጠራጠር እውነት አድርጌ የማይ ሰው ነበርኩ፡፡
“በእርግጥ ለአብዛኛው ሕዝብ በሚዲያ የሚሰራጭ መረጃ ሀሰት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠር ራሱ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ይህ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመኔታ መገናኛ ብዙኃኑ የሙያ ስነ ምግባር ያልጠበቀ ተግባር ለመፈፀም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይም በጋዜጣና በሬዲዮ ውሸት የማይነገር መስሎ የሚታየው ግንዛቤው ዝቅተኛ የሆነው የሕብረተሰብ ክፍል፣ የሚባለውን ሁሉ ወዲያው አምኖ በመቀበል፣ እኔን በየአካባቢው ለማማትና ለመሳደብም ሆነ በእኔ ላይ ለማዘንና ለመዛትም ብዙም ጊዜ አልወሰደበትም”፡፡ በጋዜጠኞች ኢ-ሥነምግባራዊ በሆነ አሠራር በርካቶች የአሉባልታ ሰለባ ሆነዋል፡፡” ከእነኚህ ግለሰቦች ውስጥ አንዱ እንደሆኑ  የሚያስረዱት አቶ ልደቱ፤በአሉባልታ ምክንያት በደል የደረሰባቸው እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የትግል አጋሮቻቸውም ጭምር መሆናቸውን በመጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ከምርጫ 97 ጋር ተያይዞ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የተከሰተውን ክፍፍልና የጸሐፊውን ተሳትፎ በስፋት የሚዳስሰው ቴአትረ ቦለቲካ፤ የጋዜጠኛውን መረጃን አጣርቶ ሃቁን የማቅረብ ችሎታ በተደጋጋሚ ይጠይቃል፡፡  በ1996 ዓ.ም. ክረምት ላይ “የአቶ ልደቱ ወንድም የድሬዳዋ ከንቲባ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሾሙ” የሚል ዜና በወቅቱ ሕትመት ላይ በነበረው ኢትኦጵ ጋዜጣ ላይ መውጣቱን ጸሐፊው እንደ አንድ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ የተሾሙት ግለሰብ ከአቶ ልደቱ ጋር አንድ ዓይነት የአባት ስም ከመያዛቸው በቀር የሚጋሩት ነገር የነበረ ባይሆንም ይህ ዜና በተለይም በውጭ አገራት ጸሐፊው ኢህአዴግ መሆናቸውን ማሳመኛ ተደርጎ እንደቀረበ ይናገራሉ፡፡ በመጽሐፉ የተጠቀሱ ይህን መሰል ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች ጋዜጠኞቻችን የግል አቋማቸውን ወደ ጎን በመተው ለሙያ ስነ ምግባራቸው ብቻ ተገዢ ለመሆን አለመቻላቸውን ለማሳየት ጸሃፊው ተጠቅመውበታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርብ አሉባልታ ምን ያህል ለረጅም ጊዜ ዕውነት ሆኖ እንደሚቆይ የምንረዳው ደግሞ አቶ ሲሳይ አያሌው (የድሬዳዋ ከንቲባ ሆነው ሲሾሙ የአቶ ልደቱ አያሌው ወንድም መሆናቸው የተወራባቸው)”በሙስና ተጠርጥረዋል ተብለው መታሰራቸው ሲወራ አንድ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ ስልክ ደውሎ ‘ስለ ወንድምዎ ስለ አቶ ሲሳይ አያሌው መታሰር ምን አስተያየት አለዎት?’ ብሎ እንደጠየቃቸው ሲገልጹልን ነው፡፡
ጋዜጠኛው ከሚያገለግለው ሕዝብ የሚለየው አንድ ነገር ቢኖር ጠያቂነቱ ነው፡፡ ሌላው የተጣራ ዕውነትን ማዳረስ፡፡ ጋዜጠኛው በጥቂቱ እንኳን እነዚህን ሆኖ ካልተገኘ ለሕዝቡ የሚያቀርበው ሥራ አስከፊ የሆነ ውጤት የሚያስከትል ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህም በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና በሌሎች አገሮች የታሪክ አጋጣሚ የታየ ነገር ነው፡፡ ከምርጫ 97 በፊትና በኋላ በነበሩት ሁነቶች ሁሉ ጋዜጠኞቻችን “ለምን?” ከማለት ይልቅ ያልተጨበጠ መረጃ ይዞ በማራገብ ሥራ ተጠምደው እንደነበር መጽሐፉ ምሳሌዎችን እየጠቀሰ ያሳያል፡፡ በ1995 ዓ.ም፣ መጨረሻ አካባቢም የሆነው ይሄ ነው፤ በቴአትረ ቦለቲካ ውስጥ እንደተገለጸው፡፡ በዚህ ወቅት ኢህአፓ አንድ አገር አቀፍ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት እንዲቋቋም ጥረት እያደረገ ነበር፡፡ አቶ ልደቱ አባል የነበሩበት ፓርቲ ጥምረቱ ውስጥ እንዲካተት ምንም ዓይነት ግብዣ ሳይደረግለት “ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ሊሠራ የማይፈልግ አፈንጋጭ ነው” እየተባለ ሲወራ በወቅቱ መጠየቅ የነበረበትን ወሳኝ ጥያቄ ለማንሳት የሞከረ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረም፤ “ኢዴፓ የወያኔ ተለጣፊ ነው ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ ለምን አብሮን ሊሠራ አይፈልግም እያላችሁ ትከሱታላችሁ?” የሚል፡፡     
የጠያቂነትና መርማሪነት ያለመኖር አንድ ነገር ነው። የሚዲያው ክፍተት ግን ከዚህም እንደሚብስ ይገልጻሉ- ጸሃፊው፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 146 ላይ የቀረበው የቅንጅት የቅድመ ውሕደት ስምምነት ለዚህ እንደ ማስረጃ ቀርቧል። በ1998 ዓ.ም. “የተፈረመው ሰነድ አራቱ ድርጅቶች በምን ሁኔታና ቅደም-ተከተል ውህደት ለመፍጠር እንደተስማሙ የሚያሳይ ቢሆንም በማግስቱ ለኅትመት የበቁት አንዳንድ ጋዜጦች ግን “አራቱ ፓርቲዎች ተዋሃዱ” የሚል የተሳሳተ ዜና ለሕዝቡ ዘገቡ”። በወቅቱ ወረቀት ላይ ሰፍሮ የነበረውን ግልፅ መረጃ አንብቦ ለሕዝቡ ማቅረብ ሲቻል፣ጋዜጠኞች ግን በግድ የለሽነት የተዛባ መረጃን ዘግበው ለሕዝቡ አቀረቡ ሲሉ ጸሃፊው ወቅሰዋል፡፡    
የአቶ ልደቱ መጽሐፍ ሚዛናዊነትን መሳትና የመረጃን ትክክለኛነት ማጣራት የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ ችግር እንዳልሆነም ይገልጻል፡፡ አቶ ኤልያስ ክፍሌ በ1998 ዓ.ም. ከፓርቲ አባልነታቸው የተሰረዙ ግለሰብ ናቸው፡፡ ስለዚህም “በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ለመስጠት የሚያስችል የኃላፊነት ድርሻ አልነበራቸውም። …ነገር ግን የቅንጅት አመራሮች በታሰሩበት ወቅት አቶ ኤልያስን፤ ‘የቅንጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል’ እየተባሉ በቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራም ቃለ-መጠይቅ ከመስጠትም አልፈው ለቢቢሲ የሀርድ ቶክ-ፕሮግራም ጭምር የቅንጅቱ ልዩ አማካሪ ነኝ በማለት ራሳቸውን ሹመው ቃለ-መጠይቅ ሰጥተዋል” (ገጽ 175)፡፡ ቢቢሲ ለጉዳዩ ሩቅ ስለሆነ ለዚህ አሳፋሪ ስህተት ይቅርታ ቢደረግለትም አቶ ኤልያስን “የቅንጅቱ ከፍተኛ አመራር አባል” ብሎ ቃለ መጠይቅ የወሰደው ጋዜጠኛ ግን በአገሩ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ከፍተኛ ተደማጭነት በነበረው ተቋም ውስጥ እያገለገለ ከተሳሳተ ምንጭ የተገኘ መረጃ ማቅረቡ የጋዜጠኛውን ስነምግባር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስህተት ነው፡፡----  
ቴአትረ ቦለቲካ  ይህን የመሳሰሉ የጋዜጠኛው የሥነምግባር ጉድለቶች ያላቸውን ክስተቶች በድፍረት  ያጋልጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚሠሩ ጋዜጠኞች ችግሮች የሚመነጩት ከሚሠሩበት ተቋም ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ከራሳቸው ግላዊ ባሕሪ እንደሆነ ይደመድማል። “…የጋዜጠኞቻችን ችግር የሚመነጨው በዋናነት ከሚሠሩበት ተቋም ፖሊሲ ሳይሆን ከራሳቸው ግላዊ ባህሪ መሆኑን እንድንገነዘብ አርጎናል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪና ሙያዊ ስነ-ምግባር በውስጡ እስከሌለ ድረስ  የኢትዮጵያ ወይም የአሜሪካ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ተቀጣሪ ሆኖ በመሥራቱ ብቻ ከችግር ሊፀዳ እንደማይችል ታዝበናል”
በመጨረሻም በመጽሐፉ ውስጥ ከተጠቀሱት አጋጣሚዎች ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የጥምር መንግሥት ለማቋቋም ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረበበትን እንደ የመጨረሻ ምሳሌ ላንሳ፡፡ በወቅቱ ሕትመት ላይ የነበረው አባይ የተሰኘ ጋዜጣ “ቅንጅቱና ህብረቱ የጥምር መንግስት እንዲቋቋም ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጥያቄ አቀረቡ” የሚል ዜና ይዞ ወጣ፡፡ ይህንን ጉዳይ በዝርዝር ያስቀመጡት አቶ ልደቱ፤”በወቅቱ ቅንጅት ውስጥ ተወካይ የነበሩትን እነ ዶ/ር ኃይሉ አርአያን ለምን ቅንጅቱ የጥምር መንግሥት ጥያቄ ለአቶ መለስ እንዳቀረበ ጠየቅናቸው፡፡ … ስለ ጥምር መንግሥት ጥያቄ የተደረገ ውይይትም ሆነ የተወሰነ ውሳኔ እንደሌለና በጋዜጣ ስለወጣው ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገለጹልን፡፡ በማግሥቱ ፓርላማ ይገባ-አይገባ? በሚለው አጀንዳ ላይ ለመነጋገር የቅንጅቱ አመራሮች ስብሰባ በግሎባል ሆቴል ተጠርቶ ስለነበር በዚያ ስብሰባ ላይ እኔ ራሴ በአካል ተገኝቼ ቅንጅቱ የጥምር መንግሥት ጥያቄ ማቅረብ አለማቅረቡን ጠየቅሁ” ይላሉ፡፡
የቅንጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልም እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እስካሁን እንዳልወሰኑና ቅንጅቱ እነሱን ሳያማክር እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሊወስን እንደማይችል መልስ ይሰጣሉ፡፡ ከስብሰባው በኋላ አቶ ልደቱ በውጭ አገር ከሚገኝ አንድ የሚዲያ ተቋም በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ ቅንጅት የጥምር መንግሥት ጥያቄ እንዳላቀረበ ይናገራሉ፡፡ ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን አዲስ ዜና በመባል ይታወቅ የነበረው የእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋዜጣ ላይ በወቅቱ አቶ ልደቱ የተናገሩት “ውሸት እንደሆነና ቅንጅቱ ጥያቄውን ተነጋግሮበትና አምኖበት ለመንግሥት እንዳቀረበው” አድርገው ቃለ መጠይቅ ይሰጣሉ፡፡  
ታዲያ ጸሐፊው ይህንን አጋጣሚ ተርከው ሲጨርሱ፤ “በወቅቱ እኔን በጭፍን ከመተቸት በስተቀር ስለዚህ ጉዳይ እውነቱን አጣርቶ ለሕዝብ ለማሳወቅ የሞከረ አንድም ጋዜጠኛ አልነበረም” ሲሉ ቁልፍ ጥያቄ በውስጠ ታዋቂነት ያነሳሉ፡- የጋዜጠኛው ጠያቂነት እስከ ምን ድረስ ነው?    
መካተት ያልነበረበት
አቶ ልደቱ በምርጫ 97 በነበረው የፖለቲካ መነቃቃት ሕዝቡ “ማንዴላ” ብሎ የሰየመኝ ከፍታ ላይ እንዳልነበርኩ ባውቅም ጥቂት ቆይቶ ያው ሕዝብ “ከሀዲ ነው” እንዳለኝም ያክል አይደለሁም ይላሉ፡፡ ራሳቸውን እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ እና ጠንካራ ጎኖች ያሉት ፖለቲከኛ አድርገው ማቅረባቸው እሰየው የሚያስብል ቢሆንም ቴአትረ ቦለቲካ ጸሐፊው ራሳቸውን ከመጠን በላይ አጋንነው ያቀረቡበት ትርክት እንዲመስል የሚያስችሉ ምዕራፎችን ከማካተት አላመለጠም፡፡ ከገጽ 117 ጀምሮ በአስር ገፆች የተተረከው ወ/ሮ የሺ የተባሉ ሴት ስለ ጸሐፊው ያዩት ሕልም አንዱ ነው፡፡ በተለይም ወ/ሮ የሺ ስለ ፖለቲካ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው፤ አቶ ልደቱንም ከዚያ ህልም በፊት የማያውቁ፤ በፆምና በጸሎት ይኖሩ የነበሩ “የእግዜር ሴት” መሆናቸውን ስናነብ፣ ጸሐፊው ራሳቸውን በምን መልክ እያቀረቡልን ነው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርጉናል፡፡ በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ የወ/ሮ የሺ ሕልም ጸሐፊው የሆነ ዓይነት በእግዜር የተመረጡ ፖለቲከኛ እንደሆኑ አድርጎ ለማቅረብ ጥረት የተደረገበት መስሎ ይታያል፡፡ የተክለ ሰብዕና ግንባታ መሠረቱን ሲጥልም እንታዘባለን፡፡
በተጨማሪም አቶ ልደቱ ከፓርቲያቸው አመራርነት ሲሰናበቱ በባልደረቦቻቸው ከተበረከተላቸው የፎቶ ስጦታ ላይ የተወሰዱ የስንብትና የመልካም ምኞት መግለጫ ጽሑፎች ምንም እንኳ እነኚያ ግለሰቦች ስለ እሳቸው የሚሰማቸው ዕውነተኛ ስሜት ቢሆንም ለአንባቢው ማቅረቡ ግን ሌላ የተክለ ሰብዕና ግንባታ ከመሆን የዘለለ ትርጓሜ ሊገኝለት አይችልም፡፡
ሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች ጸሐፊው በትክክል ምን ዓይነት ሰውና ምን ዓይነት ፖለቲከኛ እንደሆኑ በሚገባ ያሳያሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳቸውን ለመግለጽ ምንም ዓይነት አርያማዊ ጣልቃ ገብነት ላያስፈልጋቸው ይችል ነበር፡፡ የሌሎች ፖለቲከኞች ምስክርነትም እንደዚያው፡፡ ስለዚህም እነኚህ ሁለት ነጥቦች በቴአትረ ቦለቲካ ባይካተቱ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡  
መልዕክተ ልደቱ - ለወጣቱ
የተቃዋሚው ጎራ አሁንም ድረስ በ”ያ ትውልድ” የመጠፋፋት መንፈስ የሚመራ፤ አምባገነን፤ ተፎካካሪን እንደ ጠላትና ደመኛ የሚያይ፤ ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ በአገር ጉዳይ ላይ በጋራ ለመሥራት የማይፈልግ የተበታተነ ኃይል እንደሆነ በተጨባጭ ማስረጃዎች ያቀረበው ቴአትረ ቦለቲካ ፤በአገራችን ፖለቲካ የቀረንን ተስፋ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው፡፡ በእርግጥ አብዛኛው ሕዝብ በፖለቲካው ተስፋ ከቆረጠ መሰነባበቱ የሚታወቅ ነው፤በተለይም ወጣቱ፡፡ በአገሩ ጉዳይ እንደማያገባው ሁሉ ፖለቲካዊ ስሜቱ እንዲጠፋ ለተደረገው ወጣት ተስፋ የሚኖር ከሆነም ተቃዋሚዎችንም ሆነ ገዢውን ፓርቲ የሚተቹት አቶ ልደቱ በሰጡት ምክር ውስጥ ነው “… በአሁኑ ወቅት በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ዙሪያ የተሰለፉ የፖለቲካ መሪዎች የተሻለ ስርዓት ለአገራችን ያመጣሉ ብላችሁ አትጠብቁ፡፡ በእነሱ ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጥ የራሳችሁን ዘመንና አስተሳሰብ ወኪል የሆነ አዲስና ብቁ የፖለቲካ አመራር ከውስጣችሁ ለመፍጠር ታገሉ” (ገጽ 183)
በአጠቃላይ ስናየው የአቶ ልደቱ መጽሐፍ ተራ መስሎ የሚታየን የአሉባልታ ጉዳይ ምን ያክል ስር የሰደደ አገራዊ ሳንካ እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ መጽሐፉ ተዳፍኖ የነበረን መረጃ በድፍረት ለሕዝብ ለማቅረብ የተደረገ ሙከራ ከመሆንም በላይ የማሕበረሰባችን አስተሳሰብና የምንይዘው አቋም ምን ያክል ባልተጣራ መረጃ ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል እና  በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዲያው የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በዝርዝር የሚዳስስ መጽሐፍ ነው፡፡ ቴአትረ ቦለቲካ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች እንዲሁም በሚዲያ የቀረበለትን መረጃ ሁሉ እንደ ዕውነት ቆጥሮ ውሳኔ ላይ የሚደርሰውን ሕዝብ ጭምር የቤት ሥራ የሚሰጥ መጽሐፍ በመሆኑ ሊነበብ ይገባዋል እላለሁ፡፡   

Read 3869 times