Wednesday, 11 March 2015 11:30

የአማርኛ ፊልሞች በባለሙያዎቹ ዓይን ብዛት ላይ እንጂ ጥራት ላይ አልተተኮረም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

     ባለፉት ጥቂት አመታት የአማርኛ ፊልሞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረና በዘርፉም የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን እያደገ መጥቷል፡፡ የፊልም ስራ አዋጪ መሆኑ የገባቸው አያሌዎችም የኖሩበትን ስራ ትተው ወደ ዘርፉ ተቀላቅለዋል፡፡
በፊልም ኢንዱስትሪው የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን ዛሬ አንድ ፊልም በሚሊዮን ብሮች ለመሸጥ በቅቷል፡፡ ለምሣሌ “ህይወቴ” የተሰኘው ፊልም በ1.2 ሚ ብር እንደተሸጠ ታውቋል፡፡ ለፊልም ተዋናዮችና ለፊልም ስክሪፕት የሚከፈለው ገንዘብም በከፍተኛ መጠን እንደጨመረ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ዘርፉ እድገት ያሳየው በየዓመቱ በሚወጡ ፊልሞች ብዛት እንጂ ጥራት አይደለም፡፡
ከሶስት እና አራት ሳምንት በላይ በስክሪን ላይ የማይቆዩ አንዳንድ የአማርኛ ፊልሞች ገና “በዳዴ ላይ የሚገኘውን የፊልም ኢንዱስትሪ ወደ ኋላ እየጎተቱት ነው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ አንጋፋው የፊልም ባለሙያና ምሁር ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ  የኢትዮጵያን የሲኒማ ዕድገት በተመለከተ ተጠይቀው በሰጡት መልስ፤ “በመጀመሪያ አሁን የሚሰሩት ቪዲዮዎች ናቸው እንጂ ፊልሞች አይደሉም፤ በአንዲት ቅንጣት ሁነት ላይ ተመስርተው የሚሰሩ “ሲት ኮሞች” ናቸው፡፡ እናም ሲኒማና ቪዲዮን አትቀላቅሉ፡፡ ሁለቱ ፍፁም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እዚህ ፊልም ሰራሁ ይልና ቲያትሩን በክሎዝ አፕ (በቅርብ እይታ) ያሳያል፡፡ በቃ ይሄ ሲኒማ ነው ይላል፡፡ ሲኒማ እኮ እውነታዊ ምትሃት ነው፤ እያታለለ የሚያዝናናህ። ለእኔ ዛሬ ዛሬ ከሚሰሩ ሲኒማዎች ይልቅ የቀደምቶቹ ለሲኒማ እጅግ የቀረቡ ናቸው፡፡ እነ “ጉማ”፣ እነ “ሂሩት አባቷ ማነው?” እነ “አስቴር”… ከአፍሪካ ሲኒማ ጋር ሲታዩ የሚኖሩ ፊልሞች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የፊልምና ትያትር ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ኃይማኖት ዓለሙም የኃይሌ ገሪማን ሃሳብ የሚጋራ አስተያየት ሰጥቶ ነበር፡፡ “እውነቱን ለመናገር የአገራችን የፊልም ስራ ሲጀመር ከነበረበት ደረጃ ማደግና መሻሻል ሲገባው፣ እንደ ካሮት ተክል ቁልቁል እያደገ የሄደ ይመስለኛል፡፡ ሙያውን ድንገት በርካቶች ያለ እውቀትና ያለ ልምድ ገብተውበት አራክሰውታል፡፡ ዛሬ በፊልም ስራ ላይ ተሰማርተናል የሚሉ ሰዎች ቆም ብለው የሰሯቸውን ስራዎች ቢመለከቱ እነሱ ራሳቸው “ምን ነክቶን ነው?” የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ሲኒማ ከባለሙያው ይልቅ በተመልካችና በፕሮሞተሮች እየተመራ ነው፤ ይህ ነገር መቋጫ ሊኖረው ይገባል”
የብሉ ናይል የፊልም ማሰልጠኛ አካዳሚ ባለቤት ሲኒማቶግራፈር አብርሃም ኃይሌ ብሩ በበኩሉ፤ የአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ ማደግና መጠንከር ባለበት ደረጃ ባይሆንም፣ መሞከሩ በራሱ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሲኒማ ሙያ በቂ ዕውቀትና ልምድን ይጠይቃል የሚለው ሲኒማቶግራፈሩ፤ ትምህርቱ በትምህርት ቤት በሚገኝ ዕውቀት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑን ገልጿልበ - በሙያው የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ካላቸው ሙያተኞች ጋር አብሮ በመስራት፣ ደጋግሞ በመሞከርና ጊዜ በመውሰድ ራስን ማሻሻል እንደሚቻል በመጠቆም፡፡
“በውጪ አገር አንድ ሰው የራሱን ፊልም ለመስራት ከስምንት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ሊፈጅበት ይችላል። ትምህርቱን ጨርሶ ሲወጣ ሦስተኛ ረዳት ሆኖ ነው ስራ የሚጀምረው፡፡ ቀስ እያለ ልምዱን እያዳበረ ሲመጣ ረዳት ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ዋና ሆኖ የራሱን ስራ የሚሰራው፡፡ እዚህ የሚታየው ግን ከዚህ የተለየ ነገር ነው፡፡ ሁልጊዜ አዳዲስ ሰዎች ወደ ስራው ሲገቡ ታያለሽ። “ደጋግሜ ሰርቻለሁ” የሚልሽም ቢሆን ካለፈው ስራው የተማረው ነገር አይታይም፤ ስራዎቹ ይነግሩሻል፡፡ ተመልካቹ ራሱ እኮ መልስ ይሰጣል፡፡ “የፊልሙን ጅማሬ ሳየው መጨረሻውን መናገር እችላለሁ” ይልሻል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተመልካቹ ወደ ሲኒማ አዳራሹ የሚመጣው የእውነት ፊልም ልይ ብሎ ነው ወይንስ ሌሎች አማራጭ መዝናኛዎች በማጣት አሊያም ጊዜ ለማሳለፍ ፈልጎ ነው?” ያስብልሻል፡፡ እናም መሞከሩ ጥሩ ነገር ሆኖ መሻሻልና መጠንከሩ ላይ ግን ብዙ የሚቀረው ነገር አለ፡፡” ብሏል - የፊልም ባለሙያው፡፡
በበርካታ የአማርኛ ፊልሞች ላይ በዳይሬክተርነትና ፕሮዱዩሰርነት በመስራት የሚታወቀው ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዕድገት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይናገራል፡፡ ዘርፉ የራሱ ደካማ ጎኖች እንዳሉት ግን አልሸሸገም፡፡ የሲኒማ ስራ ወደ ጥሩ አቅጣጫ እየሄደና የራሱን አብዮት እየፈጠረ ነው ያለው ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜው ግሩም ባለሙያዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ይናገራል፡፡
“ከካሜራ ፊትም ሆነ ከካሜራ ኋላ  መስራት የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ልጆች እየመጡ ናቸው፡፡ እነ ሄኖክ አየለ፣ እነ ይድነቃቸው ሹመቴ፣ እነ አብይ ፈንቴ፣ እነ ቅድስት ይልማና ሄርሞን ኃይላይን የመሳሰሉ ዳይሬክተሮችን እንዲሁም እነ ሚካኤል ሚሊዮን፣ ግሩም ኤርሚያስና ሳምሶን ቤቢን የመሳሰሉ የፊልም ተዋንያኖችን እያየን ነው” ብሏል፡፡ የዚያኑ ያህልም ፊልሞች በብዛት እየተሰሩ ነው፤ ከ2004 ጀምሮ በየዓመቱ የሚወጡ ፊልሞች ቁጥር ጨምሯል፤ ከ120 ፊልሞች በላይ ለእይታ ይበቃሉ። ይህ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው” ሲል ዘርፉ ተስፋ ሰጪ እየሆነ መምጣቱን ይገልፃል፡፡ ሙያው በትምህርት መደገፍ እንዳለበት ግን ይናገራል፡፡ ጥቅሙንም ሲያስረዳ፤ “የትምህርቱ መኖር ያለአግባብ የሚወጣውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በእጅጉ ይቀንስልናል” ብሏል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፊልም ስራ ውስጥ ስሙ እየገነነ የመጣው ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ይድነቃቸው ሹመቴ በበኩሉ፤ በሲኒማ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታየ ያለው መነቃቃት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁሞ፤ በሚወጡት ፊልሞች የጥራት ደረጃ ላይ ተገድ ቅሬታውን ገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂ የሚያመጣቸው አዳዲስ ነገሮች በአነስተኛ ወጪ የተሻሉ ነገሮችን ለመስራት እንድንችል ቢያደርጉንም እኛ ግን ልንጠቀምባቸው አልቻልንም ብሏል፡፡ “ፊልሞች በብዛት የሚወጡትን ያህል ጥራት ያለው ስራ ተሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡
ሁልጊዜም ከሚወጡ አዳዲስ ፊልሞች ጋር የሚመጡት አዳዲስ ልጆች ናቸው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን እያሻሻሉ የሚመጡ ሰዎች አይታዩም” ያለው ይድነቃቸው ሹመቴ፤ “ፊልም እየተደጋገመ በተሰራ ቁጥር በራሱ የሚጨምረውና የሚያሳድገው ነገር አለ። ስለዚህም ከቀድሞ ስራዎቻችን እየተማርን የተሻሉ ነገሮችን ሰርተን ለተመልካች ማቅረብ ይገባናል” በማለት ሃሳቡን ሰንዝሯል፡፡
የፊልም ሙያ ስልጠናና ትምህርትን አስመልክቶ ሲናገርም፡- “ሙያውን ለማሳደግ የትምህርትና ስልጠና ጉዳይ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ሆኖም በአገራችን የሚገኙት የፊልም ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እጅግ አነስተኛ ናቸው፤ በቂ አይደሉም፡፡ ትምህርቱና ስልጠናው በበቂ ሁኔታ ቢኖር በትምህርት የታነጸና ታሪኮቹን በብቃት መናገር የሚችል አቅም ያለው ባለሙያ ማፍራት ይቻል ነበር ብሏል፡፡ ከትምህርት ሌላ በሙያው በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ለአዳዲሶቹ ዕውቀታቸውን ማካፈልና መንገዱን ማሳየት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ ይናገራል፡፡
የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮች ማህበር ምክትል ሊቀመንበርና የ”ስርየት” እና “ፔንዱለም” ፊልሞች ፕሮዱዩሰር እንዲሁም የቶም ቪዲዮ ማሰልጠኛ ባለቤት ቶማስ ጌታቸው፤ የአገሪቱ የሲኒማ እድገትን በሁለት ደረጃ ከፍሎ ማየት ይገባል ይላል፡፡ ኢንዱስትሪው ገና አዲስና ወጣት ከመሆኑ አንፃር ብዙ ፊልሞች በማውጣት እንዲሁም በድምፅና በምስል ጥራት ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፀው ባለሙያው፤ ከጭብጥ አንፃር ግን ብዙ እንደሚቀረው ጠቁሟል፡፡
“ፊልሞቻችን ከታሪክና ከጭብጥ አንፃር ብዙ ጉድለቶችና ድክመቶች አሉባቸው፤ አንዳንድ ጊዜ እንደውም፣ እየባሰበትና ወደ ኋላ እየተጎተተ ነው እንዴ? የሚያሰኙ ስራዎችን እያየን ነው፡፡ በዓመት ከሚወጡት ከ100 በላይ ፊልሞች አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸውበ የተሻሉ የሚባሉ” ብሏል፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪው ሌላ ማነቆ በቂ የሲኒማ ማሳያ አዳራሾች አለመኖር ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፤ ያሉትም ቢሆኑ ከተመልካቾች ምቾትና ከድምፅ ጥራት አንፃር ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ሥር በሚተዳደሩት ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ አምፔርና ሲኒማ አምባሳደር ፊልሞችን አስገብቶ ለማሳየት ቢያንስ አንድ ዓመት ወረፋ መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያስረዳሉ፡፡
አለም ሲኒማ በግል ሲኒማ ቤት ዘርፍ ግንባር ቀደም ሲሆን፤ ከዚያም ኤድናሞል፣ ሴባስቶፖል፣ አጐና፣ ፍፁም፣ ጣሊያን ት/ቤት ሲኒማ፣ ዮፍታሔ፣ ዋፋ፣ አቤልና አዶት ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡  
ብዙዎቹ የፊልም ባለሙያዎች በእነዚህ የግል ሲኒማ ቤቶች ፊልም ማሳየት ውጣ ውረድ የበዛበትና በፈተና የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ፊልሞቹ በምን መስፈርት እንደሚመረጡ ግልፅ መመዘኛ የሌለበት፣ ሲኒማው መመረጥ ያልቻለበት ምክንያት የማይታወቅበት፣ ግልፅነት የሌለው አሰራር የተንሰራፋበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንድ በሲኒማ አዳራሽ ውስጥ የተቀመጠ ፊልም መዛኝ “ይህንን አክተር ቀይረው፡፡
እስከ ማለት የሚደርስ ድፍረት አለው፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነው፡፡ ሲኒማ አዳራሾች ትርፍን ማዕከል አድርገው የተሰሩ በመሆናቸው ገበያ የሚያስገኝላቸውን ነገር መምረጣቸው ተገቢ ቢሆንም ፊልም ሰሪውንም ሆነ ተመልካቹን እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ ለመውሰድ መሞከራቸው ትክክል አይደለም” በማለት ይህም ለዘርፉ ዕድገት ማሽቆልቆል የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና እንዳለው ይገልፃሉ፡፡
የፊልም ሽልማቶችና ፌስቲቫሎች የሲኒማውን ኢንዱስትሪ ለመደገፍና ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አስተዋጽኦዋቸው የላቀ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እነዚህ ሽልማቶችና በየጊዜው የሚዘጋጁ የፊልም ፌስቲቫሎች የውድድር መንፈስ በመፍጠር ባለሙያዎችን ለተሻለ ሥራ ያነቃቃሉ፡፡
በዚህ ረገድ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሳይቋረጥ የተካሄደው “የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የፊልም ፌስቲቫል” በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ሁለተኛ ዙር የሽልማት ሥነስርዓቱን በቅርቡ ያካሄደው “ጉማ አዋርድ”ም እንደአጀማመሩ ከዘለቀ ለኢንዱስትሪው ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይቀርም፡፡

Read 2968 times