Saturday, 21 February 2015 13:31

የቀለም ቆጠራ ጉዳይ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአማርኛ ሥነ ድምፀልሳን (ፎኖሎጂ) በአጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ የቀለም ቆጠራ በሙላት እና በቅጡ ያልተጠና በመሆኑ በዚህ መስክ እስካሁን ያለን ዕውቀት ያልተሟላ፣ ያልተደራጀና “ግልብ” ዓይነት ነው ማለት ሳይቻል አይቀርም። በአማርኛ ሥነግጥም የቀለም ቆጠራ መርህ በብዙ መልኩ የተዛባና አሳሳች ሆኖ በመቆየቱ፣ የግጥም ዓይነቶች ምደባችንም እንደዚሁ ቅጣንባር የሌለው ወደመሆኑ ተቃርቧል።
ይህንን መወናበድ ዮሐንስ ሰ. የተባሉ ጸሃፊ በጋዜጣችሁ ባቀረቧቸው መጣጥፎች ማለፊያ አድርገው አቅርበውታል። ጸሐፊው ነቅሰው ያወጡዋቸው ስህተቶችና መደናገሮች ትክክለኛ እና ተገቢ ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ።
ዕውቀት እምነት አይደለም፤ ይመረመራል፤ ይፈተሻል፤ በየጊዜውም ይሻሻላል። ዕውቀትን በጭፍን ተቀብሎ አምልኮ ማድረግ ከጠማማና ከጽልመት ጎዳና አያወጣም። በቅጡ የተረዱትን ምርመራ በትሁት ድፍረት ማቅረብም ተገቢና የሕልውናም ጉዳይ ነው።
ስለ አማርኛ ሥነግጥም እስካሁን ከቀረቡት ሐተታዎች የመንግስቱ ለማ በብዙ መልኩ የተሻለው ነው፤ ጥቂት ማጠናከሪያ ግን ያስፈልገዋል። የብርሃኑ ገበየሁ፣ “የአማርኛ ሥነግጥም” በብዙ መልኩ የተሟላና  የተደከመበት ነው። ነገር ግን፣ በተለይ ቀለም ቆጠራንና፣ የግጥም ምደባዎችን በተመለከተ ብዙ እንከኖች አሉበት። መጽሐፉ ማስተካከያና እርማቶች ተደርገውበት፣ በሁለተኛ ኤዲሽን፣ ሊታተም ይገባ ነበረ። ነገር ግን ይሔን እንዳንጠብቅ የሚያደርገን አሳዛኝ ነገር አለ፤ አሁን ደራሲው በሕይወት የለም።
በየትኛውም መንገድ ቢሆን በአንድ የዕውቀት ዘርፍ ላይ አማራጭ መጻሕፍት የመኖራቸው ፋይዳ አሌ የሚባል አይደለም። በዚህ አጋጣሚ፣ በቅርቡ ለሕትመት የሚበቃ የአማርኛ ሥነግጥም መጽሐፍ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ብገልጽም መልካም ነው።
በማጠቃለያውም፣ ዮሀንስ ሰ. የተባሉት ጸሐፊ፣ ላቀረቡት ማለፊያ ትንተና፣ ከልቤ ያደንቅኋቸው መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ።
አብነት ስሜ፤ (የቋንቋና የሥነጽሑፍ መምህር፣ የ“ኢትዮጵያ ኮከብ” እና የ“ፍካሬ ኢትዮጵያ” ደራሲ)

Read 2643 times