Saturday, 14 February 2015 14:50

ትላልቅ ሆቴሎች ለፍቅረኞች ምሽት ሽርጉድ እያሉ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዳንስ ውድድር፣ ኮሜዲ፣ የፍቅር ዜማዎች፣ እራትና ወይን ጠጅ
የሆቴሎቹ የመዝናኛ ክፍያ ከ600 ብር - 5ሺ ብር ይደርሳል

   በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም የሚከበረውን የፍቅረኞች ቀን (Valentine’s day) ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባን ጨምሮ በሃዋሳ ቢሾፍቱና ላንጋኖ የሚገኙ ትልልቅ ሆቴሎች ለፍቅረኞች ምሽት ሽርጉድ እያሉ ሲሆን ለለያዩ መዝናኛዎች ከ600 ብር እስከ 5ሺ ብር ይጠይቃሉ፡፡ የቀይ አልባሳት ገበያ መድራቱንም ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡
አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጐዳና ላይ የሚገኘው ንግስተ ሳባ ሆቴል ዛሬ ማታ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ የፍቅር ዜማዎችና ግጥሞች ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡ አርቲስት አስቴር በዳኔ የንግስተ ሳባን የፍቅር ታሪክ በአጭር ድራማና መነባንብ መልክ ለታዳሚዎች ታቀርባለች፡፡ ንግስተ ሳባ ሆቴል ከአብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጁት በዚህ ልዩ የፍቅር ምሽት፤ በጥንዶች መካከል የሳልሳ፣ የትዊስትና ዋልዝ ዳንሶች ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ለሶስት አሸናፊ ጥንዶች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺ ብር የሚያወጣ የእራት፣ የአልጋና የቁርስ ግብዣ ይደረግላቸዋል፤ ብሏል - ጋዜጠኛና ፕሮሞተር አብርሃም ግዛው በምሽቱ ዝግጅት የኮሜዲ ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን ፕሮግራሙን ታዋቂ አርቲስቶች ይታደሙታል ተብሏል፡፡
በማማስኪችን እንዲሁ የፍቅረኞች ምሽት የተዘጋጀ ሲሆን አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በስራዎቹ ታዳሚውን ያዝናናል ተብሏል፡፡ መግቢያ 50 ብር እንደሆነም ታውቋል፡፡ በቫራይቲ ሬስቶራንት የፍቅረኞች ምሽት ዛሬ 11፡30 የሚጀምር ሲሆን ልዩ የእራት ፕሮግራም፣ የዲጄ ሙዚቃ፣ ለጥንዶች የሚበረከት ሰርፕራይዝ ስጦታና ሌሎች ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል፡፡
ኔክሰስ ሆቴል፤ ልዩ የቡፌ እራት ከልዩ ልዩ የወይን ጠጆች ጋር ያሰናዳ ሲሆን የቫዮሊንና የፒያኖ ሙዚቃ ይቀርባል፡፡ ሰርፕራይዝ ስጦታም ይኖራል ተብሏል፡፡ የብራይት ካፌ የፍቅረኞች ምሽት ፕሮግራም የሚጀምረው ዛሬ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሲሆን ከ10 በላይ ድምፃዊያን በአኩስቲክ ባንድ ታጅበው ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሳልሳ ዳንስ፣ ስታንዳፕ ኮሜዲና ሌሎች አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡ ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስና እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ቴዎድሮስ መኮንን (ቴዲ ማክ) በክብር እንግድነት እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ በሳሮ ማሪያ ሆቴል ደግሞ ለፍቅረኞች ልዩ የእራት ፕሮግራም፣ ሰርፕራይዝ ስጦታዎችና ሌሎች ዝግጅቶች እንዳሉ ታውቋል፡፡
ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የሚገኘውና ባለፈው አመት የተከፈተው ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል፤  ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የጥንዶች መግቢያ 600 ብር ነው፡፡  ሆቴል ሲዮናትም ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ማዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ ልዩ ልዩ የፍቅር ሙዚቃዎች በዲጄ የሚቀርቡ ሲሆን፤ የጥንዶች መግቢያ 900 ብር ነው ተብሏል፡፡ ከነአንካሬ ዛሬ ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ነው በሩን ለፍቅረኞች ክፍት የሚያደርገው፡፡ ልዩ የብፌ እራት እንዲሁም የዲጄ ሙዚቃም አሰናድቷል፡፡
ሃዋሳ የሚገኘው ኬራውድ ሆቴል፤ ፕሮግራሙን ከዋዜማው ምሽት የጀመረ ሲሆን የዲጄ ሙዚቃ፣ ልዩ የወይን ጠጅ እንዲሁም ልዩ እራት በማሰናዳት ፍቅረኞች ዕለቱን መቼም  እንዳይዘነጉት ለማድረግ እየታተረ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የአዲስ አበባው ዩጐቪያ ክለብ በበኩሉ የምሽቱን ታዳሚዎች የሚያዝናናው ከተወዳጁ ድምፃዊ አብነት አጐናፍር ጋር እንደሆነ ገልጿል፡፡ ጥንዶች ይሄ የደመቀ የፍቅረኞች ምሽት እንዳያመልጣቸው የግብዣ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የቢሾፍቱው ፒራሚድ ሪዞርት፤ የጥንዶች ውድድርና የፍቅር ፊልሞችን ለታዳሚዎቹ ያዘጋጀ ሲሆን ልዩ እራት ከልዩ የወይን ጠጅ ጋር ማሰናዳቱንም ጠቁሟል፡፡ ሀርመኒ ሆቴልም እንዲሁ ሚካኤል ለማን ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር አቀናጅቶ ምሽቱን ለፍቅረኞች ውብና አስደሳች ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ልዩ እራት ከወይን ጋር፣ የኮሜዲ ምሽትና የፍቅረኞች ስጦታ አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡ በሃርመኒ ሆቴል ምሽቱን ለማሳለፍ ላቀዱ ጥንዶች 1800 ብር፣ ብቻውን ለመጣ 900 ብር ይከፍላሉ፡፡
በደብረዘይት የሚገኘው አሻም አፍሪካ ሪዞርት፤ ለምሽቱ ልዩ ራት ከዋይን ጋርና የዲጄ ሙዚቃ ያዘጋጀ ሲሆን በሪዞርቱ የፍቅረኞች ምሽትን ለመታደም የሚሹ ጥንዶች 219 ዶላር ወይም 4423 ብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቦሌ የሚገኘው ፍሬንድሺፕ ሆቴልም የፍቅረኞችን ቀን አይረሴ ለማድረግ ዛሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሩን ለእንግዶቹ ክፍት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የተለያዩ የፍቅር ዜማዎች፣ ሰርፕራይዝ ስጦታዎችና ሌሎች…ፕሮግራሞችም እንደሚኖሩ ገልጿል፡፡
ሳሚ ካፌና ሬስቶራንትም እንዲሁ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ አኩስቲክ ባንድ ምሽቱን እንደሚያደምቀውና ዳዊት ፍሬውም ክላርኔት እንደሚጫወት ተጠቁሟል፡፡
ውሃ ልማት አካባቢ የሚገኘው ባለ አምስት ኮከቡ ካፒታል ሆቴል፤  ምሽቱን ለየት ለማድረግ የቀይ ምንጣፍ ልዩ የፍቅረኞች ምሽት ያዘጋጀ ሲሆን የሰባት ጥንዶች የዋልዝ ዳንስ ውድድርና ሙዚቃ አሰናድቷል፡፡ የፍቅረኞች ምሽቱን በሆቴሉ ለመታደም የሚሹ ጥንዶች 1800 ብር፣ ለብቸኛ ታዳሚ ደግሞ 1200 ብር እንደሚያስከፍል የገለፀው ሆቴሉ፤ እዚያው ተዝንተው፣ አድረውና ቁርስ አድርገው መውጣት ለሚፈልጉ 4500 ብር ይበቃቸዋል ተብሏል፡፡
ላንጋኖ ሪዞርት የፍቅረኞች ቀን ልዩ ዝግጅቱን የጀመረው ከትላንት በስቲያ ሲሆን ዛሬ  የአዝማሪ ሙዚቃ፣ የጀልባ ሽርሽር እንዲሁም ልዩ ልዩ ምግብና ወይኖችን መዘጋጀታቸውንና ጥንዶች 3600 ብር፣ ብቸኛ 1900 ብር እንደሚከፍል ተጠቁሟል፡፡ አፍሮ ዳይት ሆቴልም ልዩ የፍቅረኞች ምሽት እንዳዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፍቅረኞች ቀንን አምነውበት ለሚያከብሩት ብዙ አማራጮች የተዘጋጁ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ቫለንታይን የውጭ ባህል ነው በሚል የሚቃወሙትም አሉ፡፡
በ20ዎቹ መጨረሻ ዕድሜው ላይ የሚገኘው እስክንድር፤ የፍቅረኞች ቀን በአገራችን መከበሩን ከእነአካቴው አይቀበለውም፡፡ “ፍቅር በአደባባይ ልታይ ልታይ የሚባልበት ሳይሆን የልብ ትስስር ጉዳይ ነው” ያለው ወጣቱ፤ ቫለንታይን የአገራችን ባህል ስላልሆነ አልቀበለውም ባይ ነው፡፡ ቀይ መልበስና ሌሎቹም ነገሮች የእኛ አለመሆናቸውን ይናገራል፡፡ እንዲያም ሆኖ ፍቅረኛው ደሞ በቫለንታይንስ ዴይ ቀያይ ልብሶች ገዝቶ በስጦታ እንዲያበረክትላት ትፈልግ ነበር፡፡ ነገሩን ፈጽሞ ባላምንበትም ፍቅረኛዬን በጣም ስለምወዳት የማልፈልገውን አደረግሁ ብሏል፡፡  “ፍቅረኛዬ እንዳይከፋት ብዬ ቢያንስ ከውስጥ የሚውል ቀይ ፓንትና ጡት ማስያዣ ገዝቼ በስጦታ አበርክቼላታለሁ፡፡ ዋጋው ግን በጣም ውድ ነው” ሲል በመገረም ገልጿል፡፡
የ31 ዓመቱ አሳየኸኝ፤ ፍቅረኛው ለቫለንታይን እንዲገዛላት የጠየቀችው ስጦታ ዋጋው ናላውን እንዳዞረው ይናገራል፡፡ ባለፈው ዓመትም በከፍተኛ ዋጋ ምክንያት ከፍቅረኛዬ ጋር ተጋጭተን፣ ለሰባት ቀናት ተዘጋግተን ነበር ያለው አሳየኸኝ፤ “ዘንድሮም መጋጨታችን አይቀሬ ነው” ሲል የፍቅረኞች ቀን ስጋት እንደሆነበት ገልጿል፡፡
እየሰራሁ ገቢ ባገኝም እየከፈልኩ እማራለሁ፣ ወንድሜንም አስተምራለሁ የሚለው ወጣቱ፤ እንዲህ ያሉ ወጪች በእጅጉ ይጎዱኛል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል በአሜሪካ የዘንድሮው ቫለንታይን ቀን ለስጦታ የሚወጣው አጠቃላይ 18.9 ቢ.ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅና ይሄም በከፍተኛነት ወጪ ሪከርድ እንደሚሰብር ተገምቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4.8 ቢ. ዶላር ያህሉ ለጌጣጌጥ ስጦታዎች እንደሚወጣ ሰሞኑን ይፋ የተደረጉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቫለንታይን ቀን ከረሜላዎች፣ ፖስት ካርዶችና  አበቦች በስጦታነት ይበረከታሉ - የአልማዝ ቀለበትና ሌሎች ጌጣጌጦች ሳይረሱ ማለት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ የስራ ኃላፊ ስለ ቫለንታይን ቀን አስተያየታቸውን ሲናገሩ፤ “ጉዳዩ ከፍቅር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ቀኑ ቢከበር አይከፋኝም፤ አንዳንድ ነጋዴዎች ግን አጋጣሚውን በመጠቀም ትርፍ ለማግበስበስ የሚያደርጉት ሩጫ አያስደስተኝም” ብለዋል፡፡ ሴቶችም ቢሆኑ በዚህ ቀን ፍቅረኞቻቸውን ለአላስፈላጊ ወጭ በመዳረግ ማማረር የለባቸውም ሲሉ ይመክራሉ፡፡ “ውድ ስጦታ እንዲሰጣቸው ማስገደድ ፍቅርን ከማጠንከር ይልቅ ስለሚያሻክረው ጥንቃቄ ያሻል” ብለዋል፡፡ ሁሉም አምኖበት የሚያደርገው ከሆነ፣ አበባ፣ ቀይ ልብሶች የሚሸጡና የሆቴል አገልግሎት የሚሰጡ አጋጣሚውን በጤናማ መንገድ ገቢ ቢያገኙበት ክፋት እንደሌለው ጠቁመው፤ በዓሉ ወግና ስርዓት በጠበቀ መልኩ ቢከበር መልካም እንደሆነ አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 3125 times