Saturday, 17 January 2015 11:31

ሁለተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ አምስቶች ይፋ ሆኑ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛው የህይወት ዘመን ተሸላሚ እጩ ሆኗል
በመጪው የካቲት የሚያካሂደውና በኢትዮ ፊልምስ ባለቤትነት የሚመራው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ አምስቶች ከትናንት በስቲያ በሃርመኒ ሆቴል ይፋ ሆኑ፡፡ በህይወት ዘመን ተሸላሚነት አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛ እጩ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በ17 ዘርፎች በዳኞችና በተመልካች የተመረጡ አምስት አምስት እጩዎች የታወቁ ሲሆን ዘርፎቹም በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ሙዚቃ፣ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ሜክአፕ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ፣ በምርጥ ቅንብር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ህፃን ተዋናይት፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ህፃን ተዋናይ፣ በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናዮች፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ዳይሬክተርና በምርጥ ፊልም ጐራ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ መቶ ዳኞች በተሳተፉበት በዚህ ምርጫ ምርጥ አምስቶቹ የታወቁ ሲሆን በቀጣይ ከአንድ እስከ ሦስት የሚወጡት ተለይተው፣ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ደማቅ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ የኢትዮ ፊልም መስራችና ስራ አስኪያጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ ስፖንሰር ያደረገው በደሌ ቢራ ነው፡፡

Read 1653 times