Saturday, 10 January 2015 10:04

የ‘ጥር’ና የ‘ጠር’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…በትዳር አንደኛ ዓመት ባል ያወራል፣ ሚስት ታዳምጣለች፡፡ በትዳር ሁለተኛ ዓመት ላይ ሚስት ታወራለች ባል ያዳምጣል፡፡ በትዳር ሦስተኛ ዓመት ላይ ሁለቱም ያወራሉ ጎረቤትም ያዳምጣል፡፡ እናማ…‘ሁለቱም እያወሩ’ ጎረቤት የሚያዳምጥበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጥርም ገባ አይደል!… እንደ ድሮ ቢሆን “ጥር የልጃገረድ ጠር…” ምናምን እያልን ጽሁፋችንንና ዘፈናችንን እናሳምርበት ነበር፡፡ (‘ነበር’ ሊሆን…) መጀመሪያ ሦስት መቶ ምናምን ቀኑ ‘ጥር’ ሆኗል፡፡ ሌላ ደግሞ ምን መሰላችሁ…‘ጠር’ የሚባል ቃል ‘በዚህ አይነት ነገር’ ውስጥ መግባቱ እየቀረ ነው፡፡ አንድ ጊዜ… “ምን ጠር ነው፣ ጽድቅ ነው እንጂ…” ያልከው ወዳጃችን… አለ አይደል… ያኔ ቢሆን ኑሮ “የመደብ ጀርባው ይጣራ…” ምናምን ትባል ነበር፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…! አንዳንድ አባባሎች የአገልግሎት ዘመናቸውን የማያበቁትሳ! ልክ ነዋ…እንግዲህ ‘የልጃገረድነት’ ማብራሪያ ካልተለወጠ በቀር…“ጥር የልጃገረድ ጠር…” የሚለው አስቸጋሪ ነው፡፡ (ይሄ እኮ… “ነገርዬውን መልሶ እንደነበረው ማድረግ ተችሏል…” ምናምን የሚባለው ነገር ተጠራጣሪ አደረገንሳ!)
እናማ…ዘንድሮ በተለምዶ ከአንድ የህይወት ምዕራፍ ወደሌላ መሸጋጋር ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ተቋም ላይ የምናያቸው ነገሮች አሪፍ አይደሉም፡፡ እንደ ዕቃ፣ ዕቃ ጨዋታ “በቃ አልጫወትም፣ እምብዮ!” ተብሎ ‘ቆርኪ ተሰብስቦ’ የሚወሰድበት አይነት እየመሰለ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን የሚጣሉበት ነገር እፀ በለሱ ብቻ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ስሙኝማ…ስለ አዳምና ሔዋን ካነሳነ አይቀር ይቺን እዩልኝማ፡፡
አባት ለልጁ ስለ አዳምና ሔዋን አፈጣጠር እያስረዳው ነበር፡፡
“ዓለም ሲጀመር አዳም ተወለደ፡፡”
“ጧት ነው የተወለደው?”
“የተወለደው ሔዋን ከመወለዷ ከጥቂት ጊዜ በፊት ነው፡፡ እንቅልፍ ወስዶት እያለ ከግራ ጎኑ የጎድን አጥንት ተወሰደና ሔዋን ተወለደችና ሚስቱ ሆነች፡፡”
“የጎድን አጥንቱን አይፈልገውም ነበር ማለት ነው?”
“ትርፍ የጎድን አጥንት ነበረው፡፡”
ከዛም ልጁ መጮህ ይጀምራል፡፡ አባቱም “ምን ሆንክ?” ይለዋል፡፡ ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው… “አባዬ ግራ ጎኔን እያመመኝ ነው፡፡ ሚስት ላገኝ ነው መሰለኝ፡፡” ህጻንነትን የመሰለ ነጻነት የለም እኮ!
እናላችሁ…“ጥር የልጃገረድ ጠር…” የሚለው አባባል ተባለም አልተባለ…እንግዲህ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የአዲስ አበባ መንገዶች በመኪና ጡሩምባ፣ የሀብታም ገቢ በሚያካክሉ ሊሞዎች ይሞላሉ፡ እኔ የምለው…ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ‘የሊሞ ሠርግ’ ስናይ እኮ ቆም ብለን ወይ ጉድ እንባባል ነበር፤ አሁን፣ አሁን ‘የሊሞ ሠርግ’ ከመብዛቱ የተነሳ ዘወር ብሎ የሚያይ ሰው ካለ ለአዲስ አበባ እንግዳ ነው ማለት ነው፡፡ እንደ ሁሉም ነገር የሠርግ ቀን ‘መፎካከሪያ’ ሆኖላችኋል፡፡ በየቦታው ስለሚደገሱ ሠርጎችና ስለሚፈሰው ውስኪ ስትሰሙ ለማመንም የሚያስቸግራችሁ ጊዜ አለ፡፡
እሱዬው ልጃቸውን ለማግባት የአባቷን ፈቃድ ለማግኘት ቤታቸው ሄዷል፡፡
“ልጅዎትን ለትዳር እፈልጋታለሁ፡፡”
“ምን ያህል ታገኛለህ?”
“በወር አንድ ሺህ ዶላር ገደማ አገኛለሁ፡፣”
“ጥሩ፣ እሷ ደግሞ በወር ስድት መቶ ዶላር አላት…”
“ጌታዬ በወር አንድ ሺህ ያልኩት እኮ የእሷን ስድስት መቶ ጨምሬ ነው…” አለና አረፈው፡፡
ልክ ነዋ…ሀብትሽ ሀብቴ አይደል እንዴ! እንትናዎች ለሌላ ጊዜ ገቢያችሁን ከእሷዬዋ ጋር እየደመራችሁ አስሉትማ፡፡ አሀ… ገንዘቡ ‘የጋራ’ የሚሆነው ‘ሲከፋፋል’ ብቻ ነው እንዴ!
ይልቅ… ይቺን ሰሙኝማ፡፡
ሌላው እሱዬ ደግሞ እንዲሁ ልጅቱ አባት ዘንድ ይሄድና…“ልጅዎን የትዳር ጓደኛ ላደርጋት እፈልጋለሁ፡፡”
“ጥሩ፣ ስምህንና የስልክ ቁጥርህን ጻፍልኝ፡፡”
“ለምን?”
“ከአንተ የተሻለ ሰው ካልመጣ እደውልሀለሁ፡፡”
አሪፍ አይደል፡፡ እንትና… በዚህ አይነት እኮ የእኛ ቢጤዎች ስልኩ ሳይደወል የሩኒ ልጅ የአርሴናል አሰልጣኝ ለመሆን ይደርሳል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…መቼም የበዓላት ሰሞን አይደል ገና የሚወጣጥሩን መአት ነገሮች ፊት ለፊታችን አሉ አይደል…ትንሽ ፈታ እንበልማ! ለነገሩ እኮ የኮሜዲያን ትርኢት እያየን ካልሆነ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው የምንስቀባቸው ነገሮች ቀንሰዋል፡፡
የሳቅ ነገር ካነሳን አይቀር…ከመረጃ መረብ ያገኘኋትን ስሙኝማ፡፡
ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሰዎች በቀን የሚስቁት ለ15 ጊዜ ብቻ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ህጻናት ግን በቀን አራት መቶ ጊዜ ይስቃሉ ይባላል፡፡ (እኛ ዘንድ በቀን አሥራ አምስት ጊዜ የሚስቅ ከተገኘ የደላው ነው ማለት ነው፡፡)
እናማ…ሳቅ የደም ግፊትን ይቀንሳል፣ የልብ ምትን ያስተካክላል፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል፣ ሆድ አልሰር እንዳይፈጥር ይከላከላል፣ የፊት ጡንቻዎችን ያፍታታል፣ ቆዳን ፏ ያደርጋል…ብቻ ምን አለፋችሁ መአት ጥቅም አለው፡ እንደውም… ለአንድ ደቂቃ መሳቅ አሥር ደቂቃ የአካል እንቅስቃሴ እንደ ማድረግ ይቆጠራል የሚባልም ሳይንስ ቢጤ ነገር አለ፡፡  
“ልጅዎትን ለሚስትነት ስጡኝ… ማለትን በተመለከተ ይቺን አንብቧትማ…
እሱዬው ቤተሰቦቿ ዘንድ ደርሶ ሲመጣ እሷዬዋ…
“አባዬን ልጅህን ዳርልኝ አልከው እንዴ?”
“አዎ፡፡”
“ታዲያ ምን አለህ?”
“ስንት ገንዘብ እንዳለኝ ጠየቁኝና ባንክ ውስጥ ሦስት ሺህ ዶላር አለኝ አልኳቸው፡፡”
“ከዛስ ምን አለህ?”
“ሦስት ሺህ ዶላሩን አበድረኝ አሉ፣ አበደርኳቸው፡፡”
ልክ ነዋ…እሳቸው ምን አሉ ምን፣ እነሱ ዞረው መገናኘታቸው ለማይቀር ከኬኩ ትንሽ የማይደርሳቸውሳ!
ሊንዳ ዉልፍ የምትባል የ68 ዓመት ሴት ነች፡፡ 23 ጊዜ አግብታ በመፍታት በዓለም ውስጥ ቀዳሚዋ ነች ይባላል፡፡ “በቃ፣ ማግባት ደስ ይለኛል…” ትላለች ነው የሚሉት፡፡ (የእሷ የለየው ይሻላል፡፡ በትዳራቸው ላይ በየአሥራ አምስት ቀኑ አዳዲስ ባል/ሚስት ‘አግብተው የሚፈቱ’ ወንዶችና ሴቶች መአት አይደሉ እንዴ!)
እናማ…ሴትየዋ ጃክ ጉርሌ ከሚባል ሰው ጋር ሦስት ጊዜ ተጋብታ ተፋታለች፡፡ ከባሎቿ ውስጥ የተፈረደባቸው ወንጀለኞች፣ ቀሳውስት፣ ባሬስታ፣ አናጢዎች፣ ሙዚቀኞች…ይገኙበታል፡፡
 በትዳር የቆየችው ከፍተኛ ጊዜ ሰባት ዓመት ሲሆን ከመጀመሪያ ባል ጋር ነው፡፡ አጭሩ ደግሞ አንድ ቀን ተኩል ብቻ ነው፡፡
አቤት… ባልን ባንክ ያስቀመጠውን ገንዘብ አበድረኝ የሚሉ አባት ቢኖሯት የናጠጡ ሀብታም ይሆኑ ነበር!
የገንዘብ ነገር ካነሳን አይቀር…
ሰውየው ለጓደኛው …“ገንዘቤን እባክህ በአደራ አስቀምጥልኝ…“ ይለዋል፡፡
ጓደኝየውም “ምን ማለት ነው፣ መቀለድህ ነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“መቀለዴ አይደለም፡፡ ትዳር ከያዝኩ ሦስት ቀን ሆነኝ፡፡”
“ታዲያ ትዳር ይዘህ ገንዘቤን አስቀምጥልኝ ትለኛለህ!”
“አሀ… ታዲያ በደንብ የማላውቃት ሴት ያለችበት ቤት ውስጥ አምኜ ገንዘቤን ላስቀምጥልህ ነው!” ሲል መለሰ አሉ፡፡
‘ልጃገረድነቱም’ ተገኘም አልተገኘ፣ ‘ጠር’ የሚሉት ነገር ኖረም አልኖረ፣ ሙሽሮች ከማይሆን ‘ፉክክር’ ሰውሮ መልካም መልካሙን ሁሉ ያፍስስላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3522 times