Monday, 05 January 2015 08:08

ቀነኒሳና አሰለፈች ለተለያዩ ሃትሪኮች በዱባይ ይሮጣሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

          ከ3 ሳምንታት በኋላ ለ15ኛ ጊዜ በሚካሄደው የዱባይ ማራቶን ላይ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት እንደሳበ ታወቀ፡፡ የዱባይ ማራቶን ከዓለም ትልልቅ ማራቶኖች በሽልማት ገንዘቡ ከፍተኛነት እና ለቦታው ሪከርድ በሚቀርብ የቦነስ ክፍያ ግንባር ቀደም ነው፡፡  የ32 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ወደ ማራቶን ፊቱን ካዞረ በኋላ ሶስተኛውን ተሳትፎ ሲያደርግ፤ በሌላ በኩል በ2011 እና በ2012 እ.ኤ.አ ማራቶኑን ለሁለት ጊዜያት ያሸነፈችው አትሌት አሰለፈች መርጊያ ለ3ኛ ድሏ ትወዳደራለች፡፡  አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በዱባይ ማራቶን ለመሳተፍ መወሰኑ የውድድራችን ድምቀት ይጨምረዋል በማለት ደስታቸውን የገለፁት የውድድሩ አዘጋጆች፤ በተለይ ደግሞ በሴቶች ምድብ ውጤታማ የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች በብዛት በመሳተፋቸው ጠንካራ ፉክክር እንዲጠበቅ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
በአይኤኤኤፍ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የዱባይ ማራቶንን ለሚያሸንፍ አትሌት 200ሺ ዶላር ሽልማት ይሰጣል፡፡ የቦታን ክብረወሰን ለሚያስመዘግብ ደግሞ 1 ሚሊዮን ዶላር ቦነስ ይበረከታል፡፡ የዱባይ ማራቶን የቦታ ሪከርድ በሁለት የኢትዮጵያ አትሌቶች እንደተያዘ ሲሆን በሴቶች በ2011 እኤአ ላይ በአሰለፈች መርጊያ በ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ31 ሰከንዶች እንዲሁም በ2012 እኤአ በወንዶች በአየለ አብሽሮ 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ባለፉት 14 ዓመታት በተካሄዱት የዱባይ ማራቶኖች የኢትዮጵያውያን የውጤት የበላይነትም ታይቶበታል፡፡ በወንዶች 8 ጊዜ በሴቶች ደግሞ 10 ጊዜ አሸናፊዎቹ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በውድድሩ ላይ ብዙ ያሸነፈው ኢትዮጵያዊ አትሌት ከ2008 እስከ 2010 እኤአ ለሶስት ጊዜያት አከታትሎ ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ በወንዶች ምድብ ሌሎቹ አሸናፊዎች፤ በ2004 ጋሻው አስፋው፤ በ2005 ደጀኔ ጉደታ፤ በ2012 አየለ አብሽሮ፤ በ2013 ሌሊሳ ዴሲሳ እንዲሁም በ2014 ፀጋዬ መኮንን ናቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ በ2004 ለይላ አማን፤ በ2005 ድርቤ ሁንዴ፤ በ2007 አስካለ ጣፋ፤ በ2008 ብርሃኔ አደሬ፤ በ2009 ብዙነሽ በቀለ፤ በ2010 ማሚቱ ደስካ፤ በ2011 አሰለፈች መርጊያ፤ በ2013 ትርፌ ፀጋዬ እንዲሁም በ2014 ሙሉ ሰቦቃ አሸንፈዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ ሶስተኛውን ማራቶን በአዲስ አሰልጣኝ
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ወደ ማራቶን ፊቱን ካዞረ ዓመት እንኳን አልሞላውም፡፡ በመጀመርያው ውድድር ፓሪስ ላይ የቦታውን ሪከርድ በመስበር በ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ04 ሰኮንዶች እንዳሸነፈ ይታወሳል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ደግሞ ሁለተኛውን የማራቶን ውድድር በቺካጎ ማራቶን አድርጎ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ51 ሰከንዶች በመሸፈን በአራተኛ ደረጃ ጨርሷል፡፡
የዱባይ ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ የሚሮጥበት ይሆናል፡፡ ‹‹የዱባይ ማራቶንን ክትትል ሳደርግበት ቆይቻለሁ፡፡ በቀጥተኛ ጎዳና ላይ የሚካሄድ ውድድር በመሆኑ ለፈጣን ሰዓት እንደሚመች እገምታለሁ፡፡ ዱባይ ላይ የማራቶን ሪከርድ ለመስበር የሚቻል ባይሆንም ፈጣን ሰዓት ለማግኘት እቅድ አለኝ፡፡፡›› በማለት በተሳትፎው ላይ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
በፓሪስ እና በዱባይ ማራቶኖች ያገኘውን ልምድ በመጠቀም በዱባይ ማራቶን ላይ እንደሚወዳደር ጨምሮ የተናገረው አትሌቱ፤ የቦታውን ሪከርድ ለመስበር ባይቻል ቢያንስ የግሉን ፈጣን ሰዓት የሚያስመዘግበበት ብቃት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ባለፉት አራት አመታት በዱባይ ማራቶን 11 አትሌቶች ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች በታች በመግባት ስለተሳካላቸው የቀነኒሳ እቅድ ሊሳካ እንደሚችል ያመለከተ ነው፡፡
ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን የያዘ፤ በትራክ በአገር አቋራጭ እና በቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለ18 ጊዜያት የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ፤ ለሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን የተጎናፀፈ እና በሁሉም የአትሌቲክስ የረጅም ርቀት ውድድሮች በማሸነፍ ብቸኛው እና የመጀመርያው ለመሆን የበቃ አትሌት ነው፡፡
በማራቶን ደግሞ የዓለም ሪከርድን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከፍተኛ ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡  ከቺካጎ ማራቶን በኋላ ዋና አሰልጣኙን ጣሊያናዊው ሬናቶ ካኖቫ ያደረገው አትሌት ቀነኒሳ፤ ከእኝህ አሰልጣኙ ጋር እየሰራ ያለው ልምምድ እንደተስማማው ተናግሯል፡፡ አሰልጣኝ ሬናቶ ካኖቫ በርካታ የኬንያ አትሌቶችን በረጅም ርቀት በማሰልጠን ውጤታማ ያደረጉ ናቸው፡፡
በስልጠናው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፤  በአይኤኤኤፍ ሌክቸረር ሆኖ ከማገልገላቸውም በላይ በ2014 የቻይና አትሌቲክስ ፌደሬሽን በመካከለኛ፤ በረጅም ርቀት እና በማራቶን ውድድሮች የብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ከቺካጎ ማራቶን በፊት በራነርስ ዎርልድ መፅሄት ላይ ቀነኒሳ በቀለ ሁነኛ የማራቶን ሯጭ ነው በማለት የመሰከሩት አሰልጣኝ ሬናቶ ካኖቫ፤ አትሌቱ ከሁለት ማራቶኖች በኋላ የዓለም ሪከርድ የሚሰብርበትን ብቃት ማሳየቱ እንደማይቀር ገልፀው ነበረ፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በሶስተኛ የማራቶን ውድድር ተሳትፎው ከ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ለመሮጥ እንደሚችልም በወቅቱ ገልፀዋል፡፡
አሰለፈችና የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች የበላይነት
በ2014 በመላው ዓለም በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች እንደ የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች የተሳካለት አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን ትልልቆቹን የማራቶን ውድድሮች የኬንያ አትሌቶች ቢያሸንፏቸውም የኢትዮጵያ ሴት ማራቶኒስቶች ከ15 በላይ ማራቶኖችን  በማሸነፍ አስደናቂ ውጤታማነት አሳይተዋል፡፡ በ2015 የዱባይ ማራቶንም ይሄው የሴት ማራቶኒስቶቹ የበላይነት እንደሚቀጥል ነው ተጠብቋል፡፡
በ15ኛው የዱባይ ማራቶን ከወሊድ መልስ የመጀመርያ ማራቶኗን የምትሮጠው አትሌት አሰለፈች መርጊያ ለሶስተኛ ጊዜ ውድድሩን ለማሸነፍ እንደምትችል ግምት ወስዳለች፡፡ ከአትሌት አሰለፈች መርጊያ ጋር በዱባይ ማራቶን ሌሎች ምርጥ ማራቶኒስቶች መሳተፋቸው ከፍተኛ ፉክክር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡  አምና የዱባይ ማራቶን አሸናፊ የነበረችውና በተጨማሪም የቶሮንቶ ማራቶንን ያሸነፈችው ሙሉ ሰቦቃ የመጀመርያዋ ተጠቃሽ ናት፡፡ በ2014 የፍራንክፈርት ማራቶንን ያሸነፈችው ሸዋዬ አበሩ፤ እንዲሁም በ2011 እ.ኤ.አ የኒውዮርክ ማራቶንን ያሸነፈችው ፍሬህይወት ዳዶ ሌሎቹ ምርጥ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡  በዱባይ ማራቶን ለሦስተኛ ጊዜ በማሰለፍ በውድድሩ ታሪክ ለሦስት ጊዜያት ካሸነፈው ታላቁ የ29 ዓመቷ አትሌት አሰለፈች መርጊያ በ2011 እና በ2012 እኤአ የዱባይ ማራቶንን ካሸነፈች  በኋላ የመጨረሻ ውድድሯ የለንደን ኦሎምፒክ ነበር፡፡
አሁን ከወሊድ መልስ የምትሮጠው የመጀመርያው ውድድር የዱባይ ማራቶን ሲሆን ካሸነፈች በውድድሩ ለሶስት ጊዜያት አሸናፊ ከሆነው ኃይሌ ገ/ስላሴ ጋር የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን ትጋራለች፡፡
አትሌት አሰለፈች መርጊያ በ2012 እ.ኤ.አ ላይ የዱባይ ማራቶንን ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 2 ሰዓት ከ19 ደቂቃዎች ከ31 ሰኮንዶች የዱባይ ማራቶን የቦታ ሪከርድ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የማራቶን ሪኮርድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በማራቶን የምንጊዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ 7ኛ ላይም ተመዝግቧል፡፡
 በዓለም ሻምፒዮና በ2009 እ.ኤ.አ ላይ በርሊን ውስጥ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘችው አትሌቷ በለንደንና የፓሪስ ማራቶኖች እስከ 3ኛ ደረጀ በመውጣት ከፍተኛ ልምድ ያካበተች ናት፡፡

Read 3301 times