Monday, 29 December 2014 07:56

2014ን ወደኋላ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

     በ2014 በዓለም ዙሪያ ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡ ጎን ለጎን በርካታ አወዛጋቢ አጀንዳዎችም ተከስተዋል፡፡ በራሽያዋ ግዛት ሶቺ የተካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ያስወጣው ከፍተኛ በጀት ያስገረመ ነበር፡፡ ብራዚል ያስተናገደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ የምን ግዜም ምርጥ ቢባልም በውዝግቦች ታጅቧል፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተራቅቋል በአነጋጋሪ ክስተቶች የደመቀ ዓለም ዋንጫ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግዙፎቹ የስፖርት አስተዳደር ተቋማት በተለያዩ የውዝግብ አጀንዳዎች የታመሱበትም ዓመት ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ‹‹ፊፋ›› ምንም እንኳን ብራዚል ባዘጋጀችው 20ኛው ዓለም ዋንጫ እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ቢያጋብስም 2009 አባል አገራት ያሉት ፊፋ 9 ዓለም ዋንጫዎች አዘጋጆችን ምርጫ ሙስና በተንሰራፋበት አሰራር ማከናወኑ ከፍተኛ ትችት አስከትሎበታል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴም በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሎምፒክ ዙሪያ አሳሰቢ አጀንዳዎች ተፈጥረውበታል፡፡ የኦሎምፒክ አዘጋጆች የሚጠይቀው ከፍተኛ የበጀት ወጪ የአገራትን የመስተንግዶ ፍላጎት እያሳጣበት ነው፡፡ በኦሎምፒክ ውድድርና መስተንግዶ ተሃድሶ ለማድረግ መነሳቱ አበይት መነጋገርያ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ 2015 እኤአ ዓለም ዋንጫና ኦሎምፒክ ባይኖሩበትም በተለያዩ አህጉሮች የሚደረጉ ትልልቅ የስፖርት ውድድሮች ይስተናገዱበታል፡፡ በ2015 የውድድር ካለንደር በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማስተናገድ እድለኛ የሆነችው አውስትራሊያ ናት፡፡ የኤስያ ካፕ፤ የዓለም የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና፤ የዓለም የክሪኬት ዋንጫን ታዘጋጃለች፡፡ ቻይና 15ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጉዋጄንግ ቤጂንግ ስታስተናግድ፤ በአፍሪካ አህጉር ደግሞ ኢኳቶርያል ጊኒ የምታዘጋጀው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ይሆናል፡፡ ካናዳ ደግሞ የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫን ታዘጋጀለች፡፡
ስፖርት አድማስ በ2014 እኤአ በስፖርቱ ዓለም ያጋጠሙ አበይት ክስተቶችና ሁኔታዎችን ከዚህ በታች ከልሷቸዋል፡፡
የጀርመን የዓለም ዋንጫ ድል
የ2014 እኤአ ዋና የስፖርት መድረክ በነበረው የብራዚል 20ኛው ዓለም ዋንጫ የጀርመን የበላይነት የተረጋገጠበት ነበር ቢሆንም በዓመቱ በእግር ኳስ እንደ ጀርመን ስኬታማ የሆነ የለም፡፡ የጀርመን እግር ኳስ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ በ1725 ነጥብ በመሪነት በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በየውድድሮቹ ቋሚ ተፎካካሪ የሆነበር ዕድገት የዓመቱ ትልቅ ስኬት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ የፍፃሜው ጨዋታ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አርጀንቲናን 1ለ0 በማሸነፍ ለአራተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሄ  የዓለም ዋንጫ ድል ከ24 ዓመታት በኋላ የተገኘ ነበር፤ አውሮፓዊ ቡድን ደቡብ አሜሪካ አህጉር ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ክብር መቀዳጀቱም አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የጀርመን እግር ኳስ ስኬት በዓለም ዋንጫ ድል ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የአገሪቱ ክለቦች በአውሮፓ ትልልቅ ውድድሮች ቋሚ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆነዋል፡፡ የቦንደስ ሊጋ ውድድር በስታድዬም ተመልካች ብዛት እና በአስተማማኝ የኢኮኖሚ ጥንካሬው ተምሳሌት ሆኖ ይገኛል፡፡ በፊፋ የ2014 የወርቅ ኳስ ፉክክር ውስጥ ጀርመናዊያን በዋና ዋና የሽልማት ዘርፎች  የመጨረሻ እጩ ናቸው፡፡ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን ይህን ስኬት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እቅድ በ2024 እኤአ ላይ ደግሞ የአውሮፓ ዋንጫን በታላቅ ድምቀት ለማዘጋጀት ይፈልጋል፡፡ ኦሎምፒክንም ለማስተናገድ ፍላጎት አለ፡፡
የሪያል ማድሪድ ኃያልነት
በአውሮፓ እግር ኳስ  2014ን የነገሰበት የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ነው፡፡ 4 ትልልቅ ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡ አስረኛውን የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድል አትሌቲኮ ማድሪድን 4ለ1 በማሸነፍ መቀዳጀቱ የመጀመሪያው ነበር፡፡ በተጨማሪ የአውሮፓ ሱፕር ካፕ ፤ የስፔን ኮፓ ዴላ ሬይ እና የዓለም ክለቦች ሻምፒዮና ሶስት ዋንጫዎችን በሽልማት ያስገባው ገንዘብ ከ65 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ነው፡፡ አሶስዬትድ ፕሬስ በ2014 የእግር ኳስ ገድላቸው ጎልቶ ለወጡ ክለቦች በሰራው ደረጃ በ137 ነጥብ በአንደኛነት የሚመራም ክለቡ በ2015 እኤአ ተጨማሪ 4 ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ተናግረዋል፡፡
የታላላቅ ተጨዋቾች ጡረታ
በ2014 የቀድሞ ታላላቅ ተጨዋቾች እግር ኳስን  በጡረታ ተሰናብተዋል፡፡ በጡረታ ጫማቸውን ከሰቀሉት መካከል ቲዬሪ ሆንሪ፤ ሃቪዬር ዛኔቲ፤ ካርሎስ ፒዮል፤ ሪያን ጊልስ፤ ክላረንስ ሲዶርፍ፤ ቬሮንና ሪቫልዶ ይጠቀሳሉ፡፡ በተጫዋችነት ባሳለፉባቸው የውድድር ዘመናት በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች እና የውስጥ ውድድሮች 50 ዋንጫዎችን 15 የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድሎችንም አግኝተዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው 857 ጨዋታዎችን ያደረጉም ናቸው፡፡ ሶስት የዓለም ዋንጫን ያሸነፉ ፤ ሁለት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናጸፉ እንዲሁም የወርቅ ኳስ ተሸላሚ ብራዚላዊው ሪቫልዶ ይገኙበታል፡፡
የኦስካር ፒስቴርዬስ ወንጀል
በ2014 እኤአ በስፖርቱ ዓለም አስደንጋጭ እና አነጋጋሪ ከነበሩ ክስተቶች መጠቀስ ያለበት ደቡብ አፍሪካዊው የፓራኦሎምፒክ ጀግና ኦስካር ፒስተርዬስ የትዳር አጋሩን ራሴን ለመከላከል በሚል ምክንያት በጥይት ተኩሶ ገድሏታል፡፡ ፍርድ ቤት የተመላሰበት የክስ ሂደት ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ከሁለት ወራት በፊት 5 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ወህኒ ወርዷል፡፡ የ36 ዓመቱ ኦስካር ፒስቴርዬስ በፓራኦሎምፒክ የአጭር ግዜ ተሳትፎው በጣም ስኬታማ ነበር በ100 ሜትር እና በ200 ሜትር ውድድሮች 6 የወርቅ፤ 1 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን በፓራ ኦሎምፒክ ውድድሮች ተጎናፅፏል፡፡ በ100 የፓራኦሎምፒክ ሪከርድም አስመዝግቧል፡፡ ሰሞኑን በተፈረደበት የ5 ዓመት የወህኒ ቆይታ ላይ ይግባኝ ጠይቋል አልተሳካለትም፡፡ በመልካም ተመክሮ ለመፈታት ቢያንስ 10 ወራት ወህኒ እንዲቆይ ይጠበቅበታል፡፡
ዶፒንግና  አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ‹‹አይኤኤኤፍ›› በ2014 እ.ኤ.አ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ ኢንተርኮንትኔንታል ካፕ፤ የዱላ ቅብብል የዓለም ሻምፒዮና የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና፤ የዳይመንድ ሊግ እና ሌሎች ውድድሮችን በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዶፒንግ በተያያዘ የሚነሱት አጀንዳዎች በዓመቱ መጨረሻ የተከሰቱ ነበር፡፡ ከ1999 እኤአ አንስቶ ዓለምን አቀፉን የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የመሩት ሴኔጋላዊው ለሚን ዲያክ ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡ 2014 የመጨረሻ የግልጋሎት ዘመናቸው እንደሚሆን እየተገለፀ ነው በዶፒንግ ዙርያ የተፈጠሩት አወዛጋቢ አጀንዳ በስልጣን የመቆየታቸውን ተስፋ አጠያያቂ አድርገዋል፡፡ ባለፈው ሰሞን የጀርመን ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ የሰራው ጥናታዊ ፊልምም በዶፒንግ ዙሪያ ያሉ የተድበሰበሱ ችግሮችን አጋልጧል፡፡ አይኤኤኤኤፍ በዶፒንግ ዙሪያ በከፍተኛ የአሠሪር ችግር መውተብተቡን የረዳ ፊልም ሆኗል፡፡ በውድድር ወቅት አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ ባለማድረግ፤ ብቃትን የሚጨምሩ መድሃኒቶችን ለመቆጣጠር ባለመቻል እና በለዘብታ በማለፍ ዓለም አቀፉ ማህበር እና ታላላቅ አትሌቶች መጠየቅ አለባቸው የሚል ዘመቻ ከፍቷል፡፡ በጀርመኑ የቴሌቭዥን ጣቢያ በዶፒንግ ችግር ተጠርጣሪ ናቸው ተብሎ በወጣው የ150 አትሌቶች ዝርዝር የብሪታኒያ፤ የራሽያና የኬንያ አትሌቶች ይገኙበታል፡፡
በተለይ የራሽያ ኦሎምፒያኖች 99 በመቶ ብቃት የሚጨምሩ መድሃኒቶች ይጠቀማሉ በሚል የተሰራው ዘገባ እያነጋገረ ነው፡፡ ከራሽያ ባሻገር በዶፒንግ ችግር የገዘፈ ክብር እና ዝናው አደጋ ውስጥ የወደቀው ደግሞ የኬንያ አትሌቲክስ ነው፡፡ ኬንያዊ እውቅ አትሌቶች ከመደበኛ የዶፒንግ ምርመራ በማፈንገጥና ከምርመራ በኋላ ብቃት የሚያሳድጉ መድሃኒቶች  መጠቀማቸው በአንዳንዶቹ ላይ መረጋገጡ  የአገሪቱ አትሌቲክስ እያቃወሰው ይገኛል፡፡ የኬንያ መንግስት  በኬንያ አትሌቶች የዶፒንግ ችግር ዙርያ ዋና ተጠያቂ ያደረገው አትሌቲክስ ኬንያ ተብሎ የሚጠራው ፌደሬሽን ነው፡፡ አስፈላጊው ትኩረት እና ጥንቃቄ እንዲደረግ አልሰራም የሚል ምክንያት በማቅረብ አመራሮቹ ከስልጣናቸው እንዲለቁ ግፊት እያደረገባቸው ነው፡፡  የኬንያ አትሌቶች ኤጀንቶች እና ማናጀሮችም በኬንያ መንግስት ተወቅሰዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቦስተን እና የቺካጎ ማራቶኖችን ያሸነፈችው ሪታ ጄፔቶከወር በፊት  የተከለከለ መድሃኒት መጠቀሟ በዶፒንግ ምርመራ ተደርሶበታል፡፡ ብቃት ያሳድጋል የተባለውና እና እውቁ ብስከሌተኛ ላርንስ አርምስትሮንግ በመጠቀሙ አምኖ የተቀጣበትን “ኢፕኦ” የተባለ መድሃኒት መውሰዷ በመረጋገጡ ነው፡፡ በ2014 ብቻ ከዶፒንግ ምርመራ ጋር በተያያዘ የ32 የኬንያ አትሌቶች የክስ ፋይል መከፈቱ ቢነገርም በይፋ የተገለፀው የ16ቱ ብቻ መሆኑ የኬንያ አትሌቲክስ  ፌደሬሽን አመራሮች ከ25 ዓመታት በላይ በሃላፊነት መቆየታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ የፌደሬሽን አመራሮቹ በኬንያ ያለው የዶፒንግ ችግር ከራሽያና ከቻይና የባሰ አይደለም በሚል ይሟገታሉ፡፡ ለአትሌቶች ብቃት የሚያሳድጉ መድሃኒቶችን የሚያቀርቡ ህገወጥ ቡድኖች ታድነው  ለፍርድ እንዲቀርቡም አይኤኤኤፍ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በ2014 እኤአ በዓለም አትሌቲክስ በ39 አገራት የሚገኙ 225 አትሌቶች በዶፒንግ ዙርያ ክስ ቀርቦባቸው ምርመራ ተደርጐባቸዋል፡፡
ኢቦላ ያመሰው የአፍሪካ እግር ኳስ
2014 የአፍሪካ እግር ኳስ በኢቦላ የታመሰበት ዓመት ነው፡፡ ከ5 ወራት በፊት የኢቦላ ወረረሽኝ በምዕራብ አፍሪካ ሲከሰት የአህጉሪቱ የእግር ኳስ ውድድሮች ተቃውሰዋል፡፡ በአፍሪካ እግር ኮንፌደሬሽን የሚካሄዱ የማጣርያ ውድድሮች ፕሮግራማቸው ተዛብቷል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ተሰርዞ ለምትክ አስተናጋጅ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ በአፍሪካውያን ስፖርተኞች ላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የመገለል እና ከልክ ያለፈ ጥርጣሬ ተፈጥሯል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የስፖርት ክለቦች እና የውድድር አመራሮች ወረርሽኙን በመፍራት ባወጧቸው የጥንቃቄ መመርያዎች የዘረኝነት አጀንዳዎች አከራክረዋል፡፡ በ2015 እኤአ ላይ 30ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የምታዘጋጀው ሞሮኮ ነበረች፡፡ ከኢቦላ ወረረሽኝ በተያያዘ በተፈጠረ ስጋት ግን ውድድሩን በ2016 እንዳስተናግድ ይሸጋሸግልኝ ብላ ጥያቄ አቀረበች፡፡ ካፍ አልተቀበለውም፡፡ ስለሆነም ውድድሩ ለምትክ አዘጋጇ ኢኳቶርያል ጊኒ መሰጠቱ ግድ ሆኗል፡፡ ጊኒ፤ ላይቤርያ እና ሴራልዮን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን በአገራቸው መሬት እንዳያካሂዱም የኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት ነበር ታግደው ዓመቱን አሳልፈዋል፡፡
የፊፋ ቅሌት
ዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በ2014 በበርካታ የአስተዳደር ቀውሶች ተበጥብጧል፡፡ በማህበሩ አመራሮች ላይ በተደጋጋሚ የቀረቡ ክሶች የተቋሙን ተዓማኒነት አደጋ ላይ ጥለውታል፡፡ በ2018 እ.ኤ.አ 21ኛውን ዓለም ዋንጫ ራሽያ፤ በ2022 እ.ኤ.አ 22ኛው የዓለም ዋንጫ ኳታር እንዲያዘጋጁ የተመረጡት በከፍተኛ የሙስና መረብ መሆኑ መጋለጡ አሁንም እያነናገርነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተሰራጩ የምርመራ ሪፖርቶች የውስጥ ገበናው ተጋልጦበታል፡፡ ትልልቅ ባለስልጣናቱ እርስ በራስ እንዲወዛገቡ እና አንዳንዶቹም ከስልጣን እንዲለቁ ምክንያት የሆኑ ውዝግቦች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንትነት  ለ16 ዓመታት ያገለገሉት ሴፕ ብላተር ግን ቅሌቱን ለማስተባበል መሟገታቸውን አልተውም፡፡ በ2014 በከፍተኛ ደረጃ ከተወቀሱና ከተተቹ የስፖርት አመራሮች ግንባር ቀደሙ ተደንቋል፡፡ በ2015 እ.ኤ.አ ሴፕ ብላተር ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ለአምስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ፍላጐት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
የኦሎምፒክ በጀት መጥፋት
በ2014 በከፍተኛ ድምቀት ለመካሄድ ከቻሉ የስፖርት መድረኮች በራሽያዋ ግዛት ሶቺ ለመካሄድ የበቃው የ2014 የክረምት ኦሎምፒክ ይጠቀሳል፡፡ በከፍተኛ የበጀት ወጭው እና በተሳካ መስተንግዶው ተደንቋል፡፡ የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት ራሽያ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋለች፡፡ የምንጊዜም ውድ የኦሎምፒክ መስተንግዶ  ሆኖ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡ ይሁንና ከፍተኛ በጀት የሚጠይቀው የኦሎምፒክ መስተንግዶ ዓመቱን ሙሉ ሲያከራክር ነበር፡፡ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች የኦሎምፒክ ውድድር ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው በማሳሰብ ከፍተኛ ዘመቻ እያደረጉ ናቸው፡፡ በ2022 እኤአ የክረምት ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት አመልክተው በተለያዩ ምክንያቶች እቅዳቸውን የሰረዙት ሶስት ከተሞች ናቸው፡፡ ይህ ያሳሰባቸው ፕሬዝዳንቱ ታላቁ የስፖርት መድረክ ትኩረት እንዳያጣ ይፈልጋሉ፡፡ የስዊድኗ ስቶክሆልምና የዩክሬኗ ኪዬቭ ከተሞች የክረምት ኦሎምፒክ ለማስተናገድ የነበራቸውን ፍላጎት ሰርዘዋል፡፡ በጀቱን አንችልም በሚል ምክንያት ነው፡፡  የክረምት ኦሎምፒኩን ብቻ ሳይሆን ዋናውን የኦሎምፒክ ውድድር ከወጭው ክብደት አንፃር ቢሆኑም ማለት ነው፡፡ ማዘጋጀት የሚፈልጉ አገራት ጠፍተዋል፡፡  ዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሁኔታው አሳስቦታል፡፡ አስቀድሞ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ  ለአንድ አዘጋጅ አገር ብቻ የሚሰጠውን እድል በመከለስ አገራት ለጣምራ አዘጋጅነት  እንዲያመለክቱ ግፊት እያደረገ ነው፡፡ በ2016 እኤአ ብራዚል በሪዮ ዴጄኔሮ ከተማ 31ኛውን ኦሎምፒያድ እንዲሁም በ2020 ጃፓን በቶኪዮ ከተማ 32ኛውን ኦሎምፒያድ እንዲያስተናግዱ ተመርጠዋል፡፡ በ2024 እኤአ 33ኛውን ኦሎምፒያድ ማን እንደሚያስተናግድ ግን ከወዲሁ የታወቀ ነገር የለም፡፡ የመስተንግዶ ወጭዉ በየኦሎምፒኩ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱ አዘጋጅ አገር የማግኘቱን እድል እያጠበበው መጥቷል፡፡ በ1996 እኤአ አትላንታ ኦሎምፒክ 1.8 ቢሊዮን፤ በ2000 እኤአ ሲድኒ ኦሎምፒክ 3.8 ቢሊዮን፤ በ2004 እኤአ አቴንስ ኦሎምፒክ 15 ቢሊዮን፤ በ2008 እኤአ ቤጂንግ ኦሎምፒክ 40 ቢሊዮን እንዲሁም በ2012 እኤአ ለንደን ኦሎምፒክ 49 ቢሊዮን ዶላር ወጥቷል፡፡
የወርቅ ኳስ ፖለቲካ  
በ2014 እኤአ በከፍተኛ ደረጃ መነጋጋርያ ከሆኑ የእግር ኳሱ ዓለም አጀንዳዎች አንዱ የፊፋ የወርቅ ኳስ ሽልማት ነው፡፡ 3 የመጨረሻ እጩዎች ከታወቁባቸው የ2014 የመጨረሻ ወራት ወዲህ ክርክሩ በመጧጧፉም አሸናፊውን ለመገመት አዳጋች ሆኗል፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ ከ2 ሳምንታት በኋላ በዙሪክ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡ በዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫው የሻምፒዮንስ ሊግና የዓለም ዋንጫ ስኬቶች እንዲሁም አዳዲስ የእግር ኳስ ሪከርዶች የሚኖራቸው ተጽእኖ  አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአንዳንድ የስፖርት ሚዲያዎች የምርጫው ሂደት ፖለቲካዊ አጀንዳ እየተንፀባረቀበት መሆኑም ተገልጿል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሸል ፕላቲኒ የወርቅ ኳሱን የዓለም ሻምፒዮን የሆነ ተጨዋች መሸለም አለበት ብሏል፡፡ ከዚህ አስተያየት በኋላ በስፖርቱ ዙርያ ያሉ አሰልጣኞች፤ ተጨዋቾች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የወርቅ ኳሱን ማን ይሸለም በሚለው አጀንዳ ሲሟገቱ ሰንብተዋል፡፡  የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሊውስ ቫን ሃል፤ እውቁ የሆላንድ የእግር ኳስ ሰው ዮሃን ክሮይፍ፤ ለባየር ሙኒክ የሚጫወተው ዣቪ አሎንሶ የሚሸል ፕላቲኒን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ ሽልማቱ ለግብ ጠባቂው ኑዌር ይገባል ይላሉ፡፡ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ የሆኑት ካርሎ አንቸሎቲ በበኩላቸው ሽልማቱ የሚገባው በግሉ ምርጥ ብቃት ላሳየ ተጨዋች ይገባል በሚል አስተያየት ለሮናልዶ ድጋፍ ሲሰጡ፤ የክለቡ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝም በዓለም እግር ኳስ ሁሉን ያሟላ ተጨዋች ሮናልዶ በመሆኑ መሸለሙ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡  የቼልሲው ጆሴ ሞውሪንሆ በበኩላቸው የወርቅ ኳሱ ፖለቲካ ለእግር ኳስ እንደማይበጅ በመናገር ማንም ቢያሸንፍ ግድ እንደሌላቸው ይገልፃሉ ከሰሞኑ ደግሞ አንጋፋው የባርሴሎና ተጨዋች ዣቪ ኸርናንዴዝ ሮናልዶ ከሶስቱ እጩዎች ተርታ መሰለፍ እንደሌለበት ተናግሯል፡፡ የወርቅ ኳስ ለመሸለም በዓለም ዋንጫ ስኬት ማሳየት ዋና መስፈርት ሊሆን ይገባል በማለትም ሜሲ ካልተሸለመ ማኑዌል ኑዌር ቢሸለም ይገባዋል ብሏል፡፡  ባለፈው ዓመት ከሶስቱ የመጨረሻ እጩዎች አንዱ የነበረው ፈረንሳዊው ፍራንክ ሬበሪ ደግሞ ሽልማቱን አርያን ሮበን ባይወስድ እንኳን ለማኑዌል ኑዌር እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል የባርሴሎናው ኔይማር ሆኖ የሰጠው ድምፅ ሰሞኑን ግሎቦ በተባለ የአገሩ ጋዜጣ ወጥቷል፡፡ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን አምበል ለቡድን አጋሩ ሊዮኔል ሜሲ ድጋፍ እንደሰጠ ተጋልጧል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እንዳስታወቀው የፊፋ አባል ከሆኑ 209 አገራት ዋና አሰልጣኞች እና አምበሎች 87.3 በመቶ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች  94 በመቶ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በምርጫው ባለፈው ዓመት ከፊፋ 205 አባል አገራት 505 ድምፅ ተሰብስቧል፡፡ 170 አምበሎች፤ 170 አሰልጣኞች እንዲሁም 165 የዓለም አቀፍ ሚዲያ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡
ታዋቂው ጎል ስፖርት የድረገፅ አንባቢዎቹን ድምፅ እንዲሰጡ በማድረግ በሰራው ስሌት የዘንድሮ የወርቅ ኳስ ሽልማትን ማን ሊወስድ እንደሚችል በመቶኛ ተንብዮታል፡፡ ባለፈው ዓመት ሁለተኛውን  የወርቅ ኳስ የወሰደውና ዘንድሮ ሶስተኛውን ለመሸለም  እድል ያለው ክርስትያኖ ሮናልዶ በ57.2 በመቶ ድምፅ ከፍተኛውን ግምት አግኝቷል፡፡ ሮናልዶ በመጨረሻ እጩነት ሲቀርብ በውድድር ዘመኑ ከክለቡ ሪያል ማድሪድ ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን መውሰዱና  በ17 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረሱ ይታወቃል፡፡ሊዮኔል ሜሲ በጎል ድረገፅ አንባቢዎች 22.6 በመቶ ግምት በመውሰድ ለወርቅ ኳሱ ሽልማት ባለው እድል ሁለተኛ ደረጃ ተሰጥቶታል፡፡ ሜሲ በ2014 የውድድር ዘመን ከክለቡ ባርሴሎና ጋር ምንም አይነት የዋንጫ ድል  ባያስመዘግብም በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብረወሰኖችን መቆጣጠሩ ወደ ፉክክሩ አግብቶታል፡፡ ሁለቱን አጥቂዎች ክርስትያኖ ሮናልዶንና ሊዮኔል ሜሲን በመፎካከር ከሶስቱ የመጨረሻ እጩዎች አንዱ ለመሆን የበቃው ደግሞ የጀርመን ብሄራዊ ቡድንና የባየር ሙኒክ ግብ ጠባቂ የሆነው ማኑዌል ኑዌር ነው፡፡ ማኑዌል ኒዌር በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ከጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጋር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቱ ከፍተኛ ድጋፍ ያስገኝለታል፡፡ ኑዌር ከክለቡ ባየር ሙኒክ ጋር ባለፈው የውድድር ዘመን አራት ትልልቅ የዋንጫ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ በጎል ድረገፅ አንባቢዎች ለወርቅ ኳሱ በ20.2 በመቶ ድምፅ የማሸነፍ እድል ሶስተኛ ደረጃ ወስዷል፡፡ በፊፋ የዓለም የኮከብ ተጨዋቾች ምርጫ ታሪክ ከመጨረሻዎቹ እጩዎች ተርታ ለመግባት የቻለው ብቸኛው ግብ ጠባቂ  ከስምንት ዓመት በፊት የጁቬንትስ እና የጣሊያን ተጨዋች የሆነው ጂያንሉጂ ቡፎን  ነበር፡፡ በሌላ በኩል የወርቅ ኳስ ተሸልሞ የሚያውቅ በረኛ በታሪክ አንድ   ጊዜ ብቻ አጋጥሟል፡፡ በ1963 እኤአ  ‹ጥቁሩ ሸረሪት› በሚል ስም የሚጠራው ራሽያዊው ግብ ጠባቂ ሌቭያሺን የተሸለመበት ነበር፡፡
የማራቶን ሪከርድና ኃይሌ
2014 እኤአ የዓለም የማራቶን ሪከርድ በኬንያዊው አትሌት ዴኒስ ኬሜቶ በበርሊን ማራቶን መሰበሩ አበይት ክስተት ነበር፡፡ ዴኒስ ኬሚቶ ያስመዘገበው አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ 2፡02፡57 የተመዘገበ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው በ2007 እና በ2008 እኤአ ላይ ለሁለት ጊዜያት የዓለም ማራቶን ክብረወሰኖችን ለማስመዝገብ የበቃው ኢትዮጵያዊ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ራነርስዎርልድ መፅሄት ከወር በፊት ይፋ ባደረገው አንድ ዘገባ በማራቶን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ያገኙ አትሌቶችን ደረጃ እንደሚመራ ማስታወቁ ኃይሌ ገ/ስላሴን ያስነሣዋል፡፡ በ2015 እኤአ የመጨረሻ የማራቶን ውድድሩን ለመሮጥ እንደወሰነ ያስታወቀው ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በሩጫ ዘመናቸው ከፍተኛ ገቢ ከሽልማት ገንዘብ ያገኙ አትሌቶች ደረጃን የሚመራው በሰፊ ልዩነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደረጃውን ሳይነጠቅ ለዓመታት እንደሚቆይ ያመለክታል፡፡ ራነርስዎርልድ መፅሄት በዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች የምንግዜም ከፍተኛ የገንዘብ ተሻላሚዎች ደረጃን ያገኘው ከዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ስታስቲክስ ማህበር መሆኑን የሚገልፀው መፅሄቱ በወንዶች ምድብ የምንግዜም ከፍተኛ ተሻላሚ ደረጃ ኃይሌ ገብረስላሴ በ3,548, 398 እንዲሁም በሴቶች ፓውላ ራድክሊፍ በ2,236,415 ዶላር ገቢያቸው ይመሩታል፡፡ በሯጭነት ከ23 ዓመታት በላይ ልምድ ያለውና 41ኛ ዓመቱን የያዘው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከጡረታ በፊት አንድ የመጨረሻ ማራቶን የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው የተናገረው ሰሞኑን ነው፡፡ በማራቶን ተወዳዳሪነት 9 ውድድሮችን ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ ለአራት ጊዜያት የበርሊን ማራቶንን፤ ለሶስት ጊዜያት የዱባይ ማራቶንን አሸንፏል፡፡ በማራቶን ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን ያስመዘገበው ኃይሌ ከ2 ሰዓት ከሰባት ደቂቃዎች በታች በ10 ማራቶኖች፤ ከ2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ በታች በአምስት ማራቶኖች፤ ከ2 ሰዓት 05 ደቂቃ በታች በሶስት ማራቶኖች እንዲሁም ከ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች በአንድ ማራቶን ርቀቱን በመሸፈን ስኬታማ ነበር፡፡

Read 3765 times