Saturday, 13 December 2014 11:24

የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ማህበራት ከማህበራዊ ህይወት ጅማሮ አንስቶ የሚሰፈር ዕድሜ አላቸው:: በመሆኑም ሰዎች ከአንድ በላይ ሆነው መኖር ከጀመሩበት ጊዜ እስካሁን ድረስ ህልውናቸው ጉልህ ሆኖ ይታያል፡፡ ዓይነታቸውና ቅርፃቸውም እንደ ዕድሜያቸው ሁሉ ለአሀዝ አዳጋች ነው፡፡ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ ሲባል ሊቃኙ የታሰቡት በሰዎች የማህበራዊ ህይወት ውስጥ አይነተኛ ድርሻ ያላቸው ማህበራትን ነው፡፡ እነዚህ ማህበራት እንደ እድር፣ ዕቁብ፣ ደቦ፣ አፎሻ፣ ጅጌ፣ ወዘተ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህና መሠል ማህበራት የሰዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሰርዶ ከሥሩ በመመንገል የማህበራዊ ህይወታችን በሬዎች ለመሆናቸው የሚከራከር ቢኖር አንድም ጣዕማቸውን ያልቀመሰ አልያም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቀፍ ማህበራዊ ትሥሥር የከነፈ ሊሆን ይችላል፡፡
የሁላችንም የህይወት ተሞክሮ ከተለያዩ የባለሙያዎች ጥናቶች ጋር ተዳምሮ የሚያሳየን ዕውነታ - ዕድሮችና ማህበራት የሰዎችን የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ፣ አብሮ የመስራት፣ አብሮ የማዘን፣ አብሮ የመደሰት፣ ወዘተ እሴት እያጎሉ ዘመናትን መሻገራቸውን ነው፡፡
አዎ! በርግጥም ማህበራቱ በዕለት ተዕለት የማህበራዊ ህይወታችን ጉልህ ድርሻን ይጫወታሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑት በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት /socio-economic/ ዘንድ አንቱ የተባለ አስተዋጽዖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፣ በአካባቢ ንፅህናና ጥበቃ፣ በግጭት አፈታት፣ በህፃናት አስተዳደግ፣ ወዘተ ሚዛን የሚደፋ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ድጋፍና እገዛ አማካኝነት ወደ አርባ የሚጠጉ ማህበራት ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚከተሉትን ተግባራት አከናውነዋል፡፡
ሁለት ሽህ አምስት መቶ ያህል አስዳጊዎች የተለያዩ የንግድ ሥራ ክህሎት ሥልጠና በመስጠትና ከፊል ብድር ድጎማ በማቅረብ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይዎት እንዲያሻሽሉ አግዘዋል፤
አምስት ሺህ ለሚደርሱ ህፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ደግፈዋል፤
ሁለት ሺህ ያህል አሳዳጊዎቻቸውን ያጡና ተጋላጭ ህፃናት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አድርገዋል፤
አንድ መቶ ስልሳ አምስት መደበኛ ትምህርት ቤት መግባት ያልቻሉ ህፃናትን የአማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ተጠቃሚ አድርገዋል፤
የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ላላገኙ ሰባ ስድስት ህፃናት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አድርገዋል፤
ከአምስት መቶ በላይ የቤተሰብ አባላት የሚኖሩባቸውን ሃምሳ ሁለት ቤቶች አስጠግነዋል፤
በከፍተኛ ችግር ላይ ለነበሩ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ያህል ህፃናት የአልባሳትና መሰል ድጋፎችን አድርገዋል፤
በተጨማሪም ለስድስት መቶ ያህል ሥራ አልባ ወጣቶች የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችና የመሥሪያ ካፒታል ብድር በማገዝ ወደ ሥራ አሰማርተዋል፤
ይህንና መሠል ተግራባትን ያከናወኑ ማህበራት የነበሩ፣ ያሉና ምናልባትም የሚኖሩ ማህበራት ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ዕድሮች፣ የእድር ህብረቶች፣ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ማህበር፣ የተወሰነ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር፣ የመንግሥት ሠራተኞች በራሳቸው አነሳሽነት ለሌሎች ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋሙ ማህራት፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡
እነዚህ ማህበራት በውስጣቸው የተሰባሰቡ በርካታ አባላት ያሏቸው ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ በጣም ተቀባይነት ያላቸው፣ በመተማመንና በመተሳሰብ የሚሰሩ፣ የማህበረሰብ ጥቅምን የሚያስቀድሙ፣ ዲሞክራሲያዊነት - ግልፅነት - ተጠያቂነትን ያሰፈኑ፣ የሚያገለግሉትን የማህበረሰብ ክፍል ለማገልገል ቆርጠው የተነሱና በትትርና የሚሰሩ ማህበራት ናቸው፡፡ እንዲያው ባጠቃላይ ማህበራቱ ተገቢው እገዛ ቢደረግላቸው የሀገራችንን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሰርዶ ሲቻል የመመንገል አልያም የማጠውለግ ትልቅ አቅም ያላቸው የማህበረሰብ እንቁ ሀብት ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም መንግሥት፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ራሱ ማህበረሰቡ ማህበራቱን በሚፈለገውም ሆነ በሚጠበቀው መጠን ሲጠቀሙባቸው አይታዩም፡፡ ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የእነዚህ የማህበረሰቡ ምስርት ተቋማትን ልማታዊ አስተዋፅኦ አበክሮ በመገንዘብ በተለይም ካለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ በማህበራት ዙሪያ በሥፋት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በላይ ጋይንት፣ አውራ አምባ፣ ባህር ዳር፣ ደ/ማርቆስ፣ አዲስ አበባ፣ ደ/ብርሃን፣ ደ/ሲና፣ ቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን፣ መልካጀብዱ፣ ሻሸመኔ፣ አጄ፣ሃዋሳ፣ ቡታጂራ፣ እምድብር፣ ወልቂጤና ጅማ ከሚገኙ ከ140 ያህል የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት/ ማህበራት ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የማህበራቱን ነባራዊ አቅም በማጎልበት ማህበራቱ ለየማህበረሰባቸው ከሚሰጡት ማህበራዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ በማህበረሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የህፃናት፣ የወጣቶችና ሴቶች ችግር መፍታት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የማህበራት ልማት / CBOs Development/ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የማህበራቱን አቅም በተለይ ፕሮጀክት የመፈፀም፣ ሂሳብ አያያዝና የአካባቢ ሃብት አጠቃቀም ስልትና መሰል ዘመናዊ አሰራሮች ረገድ የማህበራቱን አቅም በማጎልበት ማህበራቱ በፍትሃዊነት፤ ባነሰ ዋጋ፣ በተደራሽነት፣ ወዘተ በርካታ ችግር ፈቺና ልማታዊ ሥራዎችን እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዎ! በመላ ሀገራችን ያሉ የህብረተሰቡ የሆኑ ማህበራትን በተቀናጀ መልክ ለልማት ማንቀሳቀስ ቢቻል የማይረታ የችግር ሰርዶ አይኖርም፡፡ እነዚህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ማህበራት በትንሽ ሀገር በቀል ዕገዛ፣ በሀገርኛ መንገድ፣ ሀገራዊ ችግሮችን የመፍታት ዕምቅ ችሎታና ሀይል አላቸው፡፡ ስለሆነም የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅትና የሌሎችንም ጥቂት ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ የተቀናጀ ድጋፍና እገዛ በማድረግና እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ማህበሮቻችንን ለማህበረሰቡ ፋይዳ እንጠቀም!!
ተስፋዬ ይሁኔ

Read 2313 times