Monday, 08 December 2014 14:41

የሴካፋ መዋቅር እና የውድድር ቅርፅ ሊቀየር ይችላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

38ኛው ሻምፒዮና መሰረዙ፤ መካሄዱ አልታወቀም
ዘንድሮ ለ38ኛ ጊዜ መካሄድ የነበረበት የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ‹‹ሴካፋሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ›› እንደሚካሄድ ወይንም እንደሚሰረዝ ቁርጡን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ለውድድሩ አዘጋጅነት በቅድሚያ እድል የተሰጣት ኢትዮጵያ ከ2 ወራት በፊት መስተንግዶውን እንደማትችል ካሳወቀች በኋላ በምትክ አዘጋጅነት ውድድሩን የሚረከብ አገር ለማግኘት አልተቻለም፡፡
ከሳምንት በፊት በዞኑ እግር ኳስ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ሆነው የሚያገለግሉት ኬንያዊው ኒኮላስ ሙንሶኜ፤ ሱዳን ምትክ አዘጋጅ እንደምትሆን ፍንጭ ቢሰጡም የሴካፋል አባል ከሆኑት ሌሎች 10 አገራት ለመስተንግዶው ምንም አይነት ፍላጎት አለማሳየታቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በጎል የስፖርት ድረገፅ ሰሞኑን በተፃፈ ዘገባ የሴካፋ ምክር ቤት የዞኑን ዋና የእግር ኳስ  አጠቃላይ መዋቅር እና ቅርፅ ለመቀየር እየመከረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአንዳንድ ዘገባዎች 38ኛው ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ባለቀ ሰዓት አዘጋጅ የማግኘት እድሉ እንደጠበበና መሰረዙ እንደማይቀር እየተገለፀ ሲሆን የዞኑ እግር ኳስ ምክርቤት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ከመስጠት መቆጠቡ ትችቶች እያደረሰበት ይገኛል፡፡
የጎል ስፖርት ዘገባ የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ እንደ ካፍ የኮንፌደሬሽን እና የሻምፒዮንስ ሊግ የክለብ ውድድሮች በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የዙር ውድድር በማድረግ የፍፃሜው ጨዋታ በተመረጠ የአፍሪካ ከተማ እንዲካሄድ መታቀዱን አውስቷል፡፡  
ይህን እቅድ ከሴካፋ አባል አገራት ኬንያ ታንዛኒያያ ሩዋንዳ፤ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ሲደግፉ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ሁኔታው እያጤኑት እንደሆነም አመልክቷል፡፡
የሴካፋ ምክር ቤት የውድድሩን መዋቅርና ቅርፅ መቼ እደሚቀይር በጎል ስፖርት ዘገባ ባይገለፅም በ2015 እኤአ ላይ 39ኛውን ሻምፒዮና ሩዋንዳ ለማዘጋጀት ቃል መግባቷ ተዘግቧል፡፡  ሩዋንዳ ውድድሩ ዘንድሮ አለመዘጋጀቱ በዞኑ ያለውን እግር ኳስ የሚጎዳ ነው በሚል አቋሟን በመግለፅ ግንባር ቀደም ስትሆን በ2016 እኤአ በሴካፋ ዞን ለመጀመርያ ጊዜ እንዲዘጋጅ ለተፈቀደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን መስተንግዶዋ እክል የሚፈጥር ነው ብላ አውግዛዋለች፡፡
አንዳንድ የአፍሪካ ሚዲያዎች የሴካፋ ውድድር ባለፉት 5 ዓመታት በሱፕርስፖርት የቲቪ ስርጭት ማግኘቱ እንደ በጎ ተመክሮ ቢታይም ዘላቂ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ አለመኖሩ የዞኑን የእግር ኳስ ምክር ቤት አስተዳደራዊ ድክመት እንደሚያሳይ አመልክተዋል፡፡ የዞኑ አገራት በውድድሩ አለመሳባቸው፤ የውድድሩ ሂደት ተስማሚ አለመሆኑና ተሃድሶ ማስፈለጉ፤ የበጀት እና የአዘጋጅ አገራት መጥፋት ተሳታፊ አገራትን ለማስተናገድ በቂ ፋይናንስ አለመኖሩ በሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ዙርያ የተፈጠሩ አሳሳቢ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ዘንድሮ ካልተካሄደ  የዞኑ አገራት እስከ 2017 እኤአ በሚያደርጓቸው አህጉራዊ የማጣርያ ውድድሮች ለሚኖራቸው ብቃት እና አቋም አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩም ስጋት ሆኗል፡፡
ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕን የአፍሪካ አንጋፋ የእግር ኳስ ውድድር ሲሆን  የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና በ1926 ጎሴጅ ካፕ  ተብሎ ተጀምሯል፡፡ በ1973 እኤአ ጀምሮ ደግሞ ሴካፋ ካፕ ተብሎ ሲቀጥል የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ምክር ቤት ሴካፋ በ12 አገራት አባልነት ተመስርቷል፡፡
የሴካፋ ምክር ቤት በዞኑ የእግር ኳስ  አስተዳደር ከ40 ዓመታት በላይ ልምድ ይዞ በየዓመቱ 5 ውድድሮችን በቋሚነት ያካሂዳል፡፡ እነሱም በዞኑ ብሄራዊ ቡድኖች ተሳታፊነት የሚደረገው ዋናው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ፤ የየአገራቱ ሊጎች ሻምፒዮን የሆኑ ክለቦች የሚወዳደሩትና ካጋሜ ካፕ በሚል የሚታወቀው የክለቦች ሻምፒዮና፤በቅርብ አመታት የተጀመረው የአባይ ተፋሰስ አገራትዋንጫ ናይል ቤዚን ካፕ እንዲሁም ሁለቱ የሀ17 እና ሀ 20 ውድድሮች ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ2014 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ የሚፎካከሩ አምስት የመጨረሻ እጩዎችን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ ናይጄርያን ለአፍሪካ ዋንጫ ድል ያበቃውና ዘንድሮ በራሽያው ክለብ ሲኤስኬ ሞስኮ የሚጫወተው አህመድ ሙሳ፤ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትሱ ክለብ አል አሊን የሚገኘው ጋናዊው አሳሞሃ ጊያን፤ በጀርመኑ ክልብ ቦርስያ ዶርትመንድ የሚጫወተው ጋቦናዊው ኤሞሪኮ አቡምያንግ፤ በፈረንሳዩ ክለብ ሊሌ የሚገኘውና የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ናይጄርያ ግብ ጠባቂ የሆነው ቪንሰንት ኢኒዬማ እና በእንግሊዙ ማንችስተርሲቲ ወሳኝ ተሰላፊ የሆነው ኮትዲቯራዊው ያያ ቱሬ ናቸው፡፡ በተያያዘ ቢቢሲ ስፖርት በታሪኩ ብዙ እንባቢዎችን በማሳተፍ ባካሄደው የ2014 የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ምርጫ የ24 ዓመቱ አልጄርያዊ ያሲኒ ብራሂሚ ማሸነፉን አስታውቋል፡፡ ከ207 የፊፋ አባል አገራት ድምፅ በመሰብሰብ ኮከብ ተጨዋቹ እንደተመረጠ የገለፀው ቢቢሲ ስፖርት፤ ያሲኒ ነየመጀመርያው አልጄርያዊ አሸናፊ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ያሲኒ ብራሂሚ በአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ገድል እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ቁልፍ ሚና እንደነበር ሲታወስ፤ በፖርቱጋሉ ክለብ ኤፊሲ ፖርቶ እየተጫወተ ነው፡፡

Read 1767 times