Saturday, 29 November 2014 11:37

ዲባባ በዓለም አትሌቲክስ ብራንድ ሆኖ ይቀጥላል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

የመጨረሻዋ ገንዘቤ አይደለችም  ግን ቢያንስ ሁለት አዲስ ሪከርዶች ለማስመዝገብ እቅድ አላት
ሁለት አዲስ ዲባባዎች እየመጡ ናቸው
ዲባባ አትሌቲክስ ክለብ ሊመሰረት ይችላል

ገንዘቤ ዲባባ በ2015 እኤአ ከ2 በላይ የዓለም ሪከርዶችን በቤት ውስጥ እና የትራክ አትሌቲክስ ውድድሮች ማስመዝገብ እንደምትፈልግ  ተናገረች፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት ማቀዷንም አስታውቃለች፡፡ በ2014 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሴቶች ምድብ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ተርታ የገባችው አትሌቷ ባለፈው ሰሞን የሽልማት ስነስርዓቱ በሞናኮ ሲካሄድ የክብር እንግዳ ነበረች፡፡ በሌላ በኩል የዲባባ ቤተሰብ የአትሌቶች መፍለቂያ እየሆነ መምጣቱን ያወሳው የአይኤኤኤፍ ድረገፅ ዘገባ፤ ከገንዘቤ በኋላ ሌሎች ሁለት ታናናሽ የዲባባ እህትማቾች ወደ ስፖርቱ እያተኮሩ መሆናቸውን ጠቅሶ በቤተሰቡ ዓለም አቀፍ ክብር ያላቸው እና ወደፊትም መግነነን የሚችሉ አትሌቶች ብዛት 7 መድረሱን አመልክቷል፡፡ ከታላቅየው እጅጋየሁ ዲባባ በኋላ ቤተሰቡ ታላቋን የረጅም ርቀት ጥሩነሽ ዲባቡ ለዓለም አትሌቲክስ ያበረከተ ሲሆን የትዳርአጋሯ የሆነው ስለሺ ስህን ሲጨመርበት በስፖርቱ የተካበተውን ልምድ ያስገነዝባል፡፡ 5 ጊዜ የዓለም፤ ሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ወደ ማራቶን ፊቷን ካዞረች በኋላ ታናሿ ገንዘቤ ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረከ ብቅ ብላለች፡፡ ሌላው የቤተሰቡ ወንድም ከቤተሰቡ ጋር ሰፊ ልምምድ በመስራት የሚታወቅ ሲሆን አሁን የማራቶን ሯጭ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ከዲባባ ቤተሰብ ታናሽያዋ እህት አና ዲባባ ትባላለች ብቅ ብላለች፡፡ አና ለዓለምኮከብ አትሌቶች ምርጫ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ባለፈው ሳምንት በሞናኮ በነበረችበት ወቅት የእህቷ አስተርጓሚ እና አማካሪ ሆና አብራ ነበረች፡፡ የአይኤኤፍ ዘገባ እንደሚያስረዳው ከዲባባ ቤተሰብ ከታላቋ ጥሩነሽ በኋላ የአትሌቲክስ ስፖርት ለየት ባለ የፕሮፌሽናል ደረጃ ገንቤ የወጣችበት ሆኗል፡፡ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች፤ በማይል የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ በቤትውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች፤ በወጣቶች እና በአዋቂ የዓለምሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ውድድሮች በአጭር ጊዜ ሰፊ እና ዘመናዊ ልምድ በማካበት ለውጥ አሳይታለች፡፡
 ታናሽየዋ አና ዲባባ ደግሞ ከቤተሰቡ የአትሌቲክስ ስፖርት ልምድ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆና ልዩ ተዓምር በአትሌቲክሱ ዓለም ማሳየቷእንደማይቀርም ዘገባው ያትታል፡፡ አትሌት ገንዘቤዲባባ ወቅቱን የጠበቀች ዓለም አቀፍ  ደረጃ ያሟላች ፕሮፌሽናል ሯጭ መሆና የልምምድ አሰራሯ እና የዓለም ሚዲያን ትኩረት መሳቧ ማስረጃዎች ይሆናሉ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የአትሌቲክስ ልምምዷን በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከምትሰራው ልምምድ ባሻገር ለሁለት ወራት በስፔን ለአንድ ወር ደግሞ በስዊድን መዘጋጀቷ ውጤታማ አድርጓታል፡፡ ዋና አሰልጣኟ ጃማ ኤደን ይባላል፡፡  በትውልድ ሶማሊያዊ ነው፡፡ የመካከለኛ ርቀት የዓለም ሻምፒዮን ከሆኑት ጅቡቲያዊው አይናለህ ሱሌማንና ሱዳናዊው አቡበከር ካኪ የሚሰራው ይህ አሰልጣኝ ከገንዘቤ ሌላ በስሩ ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶችንም ያሰለጥናል፡፡  እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች አሰልጣኝ ሆኖ እየሰራ ነው፡፡ የአይኤኤኤፍ ዘገባ እንዳሰፈረው ገንዘቤ ዲባባ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቢያንስ ሁለት የዓለም ሪከርዶችን  ለማስመዝገብ ከዋና አሰልጣኟ  በእቅድእየሰራችነው፡፡ በተለይ ከ3 ወራት በኋላ በ2 ማይል ሩጫ የዓለም ሪከርድን ለማሻሻል አሁን ትኩረት አድርጋለች፡፡ የ27 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በ2014 የውድድር ዘመን በ1500 ፣ 3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እና በ2 ማይል በ15 ቀናት ልዩነት 3 የዓለም ሪከርዶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡
 በውድድር ዘመኑ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እና በኢንተርኮንትኔንታል ካፕ የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፋለች፡፡
ለዚህም ይመስላል በሞናኮ በሰጠችው መግለጫ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ውጤት ያገኘሁበት ብላ አድንቃዋለች፡፡ በተያያዘ ዲባባ የሚለው ስም በዓለም አትሌቲክስ ስኬቱ መቀጠሉን ከሞናኮ ያወሳው የአይኤኤኤፍ ዘጋቢ ለምን የአትሌቲክስ ትምህርት ቤት አይከፈትም  በስማችሁ አትከፍቱም ብሎ ለገንዘቤ ዲባባ ጥያቄ አቅርቦላታል፡፡
 ‹‹ ወደፊት የዲባባ አትሌቲክስ ክለብ እናቋቁም ይሆናል፡፡ ጥሩ ሃሳብ ነው›› በማለት መልሳለች፡፡

Read 3146 times