Saturday, 29 November 2014 11:29

የምሬት ድምጾች

Written by 
Rate this item
(26 votes)

ሀና ላላንጎ የአስራ ስድስት አመት ታዳጊ ናት ፡፡ አየር ጤና አካባቢ  ከትምህርት ቤት ወደ ቤቷ ለመሄድ በተሳፈረችበት ሚኒባስ ታክሲ ተገዳ ከተወሰደች በኋላ በደረሰባት የቡድን የመደፈር ጥቃት ምክንያት ህይወቷ አልፏል፣ ጉዳዩ በህግ ተይዟል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት  ሰላም ለሴቶች ከጓዳ እስከ አደባባይ  በሚል መርህ ዘንድሮ ስለሚከበረው ዘመቻ በፆታዊ ጥቃት ዝግጅት እና በሃና ጉዳይ ላይ በራስ ሆቴል ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ መድረኩ ላይ ስለሀና የተሰጡ አስተያየቶችን መርጠን ለጋዜጣው በሚመች መልኩ ኤልሳቤት ዕቁባይ አቅርባዋለች፡፡

“አውሬ ያለ ጫካ አይኖርም”
ዶክተር ምህረት ደበበ

ለሀና ቤተሰቦች መፅናናት እንዲሆን የሀና ሞት የብዙዎች ትንሳኤ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን አንድ ጥያቄ እንድንጠይቅ እፈልጋለሁ፡፡ ሀናን ማን ገደላት ሀና በአንድ ቀን አልሞተችም፡፡ ሀናን የገደሏት ሰዎች አንድ ቀን አልተጠቀሙም፡፡ አንደኛ፤ ሀናን የገደላት የሀናን ገዳይ የፈጠረ ህብረተሰብ ነው፡፡ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ሲወለዱ እና በጨቅላ እድሜያቸው እንዲህ አይነት ሰዎች እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ የእኛ የእጅ ስራ ናቸው፡፡ ሁለተኛ፤ ሀና የዛን ቀን አባቷ እንደተናገሩት በብዙ ሰዎች አጠገብ እና የማዳን ሀይል ወይም ችሎታ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፈችው፡፡ ሀና ላይ ይህን ድርጊት የፈፀሙ ሰዎችን ብዙዎች የኮነኑ ሲሆን፤ እንዲያውም ፌስቡክ ላይ አውሬዎች ተብለዋል፣ ግን አውሬ ያለጫካ አይኖርም፡፡ እያንዳንዳችን ጫካ ሆነናል፡፡ ይዘዋት የገቡበት ግቢ ሰፊ ነው፡፡ የነዛ ሰዎች ጎረቤቶች ገድለዋታል፡፡ ቸልተኝነት ሊሆን ይችላል የአካል ሊሆን ይችላል ግን ድፍረት ነው፡፡   ድፍረት ማለት የአንድን ሰው ክብር ማዋረድ ማለት ነው፡፡ የማዳን ሀይል ያላቸው ፍትህ ማስፈፀም የሚገባቸውም ገድለዋታል፡፡ ያንን መቀበል አለብን፡፡  በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ሀናን ሆስፒታል ያሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው የገደሏት ፡፡ ደፍረዋታል፣ እኔ ሀኪም ስለሆንኩኝ አፍሬያለሁ፡፡ እኔ ግማሹን ጊዜዬን አሜሪካን ነው የምሰራው፡፡ እዛ ቢሆን ሊደረግ የሚችለውን ነገር ስለማውቅ ሀና ምንም ስለሆነች ብቻ ሳይሆን ሰው ስለሆነች፣ የማንም ልጅ ስለሆነች ሳይሆን ሰው ስለሆነች፡፡ ሀና የተገደለችው በደፈሯት ሰዎች ቤት ውስጥ አይደለም፡፡
በሆስፒታል ውስጥ ነው፣ ሰው እንዴት ሆስፒታል ውስጥ ይሞታል? መጨረሻ ላይ የምለው ሀናን የገደልኳት እኔ ነኝ፤ ነው፡፡
እዚህ ላይ ሶስት ትላልቅ ነገሮች አሉ አንዱ ፆታ ነው፡፡ ሁለተኛው ወሲብ ነው፡፡ ሶስተኛው ጥቃት ወይም ሀይል ነው፡፡ እያንዳንዳችን ስለወሲብ የምንናገረው እና ስለወሲብ የምናስበው ነገር እስኪስተካከል ድረስ እንዲህ አይነት ነገር አይቆምም፡፡  ህመሙ ያለው ሴቶች ላይ በተጫነው ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ወንድነት መስተካከል እስካልቻለ ድረስ  እንደዚህ አይነት ነገር አይቆምም፡፡ ይህ አይነቱ ትልቅ ድፍረት ከመፈፀሙ በፊት መንገድ ላይ ብዙ ትንንሽ ድፍረቶች አሉ፡፡ ትልቁ ድፍረት በቋንቋችን ውስጥ ታጭቋል፡፡ ቋንቋችን ምን ያህል ቫዮለንት እንደሆነ ፣ ምን ያህል የሰዎችን ክብር የሚያዋርድ እንደሆነ ከቤት እስከ መንገድ ማየት ይቻላል፡፡
ወንዶች ለሚያደርጉት ነገር ብዙ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ዛሬ እስቲ ገልብጠን እንየው፡፡  ግን ለምን አብዛኛው ወንድ እንደዛ አልሆነም፡፡ ወንድነት ምንድን ነው? ጀግንነት ምንድን ነው? ደካማን ማገዝ ፣መርዳት  እኔ አንድ የምለው ነገር አለ ሰዎች ካንገት በላይ ካላደጉ ካንገት በታች ነው የሚኖሩት፣ ካንገት በታች ደግሞ ምንም ማሰብ የሚችል ነገር የለንም፡፡ ስሜትን መግዛት የሚችል ነገር የለንም፡፡ እዚህ ብንቆጠር ሴቶች ይበዛሉ፣ ሴቶች እዚህ የመጡት ስላጠፉ ነው፡፡ መቆጣት እና መሰብሰብ የነበረበት ማን ነው ፡፡ ልክ እንደ ሀኪም ባለሙያነቴ አሁንም በወንድነቴ አፍራለሁ፣ አብዛኛው ፖሊስ ማን ነው?  ወንድ ነው ሴት ነው፣ አብዛኛው የጤና ባለሙያ ማን ነው? የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ማን ነው? ወንድ፡፡ እንደዚህ አይደለም ካልን ለምንድን ነው አክት የማናደርገው፡፡
 ይህ የሴቶች ጉዳይ ተብሎ ታይቶ ይሆናል፡፡ አይደለም፡፡ የወንዶች ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ልክ ድርጊቱን ከፈፀሙት ሰዎች እኩል ሀላፊነት መሸከም አለብኝ፡፡ የማህበረሰብ ለውጥ እስኪካሄድ ድረስ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡


“ከዚህ በላይ ምን ሽብር አለ”
ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ

በጣም አዝኛለሁ፣ ሆድ ብሶኛል፣ ደክሞኛል፡፡ የልብ ድካም ነገር ካለ፣ ድሮ በሽታ ነበር የሚመስለኝ፤ አሁን ግን የሚረዳ ማጣት ማለት ነው፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ልክ እንደዚህ በኢትዮጲያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ትሰራ በነበረችው በአበራሽ ላይ በተፈፀመው ድርጊት ደንግጠን አሁን በአይኔ መጣ የሚል እንቅስቃሴ ጀምረን ልክ የዛሬውን አይነት ሂደት አልፈን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እዛው ተመለስን፡፡ ማንንም ከመውቀሳችን በፊት እያንዳንዳችን ራሳችንን እንጠይቅ እንደተባለው ራሴን ጠየቅኩ፡፡ እኛ እንግዲህ በተነፃፃሪ ተጠቃሚ ከሚባው የህብረተሰብ ክፍል ነን፡፡ እውቀት አለን፣ ብዙ ነገሮችን የማየት እድል አለን፣ከሌላ የተሻለ ገንዘብ አለን፡፡ ግን እየሰራን ያለነው ስራ ውጤት የማያመጣው በበቂ እየሰራን አይደለም ማለት ነው ወይስ አልቻልንበትም ወይስ ተንቀን ነው ብዬ አሰብኩ፡፡  ወጣቶቹን ሳይ፣ ዶክተር ምህረትን፣ ሀይሌ ገብረስላሴን ሳይ ደግሞ ደስ አለኝ፡፡  ሌላው ያሰብኩት ደግሞ እዚህ አገር ሰው ሁሉ የሚፈራው ፀረሽብር ህጉን ነው፡፡ ግን ከዚህ በላይ ምን ሽብር አለ? ለኔ ሽብር ማለት በሰላም ወጥቶ አለመግባት ማለት ነው፡፡ ህጉ ይቀየርልን ሳይሆን ወደ ፀረ ሽብር ሕጉ ይቀየርልን፡፡ እነሱ ስለሚፈሩ ነው ጸረ ሽብርተኛ ህግ ውስጥ የከተቱት፡፡ ትንሽ ቀን መንግስት ቀጥቀጥ ቢያደርግ ብዙ ነገር እንደሚጠፋ መገመት ይቻላል፡፡
ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ

“ይቺን አገር ያጠፋት ምንአገባኝ ነው”
አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

የሃና ቤተሰቦችን እግዚአብሄር ያፅናቸው፡፡ይህ ነገር ዜና ሆኖ የወጣው ለምን እንደሆነ ሳንግባባ የቀረን አይመስለኝም፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ብዙ የለም ብላችሁ ታስባላችሁ እጅግ ብዙ አለ፡፡ ሀና ስለሞተች ነገ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለማይጠቋቆሙባት እና ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ ነገሮች ስለማይፈፀምባት እንጂ የሀና አይነት ሺዎች ናቸው - ሁሉንም ነገር በውስጣቸው ይዘው የተቀመጡ፡፡ ይቺን አገር ያጠፋት ምንአገባኝ ነው፡፡ጥቃት ሲፈፀም ብናይ ይበላት እንዲህ ሆኖ ነው እንዲህ አድርጋው ነው ይባላል፡፡ መንገድ ላይ የሆነ ነገር አጋጥሞኝ ጣልቃ ስገባ ምን አገባው ምን ቤት ነው የሚሉ አሉ፡፡ እነሱ ምን አገባቸው? እንዴት አያገባኝም?! የምኖርባት አገር እኮ ነች፡፡ ይቺን አገር ነው ጥሩ ሆና ማየት የምፈልገው ፡፡ ሌላው በጣም ያስደነገጠኝ በአምስት ሰዎች የተፈፀመ መሆኑ ነው፡፡ አምስት ሰዎች እንዴት አንድ አይነት አስተሳሰብ ውስጥ ገብተው ይህን ድርጊት ሊፈፀሙ ቻሉ፡፡ አንዱ እንኳን ጥያቄ አይፈጠርበትም? በዚች አገር ብዙ የሚሰቀጥጡ ታሪኮች አሉ፡፡ ነገር ግን ድርጊቶቹ የኛ ድምር ውጤት ናቸው፡፡ ይህን ከሰማሁ ጀምሮ ልጆቻችንን ለምን አመጣናቸው የሚል ስጋት ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ መፍትሄውን ከፖሊስ፣ ከፍትህ አካል ብቻ አንጠብቅ፡፡ እኔ እንዲያውም እድሜ ልክ ከማሰር በአደባባይ አርባ ጅራፍ መግረፍ ውጤት ሳያመጣ አይቀርም፡፡


Read 12108 times