Saturday, 22 November 2014 12:41

ከወር በላይ የተቋረጠው “ከሠላምታ ጋር” መታየት ሊጀምር ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

አርቲስት ፈለቀ፤ ሳልፈልግ ቴአትሩን እንዳቋርጥ ተደርጌአለሁ አለ

“Desperate to Fight” የተሰኘውና በደራሲ መዓዛ ወርቁ “ከሠላምታ ጋር” በሚል ወደ አማርኛ የተተረጎመው ቴአትር፤ ለተወሰነ ጊዜ ከተቋረጠ በኋላ የፊታችን ሰኞ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ እንደገና መታየት እንደሚጀምር ፕሮዱዩሰሩ አቶ ዘካሪያስ ካሱ ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡  ቴአትሩ ለአምስት ወራት በጃዝ አምባ አዳራሽ፣ በዓለም ሲኒማና በኤድናሞል ሲኒማ ለተመልካች ሲቀርብ እንደነበር የጠቆሙት ፕሮዱዩሰሩ፤አንድ ተዋናይ ስራ በማቋረጡ ከመስከረም 26 ቀን 2007 ጀምሮ መታየት አቁሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን አዲስ ተዋናይ እንደቀየሩና ለተመልካች መቅረብ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
ከመጀመሪያ አንስቶ በተውኔቱ ላይ ሶስት ገፀ-ባህርያትን ወክሎ ሲጫወት የቆየው አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ በበኩሉ፤ ቴአትሩን ሳልፈልግ እንዳቋርጥ ያደረገኝ የማኔጅመንቱ ችግር ነው ብሏል፡፡
“ከሠላምታ ጋር” የተሰኘው ቴአትር በፈጠራ ጽሁፍ፣ በአቀራረብና በሚቀርብበት ቦታ ተወዳጅነትን አትርፎ እንደነበር የገለጹት ፕሮዱዩሰሩ፤በተዋንያን ምክንያት ትርኢቶች የሚቋረጡበትን አካሄድ የሚያሻሽል አሰራር እንደሚተገብሩ ጠቁመዋል፡፡
“በሌላው ዓለም በቴአትር ስራ ተጠባባቂ ተዋናይ (under study) አዘጋጅቶ ማቆየት የተለመደ ነው፤በእኛ አገር ይህ አሰራር ባለመለመዱ ብዙ ትርኢቶች እየተቋረጡ ተመልካቾችን እያሳዘኑ ነው፤ይሄ ሁኔታ ማብቃት አለበት” ብለዋል - የቴአትሩ አዘጋጆቹ ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ፡፡ ከሰኞ ጀምሮ አርቲስት አለማየሁ ታደሰን በአርቲስት ፈለቀ የማርውሃ አበበ ቦታ ተክተው እንደሚያሰሩ የጠቆመው መግለጫው፤ ተጠባባቂ ተዋንያንን የማዘጋጀቱ ስራ በአርቲስት ኤልሳቤት መላኩ፣ በቴአትሩ ላይ በሚሳተፉ ዳንሰኞችና በሌሎችም ተዋንያን ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
“እንዲህ መደረጉ ቴአትር በፍፁም መቋረጥ የለበትም (The show must go on) የሚለውን መርህ ያስከብራል” ያሉት ፕሮዲዩሰር ዘካሪያስ ካሱ፤ “አሰራሩ ከጊዜ፣ ከጉልበት፣ ከገንዘብና መሰል ወጪዎች አንፃር ከባድ ቢሆንም በቴአትር መቋረጥ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው” ብለዋል፡፡
 አርቲስት ፈለቀ የማርውሃ አበበ በበኩሉ፤ “ቴአትሩን ሳልፈልግ እንዳቋርጥ ያደረገኝ የማኔጅመንቱ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ነው” ብሏል፡፡ ቴአትር በፍፁም መቋረጥ የለበትም “The show must go on” የሚለውን መርህ ከማንም የበለጠ እንደማከብር፣ የእናቴን አስከሬን አስቀምጬ መድረክ ላይ መተወኔና የቀለበቴን ስነስርዓት ቴአትር ሰርቼ ስጨርስ እዚያው መድረክ ላይ መፈፀሜ  ምስክር ናቸው ብሏል፡፡
“ይሄን መርህ ለማክበር፣ ለሙያዬ ያለኝን ክብር ለመግለፅ እንዲሁም እኔን ሊመለከት የመጣውን ሰው ማክበሬንና ማፍቀሬን ለማሳየት፣ ማኔጅመንቱ ለሁለት ወር ያለ ክፍያ ሲያሰራኝ፣ ከኪሴ ወጪ እያወጣሁ፣ በነፃ ሳገለግል ቆይቻለሁ” ያለው አርቲስቱ፤ “ከቀረኝ ክፍያ ላይ ግማሹን የከፈሉኝ እንኳን ከ15 ቀን በፊት ነው፤ አሁንም ቀሪ ክፍያ አለኝ” ብሏል፡፡
“ማኔጅመንቱ የራሱን  ችግር ሳይቀርፍ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እኔ ፈልጌ ስራውን እንዳቋረጥኩ ተደርጎ በተናፈሰው አሉባልታ በጣም አዝኛለሁ” ያለው አርቲስት ፈለቀ፤ “የቴአትር አፍቃሪያን ለስራዬ ፍቅርና ክብር እንዳለኝና ሀዘኔንም ደስታዬንም በመድረክ ላይ የማሳልፍ መሆኑን አውቆ እውነታውን እንዲረዳ እፈልጋለሁ” ብሏል፡፡ የስራ ውሉ እንዳልተቋረጠም አርቲስቱ አክሎ ገልጿል፡፡
የቴአትሩ ፕሮዱዩሰር አቶ ዘካሪያስ ካሱ፤ ከአርቲስት ፈለቀ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ ጠይቀናቸው፤ “እኛ ከሁለት ወር በፊት በተፈፀመ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማባከን ትተን አዲስ ስራ ጀምረናል፤ ቴአትሩን የፊታችን ሰኞ በአዲስ መልክ ለመጀመር ሩጫ ላይ ስለሆንን ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አይደለሁም” ብለዋል፡፡  


Read 1557 times