Saturday, 22 November 2014 12:39

ፍቅር በልጅነት በደብዳቤና ያለ ደብዳቤ

Written by 
Rate this item
(53 votes)

          ሰባተኛ ክፍል እያለን እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ አርብ የክፍል ቤስት ጓደኛዬ የሆነው ልጅ ደብተሬ ውስጥ ደብዳቤ እንዳስቀመጠና ቅዳሜንና እሁድን አስቤበት ሰኞ ምላሽ እንደሚጠብቅ ነገረኝ፡፡ ልጁ ባይጽፍልኝም እንደምንዋደድ ራሳችንም እናውቃለን፡፡ አብረን እናጠናለን፣ አብረን እንረብሻለን፣ አብረን እንጫወታለን፡፡
ክፍል ውስጥ የራሱ መቀመጫ ቢኖረውም አብዛኛውን ጊዜ የኔ ወንበር ላይ ነበር የሚገኘው፡፡ ቤቶቼ ያውቁታል፤ ይወዱታል፡፡ ከዚህ ያለፈ ምን ማድረግ እንደሚቻል አላውቅም፡፡ ብቻ ለደብዳቤው መልስ ይፈልጋል፡፡ በመርህ ደረጃ 12 ሳልጨርስ ጓደኛ ብሎ ነገር በጊዜው ለኔ ስህተት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መልሴ ሳይጠይቀኝ የታወቀ ቢሆንም የተጨነኩት ከዚህ በኋላ ምን አይነት ግንኙነት ሊኖረን ነው ብዬ ነበር፡፡ እንደፈራሁት መፈራራትና መተፋፈር ጀመርን፡፡ ቀስ እያልንም ተራራቅን፡፡
በዚህ መሃል ማን ቢቀበለኝ ጥሩ ነው….ይሄንን ሁኔታ ያየና የተከታተለ ሌላ የክፍል ልጅ ለአባቱ እንዲህ አላቸው “…ፌቨን ጐበዝ ተማሪ ትወዳለች፡፡
ወደፊት እሷን ማግባት ስለምፈልግ ካሁኑ በትምህርቴ መጐበዝ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ እሷ የማጠናከሪያ ትምህርት የምትማርበት ቦታ አስመዘግበኝ፡፡”
ይሄን እንግዲህ አባቱ ለአባቴ “ልጅህ ልጄን ጐበዝ ልታደርግልኝ ነው” ብለው ነግረውት የሰማሁት ነው፡፡ እሱ ግን ለኔ ምንም አላለኝም ነበር፡፡ ልጅት ሆዬ ሁኔታውን መከታተል ጀመርኩ፡፡ በርግጥም ልጁ የክፍል ውስጥ ተሳትፎው ጨመረ፡፡ የቤት ስራዎችን ጠንቅቆ ይሰራ ጀመር፡፡ አባቱ የልጄ የወደፊት ሚስት ብለው ይሁን ወይ እንደ ባለውለታቸው ቆጥረውኝ ብቻ…ባገኙኝ ጊዜ ሁሉ ፍሽክ ፍሽክሽክ ብለው ሰላምታ ይሰጡኛል፡፡ ስመውም አይጠግቡኝም ነበር፡፡ ታዲያ እኔ በማየው ነገር እየገረመኝ፣ ዮሲንም እየወደድኩት፣ አባቱ እየተደሰቱ፣ ዮሲ ዓላማውን ለማሳካት መንገዱን እየጠበጠበ ባለበት ወቅት የኢትዮ - ኤርትራ ግጭት በመጀመሩ ተለያየን፡፡
ዮሲን አደንቀዋለሁ፡፡ ሚስት ሁኚኝ አላለኝም፤ ራሱን ለብቁ ባልነት ማዘጋጀት ግን ጀምሯል፡፡ እንዲህ አይነቱን ማን አይወድም? እኔ እወዳለሁ!
ዮሲ ከሄደ በኋላ ልቤን ያስደነገጠ ሳይገኝ አመት አለፈ፡፡
ኛ ክፍል ላይ እንደገና ተረታሁ፡፡ ልጁ እንደሚወደኝ ነገረኝ፤ እንደምወደው ነገርኩት፡፡  በጣም አስብለት ነበር፡፡ ትዝ ከሚሉኝና ተቃውሜውም የማላውቀው ነገር ደብተሬ ላይ እየተፈላሰፈ የሚጽፈው ነገር ነው፡፡ ሁለት ገጽ፣ ሶስት ገጽ ይጽፋል (ስለ ፍቅር፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ጓደኝነት…) አልገነጥለውም፡፡ ግን ያንን ደብተሬን ለማንም አልሰጥም፡፡ ቲቸርም የደብተር ማርክ ሲሞሉ አስተውለውት አያውቁም፡፡ የ9ኛ ክፍል የCivic ደብተሬ፣ የሱን ጥራዝ ነጠቅ ሃሳቦች እንደያዘ ማን አወቀ? ከኔና ከራሱ በቀር፡፡
ዮሲ አሁን የት እንዳለ አላውቅም፡፡
ከዚህኛው ልጅ ጋር እንኳን ከብዙ አመት በኋላ ፌስቡክ ላይ ተገናኝተን አወራን፤ መለያየታችንን ኮነንን፡፡ የአንድ የቆንጅዬ ልጅ አባት ሆኖ አገኘሁት፡፡ እኔ፤ ሆዴዴዴዴን እስኪያመኝ ቀናሁ፡፡ ሚስቱ በጣም ፉንጋ ናት አይደል? “Say” አዎ በናታችሁ!
*   *   *
የመጀመሪያ ደብዳቤ የደረሰኝ 7ኛ ክፍል ሆኜ ነው፡፡ የፃፈልኝ ልጅ በጣም ቀጭን ሲሆን ስሙ ብርሃኑ ይባላል፤ ግን ሉሲ ብሬ የሚል ቅጽል ስም ነበረው፡፡ ዳር ዳሩን በአበባ ባጌጠ ወረቀት ላይ አስቂኝ ፅሁፍ ሰጠኝ “እንደ እንጀራ ለምትርቢኝ እንደ ውሀ ለምትጠሚኝ ውድ ፍቅሬ…” ይልና በመጠማትና በመራብ ዙሪያ ትንተና ይሰጣል፡፡ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ወር ሙሉ ሳቅንበት፡፡ እሱም ሰኔ 30 ጥርሴን እንደሚያስለቅመኝ ዝቶ ተለያየን (እኔ በጣም ወፍራም ስለነበርኩ ማች አናደርግም ብዬ ነው)
ሁለተኛ ደግሞ እዛው 7ኛ ክፍል ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ነው የደረሰኝ፡፡ ልጁ ሰፈር፣ ትምህርት ቤት ያስቸገረ ነውጠኛ፤ በጉልበቱ የሚያምን አይነት ነበር፡፡ ደብዳቤው የተፃፈው እንደነገሩ ነው “እወድሻለሁ ስትወጪ ጠብቂኝ” ይላል፡፡ አላመነታሁም፤ ጠበቅሁት፡፡ ምን እንዳወራን ባላስታውስም ሰፈር ድረስ ሸኘኝ፡፡ የቤታችን በር ጋ ስደርስ “ጓደኛዬ ነሽ፤ ከዚህ በኋላ ከሌላ ሰው ጋር እንዳላይሽ” ኧረ ማስጠንቀቂያ! ቤት ደግሞ ጓደኛ መያዜ ከተሰማ እገደላለሁ “እኔ ጓደኛህ መሆን አልፈልግም” አልኩት፡፡ “አስቢበት” ብሎ ጥሎኝ ሄደ፡፡ ጓደኛዬን ሳማክራት፣ ቤተሰቦቼ ሳያውቁ ጓደኛ እንዳደርገው አስማማችኝ፡፡ በበነጋታው በር ላይ ጠብቆ “እእ..” አለኝ፤ ትንሽ አመንትቼ “እሺ” አልኩት፡፡ እናም በክብር ያቺን አመት ጨረስኩ፡፡ ሰኔ ሰላሳም ሳልመታ አለፈ ግን ማርያምን ምንም አላደረግንም፡፡
ተወዳጅ መኮንን
*   *   *
ስምንተኛ ክፍል ሆኜ ነው፡፡ የሰፈሬ ልጅ ደብዳቤ ፅፎ ላከልኝ፡፡ ደብዳቤውን ያመጣው ትንሽ ልጅ ነበር፡፡ በወቅቱ ለወንድ ልጅ ካለኝ ፍርሃት የተነሳ ደፋር ነበርኩ፡፡ ፍርሃት በጣም ደፋር ያደርጋል ያሉት ለካ ወደው አይደለም፡፡
የተላከው ልጅ ከቤት አስጠርቶኝ “ለእሷ ብቻ ስጥ” ተብሏል መሰለኝ፣ ደብቆ ሰጠኝ፡፡ ገለጥ አድርጌ ሳየው ገባኝ፡፡ የልብ ቅርፅ ተስሎበታል፡፡ በአረንጓዴና በቀይ እስክርቢቶ በሚያምር የእጅ ፅሁፍ ተጽፏል፡፡ (የልጁ እጅ ፅሁፍ ማማር እራሱ ግርም ይለኛል) የወረቀቱ አስተጣጠፍ እንኳን በጣም ልዩ ነበር፡፡
በአንዴ ከድንጋጤም ድፍረትም ከየት እንደመጣ እንጃ! (አትንኩኝ ነው ነገሩ) ወረቀቱን አጣጥፌ ብጭቅ ብጭቅ አደረግሁትና፤ (ውይ ክፋቴ)
“ሲርብህ ብላው ብላሃለች በለህ” ብዬ መልሼ ሰጠሁት፡፡
አቤት…ከዚያ ወዲያ አኔም ሳላናግረው፣ እሱም ቀና ብሎ ሳያየኝ፣ ከዚያ ሰፈር ወጣሁ፡፡ በጣም ትልልቆች ሆነን እንኳን አላናግረውም ነበር፡፡
ሁለተኛውና የመጨረሻው 9ኛ ክፍል ስማር በዕረፍት ሰአት ደብተሬ ውስጥ ያገኘሁት፣ ማንነቱንና ምንነቱን ያልገለፀ ሰው በሙንጭርጭር ጽሑፍ የፃፈልኝ ደብዳቤ ነው፡፡ “መነን ት/ቤት መታጠፊያው ላይ ጠብቂኝ” የሚል ቀጠሮ ሁሉ ነበረው፡፡ (ማን እንደሆነ ሳይታወቅ!) ወይ ጊዜ፤ እንዴት ይሮጣል!
ሮሚ
*   *   *
የደረጃ…የስፔሻል ክላስ ተማሪ…ማፍቀር መፈቀር የማይታሰቡ ነገሮች…መሸ ነጋ ደብተሬ ላይ የምቸከል…ስለ ፍቅር ሲወራ “እኔ አላማ አለኝ፤ እንዲህ አይነት ነገር አላደርግም” ምናምን የምል… አካባጅ ነበርኩ፡፡ ከመምህሮቼ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ስላለኝ ተማሪዎችም ደፍረው አይቀርቡኝም፡፡ እና ደብዳቤ ምናምን አልተጻፈልኝም (አሁን ቆጨኝ!)
ሁሌም አመሻሽ ላይ ከእህቶቼ ጋር የሃይማኖት ትምህርት ለመከታተል ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፡፡ ትምህርት አልቆ ማታ ወደ ቤት ስንመለስ፣ ከመድሃኒያለም እስከ ሃያ ሁለት ጫፍ ዎክ እናደርጋለን፡፡ (በዚያ መስመር ብዙ ሰው ዎክ ያደርጋል) አንዳንዴ የማንገዛውን ቡቲክ ገብተን እንጠይቃለን… ሃሃሃ…
እዚያ አካባቢ የቀበሌ መዝናኛ ፑል ቤት አለ፡፡ ሁሌ በር ላይ የሚቆሙ ፍንዳታዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው ላይ አይኔ አረፈና ተከየፍኩበት፡፡ ታዲያ የማየው ከሩቁ ነው፡፡ ቁመናውን እንጂ ጠጋ ብዬ ፊቱን አይቼው አላውቅም፡፡ እሱም በጨለማ ነው፡፡ በመንገድ መብራት ድብዝዝ ብሎ ነበር የሚታየኝ፡፡ ቆንጅዬ፤ ጠይም እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ዛሬ ፊቱን ማየት አለብኝ ብዬ ከሩቅ አስቤ እሄድና ልክ መቶ ሜትር ሲቀኝ አንገቴን አቀረቅራለሁ፡፡ ድፍረቴ ኦና ይሆናል፡፡ መቼም አጠገቡ ቆሜ እንደማላወራው አውቀዋለሁ፡፡ በሩቁ ብቻዬን ነበር ያፈቀርኩት፡፡ ለእህቶቼም እንኳን አልነገርኩም፡፡ አንድ ቀን ብቻዬን ወደ ቤተክርስትያን ስሄድ ከኋላዬ ደረሰብኝ፡፡ ነፍሴ ተርበተበተች፡፡
“ሃይ… ሰላም ነው” አለኝ ስሜን ጠርቶ፡፡ ስሜን መጥራቱ ቢያስደስተኝም አንደበቴ ተለጉሞ ዝም አልኩት፡፡
“ከኋላ በጣም ታምሪያለሽ” አለ፤ ቀጠለና፡፡ አስቀያሚ ብሎ የሰደበኝ መሰለኝ፡፡ ተናደድኩበት፡፡
“እንትን ጋራጅን ታውቂዋለሽ? እዛ ነው ምሰራው” አለኝ
“እግር ኳስ ተጫዋችና ጋራጅ ሰራተኛ እወዳለሁ” አልኩት፡፡ በኋላ “ለምን አልኩት” ብዬ ፀፀተኝ፡፡
“እንትናንስ ታውቂዋለሽ?” (ባለጋራጁን ማለቱ ነው)
“እንጃ ብዙ አላውቀውም” አልኩት፡፡
“ስልክ ቁጥሯን ተቀበልልኝ ብሎ ነው”
“ይሄ ትልቁ ሰውዬ?” አልኩት ድንገት በመገረም፡፡
“ኧረ ትልቅ አይደለም፤ አንቺ ስለማታውቂው ነው፡፡ ስልክ ከሌላት እኔ እገዛላታለሁ ብሏል…” ለድለላ ስራ እንደመጣ ሲገባኝ ኩምሽሽ አልኩ፡፡ አግኝቼ ያጣሁት መሰለኝ፡፡
አጋጣሚ እየጠበቀ ያናግረኝ ጀመር፡፡ እኔም እሱን ለመሳብ ይረዱኛል ያልኳቸውን ፍልስፍናዎች አዘንብበት ጀመር፡፡ ስለ ሰውየው ትተን፣ ስለ ራሳችን ማውራት ጀመርን፡፡
“እነንትና እኮ ዱሩዬ ናቸው፤ ለምን ከነሱ ጋ ትቆማለህ?” እለዋለሁ፡፡ ቀስ እያለ ያስረዳኛል፡፡
“አስፓልቱ ሰው ይበዛበታል… ውስጥ ለውስጥ እንሂድ” እያልን ከህዝብ ተገንጥለን ለብቻችን መሄድ ጀመርን፡፡ ቀጥሎ አንገትና ወገብ ተቃቅፎ መሄድ መጣ፡፡
እያለ …እያለ…እያለ… ሃሃሃ… ይበቃችኋል፡፡
*   *   *
የመጀመሪያው የፍቅር ደብዳቤ የደረሰኝ 5ኛ ክፍል እያለሁ ነበር፡፡ ስሙን የማልጠቅሰው፤ በረባሽነቱና ተጫዋችነቱ በጣም የሚታወቅ የክፍሌ ልጅ ነበር፡፡ በጣምም ደፋርና ጆሊ ነገር ነበር፡፡ የክፍላችን ወንዶች በሙሉ ጓደኞቹ ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤታችን ውስጥ እሱን የማያውቅ ተማሪ አልነበረም፡፡ እናቱም አስተማሪያችን ነበሩ (ለድፍረትና ረብሻው አግዞት ይሆናል)
የሆነ ሆኖ አንድ ቀን “የቤት ሥራ አልሰራሁምና ደብተርሽን አውሽኝ” ይለኝና ደብተሬን ሰጠሁት፡፡ እኔ ደግሞ አታምኑኝም ይሆናል እንጂ ያኔ በጣም አይናፋርና ዝምተኛ ነበርኩ፡፡ ደብተሬን ከትምህርት ስንለቀቅ ግቢው በር ላይ ጠብቆ መለሰልኝ፡፡ እቤት ደርሼ ደብተሬን ስገልጥ፣ ዳር ዳሩ ላይ በአበባና ቢራቢሮዎች ያጌጠ፣ ሽቶ ሽቶ የሚሸት ወረቀት አገኘሁኝ፡፡ ከልጁ የተፃፈልኝ የ“እወድሻለሁ” ደብዳቤ ነበር፡፡ የተፃፉትን እያንዳንዱን ቃላት አላስታውሳቸውም፡፡ አንብቤው ለእህቶቼዋ አስነበብኩት፤ ለጓደኛዬም፡፡
ጓደኛዬ፤ “ታዲያ ምን ብለሽ ልትመልሽለት ነው? እሽ እንዳትይው፣ ረባሽ ነው፤ ከፈለግሽው ግን ይሁን” አለችኝ፡፡ መመለስ እንደሚገባኝ እራሱ አልገባኝም ነበርና ዘጋሁት፡፡ ልጁ በሶስተኛ ወይ በአራተኛ ቀን የተቀመጥኩበት ዴስክ ጋ መጥቶ “ምነው ደብዳቤዬን ሳትመልሽልኝ?” ብሎ ሲጠይቀኝ “አልፈልግም፤ ይኸው ደብዳቤህ” ብዬ ሰጠሁት፡፡ “እምቢ አልሽ አይደል፣ ቆይ ብቻ ሰኔ 30 ላግኝሽ” ብሎ ፎከረብኝ፡፡ እንዳለውም ሰኔ 30 ከጓደኞቹ ጋር መንገድ ላይ ጠብቆ እየፎከረ ሊመታኝ ሲያስፈራራኝ፣ እህቶቼና ጓደኛዬ ደፈር ብለው፣ ተለማምጠውና አባብለው ከመደብደብ አስጥለውኝ ነበር እላችኋለሁ፡፡
ሜሪ ፈለቀ



Read 29799 times