Monday, 03 November 2014 09:15

ማረጥ (Menopause) ተፈጥሮአዊ ወይስ የጤና እክል?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ማረጥ በየትኛዋም ሴት ላይ ሊከሰት የሚችል ተፈጥሮአዊ ክስተት ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደ አንድ የጤና እክል ሲቆጥሩት ይስተዋላል፡፡ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ፈፅሞ የተሳሳተና ከሳይንሰዊ እይታ ውጪ የሆነ ነው፡፡
 በዛሬው ፅሁፋችን እውን ማረጥ ተፈጥሮአዊ ነው ወይንስ ጥቂቶች እንደሚሉት የጤና እክል ነው? የሚለውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ NIA (National Institute On Aging) መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው በሚከሰቱ የጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ማረጥ ምንድነው?
የአንዲት ሴት የማረጫ አማካኝ እድሜ ስንትነው?
ከማረጧ በፊት እንዲሁም በኋላስ ምን አይነት የጤና እክሎች ይገጥሟታል? የሚሉትን ጉዳዮች አስመልክቶ ያወጣውን ፅሁፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-
ማረጥ ምንድነው?
ማረጥ ልክ እንደ ጉርምስና ሁሉ በተወሰነ የእድሜ ክልል ላይ የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ክሰተት ነው፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ክሰተት የወር አበባ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ሆርሞኖች     መጠን መቀነሱን ተከትሎ የወር አበባ ሲቆም የሚፈጠር ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡! በለውጡ ሶስት ደረጃዎች ይከሰታሉ፡፡
ከማረጥ በፊት፣
በማረጥ ወቅት እንዲሁም
ከማረጥ በኋላ፡፡
አብዛኛዎቹ ለውጦች አንዲት ሴት ወደ ማረጫ የእድሜ ክልል ስትቃረብ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኘው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን ሆርሞን ስለሚቀንስ በተለያየ የሰውነት ክፍሎች ላይ የተለያዩ ለውጦች ይታያሉ፡፡
 በመቀጠልም የወር አበባ መታየቱን ያቆማል፡፡ ይህም ለማረጧ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከማረጥ በኋላ ያሉ ለውጦችም የሚከሰቱት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ብዙሀኑ ሴቶች እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርሱት በሀምሳዎቹ መጀመሪያ ባለው የእድሜ ክልል ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ከዚህ ቀደም ብለው በአርባዎቹ መጀመሪያ ወይም ደግሞ ዘግይተው በሀምሳዎቹ መጨረሻ ባለው ጊዜ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከተገለፀው አማካኝ የእድሜ ክልል ቀድመው ለማረጥ ተያያዥ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም በማህፀን ላይ የተደረገ የቀዶ ጥገና በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ምልክቶቹ፡-
ሴቶች ወደዚህ የእድሜ ክልል ሲገቡ በሰውነታቸው ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀሰትሮን መጠን በጣም ስለሚቀንስ የተለያዩ ምልክቶችን ማየት ይጀምራሉ፡፡ የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው፡-
1.    የወር አበባ የሚመጣበት ቀናት በእጅጉ         መቀራረብ፣
2.    የወር አበባ መጠን መጨመር፣
3.    በሰውነት ላይ የሚወጣ ሽፍታ፣
4.    የወር አበባ ከአንድ ሳምት በላይ መቆየት፣
5.    የወር አበባ ከቆመ ከአንድ አመት በኋላ ተመልሶ ሊታይ ይችላል  
ከላይ የተጠቀሱት አንዲት ወደዚህ የእድሜ ክልል መዳረሻ ላይ ያለች ሴት የሚያጋጥሟት ምልክቶች ሲሆኑ በምታርጥበት ወቅት ደግሞ ሌሎች በሰውነቷ ውስጥ ያለው የኤስትሮጅንና ፕሮጀስትሮን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አከላዊ ብሎም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ተከታዮቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
1.    ድንገተኛና በተደጋጋሚ የሚከሰት የሰውነት         ሙቀት መጨመር፣
ይህም የሚከሰተው በሰውነታችን ያለው የኤስትሮጅን መጠን መቀነስ ጋር ተያይዞ ሲሆን አንዲት ሴት ካረጠች በኋላም ለተወሰኑ አመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ድንገተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት በይበልጥ በላይኛው የሰውነታችን ክፍል ማለትም በጀርባ፣ በአንገት እንዲሁም በፊት አካባቢ ይከሰታል፡፡ በአብዛኛውም ከ30 ሰኮንድ እስከ 10 ደቂቃ ሊቆይ ይችላል፡፡
2.    ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ይህም ለወሲብ ፍላጎት መቀነስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሴቶች የሽንት መቋጠር ችግርም ያጋጥማቸዋል፡፡
3.    እንቅልፍ ማጣት፣ በማረጥ የእድሜ ክልል         ላይ ያሉ ሴቶች በአብዛኛው በቶሎ እንቅልፍ         ለመተኛት እንዲሁም እረዥም ሰአት         ለመተኛት ይቸገራሉ፡፡
4.    የወሲብ ፍላጎት መቀነስ፣
5.    ድብርት፣ የስሜት መለዋወጥ፣ መነጫነጭ         እንዲሁም ጭንቀት፡፡ በዚህ ወቅት             የተለመዱ     የባህሪ ለውጦች ናቸው፡፡    
6.    የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የማስታወስ         ችሎታ መቀነስ፣ እንዲሁም ከአጥንት እና         መገጣጠሚያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ         ይችልሉ፡፡
ለችግሮቹ መፍትሄ፡-
ማንኛዋም ሴት ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አካላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ችግሮች ሲገጥሟት የማረጥ ምልክቶች ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግን ማረጥ እንደማንኛውም ተፈጥሮአዊ ክስተት ጊዜውን ጠብቆ ሊከሰት እንደሚችል ከዛም ጋር ተያይዞ ስለሚከሰቱ የጤና እክሎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ፅሁፉ በማረጥ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላሉ ብሎ የሚከተሉትን ነጥቦች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ከሲጋራ እንዲሁም ከሌሎች እፆች መጠበቅ፣
የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ የቅባት ምግቦችን መቀነስ፣ በአንፃሩ ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያላቸውን ምግቦች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ፣
በተጨማሪም ሰውነታችን በቂ የሆነ ካልሲየም፣ ቫይታሚን ዲ፣ ሌሎች ቫይታሚኖችን እንዲሁም ሚኒራል እያገኘ መሆኑን ማረጋገጥ፣
የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር፣
የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲያጋጥም ሳሳ ያሉ ልብሶችን መልበስ እንዲሁም ቀዝቃዛና ነፋሻማ በሆኑ ቦታዎች መቀመጥ፣
    ከላይ ከተገለፁት በተጨማሪም ለዘወትር         ሊታወሱ     ይገባል ብሎ ፅሁፍ ተከታዮቹን         ነጥቦችም     አስፍሯል፡-
ከደም ግፊት፣ ከኮለስትሮል እንዲም ከሌሎች የጤና እክሎች ጋር በተያያዘ በሀኪም የታዘዙ መድሀኒቶችን በአግባቡ መውሰድ፣
ብልት አከባቢ መድረቅ እንዲሁም የኢንፌክሽን መፈጠር ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መድሀኒት እንዲሁም የተለያዩ ቅባቶችን መጠቀም፣
በጡት አካባቢ ማበጥ እና ሲነካካ መጠጠር ሲያጋጥም ሀኪም ጋር ቀርቦ  አስፈላጊውን የህክምና ክትትል  ማድረግ፣ማረጥ የህክምና ክትትል በማድረግ ሊወገድ የሚችል የጤና እክል አይደለም፡፡ ነገር ግን የተለየ የጤና እክል በተለይም ተደጋጋሚ የሆነ ድንገተኛ የሰውነት ሙቀት መጠን ሲያጋጥም የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

የሰውነት ሙቀት ከፍ ማለት ሲኖር፡-
ቀዝቃዛና ነፋስ ያለበት ቦታ መቀመጥ፣
ሳሳ ያሉና  ከሰውነታችን የሚወጣውን ሙቀት ማስወጣት የሚችሉ ልብሶችን መልበስ፣
ቀዝቃዛ መጠጦች መውሰድ ይመከራል፡፡

Read 8743 times