Monday, 03 November 2014 08:04

በማራቶን ሊግ ኬንያውያን ብልጫ አላቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፉት 15 ዓመታት በዓለም የማራቶን ውድድሮች መድረክ  የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የበላይነት ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ ከ5 ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ የኬንያ ወንድ አትሌቶች ከኢትዮጵያውያኑ ከፍተኛ ብልጫ እያገኙ ናቸው፡፡ በአንፃሩ በማራቶን ከኬንያ አቻዎቻቸው በመፎካከር እየተሳካላቸው  የሚገኙት የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ሆነዋል፡፡ የዓለም ማራቶን ሜጀር ሲሬዬስ አካል በሆኑ ትልልቅ ማራቶኖችና ሌሎች ውድድሮች እንዲሁም፤ በዓለም የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ሰንጠረዦች በአጠቃላይ ኬንያውያን በሁለቱም ፆታዎች  በውድድር ዘመኑ ከኢትዮጵያውያን የተሻለ ስኬት ነበራቸው፡፡ በተለይ በወንዶች ምድብ በማራቶን ውጤት የኬንያ አትሌቶች ከኢትዮጵያውያን ተቀናቃኞቻቸው ጋር ያላቸው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል፡፡
በተያያዘ ነገ የኒውዮርክ ማራቶን በታሪኩ ለ44ኛ ጊዜ ሲደረግ በሁለቱም ፆታዎች ፉክክሩ በምስራቅ አፍሪካ አገራት አትሌቶች እንደሚወሰን ቢጠበቅም የተሻለውን ግምት ኬንያውያን ወስደዋል፡፡ የኒውዮርክ ማራቶን እስከ 51 ሺ ተሳታፊዎች ፤ እስከ 2 ሚሊዮን ተመልካቾች የሚያጅቡት ትልቅ ውድድር ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ማራቶኒስቶች መካከል በኒውዮርክ ማራቶን በወንዶች ምድብ በ2010 እኤአ ላይ አሸናፊ የነበረው ገብሬ ገብረማርያም እና በሴቶች ምድብ ደግሞ ለሁለት ጊዜያት ያሸነፈችው ፍሬህይወት ዳዶ ይሳተፋሉ፡፡ በሌላ በኩል የ2013/14 የዓለም 6 ማራቶኖች ሜጀር ሲሪዬስ “ማራቶን ሊግ” የደረጃ ሰንጠረዥ በመሪነት አጠናቅው 1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማትንየ ሚካፈሉት አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ኬንያውያን ናቸው፡፡ የማራቶን ሊጉ ነገ በሚካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ሲያበቃ ሲሆን በተለይ በወንዶች ምድብ አሸናፊውን የሚለይ ነጥብ ሊመዘገብበት ይችላል፡፡ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ዘንድሮ ያስመዘገበው ኬንያዊ ዴኒስ ኪሜቶ የማራቶን ሊጉን እየመራ ቢሆንም ፤ የማራቶን ሪከርዱ የተሰበረበት የተሰበረበት ዊልሰን ኪፕሳንግ በነገው የኒውዮርክ ማራቶንን ካሸነፈ የማራቶን ሊጉን በአንደኛነት በመጨረስ 500ሺ ዶላር የመሸለም እድል ይኖረዋል፡፡
ለነገሩ ከወር በፊት ከተካሄደው የቺካጎ ማራቶን በኋላ በ2013/14 የውድድር ዘመን የማራቶን ሊግ ፉክክር  በሁለቱም ፆታዎች ኬንያውያን ማሸነፋቸው የተረጋገጠ ይመስላል፡፡  በተለይ በሴቶች ምድብ የቺካጎ ማራቶንን ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ሪታ ጄፕቶ በውድድር ዘመኑ የማራቶን ሊግ አሸናፊነቷን ያረጋገጠችው ከኒውዮርክ ማራቶን በፊት ነው፡፡  ኬንያዊቷ ሪታ ጄፕቶ በሴቶች ምድብ የማራቶን ሊጉን 100 ነጥብ በመምራቷ የ500ሺ ዶላር ሽልማት ትወስዳለች፡፡
በ2014 የዓለም ማራቶኖች በወንዶች ኬንያ፣ በሴቶች ኢትዮጵያ
በ2014 እኤአ ላይ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በርካታ የማራቶን ውድድሮችን አሸንፈዋል፡፡  ትልቁ ድል የተመዘገበው የዓመቱን ማራቶን ፈጣን ሰዓት ባስመዘገበችው እና የበርሊን ማራቶንንን ባሸነፈችው አትሌት ትርፌ ፀጋዬ ነው፡፡ የትርፌ ፀጋዬ የዓመቱ ፈጣን የማራቶን ሰዓት 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች ከ18 ሰከንዶች ሲሆን በበርሊን ማራቶን አሸናፊነቷ ያስመዘገበችው ነው፡፡ ይሁንና በለንደን ፤ በቺካጎ፤ በቦስተን እና በፓሪስ ማራቶኖች የኬንያ ሴት አትሌቶች የበላይነት ማሳየታቸው በማራቶን ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከፍ አድርጓቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ  ሴት አትሌቶች በማራቶን ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በየጣልቃው ኬንያውያንን ለመፎካከር የበቁት በማራቶን ሊግ ውድድሮች ባይሆንም በሌሎች በርካታ ማራቶኖች ከወንዶቹ ኢትዮጵያውያን በተሻለ ብዛት አሸፊና በመሆናቸው ነው፡፡  ኢትዮጵያውያኑ  ሴት አትሌቶች በበርሊን ማራቶን ተከታትለው መግባታቸው አንፀባራቂው ስኬተ ነው፡፡ በሌሎች በዓለም ዙርያ በተካሄዱ ውድድሮችም በተመሳሳይ ሁኔታ ብልጫ ለማሳየት አሸንፈዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ማሬ ዲባባ የሻይናሜን ማራቶንን በቻይና፤ ትርፌ ፀጋዬ በየነ የቶኪዮ ማራቶንን በጃፓን ፤ ፍሬህይወት ዳዶ  የፕራግ ማራቶንን፤ ትእግስት ቱፋ የኦታዋ ማራቶንን በካናዳ ፤ ሙሉ ሰበቃ የዱባይ እና የዳጋኖ ማራቶኖችን በማከለኛው ምስራቅ እና በቻይና፤ አበበች አፈወርቅ የሂውስተን ማራቶንን በአሜሪካ፤ ማርታ ለማ  የሙምባይ ማራቶንን በህንድ፤ መስታወት ቱፋ የዶንግ ያንግ ማራቶንን በደቡብ ኮርያ እንዲሁም አማኔ ጎበና የሎስ አንጀለስ ማራቶንን በአሜሪካ ማሸነፋቸው ከሴት ማራቶኒስቶች አስደናቂ ስኬት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ወንድ ማራቶኒስቶች በአንፃሩ በ2014 ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምስት አመታት ውጤታቸው ከኬንያውያኑ በጣም አየራቀ እና እየወረደ መጥቷል፡፡ በዓመቱ ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ኢትዮጵያ ወንድ ማራቶኒስቶች በበላይነት በቅርብ ጊዜ የሚመለስ አይሆንም፡፡ እነዚህን ደረጃዎች የያዟቸው ኬንያውያን ናቸው፡፡ ከ6 የማራቶን ሊግ ውድድሮች አንዱንም ኢትዮጵያዊ አትሌት ሊያሸንፍ ያልቻለበት የውድድር ዘመንም ነበር፡፡
በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ የ2014 ከፍተኛ ውጤት በማስላት በወጣ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት በወንዶች ማራቶን አንደኛ ደረጃ የያዘችው በ3994 ነጥብ ኬንያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በ3901 ነጥብ፤ ጃፓን በ3618 ነጥብ ፖላንድ በ3523 ነጥብ እንዲሁም ኤርትራ በ3509 ነጥብ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ፡፡ በሴቶችም ኬንያ በ934 ነጥብ መሪ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በ3910 ነጥብ ትከተላታለች፡፡ ጃፓን በ3629 አሜሪካ በ3576 እንዲሁም ጣሊያን በ3503 እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይወስዳሉ፡፡ በዚሁ ድረገፅ በቀረቡ አሃዛዊ መረጃዎች ለመንገዘብ የሚቻለው በዓመቱ ምርጥ የማራቶን ብቃት እና ፈጣን ሰዓት ሁለቱንም የመሪነት ስፍራዎች የተቆናጠጡት ኬንያውያን ናቸው፡፡ ሪታ ጄፔቶ እና ዴኒስ ኪሜቶ 1340 እና 1456 ነጥብ እንደየቅደም ተከተላቸው በማስመዝገብ ነው፡፡ በዚሁ ደረጃ በሴቶች ምድብ እስከ 20ኛ ባለው እርከን ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ከስምንት በላይ ናቸው፡፡ በወንዶች ግን ያሉት ከ3 አይበልጡም፡፡
የኬንያ ወንድ አትሌቶች የበላይነት በርግጥም ከፓሪስ፤ ከበርሊን  እና ከቦስተን ማራቶኖች በኋላ ከወር በፊት በተደረገው የቺካጎ ማራቶንም በግልፅ ታይቷል፡፡  የቺካጎ ማራቶንን ያሸነፈው በረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮች የቀነኒሳ ተፎካካሪ ሆኖ የቆየው ኬንያዊ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ነበር፡፡ ኪፕቾጌ ወደ ማራቶን ፊቱን ካዞረ ወዲህ አራት ጊዜ ተወዳድሮ ለ3 ጊዜ በአንደኛነት መጨረሱ አስደንቋል፡፡ በቺካጎ ማራቶን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት ደግሞ  2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ15 ሰከንዶች ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሳሚ ኪርሞ በ2 ሰዓት 04 ከ18 እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ ዲክሰን ቺምቦ በ2 ሰዓት 04 25 በሆነ ጊዜ የጨረሱ ሌሎቹ የኬንያ አትሌቶች ናቸው፡፡ በወንዶች እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሲመዘገብ 7 ኬንያውያን ነበሩ፡፡ ያ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ሁለተኛ የማራቶን ውድድር ለመሮጥ የበቃው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በቺካጎ ማራቶን ላይ ቀነኒሳ በ4ኛ ደረጃ ውድድሩን ያጠናቀቀ ሲሆን ሰዓቱ 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች ከ51 ሰከንዶች ነው፡፡ ቀነኒሳ በውድድሩ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃዎችን ርቀቱን ለመሸፈን በቻለበት ብቃት እንደረካ በወቅቱ ተናግሮ ነበር፡፡  የግሉን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ከጅምሩ ማቀዱ አልቀረም ነበር፡፡ እንደውም ሌትስራን ድረገፅ እንደዘገበው ያቀደው ጊዜ  2 ሰዓት ከ3 ደቂቃዎች ከ13 ሰከንዶች ነው፡፡ በእርግጥ ከቀነኒሳ በፊት የነበሩት ታላቅ የረጅም ርቀት ሯጮች በመጀመርያ ሁለት የማራቶን ውድድራቸው ፖል ቴርጋት በ2 ሰዓት ከ08 ደቂቃዎች ሃይሌ ደግሞ 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች ነበር ያስመዘገቡት፡፡ እንደ ጆስ ሄርማንስ አስተያየት ቀነኒሳ በቀለ በቺካጎ ማራቶን በውድድሩ አይነት ለሁለተኛ ጊዜ የተሳተፈው ልምድ ለማዳበር እና ማራቶንን ለመማር ነው፡፡
የቺካጎ ማራቶን ከመካሄዱ በፊት ማራቶንን በ2 ሰዓት እና ከ2 ሰዓት በታች ይገባል ተብሎ የተጠየቀው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሰው ልጅ ያን ያህል መፍጠን አይችልም በሚል መልስ ሰጥቷል፡፡‹‹ ምናልባት ወደፊት ማን ያውቃል ሳይንቲስቶች ልዩ የሰው ልጆች ካልፈጠሩ በቀር…›› ነው ያለው ቀነኒሳ፡፡ የአትሌቱ ማናጀር የሆኑት የ64 ዓመቱ ሆላንዳዊ ጆስ ሄርማንስ ግን በተቃራኒው በሰጡት አስተያየት‹‹ ቀስ በቀስ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች እንደሚገባ አስባለሁ… ምናልባትም ከ20 ዓመታት በኋላ›› ብለዋል፡፡ ለጆስ ሄርማንስ ለዚህ ብቃት ዋና እጩ የተደረገው ራሱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ በማራቶን ስልጠናው እና ልምምዱ ላይ ስርነቀል መሻሻሎች እንደሚያስፈልጉ ጎን ለጎን አስረድተዋል፡፡‹‹ ብዙ ለውጦች ያስፈልጋሉ፡፡ በልምምድ፤ በህክምና ድጋፍ እና በጤንነት አጠባበቅ፤ በፊስዮቴራፒ ያሉትን ሁኔታዎች ማሻሻል ይገባል፡፡ በቀለ በጣም ተፈጥሯዊ ብቃት የታደለ አትሌት ነው፡፡ መልቲ ቫይታሚን ወስዶ እንኳን አያውቅም›› በማለት ጆስ ሄርማንስ በአትሌቱ ላይ ስላላቸው ተስፋ መናገራቸውን ሌትስራን ድረገፅ ዘግቦታል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለቺካጎ ማራቶን ባደረገው ዝግጅት ለውጦች ማድረጉ ግድ ነበር፡፡ የመጀመርያ ማራቶኑን በፓሪስ ከመሮጡ በፊት የሰራው ልምምድ ምንም እንኳን በውድድሩ በምንጊዜም የማራቶን ፈጣን ሰዓት 6ኛ ደረጃ አስመዝግቦ ቢያሸንፍም በወቅቱ 27ኛው ኪሎሜትር ላይ ለገጠመው የጉዳት ስሜት ምክንያቱ የልምምድ ስርዓቱ ነበር፡፡ ለፓሪስ ማራቶን ሲዘጋጅ በሳምንት ከ180 እስከ 200 ኪሎሜትሮችን ሮጦ ነበር፡፡ ለቺካጎ ማራቶን የተዘጋጀው ግን ከ160 እስከ 180 ኪሎሜትሮችን ነው፡፡የዓለም የማራቶን ሪከርድ በኬንያዊ አትሌት ሲሰበር የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በዴኒስ ኪሜቶ የተያዘው 2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሰከንዶችን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት በ177 ሰከንዶች በማሻሻል በሰው ልጅ ብቃት ማራቶንን 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃዎች መግባት እንደሚቻል ሳይንቲስቶች ይገልፃሉ፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ይህን በማሳካት ደግሞ ኬንያውያን ወንድ አትሌቶች ከኢትዮጵያውያን እጅግ በላቀ ሁኔታ ግምት አግኝተዋል፡፡
ቺካጎ ላይ በሴቶች ምድብ  ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ሪታ ጄፒቶ ስትሆን ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ24 ደቂቃዎች ከ35 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነበር፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በውድድር ዘመኑ እንዳሳዩት ስኬት በቺካጎም ዋና ተፎካካሪዎች ነበሩ፡፡ ቺካጎ ላይ ኢትዮጵያዊቷ ማሬ ዲባባ በ2 ሰዓት ከ25 ደቂቃዎች ከ37 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ሁለተኛ ደረጃን ስታገኝ፤ 3 የወጣችው የኬንያዋ ፍሎረንስ ኪፕላጋት ናት፡፡ በሴቶች ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን በ2 ሰዓት ከ27 ደቂቃዎች ከ02 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ብርሃኔ ዲባባ አራተኛ እንዲሁም ገለቴ ቡርቃ በ2 ሰዓት ከ34 ደቂቃዎች ከ17 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ስምንተኛ መውጣታቸው ይጠቀሳል፡፡

በ8 የማራቶን ሊጎች በወንዶች ኬንያ  7 ኢትዮጵያ 1፤ በሴቶች ኬንያ 3 ኢትዮጵያ 1
ማራቶን ሊግ “ዎርልድ ማራቶን ሜጀር ሲሪዬስ”  በሚል ስያሜ ዘንድሮ የተካሄደው ለስምንተኛ ጊዜ ነው፡፡ በማራቶን ሊግ ላይ በስድስት ትልልቅ ማራቶኖች  በሚመዘገብ ውጤት መሰረት 1ኛ ሆኖ መጨረስ በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ የ500ሺ  ዶላር ሽልማት ይገኝበታል፡፡ ማራቶን ሊጉ ዘንድሮ የተጀመረው   በቶኪዮ ማራቶን ሲሆን የመጨረሻው ውድድር ነገ በኒውዮርክ ማራቶን ይሆናል፡፡
የዘንድሮ ማራቶን ሊግ በኒውዮርክ ማራቶን ከመጠናቀቁ በፊት በተለይ በሴቶች ምድብ በአንደኛነት በመጨረስ 500ሺ ዶላር እንዳሸነፈች ያረጋገጠችው ኬንያዊቷ ሪታ ጂፔቶ ሆናለች፡፡ ሪታ ጄፕቶ በ2013 እኤአ የቺካጎ እና የቦስተን ማራቶኖችን ለማሸነፍ የበቃች ሲሆን በ2014 እኤአ ደግሞ መልሷ በሁለቱም ማራቶን ውድድሮች በተከታታይ ዓመት በማሸነፍ በማራቶን ሊጉ 100 ነጥብ አስመዝግባለች፡፡ በ213 በዓለም ሻምፒዮና 1ኛ፤ በለንደን ማራቶን ሁለተኛ እንዲሁም በ2014 በለንደን ማራቶን ያሸነፈችው ኤድና ኪፕላጋት በ65 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በቦስተን ማራቶን 3ኛ ደረጃ የነበራት እና በ2014 እኤአ የቶኪዮ እና የበርሊን ማራቶኖችን ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ በ51 ነጥብ 3ኛ ደረጃ በማግኘት በውድድር ዘመኑ በማራቶን ሊግ በኢትዮጵያዊ የተመዘገበውን ከፍተኛ ውጤት አግኝታለች፡፡
በሌላ በኩል በማራቶን ሊጉ የወንዶች ምድብ በነጥብ ብልጫ በአንደኛነት በመጨረስ የ500ሺ ዶላር ተሸላሚ የሚሆን አትሌት የሚታወቀው ነገ  በሚደረገው የኒውዮርክ ማራቶን ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም የኬንያውያን አትሌቶች እድል የሰፋ ነው፡፡ ሊጉን በአንደኛነት የሚመራው ከሳምንታት በፊት በበርሊን ማራቶን አዲስ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ ያሸነፈው እና በ2013 እኤአ ላይ በቶኪዮ እና ቺካጎ ማራቶን ላይ ያሸነፈው ዴኒስ ኪሜቶ በ75 ነጥብ ነው፡፡ በ2ኛ ደረጃ በ65 ነጥብ ይከተል የነበረው በ2013 በዓለም ሻምፒዮና አራተኛ ደረጃ በለንደን ማራቶን አንደኛ እና በኒውዮርክ ማራቶን 2ኛ ደረጃ እንዲሁም በ2014 በለንደን 3ኛ በቺካጎ አራተኛ ደረጃ ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊ ፀጋዬ ከበደ ነው፡፡ በማራቶን ሊጉ የዴኒስ ኬሚቶን ደረጃ በመቀናቀን ከኒውዮርክ ማራቶን ውጤት በኋላ ለማሸነፍ እድል የሚኖረው የቀድሞ የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ ብቻ ይሆናል፡፡
በማራቶን ሊጉ ለአትሌቶች እስከ አምስተኛ ደረጃ በሚመዘገብ ውጤት  ነጥብ የሚያስገኙ ዓለም አቀፍ 6 ማራቶኖች  በቶኪዮ፤ በቦስተን፤ በለንደን፤ በበርሊን፤ በቺካጎ እና በኒውዮርክ የሚካሄዱት ናቸው፡፡ የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና የማራቶን ውድድሮችም በሚካሄዱባቸው የውድድር ዘመናትም ነጥብ ይገኝባቸዋል፡፡ አንድ የማራቶን ሊግ የውድድር ዘመን በ2 የውድድር ዓመታት ውስጥ የሚወሰን ሲሆን በእዚህ ጊዜ ውስጥ የሊጉ አካል የሆኑ ቢያንስ 12 ማራቶኖች አሉ፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ቢበዛ በ4 ማራቶኖች በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች በደረጃ ሰንጠረዡ በአንደኝነት በመጨረስ 500ሺ ዶላር በየፆታ መደቡ ለመሸለም  ሰፊ እድል ይኖራቸዋል፡፡ በማራቶን ሊግ  ውድድሮች ለአንደኛ ደረጃ 25 ነጥብ ፤ ለሁለተኛ ደረጃ 15 ነጥብ ፤ ለሶስተኛ ደረጃ 10 ነጥብ ፤ ለአራተኛ ደረጃ 5 ነጥብ  እንዲሁም ለአምስተኛ ደረጃ 1 ነጥብ ይሰጣል፡፡ ከ2006 በእኤአ ወዲህ  በተካሄዱት 7 የማራቶን ሊግ የውድድር ዘመናት ኬንያውያን በከፍተኛ ብልጫ ኢትዮጵያውያን እየራቁ መሄዳቸው ይስተዋላል፡፡ የዎርልድ ማራቶንስ ሜጀር ሲሪዬስ ወይንም የማራቶን ሊግ ከተጀመረ ወዲህ 129 ውድድሮች ተደርገው ማሸነፍ ከቻሉ 102 የአፍሪካ አትሌቶች 93 የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ናቸው፡፡ የአንበሳው ድርሻ ደግሞ የኬንያውያን ነው፡፡ከቺካጎ ማራቶን በኋላ በዓለም የማራቶን ሊግ ውስጥ በሚካሄዱ 6 የማራቶን ውድድሮች ከ1989 እኤአ ወዲህ የምስራቅ አፍሪካ በተለይ  የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች  በወንዶች 72.6 በመቶ በሴቶች 90 በመቶ አሸናፊዎች ናቸው፡፡
ከ1990 ወዲህ በሁለቱም ፆታዎች በቶኪዮ ማራቶን ኬንያ 9 ኢትዮጵያ 1 ፤ በቦስተን ማራቶን ኬንያ 14 ኢትዮጵያ 4፤ በለንደን ማራቶን ኬንያ 12 ኢትዮጵያ 3 ፤ በበርሊን ማራቶን ኬንያ 13 ኢትዮጵያ 4 ፤ በቺካጎ ማራቶን ኬንያ 12 ኢትዮጵያ 2፤  እንዲሁም ከነገው ውድድር በፊት በኒውዮርክ ማራቶን ኬንያ 10 ኢትዮጵያ 2 አሸናፊዎች አስመዝግበዋል፡፡
ባለፉት ስምንት የማራቶን ሊግ የውድድር ዘመናት የደረጃ ሰንጠረዡን በአንደኛነት በመጨረስ  የተሳካላቸው በወንዶች 7 ጊዜ የኬንያ አንድ ጊ. የኢትዮጵያ እንዲሁም በሴቶች ሶስት ጊዜ የኬንያ፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ የጀርመን እና የራሽያ እንዲሁም አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ የ500ሺ ዶላር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ የማራቶን ሊጉን በማሸነፍ የተሳካላቸው ሁለት የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡ በወንዶች ምድብ ባለፈው ዓመት በ75 ነጥብ የሊጉን ፉክክር በአንደኛነት በመጨረስ ያሸነፈው ፀጋዬ ከበደ ፤ እንዲሁም በሴቶች በ2006 እና 2007 ላይ በመጀመርያው የማራቶን ሊግ በ80 ነጥብ ያሸነፈችው ጌጤ ዋሚ ናቸው፡፡

Read 2205 times