Monday, 03 November 2014 07:32

የግል ቢዝነስ፡ ተጣጥሮ በሽያጭና በትርፍ ሬከርድ መስበር የመንግስት ቢዝነስ፡ “እንዳንሞት እንዳንድን” አድርጎ ማሳደር

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(10 votes)

          መልካም ወሬ ከፈለጋችሁ አይታጣም። በቅርቡ “አይፎን 6” ሞባይሎችን፣ ሰሞኑን ደግሞ አዳዲስ የ“አይ-ፓድ” ምርቶቹን ለገበያ ያቀረበው አፕል ኩባንያ፤ እንደለመደው ዘንድሮም ሬከርድ ሰብሯል - በአመት 40 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ትርፍ በማግኘት። አትራፊነቱ አይገርምም። የጥረት፣ የፈጠራ፣ የቢዝነስ ታታሪነቱ ውጤት ነው። “አይፎን 6”ን ለመግዛት ሲጠባበቁ የነበሩ የአፕል ደንበኞች፣ በሽሚያ ነው የተረባረቡበት። በምርቶቹ ጥራት ተወዳጅነትን አትርፏላ። እናም፣ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት ብቻ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሞባይሎችን በመሸጥ ሬከርድ ሰብሯል። አምና፣ የ“አይፎን 5” ምርቶቹን ለገበያ ያቀረበ ጊዜ፣ በሦስት ቀናት ዘጠኝ ሚሊዮን ሞባይሎችን በመሸጥ ያስመዘገበውን ሬከርድ ነው የሰበረው።

ለመሆኑ አፕል ኩባንያ እና አይፎን ለኛ ምናችን ነው ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም።  መቼም፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በግዢም ይሁን በዳያስፖራ ስጦታ የአይፎን ደንበኛ ለመሆን የቻሉ ኢትዮጵያውያንም፣ አዲሱን አይፎን ከእጃቸው ለማስገባት መጓጓታቸው አይቀርም። የተመኙት ይስመርላቸው። ይሄም ብቻ አይደለም። “የአፕል ስኬታማነትና የአይፎን ተወዳጅነት ምን ትርጉም አለው?” ለሚለው ጥያቄ፣ ሌላ ትልቅ መልስ አለው። “እንዲህ ነው ጀግንነት” ብለን ማድነቅና ማክበር... ከዚያም “ይዝለቅበት” ከሚል መልካም ምኞት ጋር በአርአያነቱ የራሳችንን መንፈስ ለስኬት ማነቃቃት እንችላለን። በእርግጥ፣ ትንሽ ራቅ ይላል፤ ኧረ እጅጉን የራቀ ቢመስለን አይገርምም። ደግነቱ እዚሁ በቅርባችን ኢትዮጵያ ውስጥ፣ መልካም የስኬት ወሬ ብንፈልግም አናጣም። ከተቋቋመ ሰባት አመት የማይበልጠው አንድ የአበባ እርሻ፣ በ200 ሚ. ዶላር እንደተሸጠ አልሰማችሁም? 4 ቢ. ብር ገደማ መሆኑ ነው። ቀላል ስኬት አይደለም።
የዚህ ተቃራኒ የኪሳራ አልያም የምስኪን ወሬ ከፈለጋችሁም ሞልቷል። “መንግስት፣ እንዳንሞት እንዳንድን አድርጎናል” በማለት ቅሬታቸውን ሲገልፁ የሰነበቱ ወጣቶችን ማየት ትችላላችሁ። በአዲስ አበባ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው፣ ከ“ኮብል ስቶን” ሥራ ወደ ብሎኬት አምራችነት እንዲሸጋገሩ የተደረጉ ወጣቶች ናቸው። ብሎኬት አምራቾቹ፣ አሁን ቅሬታ ያቀረቡት፣ አዲስ ነገር ስለተፈጠረ አይደለም። ከአምናና ካቻምና የተለየ ነገር እንዳልገጠማቸውማ፣ ለቅሬታ ከተጠቀሙበት አባባል መረዳት ይቻላል - “እንዳንሞት፣ እንዳንድን ሆነናል” ነው የሚሉት። ተሳክቶልን ሳናድግ ወይም ለይቶልን ሳንሞት እንደጠወለግን እድሜ እንቆጥራለን እንደማለት ይመስላል።
በእርግጥ፣ መንግስት ለወጣቶቹ ሲሚንቶ እንደሚያቀርብላቸውና፤ ከዚያም ያመረቱትን ብሎኬት እንደሚገዛቸው ስነግራችሁ፤ “ታዲያ፣ ምን ጎድሎባቸው ቅሬታ ያቀርባሉ? እንደነሱ የደላውስ የት ይገኛል?” ትሉ ይሆናል። መስሏችኋል! ትልቁ ችግራችንም እዚህ ላይ ነው። መንግስትና ቢዝነስ ሲገናኙ መጨረሻቸው እንደማያምር ሺ ጊዜ በተግባር ቢታይም፤ ብዙዎቻችን ይህን እውነታ ለመገንዘብ በጭራሽ ፈቃደኛ አይደለንም።
የመንግስት ጥገኛ በመሆን በቢሮክራቶች እግር ስር የወደቀ ቢዝነስ፣  በየትኛውም መስክ ቢሆን... በኤሌክትሪክ ስርጭትም ሆነ በስኳር ፋብሪካ፣ በዘይት ንግድም ሆነ በመስኖ ግድብ ግንባታ... አይዋጣለትም። ለስኳር እርሻና ምርት ታስቦ፤ ከአስር አመት በፊት የተጀመረውና በሁለት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለለት የከሰም ግድብ ግንባታ፣ ከሰሞኑ 87% ላይ እንደደረሰ ዜና ስትሰሙ ምን ትላላችሁ? ምንም አይገርምም። በመንግስት የሚካሄዱት በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ በአብዛኛው... (በአብዛኛው ሳይሆን ሁሉም ፕሮጀክቶች) ለአመታት እየተጓተቱ እድሜያቸውን እየቆጠሩ ነው። ከአስር አመት በፊት በአገሪቱ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች አመታዊ ምርት 3 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ነበር። መንግስት ይህንን የስኳር ምርትን በ7 እጥፍ አሳድጋለሁ ብሎ ነው በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየመደበ ለአስር አመታት የዘለቀው። ባለፉት አምስት አመታትማ፤ የገንዘቡ መጠን ጨምሯል - በየአመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሲመደብ ቆይቷል። ነገር ግን፣ እስካሁን የሚቀመስ ውጤት ጠብ አላለም። እንደእቅዱ ቢሆንማ ኖሮ አምና፣ ቢያንስ ቢያንስ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር መመረት ነበረበት። ግን የዛሬ አስር አመት ከነበረበት መጠን ፈቅ አላለም - 3 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ብቻ ነው የተመረተው። ምን ያህል ገንዘብ በሙስናና በብክነት እንደሚጠፋ አስቡት። የፌደራል ዋና ኦዲተር ሪፖርትን ማየት ትችላላችሁ። ትልቁ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት፣ በየአመቱ በርካታ ቢሊዮን ብር ቢመደብለትም፣ ወጪና ቀሪው በቅጡ እንደማይታወቅ የኦዲተሩ ሪፖርት ይገልፃል። ለምሳሌ፤ ለፕሮጀክቱ ተገዝቶ የሚመጣ ከፍተኛ መጠን ያለው ሲሚንቶና ብረት፣ ለምን ለምን ስራ እንደዋለ በዝርዝር አይታወቅም ብሏል - የኦዲተሩ ሪፖርት። ለሙስናና ለብክነት እንዴት እንደሚመች ይታያችኋል?   
በእርግጥ፣ የመንግስት የቢዝነስ እቅዶች የማይሳኩትና ውጤታማ የማይሆኑት፤ እንዲሁም በሙስናና በብክነት ከፍተኛ ሃብት የሚጠፋው፤ “በዚህኛው መንግስት ስንፍና ወይም በገዢው ፓርቲ ድክመት፣ በባለስልጣናቱ ዝርክርክነት ወይም ሙስና ነው” ማለቴ አይደለም። ሌላ መንግስት ቢቀየር፤ አማራጭ ፓርቲ ቢመጣ፣ የባለስልጣን ሹም ሽር ቢደረግ፤ ከዚህ የተለየ ውጤት አይገኝም። ከምር አስቡት። እቅዶች ቢሳኩና ውጤታማ ቢሆኑ፤ የመንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ሰራተኞች ምን ያተርፋሉ? ሃብት በብክነትና በሙስና ባይጠፋ ምን ይጠቀማሉ? ምንም! ከወትሮው የወር ደሞዝ የተለየ ገንዘብ ኪሳቸው አይገባም። ታዲያ ለምን ብለው ይጣጣራሉ? የግል ቢዝነስ ላይ ግን፤ ስኬታማና ትርፋማ ለመሆን የሚጣጣር ይኖራል፤ ጥቅም ያገኝበታላ። ለኩባንያዎች በኮንትራት የተሰጡ አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች፤ እንደስኳር ፕሮጀክቶች አለመጓተታቸውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ተመልከቱት። እቅዶች ቢጓተቱና ቢሰናከሉስ፤ የመንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ሰራተኞች ምን ያጣሉ? ሃብት በብክነትና በሙስና ቢጠፋስ ምን ይጎድልባቸዋል? ምንም! የወር ደሞዛቸው እንደሆነ አይቀርባቸውም። ታዲያ ለምን ብለው ይጠነቀቃሉ? የግል ቢዝነስ ላይ ግን፤ ሃብት እንዳይባክንና እንዳይዘረፍ የሚጠነቀቅ ይኖራል - አለበለዚያ ይከስራላ! ጉዳዩ የዚህን ያህል ግልፅ ነው። የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች፣ የማይሳኩትና የሚባክኑት አለምክንያት አይደለም። መንግስት ቢቀየር፤ ፓርቲ ቢፈራረቅ፣ የባለስልጣን ሹም ሽር ስናደርግ ብንውል፤ የተለየ ውጤት አይገኝም። በቃ! መንግስት ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ ኪሳራና ውድቀት ተከትለው ይመጣሉ - በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም አገር - በስልጣኔ ደህና በተራመዱት አገራትም ጭምር። የዛሬ አመት፣ በአሜሪካ የተከሰቱ ሁለት አጋጣሚዎችን ላስታውሳችሁ እችላለሁ።
የአሜሪካ መንግስት በጤና አገልግሎት ኢንሹራንስ ውስጥ ይበልጥ እጁን እንዲያስገባ በ2002 ዓ.ም የወጣው አዋጅ፣ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የዛሬ አመት በዚህ ሳምንት ነው። እንደ አጋጣሚ፣ በስኬታማ ቢዝነስ ታላቅ ትርፍና ክብር የተጎናፀፈው አፕል ኩባንያም በዚሁ ወር፣ እንደዘንድሮው ሁሉ አዳዲስ የአይፎን ምርቶቹን ለገበያ ማቅረቡን አትርሱ። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ሁለቱን ክስተቶች በማነፃፀር ምን እንደተናገሩ ከመግለፄ በፊት፣ በቅድሚያ የጤና ኢንሹራንስ አዋጁ ምን እንዳስከተለ ልጥቀስላችሁ። አዋጁ ከፀደቀ በኋላ የተጨመሩ ከደርዘን በላይ ማሻሻያዎችና ጊዜያዊ ደንቦች ሳይቆጠሩ፣ አዋጁ ብቻ ከ900 ገፅ በላይ ነው። ውስብስብነቱ የዚያኑ ያህል ስለሆነ፤ የአዋጁ ይዘት ዛሬ ድረስ ገና ሙሉ ለሙሉ ተተንትኖ አይታወቅም። ለምሳሌ፣ ከአራት አመት በፊት የወጣው አዋጅ፣ “ለውርጃ የመንግስትን ድጎማ ይፈቅዳል” የሚል ክርክር የተነሳው ባለፈው ወር ነው - እስከዛሬ ሳይታወቅ ስለቆየ። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ግን ይታወቃሉ። አንደኛ ነገር፤ እንደ ድሮው፣ ሰዎች ከገንዘብ አቅማቸው ጋር የሚመጣጠን የጤና ኢንሹራንስ መግዛት አይችሉም። በኢንሹራንስ የሚሸፈኑት የጤና አገልግሎቶች በእያንዳንዱ ሰው ምርጫና አቅም ሳይሆን በመንግስት “ስታንዳርድ” እንዲወሰኑ ያደርጋል - አዋጁ። ይሄ ከብዙ ሰዎች አቅም በላይ ስለሚሆን፣ መንግስት ድጎማ እንደሚያደርግ አዋጁ ይደነግጋል።  ገንዘቡ ከየት ይመጣል? በርካታ የአውሮፓ አገራት ውስጥ እንደሚደረገው፣ መንግስት እየተበደረ ወጪውን ይሸፍናል - በእዳ ክምር የኢኮኖሚ ቀውስ እስኪፈጠር ድረስ።
ሁለተኛ ነገር፣ ለጤንነትህ የምታደርገው ጥንቃቄና የህክምናህ ወጪህ ምንም ይሁን ምን፣ ለኢንሹራንስ የምትከፍለው ወርሃዊ መዋጮ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። አዎ፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ለጤንነታቸው መጠንቀቅን ቸል ይላሉ። ለህክምና ወጪ ደንታ ቢስ መሆናቸው አይቀርም። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በ16 ቦታዎች ተሞክሮ ውጤቱ ምን እንደሆነ ሰምታችሁ ይሆናል፤ አመት ሳይሞላው፣ የህክምና ወጪ በሶስት እጥፍ ጨምሯል። በአሜሪካም መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ አቅጣጫው ተመሳሳይ ነው። በቃ፤ ለትንሽ ለትልቁ፣ በሲቲ ስካን ካልታየሁ ብሎ ከሃኪም ጋር የሚሟገት ይበዛል። ይህም ብቻ አይደለም። የራስ ፀጉር ለማስተከል የሚፈልግ ራሰ በራ፣ የአፍንጫውን ቅርፅ ለማስለወጥ የሚመኝ ወጣት፣ የጡቷን መጠን “ለማስተካከል” የምትፈልግ ወይዘሮ... ዝርዝሩ ማለቂያ የለውም።
ሰዎች ከኪሳቸው የማይወጣ ገንዘብ ለማባከን፣ እልፍ አይነት “የፈጠራ” ሃሳብ እንደሚመጣላቸው አትጠራጠሩ - ያኔ የህክምና ወጪ ሰማይ ይደርስና ሁሉም ነገር ይፈራርሳል። አዋጁ፣ ይህንን የወጪ ፍንዳታ ለመከላከል እልፍ ቁጥጥሮችን ይዘረዝራል። ለምሳሌ፤ ሰዎች እንደየፍላጎታቸው የመታከሚያ ተቋማትን እንዳይመርጡ መገደብ፣ አንድ የወጪ መቆጣጠሪያ ዘዴ ሆኗል። ሰዎች፣ ምን አይነት ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው፣ ምን አይነት መድሃኒት መግዛት እንደሚችሉ በቢሮክራቶች እየተመረመረ እንዲወሰን የሚያደርግ አሰራር መፍጠርም ሌላ ወጪ መቀነሻ ቁጥጥር ነው። አዋጁ፣ በእጅጉ የተወሳሰበውና 900 ገፅ ያልበቃው አለምክንያት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው፣ ከነቤተሰቡ የራሱን ጤንነትና ወጪ ሲቆጣጠር አንድ ነገር ነው። መንግስት የእያንዳንዱን ሰው ጤንነትና ወጪ ለመቆጣጠር ሲሞክር ደግሞ፣ ሌላ ነገር ነው - 900 ገፅ የማይበቃው የቁጥጥር ውጥንቅጥ ይፈጠራል።
ለማንኛውም፤ ለጤና ኢንሹራንስ መመዝገቢያ ዌብሳይት በመንግስት ተዘጋጅቶ፣ በታላቅ ሆይሆይታ የተመረቀው አምና በዚህ ሳምንት ነው። በእርግጥ፣ በ95 ሚሊዮን ዶላር ይዘጋጃል ተብሎ የተጀመረው ዌብ ሳይት፣ ከሶስት እጥፍ በላይ ገንዘብ ፈጅቷል (290 ሚሊዮን ዶላር ገደማ)። ምን ይሄ ብቻ! ዌብ ሳይቱ ተመርቆ ሲታይ፣ በደንብ አይሰራም። “ሲታይ”? ...ዌብሳይቱን ከፍቶ ማየት ራሱ አስቸጋሪ ሆኖ አረፈው። መንግስት የዌብሳይቱን ችግር አልካደም። glitch እንዳጋጠመው ገልጿል። እዚህ ግባ የማይባል ትንሽዬ ችግር እንደ ማለት ነው። የዌብሳይቱ ችግር ግን “ትንሽዬ” አልነበረም። ለመመዝገብ የሞከሩ ሰዎች በአብዛኛው አልተሳካላቸውም። በአብዛኛው ማለት... 99% ማለት ነው።

መንግስት “ትንሽዬ እክል” ብሎ እያድበሰበሰ መቀጠል አልቻለም። ዌብ ሳይቱ በአንድ ጊዜ ከሃምሳ እስከ ስልሳ ሰዎችን ለማስተናገድ እንደተሰራ የገለፁት የመንግስት ባለስልጣናት፣ 250ሺ የሚደርሱ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ ስላልቻለ ተንቀራፍፏል በማለት ለማስረዳት ሞክረዋል። መንቀራፈፍ ብቻ አይደለም። በመሃል ፀጥ ይላል፤ ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል። በዚያ ላይ እስከ 60ሺ ሰዎችን በአንዴ የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተሰራው ዌብሳይት፣ ገና ሁለት ሺ የማይሞሉ ሰዎች ሲጠቀሙበት ነው የሚንቀራፈፈው። በጣም የሚገርመው፤ የዌብሳይቱ ቀርፋፋነት የታወቀው በምረቃው እለት ዋዜማ በተደረገ ሙከራ ነው። ግን፣ በሆይሆይታ ተመርቆ ተከፈተ፤ ለዚያውም ሃያ ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር በወጣበት የምረቃ ስነሥርዓትና ድግስ። የግል ቢዝነስ እንዲህ አይነቱን ደንታ ቢስነት በእውኑ ይቅርና በህልሙም አይሞክረውም - ከስሮ እንደሚያርፈው ያውቀዋላ። የመንግስት ሲሆን ግን ችግር የለውም - አይከስርም። ኪሳራ ይኖራል፤ ኪሳራው ግን የባለስልጣናትን ወይም የቢሮክራቶችን ኪስ አይጎዳም። ዜጎች በሚከፍሉት ታክስ ይሸፈናል። እያደር ሲታይ ለካ የዌብሳይቱ ችግር፣ በቁጥርና በአይነት ጥቂት አይደለም - ዘርዝሮ ለመጨረስ ይከብዳል። ይልቅስ በዚሁ የመንግስት ፕሮጀክት ቀውስ መሃል፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ምን ብለው እንደተናገሩ ታውቃላችሁ? ዌብሳይቱ ትንሽ እክል እንደገጠመው የጠቀሱት ባራክ ኦባማ፤ የ“አፕል” ዌብሳይትም ሰሞኑን እክል አጋጥሞት እንደነበር እናስታውሳለን በማለት ማነፃፀሪያ አቅርበዋል። የአይፎን አምራች የሆነው አፕል ኩባንያ ነው ማነፃፀሪያቸው። በእርግጥም፤ ያን ሰሞን የአፕል ዌብሳይት ለአንድ ቀን ያህል ተጨናንቆ ነበር። እንደ መንግስት ዌብሳይት ለወራት እየተበላሸ አልተንፏቀቀም፤ ለአንድ ቀን ግን ተጨናንቋል። መቼ? አምና አዳዲስ ምርቶቹን (አይፎን 5 የተሰኙ ሞባይሎችን) ለገበያ ያቀረበ እለት ነው። ግን፤ 99% በመቶ ያህል ደንበኞቹን ማስተናገድ ያቃተው የመንግስት ዌብሳይት፤ ገና ሁለት ሺ ደንበኞች ሲጠቀሙበት ነው የተብረከረከው። የአፕል ዌብሳይት የተጨናነቀው ግን፤ በአንድ ቀን ውስጥ ከ2 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማስተናገድ፣ የግዢ ትዕዛዛቸውን በአግባቡ መቀበል እየቻለ ነው። ዘንድሮ አይፎን 6ን ለገበያ ባቀረበበት የመጀመሪያው እለት ደግሞ፤ ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በዌብሳይቱ በማስተናገድ ሽያጭ አካሂዷል። የኦባማ ዌብሳይትና የአፕል ዌብሳይት ንፅፅር የዚህን ያህል የተራራቀ ነው - በአሜሪካም ቢሆን። በየትኛውም አገርና በየትኛውም ጊዜ፣ የመንግስት ቢዝነስ ውድቀትና የግል ቢዝነስ ስኬት የዚህን ያህል የሰማይና የምድር ርቀት አለው።ብሎኬት የሚያመርቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ወጣቶች፣ ለአዲስ አበባ ቲቪ ያቀረቡትን ቅሬታ መስማት ትችላላችሁ። ለምሳሌ አንዱ ችግር ምን መሰላችሁ? መንግስት መቼ ሲሚንቶ እንደሚሰጣቸውና መቼ ብሎኬት እንደሚገዛቸው አይታወቅም። ለምን ራሳቸው ሲሚንቶ ገዝተው አይሰሩም? አይችሉም።

ምክንያቱም፣ የሚያመርቱትን ብሎኬት በቅናሽ ዋጋ ለመንግስት የመሸጥ “ግዴታ” ስላለባቸው፣ ሲሚንቶ ከገበያ ገዝተው ቢሰሩ ይከስራሉ። በቅናሽ የመሸጥ ግዴታ... ማለት እንዴት? እንግዲህ፣ የቤቶች ግንባታ በአብዛኛው በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ ስለሆነ፤ አብዛኛውን ብሎኬት የሚገዛው መንግስት ነው። ታዲያ፣ እንደሌላው ገበያተኛ አይደለም። “ሲሚንቶ በቅናሽ ዋጋ እያቀረብኩ፤ ብሎኬት በቅናሽ ዋጋ እገዛችኋለሁ” የሚል መመሪያ አውጥቶላቸዋል - ለአነስተኛና ጥቃቅን አምራቾች። እናም፤ ሲሚንቶ እስኪያቀርብላቸው ድረስ እጃቸውን አጣጥፈው ይጠብቃሉ። ለሁለት ለሦስት ቀን ስራ የሚበቃ ሲሚንቶ ሲሰጣቸው፤ እሷን ተጠቅመው እንደገና ለሳምንታት ያህል በየቢሮው ለባለስልጣናትና ቢሮክራቶች አቤቱታ ማቅረብ ይቀጥላሉ። ያመረቱትን ብሎኬት ለመንግስት ለማስረከብና ክፍያ ለመቀበልም፤ ውጣውረዱና ደጅ ጥናቱ ቀላል አይደለም። በእርግጥ ውሎ አድሮ፣ ሰንብቶና ከርሞ... ትንሽ ሲሚንቶና ክፍያ ያገኛሉ። ለውጥ የሌለው አዙሪት ነው። ታዲያ፤ “መንግስት፣ እንዳንሞት እንዳንድን አድርጎናል” ቢሉ ይገርማል?

Read 3490 times