Saturday, 11 October 2014 13:29

አይ! የሆድ ነገር

Written by  ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
Rate this item
(1 Vote)

           አንድ ሰው ፈሪ ነው ወይም አድር ባይ ነው የሚባለው በምን ሁኔታ ነው? አንድ ግለሰብ እንዴት እንዲያ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል? የወሬኛና አሉባልተኛ ነገርስ እንዴት ነው? አቀባባይ ምንድነው? ውድ አንባቢያን፤ ከሰሞኑ እኒህ ከላይ የደረደርኳቸው ጥያቄዎች ከሆዴ ውስጥ ይገለባበጡ ይዘዋል፡፡ ከምምገው አየር ይሁን ከማየውና ከምሰማው ነገር፣ ብቻ እንዲሁ አላስቆም አላስቀምጥ ብለውኝ ሰነበቱ፡፡ እናም አውጥቼ መገላገል አለብኝና፣ እነሆ ዛሬ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ትንሽ ነገር ለማለት ፈለግሁ፡፡ ኮርኳሪ አያሳጣ ነው! ማንም ሰው ፈሪ ወይም አድር ባይ ሆኖ አይወለድም፡፡ ወደ እዚህ ዓለም ሲመጣ ወሬኛም አሉባልተኛም ሆኖ አይደለም፡፡ ከሁሉም ነገር ፍፁም የፀዳ ንፁህ ፍጡር ሆኖ ነው ወደ ዓለም የሚመጣው፡፡ በእርግጥ አንድን ሰው እንዲህ ነው ወደ ብሎ መፈረጅ ከመግባት በፊት ራስን ወደ ውስጥ ማየት ከሁሉም በፊት መቅደም ያለበት ነገር ነው፡፡ እኔ ማነኝ? ሌላውን አጥርቼ የማየት ብቃቱ አለኝ ወይ? ከስሜታዊነትስ ነፃ ነኝ? ተንኮል፣ ውሸትና ክህደት የሉብኝም? … እነዚህንና ሌሎችም ጥያቄዎች እያነሱ ራስን እየፈተሹ አጥቦ ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው፤ (ምንም እንኳ ሁሉም ሰው ከምንም ነገር የፀዳ ምሉዕ በኩለሄ ባይሆንም) ራሱን በዚህ መንገድ ካዘጋጀ በኋላ፣ ስለ ሌላው ለመናገርም ሆነ በቅንነት ለመተቸት ቢነሳ ለተባለው ግለሰብ ትልቅ እርማትና ትምህርት ይሆነዋል፡፡ የኔ ወይም የኛ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክል ከሚል ወይም ከሚሉ ትናንሽ ጭንቅላቶች ይሰውራችሁ እንጂ፣ ድካማችሁ ከመሬት አይወድቅም፡፡ ብዙ ፍሬ ታፈሩበታላችሁ፡፡ እኔ ፈሪ ከሆንሁ፣ ማንም እየተነሳ በፈለገው መንገድ ልክ እንደ ጠላ ቂጣ ያገላብጠኛል፡፡ ፍርሃትን እየፈራሁት ለማንኛውም የጭነት ዓይነት ለሸክም ጫንቃዬን አዘጋጃለሁ፡፡ ከፈራሁ አድር ባይ እሆናለሁ፡፡ ፈሪም አድር ባይም ሁለቱንም ስሆን ደግሞ፣ ራሴን ብቻ የምወድድ ትርፍ ዜጋ ነኝና ለህዝብም ለሀገርም አሜኬላ ነኝ፡፡ ራሴን ከመጠን በላይ ግምኛ ወደድሁ ጊዜ ሆዴ ይጠልፈኛል፡፡ ሆዴ ደግሞ ጅራት ከሚያስቆላ፣ ተለማማጭና አንገት ደፊ ከሚያደርግ አድር ባይነት ላይ ይጥለኛል፡፡ ይህ ሀቅ ላይዋጥላቸው የሚተናነቃቸው ቢኖሩም፣ እውነቱ ግን ይህ ነው፡፡ ፍርሃት፣ ሆድ ወዳድነት እና አድርባይነት - እነዚህ ሶስቱ፤ አንዱ በአንደኛው ውስጥ ያለ፣ የተለያዩ የሚመስሉ ግን አንድ ሥጋና ነፍስ ያላቸው አንድ አካል ናቸው፡፡ ዓይን ይጋርዳሉ፡፡ አዕምሮ ያስታሉ፡፡

ምላስን ያስቀባጥራሉ፡፡ አካልን ያረክሳሉ፡፡ ሰብዕናን ያጠፋሉ፡፡ ምድሪቱን ያሳዝናሉ፡፡ ከዚህ መሰል ባህርይ በላይ በዓለም ላይ የሚጠላ ነገር ይኖር ይሆን? ወሬኛና አሉባልተኛነትም ከዚሁ መደብ ናቸው፡፡ የወሬ ጫፍ አንጠልጥሎ ጡል ጡል የሚለው ሰው፣ አንድም አጉል ክፉ ልማድ ኖሮበት ሲሆን፣ በአብዛኛው ግን በለውጡ ለሆድ የሚሆን ነገር ለማግኘት ሲባል ነው፡፡ በስራቸው ከመተማመን ይልቅ ለራሳቸው የተሻለ ነገር ለማግኘት ላይ ታች ይባዝናሉ፡፡ በሬ ወለደ ይላሉ፡፡ ነጩን ጥቁር ያደርጋሉ፡፡ ቀባጣሪዎችና ውሸታም ናቸው፡፡ ውሸታቸው ልክና መጠን የለውም፡፡ ዓይናቸውን አጥበው፣ ጥርሳቸውን አግጥጠው፣ ሞራል ካላቸው ያንኑ ደፍጥጠው፣ ያለ ሃፍረት በአደባባይ ይዘላብዳሉ፡፡ የትውልድና የሀገር ነገር ቁባቸው አይደለም፡፡ ለገንዘብና ለምቾታቸው ሲሉ የማይቀጥፉትና የማይሉት ነገር አይኖርም፡፡ ዛሬ ሌላ፣ ነገ ሌላ ስለሚሆኑ ተለዋዋጮች ናቸው፡፡ ቆዳቸው ስስ ስለሆነ ብርሃንንም ጨለማንም ያስገባላቸዋል፡፡ ዛሬ ይመቻቸው እንጂ ለእነዚህ ሰዎች ነገ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሉንም ነገር በዛሬ መነፅር ውስጥ ብቻ ስለሚመለከቱ፣ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም የጋራ አመለካከት የላቸውም፡፡ በደፈናው ግን የሀገር ክፉ ደረመን (እከክ) ናቸው፡፡ “ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው” እንዲሉ፣ መርዛቸው ክፉ ነው፡፡ አቀባባይ ደግሞ የሸማኔ መወርወሪያ ነው፡፡

ለፍርፋሪ ሲል ጌቶቹ ወደፈለጉት ሁሉ የሚላላክና የሚንከባለል ፍጡር ነው፡፡ ይህን ይወስዳል፣ ያንን አምጥቶ ያቀብላል፡፡ ይደልላል፣ ያሻሽጣል፡፡ የማሩ ዕቃ ገረወይናው ሲከደን፣ የተንጠባጠበውን ብቻ ለራሱ ላስ ላስ አድርጎ፣ የሞላውን ዕቃ እንዲሁ እንዳለ ለጌታው ወስዶ ያስረክባል፡፡ አቀባባይ በልቶ አይጠረቃም፡፡ ዘወትር ነጭና ቡላ ነገር ነው፡፡ የሀገር ቅርስን፣ የወገን ውርስን ወዲያ ወዲህ ለማድረግ ከተላከ፣ ምንም ሳይሰቀጥጠው የሚያደርግና ሞራል አልባ ሰው ነው፡፡ “ቀበሮ የበሬ … ይወድቅልኝ ብላ ስትከተል ትውላለች” እንዲሉ፣ አቀባባይም የሚጣልለትን እየጠበቀ ዘወትር ሲያንጋጥጥ ይኖራታል፡፡ ይህን በተመለከተ ቆየት ካለችው ግጥሜ ውስጥ ጥቂት ስንኞች መዝዤ ላስነብባችሁ፡- …ለፍርፋሪ ተሸንግሎ፣ ሰው ነው ውሻ መስሎ፣ ቅቤ ቢውጥ ሊነጣ፣ ላይታመም ሊገረጣ፣ ጉንጨ - ነጭ ነው አመዳም፣ አቀባባይ አይጠረቃም፡፡ (መስከረም 1994 ዓ.ም) እነዚህ ምግባረ - ቢስ አድርባይ ግለሰቦች ባህል ያረክሳሉ፣ ትውልድ ይበክላሉ፡፡

ከህዝብ በላይ ወጥተው እንዲያው ሳይገመት ሀገር አመራር ላይ የተቀመጡ ጊዜ ደግሞ ያቺ ሀገር አበቃላት ማለት ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ እስካሁን በተገለጸው መንገድ ማህበረሰባችን ውስጥ ብዙዎችን ተመልክተን ስንታዘብ ቆይተናል፡፡ ለታሪክም ተመዝግበው ተቀምጠዋል፡፡ ዕለታቱ፣ ወራቱና ዓመታቱ እንዲህ የመሳሰሉትን አዳዲስ ሰዎች እየፈጠረልን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ለማንኛውም ግን፣ የብዕር ሰዎች ሁሉ ጧት ከመኝታችሁ ስትነሹ፣ ለሰማያዊ አባታችሁ ከምታቀርቡት የዘወትር ፀሎት በኋላ፣ “እባክህ!... ኮርኳሪ አታሳጣኝ!” የምትለዋን ምድራዊ ፀሎትንም ጨምሩባት፡፡

Read 2268 times