Monday, 06 October 2014 08:44

የተፈጥሮ ውበትና ግልምጫ - በስንኞቻችን

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

         አዲሱ ዓመት አደይ አበባ ነስንሶ፣ በጀንፈርዋ ትኩስ ፈገግታ ጣዕም ነፍሳችንን መቀነት እያስፈታ ማታለሉን ለምዶበታል፡፡ … ወንዞች እየሳቁ ተራሮች እየተጀነኑ ከፀሐይ ጋር ሲስቁ፣ እኛም ከበሮዋችንን ይዘን “አበባየሁ ወይ!... ለምለም!” እንላለን፡፡ እግዜርም ለደሀውም ለሀብታሙም ደስ ይበለው ብሎ ተፈጥሮ በዓመት አንዴ ፊቷን እንድትታጠብ ሳሙና ያቀብላታል፡፡ ውበት ስንል ታዲያ ሁሌ ተፈጥሮው ያመዝናል፡፡ ለምሳሌ ዮሐንስ አድማሱ ስንኞች ከርክሞ የሚናገርላት ውበት፤ ደስታን እንደክብሪት መጫርዋ ይቀራል እንዴ?
ቀስተ ደመናው፣
በህብሩ አሸብርቆ፣ ጎበብ ቀለስ ብሎ፣
ባድማስ በሰማዩ ሰፍኖበት ተንጣሎ፣
ይሰለቻል ወይ?
ጎበዝ ይሰለቻል? … አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም የሰው ልጅ ማግባቢያ፣ ተስፋ መቋጠሪያው ይህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከአንዱ ተራራ ግርጌ ሌላው ተራራ ግርጌ የተሰካው የነጠላ ጥለት የመሰለ ህብረ ቀለማዊ መቀነት እንዴት አያጓጓም! … እንዴት ይሰለቻል? … ከላይ እንዳልኩት ማዘጋጃ ቤት እንደሚሰቀል ባንዲራ በየዕለቱ እንዳንለምደው ቀስ እያለ ብቅ የሚለውም ለዚህ መሰለኝ! … እንደመስቀል ወፍም ባይሆን!
የልምላሜ ምሥጢር በልምላሜ ሰልቶ
አምሮ ተሰንግሎ በተፈጥሮ ጠርቶ
ይሰለቻል ወይ?
ይህ አሁን ያለንበትን ወቅት ነው የሚያሳየን፡፡ አረንጓዴ ምንጣፍ ለብሶ በእግር ሊረግጡት በሚያሳሳበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ይሰለቻል እንዴ?
የመፀው ምሽቱ
አብራጃው ሲነፍስ የህዳር የጥቅምት
የትሳስ አየር
ጨረቃ አደድላ ተወርዋሪ ኮከብ
ሲነጉድ ሲበር፣
ይሰለቻል ወይ?
በክንድ ላይ ሁና
ብላ ዘንጠፍ ዘና
ሶባ ቀዘባዋ የሚያፈቅሯት ልጅ
ፍቅር ሲፈነድቅ ሲሰራ ሲያበጅ
ይሰለቻል ወይ?
የውበት የፍቅር የሀሴት ሲሳይ፡፡
ውበትን ከየወቅቱ መዝዞ፣ የሌቱን ለሌት፣ የቀኑን ለቀን ማስጌጫ ያደረገው ገጣሚስ ውበት የሚያሸትበት አፍንጫ ረጅም አይደለም?
ተፈጥሮ ሁሌ ውበት አጥቅሳ፣ ቀለም ነክራ የምታስጨፍር ብቻ አይደለችም፡፡ በከሰል ፊትዋ ታሳርራለች፤ በፍም ገላዋ ታነፍራለች፡፡ በነደደ ገላዋ እምባ ትጠባለች፡፡ ይህንንም በጦፈ ስሜት ባዘነ ድምጸት የሚነግረን ገጣሚ ነቢይ መኮንን ነው፡፡
የተፈጥሮ ጥርሶች እየሳቁ ማሳቅ፣ እየፈነደቁ ማማለል ብቻ ሳይሆን፣ በተፋቀና በሚያምር ውበት ውስጥ ተደብቀው ይናከሳሉ፤ አጥንት ይቆረጥማሉ፡፡ የሎሌያቸውን ያዳም ልጅ እግር ነክሰው ሩጫውን ያቆማሉ - ይላል፡፡ ጎምላላው ደመናም ሲያሻው አናታችን ላይ እንደ ጦር መሪ ይጀነን እንጂ ሲለው በናፍቆት እስክንቃጠል ፊቱን ያሻሸናል፡፡ የነቢይ “የደመናው ሎሌ” እንዲህ ይላል፡-
ለወትሮው፤
ደመና
ፊቱ እየጠቆረ
ዐይኖቹን አሻሽቶ ያነባ ነበረ፡፡
ይዘንብ ነበረ፡፡
የዘንድሮ ሰማይ፤
እየሳቀ ገዳይ፤
ፈጋግ ሰማያዊ መልኩን አሳምሮ
ስንቱን ፈጀ በላ፣ ከራብ ተመሳጥሮ፡፡
የምድር ከርስ አረረ፡፡
ሀገር ጦም አደረ፡፡
ሰው ምጡ ጠናና ዐይኖቹን አቀና፡፡
እንደው ከርተት ከርተት፣ ሰማይ ለሰማይ
ዋ ምስኪን ገበሬ፣ ምን ውሃ እህል ሊያይ!
ውሃ - የለሽ ኅዋ፣ ጠብታ አልባ ጠፈር
ሰማይ አይታረስ ባይን ብሌን ሞፈር፣
የደመናው ሎሌ የደመናው አሽከር
የዕለት ግብሩ ሆነ ጦም ውሎ ጦም                ማደር …
እንግዲህ ውቡ የመስከረም ሰማይ፤ ቅድመ ዮሐንስ ያለው … የመጸውም ወራት ሁሉም ጀርባ ሰጥተው፤ ብሩህ ገፃቸውን የቁጣ እሳት፤ የፍርሀት ጠላሸት አልብሰው የሚከሰቱበትም ጊዜ አለ፡፡ ተፈጥሮ ቁማርተኛ ናት፡፡ ታባብልና ትበላለች፡፡ ታሳስቅና እግሯ ስር ትጥላለች፤ ታዲያ ገጣሚውም እንደየጊዜው ስሜቱ፣ እንደ ወቅቱ ትዝብት ነፍስ ያንከባልላል፤ ቃላት እንደጥይት ያቃጥላል፣ ብዕር እንደጠመንጃ ይወለውላል!
ሰማይ እየሳቀ፣ ገደለ፡፡ ከራብ ጋር ገጥሞ የአዳምን ዘር አጠቃ፡፡ የአዳምን ልጅ ደለለ፡፡ ቢለማመጠው እንኳ ጆሮ ዳባ ልበስ አለ ነው የሚለው፡፡ ሰማይ ስለከዳው ጦም አዳሪ ሆነ፡፡ ጦም ማደሩ ብቻ አይደለም፤ ጦማደሩ ግብሩ ሆነ፡፡ እንግዲህ ግብሩ ጦም ማደር ከሆነ፣ ለተከታዩ ክስተት ነቢይ ፍለጋ መሄድ አይሻም! … ተከታዩ እልቂት ነው፡፡
ወጣትዋ ገጣሚት ሰናይት አበራም ስለ አዲስ ዓመት ተፈጥሮ፣ ስለወፎች ዝማሬ፣ ስለነሐሴ ሰማይ መልክ ታወራለች በስንኝ፡-
ወፎች - ሲዘምሩ
ዛፎች - ሲሸልሉ
ሲደንስ - ተራራ
የነሃሴ ሰማይ
ሲሄድ - እየጠራ
ከርሞ - ተፋጠጠ
ሰው - ከራሱ ጋር
ይሄኛው የተለየ አተያይ ነው፡፡ ሰው ጉዱ ፈላ፣ ገመናው ተገለጠ፤ እያለች ነው፡፡ አምና የነበረው ተፈጥሮ ሌላ መልክ ይዞ ብቅ ሲል፣ መልኩን አሳምሮ ጠጉሩን አበጥሮ መስታወት ፊት ሲቆም፣ ሰው ግን ባለበት ሲረግጥ ወዮለት! እያለች ነው ታምቡር የምትመታው!...
ግጥሙ ከሌሎቹ ግጥሞቿም በደረጃ ዝቅ ያለ ነው፤ በውበትም በቋንቋ አጠቃቀም ጭምር፣ ዜማ ለመፍጠር እንኳ ተንገዳግዶ ነው፤ ግድግዳ የሚቧጥጥ ዓይነት ነው፡፡ ክረምትና በጋ እንደጨለማና ብርሃን ይታያሉ፡፡ ክረምቱ ደመና ቆልሎ፣ ሰማይን ጨፍጋጋና አኩራፊ ያደርገዋል፡፡ ያኔ ሰው ደግሞ ጭራሮ ቆልሎ እያነደደ ባንድ በኩል ብርዱን፣ በሌላ በኩል ጨለማውን እያሳደደ ይገርፈዋል፡፡ ያ ክረምት ደግሞ የተፈጥሮ እርግዝና ወቅት ነውና አበቦችን አርግዞ ይቆይና - መስከረም ብቅ ሲል ይወልዳቸዋል፡፡ ከዚያ ሰማይም ፈገግታ ለኩሶ ብቅ ይላል፤ ሰውም የሰማዩን ፈገግታ ሲያጅብ ችቦ ይዞ ይዘምራል፡፡ ሳቅ በሳቅ ነው፡፡ ገጣሚዎቹ እንደሚነግሩን፤ ተፈጥሮ ውበትዋንም ታሳይ ወይም ታሥቀይም ሰው አማካይ ሆኖ ድል መንሳት አለበት፡፡ እንደሰናይት ግጥም ባዶ መሆንም የለበት፡፡ ይልቅስ ሲሳይ ታደስ ሌላ የሚለው ነገር አለ፤ “ሰው ብርሃን ሰው ጨለማ” በሚለው ግጥሙ፡-
ብርሃን በለበሰች
ፅልመት በደረበች
በዚች ሰፊ ዓለም፣
ከራስ ጨለማ እና - ብርሃን በስተቀር
ሌላ ጨለማና - ሌላ ብርሃን የለም!
እና እሳቤውን - ሰው ማብራት ካወቀ፤
በእኩለ ሌሊትም - ብርሃን ባልጠለቀ፡፡
ምሽት ብሎ ነገር - ባልኖረ የቱም ጋ፣
ሰው ውስጡን ካበራ ሰው ልቡን ካነጋ!
ጨለማና ብርሃን ወይም የበጋና ክረምት ተምሳሌት ያለው እኛው ራሳችን ውስጥ ነው ባይ ነው ሲሳይ፡፡ ብርሃን ለብሳ ብርሃን የደረበችው ዓለም፤ በሰው የውስጥ ብርሃን ፈፅሞ የማያቋርጥ የብርሃን ጅረት ሊፈስስባት ይችላል በማለት፣ የሰው ልጅ ለችግሮቹ በተፈጥሮ ላይ ማሳበብ የለበትም ነው የሚለን፡፡
እንግዲህ ገጣሚዎቻችን ከፊሉ በተለይ ዮሐንስ አድማሱ፣ ተፈጥሮ ሸጋዋን በክንድዋ ስር አቅፋ፣ በውበትዋ እያማለለች ህይወት እንዳይሰለቸን የምታደርግ ቅመም ናት ይለናል፡፡ ነቢይ መኮንን ደግሞ ሰው የደመና አሽከር ነው ይላል፤ በተለይ ያገራችን ገበሬ፡፡ ደመና ሰማይ ላይ ተነስንሳ፣ ከሳሎን ወደ ጓዳ መሶብ ይዛ ሽር እንደምትል እመቤት እያስጎመዠች ምራቅ ታስውጠዋለች በማለት ቁጭቱን ፅፏል፡፡ ሰናይት አበራ ደግሞ ተፈጥሮ አንዴ ጸጉሯ ላይ አበባ ሰክታ፣ ሌላ ጊዜ ፊቷ ላይ አመድ ነፍታም ብትወጣ ሰው ካልተነቃነቀ ባዶ ነው የምትል ይመስላል፡፡ ሲሳይ ደግሞ የዓለም ሁሉ ብርሃን የተካተተበት ቋት ሰው ራሱ ነው እያለ ይወቅሳል! እና ማንን እንስማ? … ሁሉንም! … ሁሉም በየራሳቸው ዓይን የየራሳቸውን ቀመሩልን፣ የየራሳቸውን ችቦ አበሩልን!... እኛም በምርቃት አጀብ፡- ብርሃን ያውጣላችሁ እያልን እናጣጥም፤ እናስብ፤ እንሳቅ፤ … እንተክዝም ጭምር!


Read 2195 times