Monday, 22 September 2014 13:48

እንቁጣጣሽ

Written by  መሐመድ ኢድርስ
Rate this item
(6 votes)

ጀማል ከዕንቅልፉ ማልዶ ተነሳ፡፡ በእንቁጣጣሽ ቀን አርፍዶ መዋል አልፈለገም፡፡ ለወትሮው እንቅልፍም ቢሆንም
ዛሬ ግን ስራ አለሙ፡፡ ትላንት በዋዜዋማው ቸበርቻቻ ከተመነዘረው ብር የቀሪውን ለማየት ኪሱን ዳበስ፡፡ አስር
ብር ብቻ ነበር የቀረው፡፡
ገንዘብ ሊያገኝ የሚችልበት ምንም ጭላንጭል አልታይህ ስላለው ተስፋ ቆርጧል፡፡ የሚተዳደረው ከሴት አያቱ
ከወረሰው ሶስት ክፍል ቤት ሁለቱን በማከራየት ሲሆን እሱንም ቢሆን ኪራዩን ለበቅድምያ ተቀብሎ ስለጨረሰው
ተከራዮቹን ገንዘብ መጠየቅ የማይሞከር እንደሆነ ያውቃል፡፡ ከቤት ኪራዩ ውጭ ሌላው የገንዘብ ምንጩ
ተማሪዎችን እንግሊዝኛ በማስጠናት የሚያገኘው ገቢ ነበር፡፡ እሱም ባለፉት ሶስት የክረምት ወራት ትምህርት
ቤቶች ዝግ ስለነበሩ ደርቋል፡፡ ሶስተኛውና አልፎ አልፎ የሚሰራው የገንዘብ ማግኛ ዘዴው “ወዲህ በሉ” ማለት
ሲሆን ይሄም ዛሬ እንደማይሰራ ግልፅ ሆኖ ታይቶታል፡፡ ምክንያቱም በሱ አነጋገር ሰው ሁሉ ተፈልጦ አልቋል፡፡
አዲሱን ዓመት እንደሰው በልቶ ጠጥቶ፣ ተደስቶና ተዝናንቶ እንደማያሳልፍ ሲያስብ ከዓለም ተገልሎ ብቻውን
የቀረ መስሎ ተሰማው፡፡ ጀማል ታጣፊ አልጋው ላይ እንደተቀመጠ ቤቱን ቃኘ፡፡ የሚሸጠው እቃ እንዳለ
ማጣራቱ ነበር፡፡ አንድ እግሩ የወለቀም ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ አሮጌ ፊሊፕስ ሬዲዮና አያቱ ቡና ሲያፈሉበት
የነበረው ትልቅ ጀበና ብቻ ነበር አይኑ ውስጥ የገባው፡፡
ነፍሳቸውን ይማርና አያቱ የእንቁጣጣሽ ዕለት ጠዋት በማለዳ ተነስተው ነበር ጉድ ጉድ የሚሉት ብዙ ጊዜ፡፡ ቡና
ሲቆሉ ከእንቅልፍ ይነቃል፡፡ እየተነጫነጨ ነው፡፡ ከአልጋው የሚነሳው የሚነጫነጨው አንድም በማንከሻከሽ
በሚቆላው ቡና ድምፅ እንቅልፉን ሳይጠግብ ስለሚነሳ ሲሆን ሌላው አያቱ በባዶ ሆዱ ሆዱ እስኪገላበጥ ደረስ
የሚጎመዝዘውን የፌጦ ፍትፍት በግድ ስለሚያጎርሱት ነበር፡፡ ቡናቸውን ሲያፈሉ ታዲያ በስርአት ነበር፡፡
ከረከቦቱ ጎን ካለ ሰፌድ ላይ የማሽላ ፈንዲሻ፣ ኑግና ከረሜላ አይጠፋም፡፡ ማጨሻው ላይ ቀበርቾና የባህር ዕጣን
ቤቱ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ይጨሳል፡፡ የህንን ሲያደርጉ ታዲያ ነጭ የሐበሻ ቀሚሳቸውን ለብሰው ከላይ
ቀይ ድርያ ጣል አድርገው ነው፡፡ ቡናውን ሲቀዱ ጀማል እንደተገረፈ ህፃን ልጅ አፏን ለጉሞና እጁን አጣምሮ
ይቀመጣል፡፡ ይህንን ካላደረገ ምን እንደሚከተለው ያውቃል፡፡
“ምን ይንከወከዋል ይሄ ቀልበ ቢስ” ካሉ በኋላ የእርግማን መዓት ያወርዱበታል፡፡ እሳቸውን የሚያመለኩትንና
“ደምና ፈርስ ሳይነካህ ሆድ ውስጥ ገብተህ የምትወጣ ያባት የናቴ አምላክ” እያሉ የሚለማመኑት አውልያቸውን
እየፈራ ነበር ያደገው፡፡
በእድሜ ሲጎለምስ በእውቀት ሲበስልና ቅዱሱን መጽሐፍ ቃል በቃል እስኪያስታውስ ካጠና በኋላ ነበር “እኔ
አንድ አምላክ ነኝ፡፡ ከኔ ሌላ አታምልክ” የሚለው ፈጣሪ ቃል ውስጥ የገባው፡፡ ያኔ ነበር አያቱ በባዕድ አምልኮ
የተተበተቡ መሆናቸውን የተረዳው፡፡
“ይሄ ጀበና ነው የኔ ጠላት” ሲል አልጎመጎመ ለብቻው፡፡ የአያቱ ባዕድ አምልኮ መንፈስ በዚህ ጀበና ላይ አርፎ
ህይወቱን እንዳጨለመው አሰበ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጨለማ መንፈስ ተላቆ የፈጣሪውን በረከት ለማግኘት ጀበናውን
ከዚህ ቤት አርቆ መወርወር እንዳለበት ወሰነ፡፡
ትላንት በዋዜማው ከጓደኞቹ ጋር አሸሼ ገዳሜ ሲልና የነበረችውን ገንዘብ ሲያጠፋ ወ/ሮ ፀሐይን ተስፋ አድርጎ
ነው፡፡ ወ/ሮ ፀሐይን የእንቁጣጣሽ ቀን ቢጎበኛቸው እንዴት ደስተኛ እንደሚሆኑ ተሰምቶት ነበር፡፡ ታዲያ እግረ
መንገዱን ሁለት መቶ ብር ቢበደራቸው በዓሉን በደስታ አሳለፈ ማለት ነው፡፡
ወ/ሮ ፀሐይን የሚያውቃቸው ሁለቱ ልጆቻቸውን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲያስጠና እቤታቸው ሲሄድ ነበር፡፡
ከደሞወዙ ውጭ ለታክሲ እያሉ የሚሰጡት ጉርሻ ሶስት ቀናት የሚያውል ነበር፡፡ ወ/ሮ ፀሐይ ሞልቶ የተረፋቸው
ሴት ስለሆኑ ሁለት መቶ ብር ለሳቸው ሁለት ብር ማለት ነው፡፡
ለመጨረሻ ግዜ ያያቸው የዛሬ ሁለት ዓመት ሲሆን ድሮ ከነበሩበት ሰፈር ወደ ፍልውሐ አካባ ቤት እንደቀየሩ
ሰምቷል፡፡ አዲሱን ቤታቸውን ባያውቀውም ስልካቸው ስላለው ደውሎላቸው ይሄዳል፡፡ ከሁሉም በፊት ግን
ይሄን አጋንንታም ጀበና ድራሹ ማጥፋት አለበት፡፡
ጀበናውን አንስቶ ከቤት ወጣና ወደ ፍልውሃ የሚወስደውን ታክሲ ያዘ፡፡ ታክሲ ውስጥ እንዳለ ለወይዘሮ ፀሐይ
ደውሎ እንደሚመጣ ነገራቸው፡፡ ቤታቸውን በምልክት ከነገሩት በኋላ በመምጣቱ ደስ እንደሚላቸው በሰለለ
ድምፅ ነገሩት፡፡ ስልኩን ሲዘጋ ድምጻቸው እንደወትሮው እንዳልነበረ አስተዋለ፡፡
ፍልውሃ ፖስታ ቤቱ ጋ እንደወረደ መደዳውን የባህል እቃ መሸጫ ሱቆች ባሉበት ቀጭን መንገድ ወደ አምባሳደር
አቀና፡፡ ወደ ወይዘሮ ጸሐይ ቤት ከመሄዱ በፊት ጀበናውን ሲኒማ ቤቱ ፊት ለፊት ያለው ወንዝ ውስጥ ለመጣል
አስቧል፡፡ አንዲት ወርቃማ ፀጉር ያላት የሐበሻ ቀሚስ የለበሰች ፈረንጅ ከአንዲት ዘመናዊ አለባስ ከለበሰች
ወጣት ሴት ጋር በመንገዱ እያለፉ ነበር፡፡ ጀማል የሐበሻ ቀሚስ የለበሰች ፈረንጅ አይቶ ስለማያውቅ በመገረም
ሲያት እስዋም በፈገግታ አተኩራ እያየችው ተላለፉ፡፡ ጥቂት እርምጃዎችን እንደተራመደ ነበር “ወንድም” የሚል
የጥሪ ድምፅ የሰማው፡፡ የጠራችው ከፈረንጇ ጋር የነበረችው ወጣት ሴት ነበረች፡፡
ዝግ ባለ እርምጃ ወደነሱ ተጠጋ፡፡ ሁለቱም ሞቅ ባለ ፈገግታ እያዩት በአክብሮት እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉ፡፡
“ሊንዳ ትባላለች፡፡ ከአውስትራልያ የመጣች ጓደኛዬ ነች፡፡ ሜልቦርን ውስጥ የአፍሪካን ባህል የሚያሳይ
ሬስቶራንት ከፍታለች፡፡ የዚህ አይነት ትልቅ ጀበና አይታ አታውቅም፡፡ የት እንደሚገኝ ልትነግረን ትችላለህ?”
ስትል ጠየቀችው ፈገግ እያለች፡፡
“አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ያለ አይመስለኝም፡፡ ድሮ አያቴ ከትግራይ ይዘውት የመጡት ነው፡፡ ስልክ
ከሰጣችሁኝ አጠያይቁ ላስመጣላችሁ እችላለሁ፡፡” አለ፤ አዲስ የቢዝነስ ሐሳብ ጭንቅላቱ ውስጥ እየታው፡፡ በጣም
የሚገርምህ ነገር ዛሬ ማታ ነው ወደ አገርዋ የምትመለሰው፡፡ ተመልሳ የምትመጣው ደግሞ ከሁለት ኣመት በኋላ
ነው አለችው አይኖችዋ አይኖቹን እየተሰማመጡ፡፡
“አይ ታዲያ ምን ይሻላል?” አለ በማስተዛዘን፡፡ በልቡ ግን “ልጥለው አልነበር?” ብሰጣቸውስ!” የሚል ሐሳብ
መጥቶበታል፡፡
“ደፈርሽኝ አትበልና ትሸጠዋለህ?” የፈለግከውን እንከፍላለን”
ጀማል አሁን ባነነ፡፡ ሴቶቹ ጀበናውን በጣም ይፈልጋሉ፡፡ እሱ ደግሞ ገንዘብ ስፈልገዋል፡፡ እዚህ ላይ ጭንቅላቱን
መጠቀም አለበት፡፡
“እንደዚያ እንኳን አልችልም፤ የአደራ እቃ ነው”
“ገዝተህ ልትተካላቸው ትችላለህ”
“እንደዚ ከባድ ነው I am sorry – I cant” አለ በእንግሊዝኛ
ፈረንጅዋን እያየ፡፡
“I will give you one hundred” አለች ፈረንጅዋ ቦርሳዋን እየከፈተች፡፡ ጀማል ልቡ መታ፡፡ ሴትየዋም
ጀበናውን ፈልጋለች፡፡ እሱ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ለዓመት በዓል ያስፈልገዋል፡፡
“Two hundred” አለ የመጣ ይምጣ ብሎ፡፡ ፈረንጇ ትኩር ብላ ካየቸው በኋላ ፈገግ አለችና ቦርሳዋን መበርበር
ጀመረች፡፡ ገንዘቡን አውጥታ ስትሰጠው ያየውን ማመን አልቻለም፡፡ ሁለት መቶ የአሜሪካን ዶላር!
ጀበናውን ሰጥቷቸው፣ ሃሳባቸውን ቀይረው ፖሊስ ጠርተው እንዳያስይዙት እየፈራ ልቡ እየመታ መንገዱን
ተያያዘው፡፡
“Thank you God bless you” የሚለው የፈረንጅዋ ድምፅ ይሰማዋል፡፡ በፍጥነት ወደ አምባሳደር ሲቆለቁል
እንደ ዕድብ ብቻውን እየሳቀ ነበር፡፡
በወንዙ በኩል ሲልፍ ጀበናውን እዚያ ሊጥለው አስቦ እንደነነበር አስታወሰና ሁለት መቶ ዶላር ከመጣል
ያዳነውን አምላኩን አመሰገነ፡፡ ፈጣሪው እያስተማረው እንደሆነ የገባው ዶላሩን ሲመነዝር ነበር፡፡ ባዕድ አምልኮ
አስወግዶ ፈጣሪውን ብቻ በማየቱ የተሰጠው ሽልማት እንደሆነ አውቆዋል፤ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ኪሱ
ሲከት፡፡
ወይዘሮ ፀሐይ ቤት የመሄዱን ነገር አልተወውም፡፡ አሁነ በያዘው ገንዘብ ላይ ሌላ ሁለት መቶ ብር ቢጨመርበት
ምን ይጎዳዋል? ሴትየዋንም በእንቁጣጣሽ ቀን መጠየቁ ደግ ተግባር ነው፡፡
የሰጡትን ምልክት እስታወሰ መስጊዱን አልፎ በስጋ ቤቶቹ አቋርጦ ፀጉር አስተካካይ ቤቱን አልፎ የቦይ ውሃ
ያለበት አጠገብ ሲደርስ ቆም አለ፡፡
እንደተሳሳተ ገምቶዋል፡፡ እንዴት ወ/ሮ ጸሐይን የመሰሉ ሴት እዚህ ቤት ውስጥ ይኖራሉ? የሚል ጥያቄ
መጥቶበታል፡፡
ፈራ ተባ እያለ አንዱን ጎረምሳ ያውቃቸው እንደሆን ጠየቀው፡፡ ሰማያዊ የእንጨት በር ያለው ቤት እንደሆነ
ነገረው፡፡
“ይሄ ቤት?” ሲል ጠየቀ በመገረም፡፡
ጎረምሳው በእርግጠኝነት ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡
በሩን አንኳኩቶ ገባ፡፡ ሴትዮዋ አሮጌ ብርድልብስ ተከናንበው አልጋ ላይ ተኝተዋል፡፡ ፊታቸው ገርጥቶዋል፡፡
ከተኙበት አልጋና ከአንድ አሮጌ የዕቃ መደርደር በስተቀር ሌላ ዕቃ ክፍሉ ውስጥ የለም፡፡ ሰላምታ ሰጥቶዋቸው
ተቀመጠና ምን እንዳገኛቸውና ለምን እንደዚህ እንደሆኑ በሐዘንና መገረም በተቀላቀለበት ድምፅ ጠቃቸው፡፡
ምኑን ልንገርህ ልጄ! ሰውየው በሐሰት ማስረጃ ከስሶ ቤቴን ወሰደው፡፡ ልጆቼንም አልሰጥሽ አለኝ፡፡ ገንዘቤ
የጠበቃ ሲሳይ ሆነ፡፡ እስሩም እንደዚህ ጨረሰኝ፡፡
መድሐኒት መግዣ እንኳን አጣሁ፡፡ ፈጣሪን የፈራ ሰው በሚጥልልኝ ምፅዋት ህይወቴን እየገፋሁ ነው ልጄ አሉት
እንባ እያደናቀፋቸው፡፡ እጁን ወደ ኪሱ ላከና ሁለት መቶ ብር አውጥቶ ሰጣቸው ከሳቸው ቤት ወጥቶ ወደ
ታክሲው መያዣው ሲያመራ “የሚመካ በእግዚአብሄር ይመካ” የሚል ጠቅስ የፀጉር አስተካከይ ቤት መስተዋት
ላይ ተለጥፎ አይቷል፡፡

Read 3246 times