Saturday, 13 September 2014 13:52

4ኛው ኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ነገ ይፈፀማል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

      ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያዘጋጀው 4ኛው ኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በነገው እለት በሚካሄደው የመጨረሻ ዙር ውድድር ይፈፀማል፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር በመጀመርያዎቹ ሁለት ዙሮች ባስመዘገቡት ውጤትና ነጥብ መሰረት በሁለቱም ፆታዎች ተቀራራቢ ነጥብ ያስመዘገቡ ከሁለት በላይ አትሌቶች መኖራቸው በፍፃሜው ከፍተኛ ፉክክር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአትሌቶች ደረጃ በሚካሄደው ፉክክር በሴቶች ምድብ አስቀድመው በተካሄዱት ሁለት ውድድሮች 14 ነጥብ በማስመዝገብ የምትመራው አለሚቱ ሃዊ ናት፡፡ ዘውድነሽ ሃይሌ እና ሽቶ ውዳሴ በእኩል 10 ነጥብ ይከተሏታል፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ ጌታነህ ሞላ፤ ዘውዱ መኮንንና እና ጋዲሳ ብርሃኑ በእኩል 10 ነጥብ ለመጨረሻው እና ለሶስተኛው ዙር ውድድር ነገ ይተናነቃሉ፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ከአንድ እስከ ሶስት ደረጃ ለሚያገኙ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው 50ሺ ብር፤ 25ሺህ ብርና 1ሺ 500 ብር ሽልማት እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው ኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ሲካሄድ ለየት የሚያደርገው ሶስቱን ዙር ለሚሮጡ የጤና ስፖርተኞች የሚሸለመው ፕሮፌሽናል የመሮጫ ሰዓት እና ኮርፖሬት ቻሌንጅ በሚል ዘርፍ በለቡድን ሯጮች የተዘጋጀው አዲስ የውድድር አይነት እና ሽልማት ነው፡፡ ከዋናው የአትሌቶች ውድድር ጋር በኮካ ኮላ ተከታታይ የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ ከ4ሺ በላይ የጤና ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን ነገ በሶስቱም ውድድር ለተሳተፉት ለእያንዳንዳቸው ፕሮፌሽናል የመሮጫ ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ በኮርፖሬት ቻሌንጅ እያንዳንዳቸው 10 ስፖርተኞች በማስመዝገብ በቡድን ለሚወዳደሩት በተዘጋጀው ሽልማት ደግሞ ለአንደኛው ሙሉ የአዲዳስ ትጥቅ፤ ለሁለተኛው የአዲዳስ ሙሉ ትጥቅ ያለጫማ እንዲሁም ለሶስተኛ ደረጃ የሁለት ወር የጂም አገልግሎት ክፍያ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

Read 1275 times