Saturday, 06 September 2014 11:27

ዋልያዎቹ የበረሃዎቹን ቀበሮዎች ይፋለማሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

           የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሞሮኮ ወደ 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 2 ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታው ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም አልጄርያን ያስተናግዳል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ባማኮ ላይ ማሊ ካሙዙ በተባለው ስታድዬም ከማላዊ ትገናኛለች፡፡
በምድብ 2 ያሉት አራት ቡድኖች የምስራቅ፤ የሰሜን ፤ የደቡብ እና የምእራብ አፍሪካ ዞኖችን በመወከል ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉ ሲሆን ማጣርያውን በመሪነት በማጠናቀቅ እንደምታልፍ ቅድሚያ ግምቱን የወሰደችው አልጄርያ ብትሆንም  ኢትዮጵያ እና  ማሊ  የማለፍ እድል እንደሚኖራቸው የተለያዩ ትንተናዎች አመልክተዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ 10 ጊዜ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በ1962 እኤአ ሻምፒዮን ስትሆን 14 ጊዜ የተሳተፈችው አልጄርያ ደግሞ በ1990 እኤአ ዋንጫውን ወስዳለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጊዜ የተሳተፈችው ማላዊ በሁለቱም ከመጀመርያው ዙር ስትሰናበት፤ በአፍሪካ ዋንጫ 8 ጊዜ የተሳተፈችው ማሊ ትልቁ ውጤቷ በ1972 እኤአ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችበት ነው፡፡
የምድቡ ሁለተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች ከአራት ቀናት በኋላ ይቀጥላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ በብላንታዬር ከተማ በሚገኘው  ስታዴ ዱ 26 ማርስ  ስታድዬም ማላዊን የሚገጥም ሲሆን አልጄርያ በዋና ከተማዋ አልጀርስ ላይ ማሊን ታስተናግዳለች፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ለሚካሄደው የኢትዮጵያና አልጄሪያ ጨዋታ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የህዝብ ግንኙነቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡
የስታድዬም መግቢያ ትኬት ሽያጭ ስርዓቱን እንዲጠብቅ ፌዴሬሽኑ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ገልፆ፤  ከጨዋታው በፊት የዋሊያዎቹ ብቸኛ ስፖንሰር ከሆነው በደሌ ስፔሻል ጋር በመተባበር የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያና አልጄሪያ ጨዋታ የመግቢያ ዋጋ ከሚስማር ተራ እስከ ጥላ ፎቅ 10፣ 20፣ 30 ፣100 ፣500 ብር  እንዲሁም ክቡር ትሪቢዩን ብር 1000 እንዲሆን ተወስኗል፡፡  በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚካሄደው የኢትዮጵያ እና አልጄርያ ጨዋታ በዲኤስቲቪ እና በስፖርት ፋይቭ ቻናሎች የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት ይኖረዋል፡፡
በተለይ ስፖርትፋይቭ የተሰኘውና ሁሉንም የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያና የመጨረሻ ጨዋታዎች የማሰራጨት ሙሉ መብት ከካፍ የተሰጠው የማርኬቲንግና የሚዲያ ኩባንያ የመደባቸው ከ20 በላይ ከፍተኛ ሙያተኞች ይህንን ወሳኝ ጨዋታ በሳተላይት ስርጭት ለማስተላላፍ ሰሞኑን ከነሙሉ የማሳራጫ መሳሪያዎቻቸው አዲስ አበባ እንደገቡ ፌደሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ የተዘጋጁት ዋልያዎች በሜዳቸው አጀማመራቸውን ማሳመር ይፈልጋሉ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሞሮኮ ወደ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ከሁለት ወራት ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡ በፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ የሚመራው ቡድኑ ዝግጅቱን እንደጀመረ ከሜዳው ውጭ ከአንጎላ ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 1ለ0 ተሸንፎ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ብራዚል በመጓዝ ጠንካራ ዝግጅት ነበረው፡፡ በብራዚል በነበረው ቆይታ ከመደበኛ ልምምዶች ጎን ለጎን በአገሪቱ አራተኛ ዲቭዝዮን ከሚወዳደሩ 5 ክለቦች ጋር  የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ከአናፖሊ ጋር 2ለ2፤ ከክለብ ጋማ ጋር 1ለ1 አቻ ሲለያዩ፤ በክለብ ዶ ሮምዮ እና በሊውዚና በተመሳሳይ 1ለ0 እንዲሁም ብራዚሊኒሴ 2ለ0 ተሸንፏል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ብሄራዊ ቡድኑ ለሁለት ሳምንታት በብራዚል ያደረገው የዝግጅት ቆይታ ጠቀሜታው ያመዘነ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች ሊገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ነጥብ ለመሰብሰብ ዝግጁ ነን ያሉት ዋና አሰልጣኙ፤ ቡድኑ በብራዚል በነበረው ቆይታ በፕሮፌሽናል የግብ ጠባቂ እና የአካል ብቃት አሰልጣኞች በቀን ሁለቴ ልምምዶቹን በተሟላ የስፖርት መሰረተ ልማት መስራቱ እንዳረካቸው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የታመነባቸው እና ከአገር ውጭ የሚጫወቱት የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ  አዲስ አበባ በመግባት ልምምድ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር በብራዚል በነበረው ዝግጅት ባይሳተፉም ፤ በግብፆቹ ክለቦች አልሂላልና አልኢትሃድ አሌክሳንድርያ የሚጫወቱት ሳላዲን ሰኢድ እና  ኡመድ ኡክሪ እንዲሁም በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሸንዲ የሚገኘው አዲስ ህንፃ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለ1 ሳምንት ከቡድኑ ጋር ለመቀናጀት ሰርተዋል፡፡በደቡብ አፍሪካው ቢድቬስት ዊትስ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደም ቡድኑን በመጨረሻ የተቀላቀለ ሌላኛው ወሳኝ ተጨዋች ነው፡፡
የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቹ ሳላዲን፤ ኡመድ እና ጌታነህ ከኢትዮጵያ ውጭ በሚጫወቱባቸው ክለቦች በከፍተኛ ብቃት ላይ መቆየታቸው ለምንፈልገው ውጤት አስደሳች ዜና ነው በማለት ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ባሬቶ በብራዚል በነበሩበት ጊዜ የቡድናቸውን አቅም ለማጠናከር በየትኛውም አገር እና  ክለብ ለሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ጥሪ ሲያቀርቡ ሁሉም ተጨዋቾች ለቀረበላቸው ግብዣ በደስታ ምላሻቸውን ገልፀው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ከቀረበላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጨዋቾች መካከል  በስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን የሚገኘው ዩሱፍ ሳላህ ቡድኑን በመቀላቀል ብቸኛው ነው፡፡ በሌላው የስዊድን ክለብ ኢክ ሲሩስ የሚጫወተው ዋዲል አታ ጥሪውን ቢቀበልም ባለቀ ሰዓት በደረሰበት ጉዳት በብሄራዊ ቡድኑ ለመካተት ሳይሆንለት ቀርቷል፡፡ እንዲሁም በኖርዌይ ሊግ ለሚጫወት ክለብ የሚሰለፈው አሚን አስካር ብሄራዊ ቡድኑን በቀጣይ የማጣርያ ጨዋታዎች ለመቀላቀል ፍላጎቱን እንዳለው ተናግሯል፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ አንደኛ ደረጃ የያዘችው አልጄርያ፤ በፕሮፌሽናሎች ስብስብ ተጠናክራና በዓለም ዋንጫ ልምድ ገዝፋ ትቀርባለች
ጋዜጠኞችን ጨምሮ 70 ያህል ተጨዋቾች አሰልጣኞች ሃኪሞችና የቡድን መሪዎች የሚገኙበት የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡  ፈረንሳዊው የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክርስቲያን ጉርኩፍ  በምድብ 2 ከኢትዮጵያ እና ከማሊ ጋር በአንድ ሳምንት ልዩነት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አጠቃላዩን የማጣርያ ጉዞ የሚወስን አጀማመር እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከሶስት ሳምንት በፊት  ከኢትዮጵያ እና ከማሊ ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚያሰልፏቸውን የ27 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር  አስታውቀዋል፡፡  
የተጨዋቾች ስብስቡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ አልጄርያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥሎ ማለፍ ምእራፍ ያበቋት በብዛት ሲገኙ፤ 23 ያህሉ በተለያዩ አገራት በፕሮፌሽናልነት የሚጫወቱ ናቸው፡፡ በፖርቱጋል፤ ስፔን እና እንግሊዝ ክለቦች የሚሰለፉ ምርጥ ተጨዋቾች የበዙበት የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን እንደኢትዮጵያ አቻው በቂ የዝግጅት ጊዜ አልነበረውም፡፡ በአጠቃላይ ግን ቡድኑ ባለው የተደራጀ ፕሮፌሽናል አቅም እና የዓለም ዋንጫ ልምድ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተጠብቋል፡፡ ከ3 ሳምንታት በፊት አልቤርቶ ኤቦሲ የተባለ ካሜሮናዊ ተጨዋች በስታድዬም ከነበሩ ደጋፊዎች በተወረወረ ቁስ ህይወቱ በማለፉ  የአልጄርያ እግር ኳስ ከማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታገድ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ እንደሌለ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገልጿል፡፡  የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ  በአፍሪካ አንደኛ መሆኑና ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ ወደ ትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች ስኬታማ ዝውውር ያደረጉ ተጨዋቾች በስብስቡ መብዛታቸው የቡድኑን ወቅታዊ ጥንካሬ ያመለክታል፡፡

Read 2494 times