Saturday, 09 August 2014 11:57

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹ውዱ›› ተጨዋች ፤ ዳዊት እስጢፋኖስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን ባልተጠበቀ የአስተዳደር ችግር እየተናጠ ያለው ኢትዮጵያ ቡና በካጋሜ ካፕ አለመሳተፉ ትልቅ ኪሳራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በክፍለ አህጉራዊው የክለቦች ሻምፒዮና  ያልተሳተፈበት ምክንያት ከተፈጠረው ችግር ከተያያዘ የሚያሳዝን ነው፡፡ ካጋሜ ካፕ የክለቡን ብራንድ የሚያሳድግ ውድድር ነበር፡፡ ለሚቀጥለው የፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ዘመን ከፍተኛ መዘጋጂያ ሊሆን የሚችልም ነበር፡፡
የ27 ዓመቱ ዳዊት እስጢፋኖስ በአማካይ ተጨዋችነት ምርጥ ከሚባሉ ዋልያዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ የታላቁ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና አምበል እና ወሳኝ ተጨዋች ሆኖ የሚያገለግለው ዳዊት፤ ከዋልያዎቹ ጋር ወደ ብራዚል የመሄድ እድል አልገጠመውም። በጉዳት ላይ ሲሆን እያገገመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ የሚያቀርበው ዳዊት ዋልያዎቹ ከማርያኖ ባሬቶ ጋር እየሰሩ ያሉት ዝግጅት ከሞላ ጎደል ጥሩ ብሎታል፡፡ በተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ደህና ክፍያ መሰማቱን ደግሞ የስፖርቱ እድገት መገለጫ መሆኑን ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዳዊት እስጢፋኖስን ለቀጣይ 2 ዓመት ኮንትራቱን እንዲያራዝም የከፈለው 1.2 ሚሊዮን ብር ነው ፡፡  በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ አዲስ ሪኮርድ የፊርማ ሂሳብ ተብሏል፡፡  የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች  አይናለም  ሃይሉ ከዓመት በፊት ከደደቢት ክለብ ወደ ዳሸን ቢራን የተቀላቀለበት  1.1 ሚሊዮን ብር ቀድሞ የተመዘገበው ሪከርድ ክፍያ  ነበር፡፡
ከውጭ አገር ክለቦች የባርሴሎና  እና አርሰናል ክለቦችን አደንቃለሁ የሚለው ዳዊት እስጢፋኖስ በእረፍት ጊዜው ከብዙ ጓደኞቹ ጋር ተሰባስቦ በሁሉም ጉዳይ መጫወት ያስደስተኛል ብሏል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፊልሞችን በመከታተል እየተመለከተ ነው፡፡
ዳዊት እስጢፋኖስ ከስፖርት አድማስ ጋር ያደረገው አጭር ቃለምልልስ ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡    
ስለ ኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ሁኔታ
ለማንም ወገንተኛ በመሆን የምናገረው ነገርየለም። እኔም የቡና ነኝ ፤እነሱም የቡና ናቸው፡፡ የሁላችንም ለሆነው ታላቅ ክለብ ብለው በቶሎ ያለባቸውን ልዩነት አጥብበው በቶሎ መስማማታቸውን በጉጉት እጠብቀዋለሁ፡፡
ስለ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድንና ማርያኖ ባሬቶ
 ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በሰራሁባቸው ቀናት የታዘብኩት በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ ነው፡፡ አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶን በሁለት ነገር አደንቃቸዋለሁ። በቡድኑ ተጨዋቾች የአካል ብቃት ላይ በማተኮር መስራታቸው ለውጥ ነበረው፡፡ በሌላ በኩል የወዳጅነት ጨዋታዎችን መተግበር የቻሉ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ አስቀድሞ በነበረው የብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታዎች ብዙም የሚሳኩ አልነበሩም፡፡
በአጠቃላይ በታክቲክ እና በአካል ብቃት የሚሰሩ ስልጠናዎች እድሜያቸው ለገፋ 25 እና ከዚያም በላይ ለሆኑ ተጨዋቾች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለመስራት አድካሚ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ከታዳጊዎች ተነስቶ በመስራት በሁለት እና ሶስት ዓመት ለውጥ የሚታይበት ነው፡፡ ይህ ቡድን በጣም አብሮ የቆየ ነው፡፡ በመሰረታዊ ነገር መጎተት የለበትም፡፡ የወዳጅነት ጨወቃታዎቹን በተመለከተ ግን እሰከዛሬ የማይሳካው አሁን መገኘቱ ጥሩ ርምጃ ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን የወዳጅነት ጨዋታዎቹ በጥናት መደረግአለባቸው፡፡ በገባንበት ፉክክር በሚገጥሙን ቡድኖች አቋም እና የኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ያላቸውን አቅም ተተንተርሶ የወዳጅነት ጨዋታ መዘጋጀት አለበት፡፡ የተጋጣሚ አገር ሜዳ እና የራስ ሜዳ ሁኔታ እና አየር በማጥናት የሚደረግ ዝግጅትን የሚያግዝ የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልጋል፡፡
ስለ ምድብ 2
የምድብ ማጣርያው ላለፈውአፍሪካ ዋንጫ ከነበረው ድልድል ይከብዳል፡፡ በራሳችን አጨዋወት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን እንችላለን፡፡ በተለይ በሜዳችን ለምናደርጋቸው ጨዋታዎች ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ በጠንካራ ብሄራዊ ስሜት በመስራት ውጤታማ ለመሆን የተነሳሳን ይመስለኛል፡፡ በስነልቦና የምናደርገው ዝግጅትም ወሳኝ ይሆናል፡፡
ስለ ተጨዋቾች የዝውውር ገበያ
ከቅርብ ዓመታትወዲህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማደጉ በተለያየ መንገድ ይገለፃል፡፡ አንዱ መገለጫ ደግሞ የተጨዋቾች የዝውውር ገበያው በከፍተኛ ሂሳብ መካሄዱ ነው፡፡ ካለፉት አራትአመታት ወዲህ ተጨዋቾች በብቃታቸው ተፈላጊ ሆነው ከክለብ ወደ ክለብ ለመዘዋወር የሚያገኙት የፊርማ ሂሳብ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ተጨዋቾች በክለባቸው ልምምድሰርተው በግላቸውም ብቃታቸውን ለማሳደግ የሚጥሩበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ 1 ሚሊዮን ብር እየተከፈለ ማንም የሚተኛ የለም፡፡ የስፖርቱ እድገት በኢኮኖሚ በሚኖሩ መሻሻሎች የሚፋጠን ይመስለኛል፡፡


Read 3146 times