Saturday, 02 August 2014 11:40

ያልተዘመረላቸው ምሁር ፕ/ር ፍስሃ ገ/አብ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(22 votes)

         በ1933 ዓ.ም በአምቦ ከተማ ነው የተወለዱት - ፕሮፌሰር ፍስሃ ገ/አብ፡፡ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚታወቁት በአህያ መብት ተከራካሪነታቸውና በስኬታማ የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ባለሙያነታቸው ነው፡፡ በ1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በደብረዘይት የሚገኘውን የእንስሳት ህክምና ፋካልቲ የመሰረቱት ፕሮፌሰሩ፤ በጡረታ ከስራቸው እስኪለቁ ድረስ የፋካልቲው ዲንና መምህር በመሆን አገልግለዋል፡፡
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮከበ ፅባህ ት/ቤት የተከታተሉት ፕ/ር ፍስሃ ገ/አብ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእንስሳት ሳይንስ ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ በትምህርታቸው በመግፋት ፖላንድ ከሚገኘው የግብርና ዩኒቨርሲቲና ከፈረንሳይ አገር በማስተርስ ኦፍ ቬተሪናሪ ሳይንስ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
በእንስሳት ህክምናና በእንስሳት መብት ተከራካሪነታቸው የሚደነቁት ፕ/ር ፍስሃ፤ በስራቸውና ባስመዘገቡት ስኬት ካደነቁዋቸው ተቋማት አንዱ የሆነው የስኮትላንዱ ግላስኮው ዩኒቨርሲቲ 500ኛ አመቱን ሲያከብር የክብር ዶክትሬት የሰጣቸው የመጀመሪያው አፍሪካዊ ምሁር እንደሆኑም ይታወቃል። ፕሮፌሰሩ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለአገራቸው የሰሩ ምሁር ቢሆኑም የስራቸውን ያህል ያልተነገረላቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ስለመሆናቸው የስራ ባልደረቦቻቸውና በእንስሳት ህክምና የላብራቶሪ ቴክኖሎጂ የሆኑት የፕሮፌሰሩ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ ሻረው ይናገራሉ፡፡
ምሁሩ በበርካታ የእንስሳት በሽታዎች ላይ ምርምር በማድረግ ውጤታማ ሲሆኑ ዕውቅ በሆኑ አለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ስራዎቻቸው ታትመው ለንባብ በቅተውላቸዋል፡፡ በተለያዩ የዓለም አገራት በተካሄዱ ከ50 በላይ ስብሰባዎች ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ፤ የመማሪያ መፅሃፍትን በማዘጋጀትና የእንስሳት ጤና እና ደህንነት ላይ በእንግሊዝኛ የተፃፉትን ወደ አማርኛ በመመለስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ፕ/ር ፍስሃ ስለ ህይወታቸው፣ ስለ እንስሳት ህክምና እና ስለ እንስሳት መብት ትልቅ መፅሐፍ ለማዘጋጀት አቅደው የነበረ ሲሆን ድንገት ባደረባቸው ህመም ምኞታቸውን ሳያሳኩ ሐምሌ 19 ቀን 2005 ዓ.ም በተወለዱ በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ፕ/ር ፍሰሃ ገ/አብ ከምርምርና ከእንስሳት መብት ተከራካሪነታቸው በተጨማሪም በደብረዘይት መለስተኛ የእርሻ ኮሌጅ፣ በአለማያ ዩኒቨርስቲ በቅድመና ድህረ ምረቃ፣ ፕሮግራም፣ በህብረተሰብ ጤና፣ በኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ሪሰርች ኢንስቲትዩት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚገኙ የግብርና ቢሮዎች በተካሄዱ የስልጠና ፕሮግራሞች ላይ በአሰልጣኝነት ሰፊ ተሳትፎ እንደነበራቸው ባለፈው ቅዳሜ የአንደኛ ሙት ዓመት በመታሰቢያ ስነ - ስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡ ምሁሩ አሜሪካ በሚገኘው “ተስከጊ” ዩኒቨርስቲ በተጋባዥ መምህርነት ለአንድ አመት የሰሩ ሲሆን፤ በካርቱም ዩኒቨርስቲና በጀርመን ፍሪ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ በርሊን የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎችን በተጋባዥ ፈታኝነት ማገልገላቸው ተገልጿል።
“ስለሰሩት ስራ ብዙ ባይወራላቸውም ፕ/ር ፍሰሃ ለአገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ያሉት የፕ/ሩ ታላቅ ወንድም አቶ ነጋሲ ገ/አብ፤ “ፍሰሃ በሰብዕናውም ሙሉ ሰው የነበረና ለትምህርት ቅድሚያ የሚሰጥ በመሆኑ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል፡፡ እኔ ከወንድምነቱ ጓደኝነቱ ይበልጥብኛል ሲሉ ስለወንድማቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በሙት አመቱ መታሰቢያ እለት የእንስሳት ህክምና ፋኩልቲው በጋዜጠኞች የተጐበኘ ሲሆን፤ በዚሁ ግቢ ውስጥ የእንስሳትን መብትና ደህንነት ለመንከባከብ ከ18 ዓመት በፊት የተቋቋመው “ሶሳይቲ ፎር ዘ ወርኪንግ አኒማልስ ኦፍ ዘ ወርልድ” (Spana) የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅትም ተቋቁሞ፣ በእንስሳት መብት፣ ደህንነትና ጤንነት ላይ እየሰራ ሲሆን አህዮች ነፃ ህክምና ያገኙበታል፣ የእንስሳት አርቢዎችና ባለቤቶች ስለ እንስሳት ደህንነትና እንክብካቤ የግንዛቤ ትምህርት ያገኙበታል ተብሏል፡፡
ፕ/ር ፍስሃ አስተማሪያቸው እንደነበሩና ፈለጋቸውን እንዲከተሉ እንዳደረጓቸው የገለፁት የእንስሳት ህክምናና ግብርና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዲንቃ አያና፤ ፕሮፌሰሩን የሚዘክር መታሰቢያ ለመመስረት ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ “የፕሮፌሰሩን ስራ ሌላው አርአያ አድርጐ እንዲከተል እሳቸውን ለህዝብ የማስተዋወቁ ስራ አለመሰራቱ የእኛ ድክመት ነው” ያሉት የስፓና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ በኋላም ቢሆን ስራቸውን በስፋት ለማስተዋወቅና በተለይም በእንስሳት ደህንነትና ጤና ላይ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለህዝብ እንዲደርስና መማሪያ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በሚተዳደረው የእንስሳት ህክምናና የግብርና ኮሌጅ ውስጥ ለምሁሩ መታሰቢያ የሚሆን ሁነኛ ነገር ለመስራት በመጪው መስከረም ወር ጉባኤ ከተደረገ በኋላ መታሰቢያቸው ምን ይሁን የሚለውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዲንቃ አያና ተናግረዋል፡፡
ፕ/ር ፍስሃ ገ/አብ የታዋቂው አርቲስት ዓለሙ ገ/አብ ታላቅ ወንድም ሲሆኑ ባለትዳርና የሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

ፍቺ የልጆችን የመማር አቅም ያዳክማል - የሥነልቦና ቀውስ ይፈጥርባቸዋል
የወላጆች እልህ መገባባት የልጆችን ህይወት ክፉኛ ይረብሻል 

Read 5742 times