Wednesday, 30 July 2014 07:41

የአወዛጋቢው መጽሐፍ ደራሲ ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(6 votes)

አቶ ሀይለማርያም ወልዱ በቅርቡ “ህልፈተ አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢህአፓ” የሚል መፅሀፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ከመፅሀፉ ጋር በተያያዘ  የኢሕአሠ ቤዝ የነበረውን የኢሮብ ህዝብ አስመልክቶ ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡



ኢህአፓ አለሁ ነው የሚለው፤ አንተ በመጽሐፍህ “ህልፈት አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢሕአፓ” በማለት ሞቷል ትላለህ፡፡
ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ አለሁ የሚለው ወገን መኖሩን ማሳየት መቻል አለበት፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ (ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለሁት) ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአፓ እንደ ድርጅት የለም ፣አመለካከቱ ራዕዩ አለ፡፡ የኢህአፓ ልጆች የታገሉለት ነገሮች በህገመንግስቱ ተረጋግጧል። አተገባበር ላይ “እንዴት ነው” ብትይኝ ሌላ ነገር ነው፡፡ በዚህ አይን ከታየ ኢህአፓ አለ፡፡ ከዚያ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአፓ እንደ ድርጅት የለም። ሜዳው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ዳያስፖራ አለሁ ማለት የትም አያስኬድም፡፡
የበረሃ ስም እስኪለምዱት አይከብድም?
ምንም አይከብድም ግዴታ ነው፡፡ እኔን፤ ብርሃነመስቀል በዛብህ ነህ አለኝ፡፡ ተቀበልኩት። እሱን ክርስቲያን አካባቢ ሰለሞን፤ ሙስሊሞች አካባቢ ሱሌይማን እንለው ነበር፡፡
ከኢህአፓ ሠራዊት ከኢህአሠ የምታደንቀው የጦር መሪ ማን ነበር?
እኔ ጦርነት ላይ የመሳተፍ ዕድል አልነበረኝም፡፡ ሮባ ጥሩ ተዋጊ ነው ሲሉ ግን እሠማለሁ፡፡ ሠራዊቱ የምሁር ሠራዊት ነበር፡፡ ምሁር ሁለት ልብ ነው፤ ለጦርነት ምቹ አይደለም፡፡ እኔም ያው ነበርኩ፡፡
እስቲ ወልዱ ስለ ራስህ ንገረኝ
ትውልዴ ኢሮብ ነው፡፡ የተወለድኩት አሊቴና ነው፡፡  እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማርኩት አዲግራት ነው፡፡ አዲስ አበባ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አመት ተምሬያለሁ፡፡ በደርግ ዘመን ወደ ትግል ገባሁ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የትግል አመታት ጥሩ አልነበሩም፡፡
ለምን የመጀመሪያዎቹ የትግል አመቶች ጥሩ አልነበሩም?
በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ደርግ እጅ ላይ የወደቅሁት፡፡ የድርጅቴን ስም አጋልጦ ላለመስጠት ራሴን ጀብሀ ነኝ አልኩ፡፡  የታሠርኩት አስመራ ውስጥ ስንበል የሚባል ቦታ ነበር፡፡ የተለመደው የደርግ ምርመራ ከተደረገብኝ በኋላ፣ ጉዳዬ ወደ ጦር ፍርድ ቤት ተላለፈ፡፡ በጦር  ፍርድ ቤት በመታየት ላይ እያለ  ወህኒ ቤት ሆኜ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ።
ምን ጥሩ ነገር አገኙ?
በአጋጣሚ ከአዲስ አበባ የወህኒ ቤት አስተዳዳሪዎች ወደዚያ ሲመጡ የጠየቅሁት የመብት ጥያቄ (ት/ቤትና ላይብረሪ እንዲከፈት) ምላሽ በማግኘቱ፣ በእስረኞቹ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኝ አደረገኝ፡፡ ለእኔ የመጀመሪያ ሹመት ማለት ይቻላል። የእስረኞቹ ፀሐፊ ሆንኩ፡፡ ቋንቋ ተማርኩ፣ ብዙ መፃሕፍት አነበብኩ፡፡
ከመታሰሬ በፊት የነበረኝ የማርክሲዝም ዕውቀት ውሱን ነበር፡፡ ከታሠርኩ በኋላ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም፣ ማኦይዝም ከዚያም አልፎ ስለ ፎኮይዝም፤ በደንብ በማንበቤ የቲዮሪ ትጥቅ አገኘሁ፡፡  ስለ ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅት አሠራር በተግባር የተማርኩትም ወህኒ ቤት ነው፡፡ ከሁሉም ጋር በነበረኝ ግንኙነት የህዝባዊ ግንባር አይን ውስጥ ገባሁ፡፡ በተማርኩት መሠረትም የቤት ስራ ተሰጥቶኝ በብቃት ተወጥቻለሁ፡፡
የቤት ስራው ምን ነበር?
እስረኞችን ማስፈታት ነበር፡፡ ይሄን ያደረግሁት ከተራ ወታደር እስከ ሃላፊዎች ድረስ በድርጅት እንዲታቀፉ በማድረግ ነው፡፡ ኤርትራዊያኑን በኤርትራ ድርጅት ኢትዮጵያውያኑን በኢትዮጵያ ድርጅት፣ እንዲደራጁ በህዋስ ማዋቀር ነበር፡፡
ማን ነበር የመለመለህ?
አንዲት አዜብ የምትባል ልጅ ናት፡፡ አዲስ አበባ እንደምታውቀኝ ነግራኝ የመለመለችኝ፡፡ በኋላ ላይ ግን እሷን ያሠማራት ሰው አስመራ ውስጥ የታወቀ (ከ1966 እስከ 1983 ድረስ የፌዳይን መሪ የነበረ) ልጅ መሆኑን አወቅሁኝ፡፡ የበረሃ ስሙ ቫይናክ ይባላል፡፡
ቫይናክ በቅርብ በመኪና አደጋ ከሞቱት የኤርትራ ጀነራሎች አንዱ ነው አይደል?  ቫይናክ የተባለው ለምንድን ነው?
አዎ በቅርቡ ነው የሞተው፡፡ ቫይናክ ማለት የመድሃኒት ስም ነው፡፡ የራስ ምታት መድሃኒቶች ካፌኖል፣ ቫይናክ፣ አስፕሪን ናቸው፡፡ ቫይናክ እንግዲህ “አስቸጋሪውን የሚያስታግስ” ለማለት የወጣ ይመስለኛል፡፡
ኢሮብ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ሠራዊት (የኢህአፓ ወታደራዊ ክንፍ) ይንቀሳቀስበት የነበረ ቦታ ነው፡፡ እስቲ ስለአካባቢውና ስለህዝቡ ንገረኝ…
ስለ ህዝቡ ማንነት የተለያዩ አፈታሪኮች አሉ። በአብዛኛው ተቀባይነት ያገኘው፣ አሁን ያለው የኢሮብ ህዝብ ከደጋ አካባቢ  ከውቅሮ በስደት መጥቶ ነው የሚለው ነው፡፡  በኔ እይታ ግን  እዚያ የቆየ ነው የሚሉትን እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም ቋንቋው ከኩሽ ቋንቋዎች የሚመደበው ሳሆ ነው፡፡ ይህ ቋንቋ ከአፋርኛ ጋር ከቀበሌኛ ልዩነት በስተቀር ይግባባል። በምስራቋ አፍሪካ የህዝቦች እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ ግን የሚንቀሳቀሰው ወገን እምነቱንም ሆነ ቋንቋውን አይለቅም፡፡ እኔ ራሴን እንደሳሆ ነው የምቆጥረው፡፡ በሀይማኖት እስከ አስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሶስት ቤተክርስትያኖች ነበሩ፣ ህዝቡም ክርስትናን ተቀብሎ ነበር ይባላል፡፡ ነገር ግን የባህላዊ እምነት ተከታዮች ነበሩ፡፡ በየቦታው መስዋዕት የሚያደርጉባቸው ቦታዎች ነበሩ፡፡ ዝናብ ከጠፋ ላም ወይም  በሬ ስጋውን ትልቅ አምራ መጥቶ ሲወስደው መንፈስ ወሰደው ይህን የሚያሳይ እስከአሁን አሁንም ድረስ ህብረተሰቡ በዘፈኑ ላይ የሚያስገባው ሀረግ አለ፡፡ “አኸዬ ጉማይቶ” (“አሞራው ናና ውሰደው” ማለት ነው፡፡) ከዚያ ዝናብ ይመጣልናል ብለውም ያምናሉ፡፡
ቤተክርስቲያኖች አሉ ይባል እንጂ ቄሶች የሚመጡት ከጉንደጉንደ ነበር፡፡ ጉንዳጉንዲ ደቀ እስጢፋኖስ በመባል በሚታወቅ በ13ኛውና 14ኛው ክፍለዘመን አካባቢ በስራዬ የተጀመረ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ መነኮሳቶች የነበሩበት ነው፡፡ እንቅስቃሴው በመሪዎች ተወገዘና ተከታዮቹ ተገደሉ፡፡ ከሠራዬ ታቦታቸውን ይዘው ወደ ሽሬ መጡ፣ ወደ ጐንደር ሄዱ፤ ከዚያ ወደ ጐጃም፣ ወደ ሰሜን ሸዋ መጡ፡፡ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ላይ እንዲቃጠሉ ተደረጉ፡፡
ከዚያ ያመለጡት በወሎ አድርገው ትግራይ ገብተው ያረፉት ጉንደጉንደ ላይ ነው፡፡ ከደጋ ወደ ኢሮብ ተሰደደ የሚባለው ህዝብ ከዚህ ታቦት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢሮብ የሚለው ቃልም ከዚያ ጋር ይያዛል፡፡
እንዴት?
ቆላ ላይ አንድ እንግዳ ሲመጣ “እንደምን ዋላችሁ” ወይ “አመሻችሁ” ካለ፣ አባወራው አይወጣም። እዛው ሆኖ ግቡ ነው የሚለው፡፡ በሳሆ ኦሮባ ይባላል፡፡ ግቡ ማለት ነው፡፡ እኔ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ታቦት ይዘው የመጡት ጉንዳጉንዳ እንደደረሱ ሰዎች ያገኙና “እዚህ ቤት” ሲሉ ኢሮባ አሏቸው፡፡ ለቀሩት ተከታዮቻቸው በፃፉት ደብዳቤ፤ “እኛን የተቀበሉን ህዝቦች አግኝተናል፤ ህዝቡም ኢሮብ ይባላል” ብለው ፃፉ የሚል ነው፡፡
ኢሕአሠን  እንዴት ነው የኢሮብ ህዝብ  ኦሮባ ያለው?
አንደኛው ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ የሆነው ተስፋዬ ደበሳይ የአካባቢው ተወላጅ ነው፡፡ ተስፋዬን    ጨምሮ ብዙ የአካባቢው ተወላጆች አውሮፓ በተለይ ቫቲካን ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ከኢሮብ ጐሳዎች አንዱ የሆነው ቡክናይተአረ የሚባለው  የካቶሊክ እምነት ተከታይ ስለሆነ የትምህርት እድል ይሰጣቸው ነበር።
የኢሕአሠን ትግል  ጐጃም  ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሱዳን በዚያን ወቅት አስተማማኝ ሀይል አልነበረም፡፡ ባሌም ታስቦ ነበር፡፡ ሶማሌያም አስተማማኝ አልነበረም፡፡ ሌላው ደግሞ አወሮፓ የነበሩ የኢሮብ ተወላጆች የተወሰኑት የኢህአፓ አባል ስለነበሩ ከህዝቡ ተቀባይነት ማግኘት ከባድ አይሆንም በሚል ይመስላል፡፡ ቦታው ለቀይ ባህርም ቅርብ ነው፡፡ አዱሊስ ቅርብ ነው፡፡ አሲምባ ተራራ ጫፍ ላይ የየመን ዋና ከተማ ትታያለች፡፡ ስንቅ ለማጓጓዝም አመቺነቱን በማየት፣ ጂኦግራፊውም ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ስለሆነ ነው፡፡  
ህዝቡስ?
የኢሮብ ህዝብ አንድን ነገር ቶሎ አይቀበልም። ከተቀበለ ደግሞ ጽኑ ነው፡፡ እንዲቀበል ደግሞ የራሱን ሰው ይፈልጋል፡፡
የኢሮብ ህዝብ ዛሬ ላይ የኢሕአሠን ሠራዊት እንዴት ያስታውሰዋል?
የልጆቻችን ወንድሞች እና ጓደኞች እንደሆናችሁ ሰምተናል፡፡ እንደ ልጆቻችን እንቀበላችኋለን፡፡ ግን ከድታችሁን ለጠላት አጋልጣችሁን እንዳትሄዱ” ነበር ያሏቸው፡፡ አሁን ህዝቡን እንዴት ያዩታል ላልሽኝ፤ ኢሕአሠን በደንብ ነበር የተቀበሉት፡፡ ወደኋላ ግን በኔ እይታ  በጣም አዝነውበት ነበር፡፡
ለምን
ካዘኑባቸው ምክንያቶችም አንዱ፣ አንጃ ተብለው በተገደሉ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ አንጃ በሚል ተይዘው የነበሩትን ሰዎች አስመልክቶ የኢሮብ ህዝብ ሽማግሌ ልኳል፡፡ እነዚህን ልጆች እንዳትገድሉ ብሏል፡፡ በወቅቱ የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው ዘርዑ ክህሸንም አይገደሉም ብሎ ቃል ገብቶላቸው ነበር። ግን ተገደሉ፡፡ ጨካኞች ናቸው አሉ፡፡ ሌላው ባልጠበቁት ሁኔታ ሲሸነፍ አዩት፡፡ ሀይል ነበረው ፣መሳሪያ ነበረው፡፡ ሠራዊት ነበረው ግን ተሸነፈ። አላማውን ሲያነሱ ግን እስከአሁን “ያ ሠራዊት” ይላሉ፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጣ በመሆኑ ልዩ ነው፡፡ ስሜቱ የተዘበራረቀ ነው፡፡
መጽሐፍህ ላይ “ገበሬ የሀይል ሚዛን ወደሄደበት ፊቱን ያዞራል” ብለሀል፡፡ የኢሮብ ህዝብን ከዚህ አባባል ጋር በማገናኘት  አስረዳኝ?…
ይህ በሁሉም ገበሬ የሚታይ ነው፡፡  ኢሮብ አንደኛ ገበሬ አልነበረም፡፡ አርብቶ አደር ነበር። የጐሳ ትስስር ነው የነበረው፡፡ የኔ ወገን የሆነው ለኔ ሲል ለኔ ያደላል፤ ወደኋላ ግን ትክክለኛ የገበሬ ጥቅመኝነት አይቼበታለሁ፡፡ ሠራዊቱ አካባቢውን ለቆ ከወጣ በኋላ እኔ እዚያ ቆይቻለሁ፡፡ አጋፍጠው ሊሰጡኝ ባይፈልጉም ስጋት ግን አለባቸው፡፡ ብሄድላቸው ደስታቸው ነው፡፡ የገዛ ዘመዶቼ ከዚያ አካባቢ ብጠፋላቸው ደስ ይላቸው እንደነበር አውቃለሁ፡፡
ስለአባትህ ንገረኝ…
አባቴ በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ከወሰዱት ውስጥ ነው፡፡
አባትህ ሽፍታ ነበሩ ይባላል ዕውነት ነው?
አዎን
የአካባቢው ዳኛም፣ አስተዳዳሪም፣ ፖሊስም ሁሉንም ነው፡፡ አባቴ በአካባቢው ተወዳጅ ነበር፡፡ በለቅሶም ሆነ በሠርግ ስሙ ይነሳል፡፡ ተስፋዬ ደበሳይ በእረፍት ጊዜው የሚውለው ከአባቴ ጋር ነበር፡፡ ብዙ የህግ እውቀት ከአባቴ እንዳገኘ ነግሮኛል፡፡ የትግል ሜዳ ላይ ከብርሃነመስቀል ጋር ሲያስተዋውቀኝ፣ አባቱ በህይወት ቢኖሩ ከኛ ጋር ይሠለፉ ነበር ብሎታል፡፡
በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ለኤርትራ እንዲሰጡ የተወሰኑ የኢሮብ አካባቢዎችን አንተ እንዴት ነው የምታያቸው?
አባቴ በሀላፊነት ላይ በነበረ ጊዜ ትልቁ ራስምታቱ እሱ ነበር፡፡ በተለይ አይጋ የውጥረት ቦታ ነው፡፡ በደንብ ሳይካለል የቀረ ቦታ ነው፡፡
ኢሮብ በትግራይ በኩልና ኢሮብ በኤርትራ መሠረታቸው አንድ ነው?
አዎ አንድ ነው፡፡ የሶስት ወንድማማቾች ልጆች ናቸው፣ ኢሮቦች፡፡ ሀሳበላ፣ ቡክናይተአረ  እና ጋዳ ይባላሉ፡፡ ጋዳ በሰሜን በኩል ነው ወደ ኤርትራ የሚጠጋው፤ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ናቸው። የነሱ ግንኙነት ከኤርትራ ጋር ነው - በጣም ተቀላቅለዋል፡፡ ቋንቋው ትግርኛ እና ሳሆ ነው፡፡ መሀል ያለው ቡክናይታ ካቶሊክ ነው፤ ከነሱ  ወደ ሰሜን ስትሄጂ መነኩሲቶ የሚባል የኤርትራ ቦታ አ። እነሱም ካቶሊኮች ናቸው፡፡ የጋብቻ ግንኙነታቸው ከካቶሊኮቹ ጋር ነው፡፡ ብቻውን የሚቀረው ሃሰበላ ነው፤ ከአጋመ ጋር ይዋሰናል፤ ኦርቶዶክስ ነው፡፡ በዘር የተሳሰሩ ናቸው፤ በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት፤ ብክናይተአረና ጋዳ ለኤርትራ  ተወስነው ሀሰበላ ነው ለኢትዮጵያ የቀረው፡፡ ቦታዎቹን ሳውቃቸው በኢትዮጵያ ግዛት ስር የነበሩ ናቸው፡፡
የታሪክ ተማሪ ነህ ድንበር ማስመር ላይ ስህተት እንዳለ ነግረኸኛል፡፡ እሰቲ ስለእሱ አብራልኝ …  
ከአድዋ ጦርነት በኋላ በማካለል ላይ የተደረገ ስህተት ነው፡፡ መረብ፣ በላሳ፣ ሙና የሚለው ነው። በካርታው ላይና መሬት ወርዶ ያለው ላይ ማለት ነው፡፡ በጣሊያን ጊዜ ራሱ ቦታው የአርበኞች ቦታ ነበር፡፡ ከኤርትራም ሆነ ከትግራይ በኩል ጣሊያንን የተዋጉ አርበኞች የተሸሸጉት ኢሮብ ነው፡፡ ኢሮብ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳህ ምንድንነው?
መጽሐፉን ለመፃፍ ካሰብኩ ቆይቻለሁ፡፡ ግን የጽሑፍ ችሎታ የለኝም፡፡ ብዙ መፃሕፍቶች እየወጡ ነው፤ አንብቤያለሁ፡፡ አንድ ሳይነኩዋት የሚያልፉዋት ቦታ አለ፤ ሁሌም ይከነክነኛል፡፡ ይህ ድርጅት በአንድ ወቅት በጣም ገንኖ የወጣ፣ ተቀባይነት ያገኘ ነበር፡፡ የተቀጨው ግን በአጭሩ ነው፡፡  
ለውድቀቱ መፍጠን አስተዋጽኦ ያደረጉት ምንድን ናቸው? ውስጣዊ ችግሩ ወይስ ውጫዊው? የሚለውን ለማሳየት በክፍፍሉ ላይ አተኮርኩ፡፡ የተወሰኑ ዶክመንቶች፣ ግለሰቦችና የራሴን ተመክሮ አካትቼ አስቀመጥኩ፡፡ የቀረውን ሌላው ሊሞላው ይችላል ብዬ ነው፡፡
መጽሐፉ ከዚህ በፊት በሌሎች መፃሕፍቶች ወይም ሰነዶች ላይ ያሉ መረጃዎችን ነው የገለበጠው የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡
አዎ ትክክል ነው፡፡ የማውቃቸውም ያነበብኳቸውም  የማምንባቸውም ስለሆኑ ነው የተጠቀምኩባቸው፡፡
ከኢሕአሠ ሸፍተህ ነበር፡፡ ከደርግም ሸፍተሃል ይሄ ነገር እንዴት ነው?
አዎ ሸፈትኩ ድርጅትህን ከድተህ መሳሪያ ይዘህ መጥፋት ከባድ ወንጀል ነበር፡፡ እኔ እርምጃ አልተወሰደብኝም፡፡ የሸፈትኩት እስር ቤት አያለሁ ለሠራዊቱ የነበረኝ ግምትና ስሄድ ያገኘሁት  በጣም የተለያየ ስለነበረ ነው፡፡ መጽሐፌ ላይ የአሊቴናን ካርታ ያስገባሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡
አሊቴና በጣም ስትራቴጂክ ናት፣ ሁለት በር አላት፡፡ ያንን ጥሶ የህወሓት ሠራዊት ሲገባ ኢሕአሠ እንዳለቀለት ገባኝ፡፡ ከዛ ደግሞ ማጋለጥ ውስጥ ተገባ፡፡ ተጠርቼ ነበር አልሄድኩም፡፡ ሠራዊት ሆኖ መቀጠል አይችልም፡፡ ለውጥ ያስፈልገዋል ብዬ አሰብኩ፡፡ እና መጀመር አለብኝ ብዬ ከጓደኛዬ ጋር ተመካከርኩና እንገንጠል አልን፡፡ ለውጥ እናድርግ ወይ ለውጥ አድርገው ይቀላቅሉን አልን፡፡ ጓደኛዬ የትጥቅ እና ስንቅ ሃላፊ ነበረ፡፡ የተቀበሩ መሳሪያዎች ያሉበትን ቦታ ያውቃል፤ ችግር እንደማይገጥመን ደምደመን፤ ሄድን፡፡ ከዚያ ብዙ ሽማግሌዎች ተላኩብን በኋላ ግን ሃሳቤን የሚያስቀይር ሚስጥር አገኘንና ለመመለስ ወሰንኩ ፡፡ ህወሓት ለጦርነት እንደተዘጋጀ ሰማን፡፡ በዛ ሰአት ጥሎ መሄድ ስላልታየኝ ተመለስኩና ያገኘሁትን መረጃ ሰጠሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል ያልታሠርኩት፡፡
የመጨረሻዎቹ የኢሕአሠ ቀኖች  በትግል ሜዳ ላይ ምን ይመስሉ ነበር?
በጣም አስቀያሚ፡፡  ጦርነት እየገፋ መጣና ኢሮብ አካባቢ ደረሰ፡፡ ለመውጣት በኤርትራ በኩል  መንገድ መከፈት ነበረበት፡፡  ጀብሀ፤ አይሀ በምትባል ቦታ ብቻ ነው ማለፍ የሚቻለው ብሎ ቢስማማም  አንድ ጋንታ በሌላ መንገድ ለመግባት ስትሞክር ትያዛለች፡፡ ስንደርስ ትጥቅ አስፈትተዋቸው አናስገባም ይሉናል፡፡ ከዚያ መሳሪያቸውን ተረክበን ከሚሊሺያዎቹ ጋር አንድ ኮረብታ ላይ ቁጭ ብለን ሸመዛና በሚባል ሜዳማ ቦታ ላይ የኛ ሠራዊት ይተማል (ለቅሶ)፡፡
አንተ እዚያ ቀረህ?
ለአንድ አመት ኢሮብ ቆየሁ፡፡ መቆየቴ ጥሩ ነበር። ደርግ አዲስ አበባ ውስጥ ያደርግ የነበረውን ሰቆቃ ለማምለጥ የሚመጡትን እየተቀበልን እናሳልፍ ነበር፡፡ ማህተም ያለው ሰነድ እጃችን ላይ ነበር፡፡
በኋላስ አንተ ምን ሆንክ?
እዚ መቆየት ከባድ ነበር፡፡ የቀረሁት ከገበሬዎች ጋር ነው፡፡ ቀድሞ ያነሳነው የገበሬ ባህርይ እየገፋ ሲመጣ፣ መቆየት የሚፈልጉት እዚያው ቀሩ፡፡ ህወሓትን የሚቀላቀሉ፡፡ ተቀላቀሉ እኔ አዲስ አበባ ት/ቤት ገባሁ፡፡
ቀጣዮቹ አመታትስ?
አስተማሪ  ነው የምትሆነው፣ ተብዬ ጐጃም ተመደብኩ፡፡ ጐጃም ሳለሁ እስከ 1983 ድረስ ስለነበሩት ጓዶች እንዴት እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡
እንዴት ነበሩ?
ቻግኒ  እና ዳንግላ እነሱን ለመፈለግ ሄጃለሁ።  ግን እኔ የማውቀው የኢሕአሠን አይነት ሆኖ አላየሁትም፡፡ በሽፍትነት ደረጃ እንደነበሩ ነው የሰማሁት፡፡
ከዚያስ
ወደ መጨረሻ አካባቢ (ከሁለት አመት በኋላ) የኢህድን ወሬ እሠማ ስለነበር “እነሱ ይሆኑ እንዴ እውነተኞቹ ኢህአፓዎች?” በሚል ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ 79 እና 80 አካባቢ ከማን ጋር እንደሆነ በትክክል ባላውቅም (ኢህዴን፣ ህወሓት፣ ሻዕቢያ) አዲስ አበባ ውስጥ በትክክል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ነበርኩ፡፡
ደርግ እንዲወድቅ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉት ከማናቸውም ጋር በህቡዕ እሠራ ነበር፡፡ ደርግ ሲወድቅ ቀጥታ ያገኘኋቸው ኢህዴኖችን ነው፡፡ ፎረም 84 የሚመራው በነሱ ነበር፡፡  ከአመራሮቹ አንዱ ሆንኩ፡፡ እራሴን እንደ ኢህዴን ቆጠርኩ፡፡ የክልል 14 ፀሐፊ ነበርኩ፡፡
ኢህዴንን ለምን መረጥክ?
አንደኛ ከኢሕአሠ የማውቃቸው ስለነበሩ፡፡ ሲሆን ቀጥሎ ህብረ - ብሔራዊ ስለነበር ነው፡፡
ለምን ከሃላፊነትህ ለቀቅህ?
ኢህዴን ወደ ብአዴን ሲቀየር ወደ የብሔር ድርጅት የሚል ነገር  ሲመጣ ስላልተስማማኝ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ያነበብኳቸው መፃሕፍቶች በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ ያሳደሩብኝ ተጽእኖዎች ሊያስቀጥለኝ ስላልቻለ! አልቻለም፡፡ በ1989 ዓ.ም በፈቃዴ ለቀቅኩ፡፡

Read 4269 times