Saturday, 19 July 2014 12:41

የጋሽ መስፍን ናፍቆት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

እንዲህ ተጫጭሰን
እንዲህ ተጨናብሰን
ውሃ እንዳለዘዘን
ከውሃ ተዋግተን ተዋግተን…ተዋግተን
ውሃን አሸንፈን፤
እሳትን ፀንሰን
እሳትን አምጠን…አምጠን …አምጠን
እሳትንም ወልደን፤
እሳትንም ሁነን፤
ካጮለጮልንለት የድሃውን ጐጆ፣ ቀሣ ከል ጭራሮ
ካበስልንለት ዘንድ፣ የአርሶ አደሩን ንፍሮ
የሰርቶ አደሩን ሕዝብ፣ ለስሰስ ያለ ሽሮ፣
ታሪክ ይዘምረው የኛን እንጉርጉሮ፡፡
ዘመን ይመስክረው፣ የኛን ውጣውረድ
    የእንግልት ኑሮ፡፡
ደበበ ሰይፉ “የክረምት ማገዶች”
ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሀብተማርያም በሀገራችን ሥነ - ጽሑፍ ደማቅ ታሪክ ያለው፣ በተለይም በወግ ጽሁፎቹ የሚታወቅና በርካታ መጽሐፍትን ለሕዝብ ያቀረበ ሰው ነው፡፡ ልቡ ወደ ደሳሳ ጐጆዎች፣ ሃሳቡ ወደምስኪኖች ድንኳን ገብቶ፣ የየዕለት እንጀራውንና ኑሮውን፣ አንብቦ ጽፎልናል፡፡ ዓውደ ዓመትና አዘቦቱን፣ ክብሩንና ውርደቱን አሳይቶናል፡፡ የሚያሳዝነውን ሕይወት፣ የትራጀዲውን ሥዕል ቀለም ነክሮ እያሳቀና እያስደመመ ጠቢብነቱን አስመስክሯል፡፡ ጋሽ መስፍን የዩኒቨርሲቲም መምህር ነበር፡፡ ለዚያውም ጐበዝ መምህር! ብቻ አንዳንዴ ክፍል መግባቱ አይሆንለትም ነበር! ግና ተማሪዎቹ ሲናገሩ” አንዴ የገባ ቀን ግን አፍርጦ ያስተምራል፡፡ ጨምቆ ያቀብላል” ይላሉ፡፡ ይህንን ነገር ጋሽ መስፍንም ያውቃል፡፡ “ለምን ነበር የምትቀረው?” ስትሉት ይነግራችኋል፡፡ ግንባሩን ሸብሸብ አድርጐ፣ አይኑን በትኩረት በናንተ ላይ ተክሎ፡፡ ምክንያቶቹ ሁሉ አሳማኝ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ የሕይወቱ መንገዶችም አሳዛኝ ናቸው፡፡
በተለይ ያለፉትን ዘመናት መጽሔቶች፣ በተለይ “የካቲት”ን ስታገላብጡ፣ የሠራቸውን ሂሶች አድናቆት ይፈጥሩባችኋል፡፡ ጋሽ መስፍን ደፋር ነው፤ በተለይ በትርጉም ሥራዎች ላይ የሠራቸው ሂሶች ግሩም ነበሩ፡፡ ስለ ፈሊጣዊ አነጋገር ብቁ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ተርጉመው ያስነበቡንን ገላልጦ ሲያሳይ አጀብ ያሰኛል፡፡
በተለይ ደግሞ ሲያወራ እንዴት እንደሚመስጥ የቀረባችሁት ሰዎች ታውቁታላችሁ፡፡ ስለ ድሮ አራዶች፣ ስለ ሰካራሞች፣ ስለ ጥላሁን ገሰሰ፣ ስለ ወጣትነት ፍቅር… ብዙ ብዙ ነገር ያወራል፡፡
ከሁሉ የሚገርመው ግን ያ አይደለም፣ ያ በተቀላጠፈ ንግግር በአራዳ አይኖችና ከናፍርት የሚያስደንቃችሁ ጋሽ መስፍን ድንገት የሚያሳዝን ነገር ሲገጥመው፣ ያ ወደ ውስጥ የራቀው አንጀቱ ይንሰፈሰፋል፡፡ “አፈር ልብላ!” ይላል፡፡ የጋሽ መስፍን ርህራሄና ደግነት ልክ የለውም፡፡ ልዩ ሰው ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ሰዎች በአፀደ ሥጋ ሲለዩን ደግ ያልሆኑትን ደግ፣ ቸር ያልሆኑትን ቸር ማለት የተለመደ ነው፡፡ እኔ ግን ይህንን ልማድና ስርዓት አልቀበለውም፡፡ ክፋትን ደግነት ነው ብሎ መናገር በራሱ ለሕሊና ወንጀል ነው፡፡ ለነፍስ መራራ ነው። ይሁንና ክፉ የምንለው ሰው እንኳ ጥቂት ደግ ነገር አያጣውም፡፡ ምናልባትም ባይሞት በአንድ ነገር ሊጠቅመን ይችላል ብለን በቅንነት ልናስብ እንችላለን፡፡ ጋሽ መስፍን ግን - ከልቡ ቅንና የሚራራም ሰው ነበር፡፡  
ከረጅም ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምር ሳለ አንድ ቮልስ ዋገን መኪና ነበረችው። እና ያቺን መኪና ከግቢ ውጭ ራቅ አድርጐ ያቆማል፤ እንደዚያ የሚያደርገው ደግሞ መኪናዋ የኋላ ማርሽዋ ስለማይሰራ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን “መስፍን ነው ሰው ማለት፤ መኪናዬን እዩልኝ ብሎ ፊት ለፊት አይገትርም፣” ብለው ያደንቁታል፡፡ ጋሽ መስፍን ይህንን ያወራልኝ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በነበረውና ሁልጊዜ ተቀምጦ (በተለይ ከሰዓት) በሚያሳልፍበት የጓደኛው ሆቴል ውስጥ እየሣቀ ነበር፡፡
ጋሽ መስፍን “የአፍሪካ ፀሐይ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ፣ እኔ መጣጥፍ አቅራቢ ሆኜ ጽጌረዳ ሃይሉና ሶስና አሸናፊ (ጋዜጠኞች) በኋላ ደግሞ ጋዜጠኛ ገዛኸኝ መኮንን በየዕለቱ እንገናኝ ነበር፡፡ ምናልባትም ያኔ ባይሰንፍ ኖሮ የሕይወት ታሪኩን ለሕዝብ የምናቀርብበት ጊዜ ከዛሬ በቀደመ ነበር፡፡ ግን “ቆይ’ስቲ” ይላል። እዚያ ሠፈር ቤተኛ እስክሆን፣ ወዳጆቹን ሁሉ እስክግባባ ድረስ ተዛምደን ነበር፡፡ በኋላ ግን እኔ ድሬደዋና ናዝሬት ለሥራ የሄድኩባቸው ዓመታት ለመራራቃችን በር ከፈቱ፡፡ አሁን ሳስበው “እንኳን ተራራቅን” እላለሁ፡፡ በያኔው መንፈስና ቅርበት ብሆን ኖሮ ሀዘኑን እንዴት እችለው ነበር?
ጋሽ መስፍን ነገሮቹ ያሳዝናሉ፣ ያስቃሉ፡፡ እንደብዙዎቹ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ነፍሱ ቅብጥብጥ ናት፡፡ ጥርሳቸውን ነክሰው ለንግድ የሚጽፉትን ነጋዴዎች ማለቴ አይደለም፤ ውስጣቸው እየነደደ የሚያበሩትን እሣቶች እንጂ!
ከጥቂት አመታት በፊት በፓትርያሪኩ ቢሮ ለሥራ ተቀጥሮ በነበረ ጊዜ የተሰማው መንታ ስሜት ሳስበው ይደንቀኛል፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ክፍያ፣ ለቀጣዩ ዘመንም ጥሩ ዕድል ከፊቱ ሲደቀን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት የሚፈልገው ሥነ ምግባራዊ ጥንቃቄ አስጨንቆት ነበር፡፡ እዚያ ቢሮ ከገባ በኋላ ከአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ካለው ዩኒቨርሳል መጽሐፍ መደብር ጐን ካለው በርገር ቤት በር ላይ ተገናኘን፡፡ እንደሌላው ቀን ዘና ብዬ ሠላም ልለው ስል - እጄን ይዞ እንዳሞራ አስገባኝ፡፡ በሲጋራ ጥም ተንገብግቧል፡፡
“ተሰቃየሁ!” አለኝ ግንባሩን ሸብሽቦ፡፡ “ከነጋ ገና ሁለተኛ ላጤስ ነው፡፡ መውጫ የለም፤ ይገርምሃል… ሰውየው ግን ውጭ ሀገር ሁሉ ለሥራ ሊልኩኝ ያስባሉ፤ ከተወሰኑ ወራት በኋላም ለራሴ መኪና ይሰጠኛል፡፡ ግን ከበደኝ፡፡” ብሎ በራሱ ተማረረ፤ አዘነ፡፡ ጋሽ መስፍን ገርነቱ ያሳዝናል፤ እውነተኝነቱ ይገርማል፡፡ ቀርበው ያዩት ሁሉ ጋሽ መስፍንን ከቸልተኝነቱ በስተቀር በምንም ሊከስሱት አይችሉም፡፡ ጋሽ መስፍን ሰው ያከብራል፣ ሰው እንዲያከብረውም ይፈልጋል፡፡ የሰው መብት አይነካም፤ እንዲነኩበትም አይፈቅድም፡፡ ገንዘብ እንዲኖረው ይፈልጋል፣ ባይኖረውም ግን ነፃነቱን አይሸጥም ሲበሣጭ ቀበቶውን በሁለት እጆቹ ከፍ ከፍ እያደረገ ይንቆራጠጣል፡፡ ጋሽ መስፍን ደግ ነው፤ ለሰዎች መልካም ማድረግ ይወዳል፡፡ “ብልጥ ጀንበር” የሚለውን መጽሐፌን ሳሳትም የፍቅር ደብዳቤዎችን ማካተት በሀሳቤም አልነበረም፡፡ ጋሽ መስፍን ነው “አንጀት ይበላሉ” ብሎ አብረህ አሣትመው ያለኝና የጀርባ አስተያየት የፃፈልኝ፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ ቸልተኛ ነው ብዬ የምጠረጥረው ጋሽ መስፍን አዲስ አድማስ ላይ የምጽፋቸውን መጣጥፎች እያነበበ፤ በግንባርና በስልክ አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡ ከዚያም ባለፈ ስለ እኔ ጥሩ ምስክርነት በመስጠት በትርፍ ጊዜዬ በአንድ ጋዜጣ ላይ በአርትኦት ሥራ እንድቀጠር በማድረግ ተጨማሪ ገቢና ሥራ እንዳገኝ አግዞኛል፡፡
ከዚህም ባለፈ የሕይወት ታሪኩን ብዙ አጫውቶኛል፡፡ ግና ሰው ተፈጥሮ ማለፉ አይቀሬ ነውና ጋሽ መስፍን ታምሞ ሳልጠይቀው በማለፉ ከልብ አዝኛለሁ፡፡ የጋሽ መስፍንን ሕልፈት የነገረኝ ገጣሚው ወዳጄ ታገል ሰይፉ ነው፡፡ ታገል ከጋሽ መስፍን ሞት ቀደም ባለው ሣምንት መታመሙን ሲነግረኝ፤ በዚህ ሣምንት ሄደን እንድንጠይቀው አደራ ብዬው ነበር፡፡ ግን ክፍለሀገር ደርሼ ስመለስ ጋሽ መስፍን በሞት መለየቱን አረዳኝ፡፡
ከታገል ሰይፉ የምወድለትን አንድ ባህሪ ያስታወስኩት ይሄኔ ነው፡፡ ታገል ሰው ሲሞት እምብዛም አያለቅስም፡፡ ሰው ሲታመም ግን ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡ የሚችለውን ነገር ሁሉ ያደርግለታል። ከዚያ በኋላ “በቃ ሆነ” ይላል፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ሰውን መጠየቅ በሕይወት ሳለ ነው፡፡
ያ - ቀልድ አዋቂ፣ ያ- ገራገር ጋሽ መስፍን፤ በቀላሉ እንደሚለየን አልገመትንም ነበር፡፡ ለአስተርጓሚነት ከላይቤሪያ ሄዶ ሲመለስ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ታሞ ሊጠይቁት ከሄዱት ሰዎች ውስጥ ጋዜጠኛና ደራሲ ሶስና አሸናፊ አንዷ ነበረች፡፡ ጋሽ መስፍን እንዲህ ብሏት ነበር፤ “አትሥጉ ከሰባ ዓመት በላይ ሳልዘጋ አልሞትም!...ቤተሰባችን ሁሉ ሰባ ይገባል!” ግን እንዳለው አልሆነም! በ69 ዓመቱ  - ሕይወቱ ተደመደመ! ያሳዘነኝ ነገር ቢኖር የጋሽ መስፍን ናፍቆት ነው፡፡ ባገኘሁት ቁጥር አንድ የሚለኝ ነገር ነበር። “አንድ ኖቭል ሳልጽፍ አልሞትም!” ግን ናፍቆቱን አላገኘም፤ ተስፋውን አልጨበጠም! ዋ ጋሽ መስፍን!  


Read 2438 times