Saturday, 19 July 2014 11:54

ህልውና የሌላቸው ክዋክብት!

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(8 votes)

ይህን አጭር ጽሑፍ ለመፃፍ ስዘጋጅ የሮን ሃወርድ ፊልም የሆነውንና ራስል ክሮው የሚተውንበትን Beautyfull mind የተባለውን ፊልም እየተመለከትኩ ነበር፡፡ በፊልሙ ላይ ዋናው ገጸ ባህሪ ለፍቅረኛው ክዋክብትን  ሲያሳያት ይታያል፡፡
ድቅድቅ ባለው ጨለማ ውስጥ ከሚታዩት ክዋክብት መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ህልውና እንደሌላቸው ያውቃሉ?
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ለምሳሌ ለእኛ ፕላኔት ምድር ቅርቡ የሆነው ኮከብ አልፋ ሴንቸሪ፣ ከኛ አራት የብርሃን አመታት ይርቃል፡፡ ይህ ማለት ብርሃን በሰከንድ ሶስት መቶ ሺህ ኪሎ ሜትር እየተጓዘ አራት አመታት ያህል የሚወስድበት እርቀት ሲሆን ይህ ርቀት በኪሎ ሜትር ሲለካ ከሰላሳ ስድስት ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን የምናየው የኮከቡ ገጽታ አሁን ያለውን መልኩን ሳይሆን ከአራት የብርሃን አመታት በፊት የነበረውን ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ከኮከቡ የዛሬ አራት አመት በፊት የተነሳው ብርሃን ከርቀቱ  የተነሳ እኛ ጋ የደረሰው አሁን በመሆኑ ነው፡፡ አሁን ያለውን የኮከቡን መልክ ለማየት አራት የብርሀን አመታት መጠበቅ አለብን። ምክንያቱም ብርሃኑ ከኮከቡ ዛሬ ቢነሳ እኛ ጋ የሚደርሰው ከአራት የብርሃን አመታት በኋላ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለእኛ ቅርቡ የሆነው ኮከብ ያለው ርቀት ሲሆን በሚሊዮን የብርሃን አመታት ከእኛ የሚርቁ ከዋክብት አሁን የምናየው መልካቸው ከሚሊዮን አመታት በፊት የነበረ ነው፡፡  ምናልባት በአሁኑ ሰዓት በእድሜ ብዛት ሞተው ወይም ፈንድተው ድምጥማጣቸው ጠፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገሩ አጃኢብ ነው፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ግን እርስ በእርሳቸው በብዙ መቶ ሺህ የብርሃን አመታት የሚራራቁ አራት መቶ ቢሊዮን ከዋክብትን የያዘው ሚልኪ ዌይ የተባለው የእኛ ስርዓተ ፀሐይ ወይም Solar System ያለበት ጋላክሲ ትልቅነት ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የስነ - ፈለግ ተመራማሪዎች ህዋ ላይ ያለ ደመና ይመስላቸው ነበር፡፡ ነገሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩት ከዋክብት ክምችት መሆኑ የታወቀው በ1610 ጋሊልዩ ጋሌልይ በቴሌስኮፑ ካየው በኋላ ነበር፡፡
ይህ የእኛ ፀሐይ የምትገኝበት ጋላክሲ ከመቶ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የብርሃን አመታት የሚርቅ ዲያሜትር አለው፡፡ እንግዲህ የአንድ የብርሃን ዓመት ርቀት ከዘጠኝ ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር በላይ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡ የእኛ ፀሐይ በዚህ አይነቱ Spherical ወይም ዝርግ በሆነው ጋላክሲ ውስጥ Minor arm በተባለው ክልል ውስጥ ትገኛለች፡፡ ጋላክሲው ማይነር እና ሜጀር አርም በመባል የሚታወቁ ክልሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ከGalactic Center ወይም ከጋላክሲው መሐል ክፍል ሃያ ሰባት ሺህ የብርሃን አመታት ትርቃለች፡፡ ፀሐይ ከነጭፍሮችዋ የጋላክሲውን ማዕከል ስትዞር ወይም Rotation Period ሁለት መቶ አርባ ሚሊዮን አመታት ይፈጅባታል፡፡ ፀሐይ ከሌሎች ከዋክብት ጋር ይህንን የሮቴሽን ዑደት ስትፈጽም በሰከንድ 220 ኪሎ ሜትር ባለው ፍጥነት እየተጓዘች ነው፡፡ ጋላክሲው በራሱ የሚንቀሳቀስ ሲሆን በሰከንድ 600 ኪሎ ሜትር ይጓዛል፡፡
የዚህ ጋላክሲ ዕድሜ 13.6 ቢሊዮን አመታት እንደሆነ ሲገመት የተፈጠረው ለመላው ዩኒቨርስ መፈጠር ምክንያት ከሆነው ትልቁ ፍንዳታ ወይም Big bang በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡
የዚህ ጋላክሲ ማዕከል የሆነውና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩት ከዋክብቶች የሚዞሩት ነገር ምንድነው ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ A Masive Black hole የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
Black hole ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት ከባድ ቢሆንም ለመሞከር ያህል---የስበት ሃይሉ በጣም ሐይለኛ ከመሆኑ የተነሳ አንዴ ወደ ውስጡ የገባ አካል ለዘላለም ፈጽሞ የማይወጣበት፣ ዕድሜአቸውን የጨረሱ ክዋክብት መቃብር ሲሆን አንድ ብላክ ሆል ከ50 ቢሊዮን ፀሐዮች በላይ ሰልቅጦ አየሁ የሚል አይደለም፡፡
የዚህ ሚልኪ ዌይ የተሰኘው ጋላክሲ ጐረቤት የሆነው ጋላክሲ ኢንደሮ ሜዳ የሚባል ሲሆን የያዛቸው የክዋክብት መጠን ከሚልኪ ዌይ የሚተናነስ አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ጋላክሲው ሚልኪ ዌይ የሚለውን ስሙን ያገኘው ከግሪኩ Via እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ግዙፍ ጋላክሲ በዩኒቨርስ ውስጥ ከሚገኙት አምስት መቶ ቢሊዮን ጋላክሲዎች አንዱ ብቻ ነው፡፡  

Read 7428 times