Saturday, 12 July 2014 12:19

ግሩም የንባብ ማነቃቂያ!!

Written by  ኢ. ካ
Rate this item
(2 votes)

      ከአሁን በኋላ ሰኔ 30 ዓመታዊ የሂሳብ መዝጊያ ዕለት ብቻ ተደርጐ አይታሰብም ስል አሰብኩ፡፡ ዕለቱ ብሔራዊ የንባብ ቀን ይሆን ዘንድ አንጋፋው የደራሲያን ማህበር ንቅናቄ መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ እኛም አበጀህ ብለናል። “በዕውቀትና በመረጃ ለበለፀገ ህብረተሰብ መጽሃፍትና ሚዲያ በአንድ ሥፍራ”  በሚል መርህ ባለፈው አርብ ሰኔ 27 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተውና ለአራት ቀናት የዘለቀው “ኢትዮ - ዓለም አቀፍ የመፃሕፍት አውደርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ” የተጠናቀቀውም ባለፈው ሰኞ ሰኔ 30 ነበር፡፡ እኒህ ግጥምጥሞሽ ለእኔ ልዩ ስሜት ፈጥረውብኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይሄ ታላቅ የንባብ ንቅናቄ ነው፡፡ ግሩም የንባብ ማነቃቂያ!
ከዚህ ቀደም በተደረጉ የመፃሕፍት አውደርዕዮች፣ መፃሕፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች በአንድነት ተሳትፈው ይሆናል፡፡ የአሁኑ ግን ከዚያ በጣም የላቀና የሰፋ ነው፡፡ ዝግጅቱ   የመንግስት ተቋማትንም ማሳተፉ በእጅጉ ይደነቃል፡፡ ምንም እንኳን ዋናው የዝግጅቱ ተባባሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ቦታ ላይ ባይሳተፍም (ስታንዱ ኦና ነበር) አውደርዕዩን የከፈቱት ግን የትምህርት ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ የዝግጅቱን ፋይዳ ተገንዝበው በመገኘታቸው ምስጋና ሲያንሳቸው ነው፡፡
እንዳልኳችሁ በተሳታፊዎች ዓይነትና ብዛትም ቢሆን የአሁኑ ከቀድሞዎቹ በእጅጉ ይልቃል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና አንጋፋው ኬኔዲ ላይብረሪ በየግላቸው ተሳትፈዋል፡፡ እንደ ቡክ ዎርልድ (ሻማ ቡክስ) ያሉ አሳታሚዎችና የመፃሕፍት መደብሮች፣ የህፃናት ቤተመፃሕፍት፣ ማተሚያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ በርካታ መፃሕፍት አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች የተሳተፉበት፣ የህትመት ውጤቶቻቸውን ለዕይታና ለሽያጭ (በቅናሽ) ያቀረቡበት አውደርዕይ ነበር፡፡
ሌላው ይሄን ዝግጅት ለየት የሚያደርገው ደግሞ ሚዲያዎችም ተሳታፊ መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሚዲያ ኤክስፖ የሚባል ነገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ በእርግጥ በተከታታይ ሲወጡ በነበሩት ማስታወቂያዎች ላይ እንደተገለፀው፤ የመንግስት ሚዲያዎች ተሳታፊ አልነበረም፡፡ (በራሳቸው ምክንያት ቀርተው ይሆን?) ከግል ፕሬሱም ያልተሳተፉ አሉ - ከጋዜጣም ከመጽሔትም፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ግን ከተሳታፊዎቹ አንዱ ነበር፡፡
በነገራችሁ ላይ ስታንድ ተይዞላቸው በስፍራው ዝር ያላሉ የግል ተቋማትም እንደነበሩ መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ባይሆን ስማቸውን እንለፈው፡፡ አንባቢ የለም እያልንና ለንባብ ባህል መዳበር እንተጋለን ብለን የምንደሰኩር ወገኖች ሁሉ ቢያንስ በእንዲህ ያሉ ዝግጅቶች በመሳተፍ ቃላችንን ከምግባራችን የሰመረ ማድረግ ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለነገው ትውልድ የምናስረክበው የንባብ ባህል፣ ዛሬ እያንዳንዳችን በምንገነባት ትናንሽ ጡቦች ላይ የተመረኮዘ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መቼም የእዚህ ሁሉ ግርግር… የእዚህ ሁሉ ፌስቲቫል… የእዚህ ሁሉ የመፃሕፍት አውደርዕይ… የእዚህ ሁሉ ዝግጅት…. ድምር ውጤት በንባብ ባህላችን ላይ ትንሽም ብትሆን አዎንታዊ ለውጥ ታመጣለች የሚል ተስፋ አለን፡፡ ትንንሽ ለውጦች ተጠራቅመው ትልቅ ለውጥና ልዩነት መፍጠራቸው ደግሞ አይቀርም፡፡ ለስጋህ አደላህ አትበሉኝና የግል ፕሬሶች (የሚዲያ ኤክስፖው ክፍል ማለት ነው) ራሳቸውን ፕሮሞት በማድረግ ረገድ ተዋጥቶላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ የእንግሊዝኞቹ ሳምንታዊ ጋዜጦች “ካፒታል” እና “ፎርቹን” እንዲሁም የአማርኞቹ ሳምንታዊ ጋዜጦች “ሪፖርተር” እና “አዲስ አድማስ” ስታንዳቸውን በባለቀለም ፖስተሮች አስውበው፣ ህትመቶቻቸውን በትላልቅ የመስተዋት ፍሬም ሰቅለው የጐብኚዎችን ቀልብ ይስቡ ነበር፡፡ “አዲስ ጉዳይ” መጽሔትም የተለያዩ ሽፋኖቹን በትላልቅ ፖስተሮች አሳትሞ በመለጠፍ የጐብኚዎችን ስሜት ሰቅዞ ለመያዝ ችሏል፡፡ ጋዜጦች የቀድሞ እትሞቻቸውን ጠርዘው ለዕይታ ማቅረባቸው የተመልካቾችን ትኩረት የሳበ ነበር። በአዲስ አድማስ በኩል ለሽያጭ የተዘጋጁ ጥራዞች አልነበሩም እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ጐብኚዎች የቀድሞዎቹን ጥራዞች ለመግዛት ጠይቀው ነበር፡፡ የግል ፕሬሱ ከዚህ ዝግጅት ምን ተጠቀመ የሚለውን ለማሳየት የራሴን ተመክሮ (የአዲስ አድማስን ማለቴ ነው) በጥቂቱ ልግለጽ፡፡ እኔና ለአራት ቀናት በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ የጋዜጣው ባልደረቦች፣ ከአንባቢያን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተን ስለጋዜጣው ያላቸውን ገንቢ አስተያየት ለመቀበል ችለናል፡፡ አብዛኞቹ ጐብኚዎች በአዲስ አድማስ የተዘጋጀውን መጠይቅ (questionnaire) ያለማንም ገፋፊነት በፈቃዳቸው እያነሱ ለመሙላት ያሳዩት ተነሳሽነትም መገረምና መደነቅን ፈጥሮብናል፡፡ የአንባቢያን ደፋርና ግልጽነት የተመላበት አስተያየትም ለጋዜጣው ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት ፍንትው አድርጐ አሳይቶናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አስተያየታቸውን መነሻ በማድረግ የጐደለውን ለመሙላት፣ መታረም ያለበትን ለማረም እንዲሁም የአንባቢያንን ፍላጐት ለማርካት በትጋት እንደምንሰራ እየገለጽን፣ አስተያየታቸውን ለለገሱን ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
ጐብኚዎችን በማስተናገድ ተወጥረን አልተሳተፍንም እንጂ ከአውደርዕዩ ጐን ለጐን የዲስኩር፣ የግጥም ንባቦችና መሰል የጥበብ ፕሮግራሞችም ተካሂደዋል፡፡
እንደኔ ምልከታ ከሆነ፣ ይሄ የአራት ቀናት የመፃህፍት አውደርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ ፍፁም የሰመረና የተሳካ ነበር፡፡ ይሄን ታላቅ የንባብ ማነቃቂያ ፌስቲቫል ላይ ታች ብለው እውን ያደረጉት አዘጋጆች፤ አድናቆትና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡  ባይሆን በጅምር እንዳይቀር አደራ እናክልላቸዋለን፡፡  ቺርስ ለንባብ ባህላችን ዕድገት!!

Read 3340 times