Saturday, 24 May 2014 14:39

የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

ገፅ ለገፅ! [Interface Meeting]
ተፋጠጥ፣ ተገላለጥ፣ ተሞራረድ፣ ችግር ፍታ!


የዛሬው የጉዞ ማስታወሻዬን ለየት የሚያደርገው ኃላፊነት በመውሰድና በተጠያቂነት ላይ ባተኮሩ ሁለት ስብሰባዎች ላይ መሳተፌ ነው - አንዱ ብሾፍቱ/ ደብረዘይት ነው፡፡ ሁለተኛው ድሬዳዋ ነው፡፡
ሁኔታው እጅግ እንዲያስደምመኝ ያደረገው፤
1ኛ/ ህዝብ አንዳችም ወደኋላ ሳይል ብሶቱን፣ ምሬቱንና ጥያቄውን ለማቅረብ መቻሉ፤
2ኛ/ መንግሥት በቀጥታ ይሄ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ይቅርታ አድርጉልን፤ አልሠራነውም፡፡ ይሄንን በትክክል ሠርተናል፡፡  ይሄ መንገድ ላይ ነው ትንሽ ታገሱን ለማለት መቻሉ ነው።
በባለሙያዎቹ ቋንቋ ህዝብ “አገለግሎት ተቀባይ”፣ መንግሥት “አገልግሎት ሰጪ” ነው የሚባለው፡፡ ሁለቱ ፊት ለፊት የተገናኙበትን ሁኔታ “ገፅ ለገፅ” የሚሰኝ ርዕስ ሰጥተውታል - ፕሮጄክታውያኑ፡፡
ነገሩ የተካሄደው ብሾፍቱ/ደብረዘይት ውስጥ ነው፡፡ በተገልጋይ ወገን ህዝቡ፡፡ በአገልጋይ ወገን ቁንጮው ከንቲባ ሆነው፤ የየዘርፍ ኃላፊዎችና የወረዳና ቀበሌ ሹማምንት ተገኝተዋል፡፡ እንደዚህ ስብሰባ የማረከኝ ወደግልጽነት የሚያመራ ጉባዔ አላጋጠመኝም፡፡ ተግባር ሌላ ጉዳይ ነው ብዬ ማለት ነው፡፡
የብሾፍቱን (የደብረዘይቱን) ገፅ ለገፅ (interface) ፕሮግራም ሳይ ትዝ ያለኝ፤ አንድ ጊዜ አቶ ሃይማኖት ዓለሙ በቴሌቪዥን ማቅረብ ጀምሮ የነበረው ፕሮግራም ነው፡፡ ነገር ነገሩ አልቀጠለም እንጂ እንደ የአበሻ “ሀርድ-ቶክ” መሆኑ ነበር፡፡ አሁን ያየሁት የደብረዘይት “ገፅ-ለገፅ” ከዚያኛው የሚለየው፣ ያኛው አንድ ሰው ለአንድ ሰው የሚያደርገው ሲሆን፤ ይሄኛው ግን አገልግሎት ተቀባይ ህዝብ እና የመንግሥት ኃላፊዎች ግንባር ለግንባር የሚጋጠሙበት፣ የሚተቻቹበት፣ ነገሩን የሚያፍረጠርጡበት፤ መፍትሄ ለመስፍጠርም ከማን ምን ይጠበቃል? የሚባባሉበት፤ ህይወት ያለው ውይይት ነው፡፡ በመጨረሻ ጉዳዩን መሬት አውርዶ የሚተገብርና የሚከታተል የተግባር ኮሚቴ የሚመሰርትበት ነው፡፡
የከተማይቱ ዋና ችግር የውሃ እጦት ነው። እንደ ብሾፍቱ ላለች በውሃ ለተከበበች ከተማ ጉዳዩ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ነው፡፡ ሁለተኛው መነጋገሪያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነው፡፡ ቡጥ ቡጡን ወደኋላ ላይ እተርክላችኋለሁ፡፡ ብዙ ትምህርት - ተኮር ችግሮች ተወስተዋል፡፡  
“ሬሣ እንኳ አጥበን አንቀብርም!”
ከአገልግሎት ተቀባዩ ህዝብ መካከል ልቤን የነኩኝ አንድ ሴት አይቻለሁ፡፡ የውሃ ችግርን ለማሳየት ከዚህ የተሻለ አገላለፅ አላጋጠመኝም፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
“ዛሬ የምታዩትን ነጭ ሸማ ለብሼ የመጣሁት ለዚህ ስብሰባ ስል ነው፡፡ የክት ልብሴን አውጥቼ ለብሼ ነው የመጣሁት፡፡ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ያቃል ይህን ለብሼ እንደማላውቅ፡፡ ቆሻሻ፣ አዳፋ ልብስ ነው የምለብሰው - ከወር ወር የማይታጠብ፡፡ ምነው ቢባል በምን ውሃ አጥበን እንልበስ! እናንተ ስለ ልብስ ሳወራ የውሃን ችግር በቀላሉ ታዩ ይሆናል፡፡ ዛሬ እኛ ሬሳ አጥበን አንቀብርም!
አንድ ጀሪካን ውሃ 20 ብር ነው /ሸክሙን ትተን/!!  ሁሉ ነገር ከአቅማችን በላይ ነው ይሉናል ለሚመለከታቸው ስንነግር፡፡ 98 ከመቶ ደርሰናል ይሉናል 40ውን ብቻ ለእኛ ይስጡን፡፡ (ተሰብሳቢው በሳቅና በውካታ ተሞላ!) በሽንት ቤት ሽታ አስም ከያዘኝ ቆየሁ፡፡ የቆሻሻ ማንሻ መኪና የለም! ቢኖርም የግለሰብ ነው፡፡ በአመድና ቆሻሻ ክምር፣ በሽንት ቤት ጠረን ውስጥ የምንኖረው ከሙታኖች በላይ ብቻ ነው፡፡ እኛ የ08 ነዋሪዎች ነን! ቅድም እንዳልኩት ሬሳ እንኳ አጥበን አንቀብርም!”
ልብ በሉ እኒህ ሴት ግልፅ በግልፅ የሚናገሩት ፊት ለፊታቸው ለተቀመጡት ለከተማይቱ ከንቲባ ለአቶ ከፍያለው አያና እና ለውሃ፣ ለትምህርት፣ ለጤና ሴክተር ባለስልጣናት ነው፡፡ ይሄ ነገር ምነው በሀገሪቱ ሁሉ እንዲሁ ቢቀጥል፤ አልኩኝ በሆዴ፡፡
የከተማይቱ ከንቲባ የመለሱትም የዋዛ አደለም። ችግሩ ሲገለፅ መቀበል፣ መፍትሔ እጅ - በጅ መስጠት የሚችሉ ከንቲባ ናቸው፡፡ በፊት ለፊት መፍትሔውን መጠቆምና ግልፅ ውሳኔ ለማበርከት ይችላሉ፡፡ “የስራ ተቋራጮቻችን እየዋሹ ሲያስዋሹን ነበር” ሲሉ ሰው በሳቅ ፈነዳ። “ገፅ በገፅ በመነጋገራችን መንግስትም ህዝብም ተጠቃሚ ነው፡፡ ዋናው ግን ህዝብ ነው፡፡ ህዝባችን ችግሩን ማወቅ አለበት! ስኬቱ የህዝብ ስኬት ነው!፡፡ ክፍተቱም የህዝብ ክፍተት ነው!
ሁሉም የየድርሻውን ይወስዳል!...
“… የኃላፊነትና የተጠያቂነት ስብሰባ ትልቁ ጥቅሙ እንደግለሰብ ልናገኛቸው የማንችላቸውን የመንግስት ኃላፊዎች በግልፅ ማግኘታችን ነው። ስለዚህ ሐሜት ይወገዳል፡፡ ሁሉም የየድርሻውን ይወስዳል…98% ስራ መገባደዱ እውነት ነው ግን አገልግሎት ካልሰጠ ዋጋ የለውም፡፡ የውሃውን ችግር ታሪክ እናደርጋለን! ሆኖም የአቅማችንን ብቻ ነው የምናደርገው ታገሱን!
ረዥም በማይባል ጊዜ እንጨርሰዋለን፡፡ በቂ ውሃ አዘጋጅተናል፡፡ ስለዚህ ተስፋ አለን፡፡
የፍሳሽ ቆሻሻን ችግር እንደ ቤት ሥራ ለመውሰድ ቃል እንገባለን፡፡ በትምህርት ጉዳይ ህዝቡም መገምገም አለበት፡፡ የትምህርት ጉዳይ የእያንዳንዱ ቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ ለመምህሩም ተገቢው አክብሮት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የጎረቤት ልጆች የእኔም ልጆች ናቸው ለማለት መቻል አለብን፡፡…”
“በት/ቤት ቅፅር ግቢ ያሉ የመኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ አሁኑኑ ውሳኔ እንስጥ” አሉና፤
“እኛ/መንግሥት/ ቦታ እናዘጋጅ፡፡ ቤት መስራት ለማይችሉ ቤት እንስጣቸው፡፡ ግቢውን ለት/ቤት ብቻ እናድርገው፡፡ ይኸው በፊት ለፊት የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ውጤቱን እናመጣላችኋለን!...” ጭብጨባው ቀለጠ፡፡ ዕውነት ለመናገር አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዲህ ገፅ በገፅ የሚችለውን እችላለሁ፣ የማልችለውን አልችልም፤ ሲል ማየትና መስማት በበኩሌ የለውጥ ሀሁ ተጀመረ ፤ አሰኝቶኛል፡፡  
ከንቲባው ቀጥለው፤ ወደትምህርት ትኩረታቸውን አዙረው፤
“ተማሪ ለመማር 5 ሣንቲም መክፈል የለበትም። የሚያስከፍል ካለ ወንጀለኛ ነው!!” አሉ፡፡
“ከህዝቡ የሚጠበቀውስ?” አሉ ቀጥለው። “የትምህርት ሂደቱን መደገፍ! 50% የድምር ወጪውን ህዝቡ እንዲሸፍን ተነጋግረናል፣ ወስነናል፣… በጉልበት፣ በጊዜ፣ በገንዘብ! ተግባራዊ እናድርገው። ውሃ ሲፈስ ብታዩ የምትጠቁሙ እነማን ናችሁ? አለቃ ሲሰርቅ እምቢ /No!/ የምትሉ እነማናችሁ? የራሳችሁ ሀብት ነው ሚሰረቀው! እንደዛ ከሆነ ብሾፍቱ የጥቂት ሰዎች ናት ማለት ነው! ከህዝብ የማያስፈልገን ሰው የለም! አቅም ትሆኑናላችሁ ኑ! ያደግንበት አካባቢ ለፈጣን ዕድገት አመቺ አልነበረም አይፈቅድም፡፡ መለወጥ አለበት። አንዱ አንዱን አይርገም! ዛሬ ማይክሮ - ሰከንድ ሚሊዮን ያሳጣል፡፡ እንፍጠን፡፡…” ተቀባይነታቸው አያጠያይቅም፡፡
*       *        *
ይሄ ሁሉ የሚወራበት ስብሰባ፤ ርዕሱ፤ “የዜጐችና የመንግሥት ተወካዮችና ባለሥልጣናት “የውሃ፣ የአካባቢ ፅዳትና የመጀመሪያ ደረጃ አገልግሎት፤ የብሾፍቱ ወርክሾፕ ሲሆን፤ የፕሮግራም መሪው ባስረዱት መሠረት (ፕሮግራሙ ላይም አለ) በመጀመሪያ የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ከዚያ በየጉዳዩ ላይ ጥናት የሚያቀርቡ ይኖራሉ፡፡ በአጥኚዎች የ06/ 07/ 08/ 09 ቀበሌ ሁኔታ ይቀርባል፡፡ ውይይት ይካሄዳል፡፡ በመጨረሻም ለመፍትሔ ጉዳይ የተግባር ኮሚቴ ተመርጦ፣ ይቋቋማል አሉን።  አቶ ሙሉጌታ ገብሩ የጄክዶ ሥራ አስኪያጅ ባደረጉት ንግግር ጥሪ የተደረገላቸውን እንግዶች  እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ፤ “የኢየሩሣሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት በ1984 ዓ.ም የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረውን የአገራችን ችግር ለመፍታት የተመሠረተ ድርጅት መሆኑንና ህፃናትና ማህበረሰብ ላይ” እንደሚያተኩር ገልፀው፤ 5 ቅርንጫፍ መ/ቤቶች በብሾፍቱ፣ ድሬዳዋ፣ አዋሳ፣ አዳማ፣ ባህርዳርና ደብረ ብርሃን እንዳለውና በ18 የአገራችንንሰ ክፍሎች እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ 1ኛ) ለትምህርት ለጤናና ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት አገልግሎት ማስገኘት፤
2ኛ/የአየር ንብረት ለውጥ የአደጋ ቅነሳ (Climate Change እና disaster risk reduction) 3ኛ/ በአቅም ማጐልበት ዙሪያ እንሠራለን፡፡ ማህበራትን ማጐልበት፡፡
በ1983 በብሾፍቱ ሥራ የጀመርን ይመስለኛል፡፡ ለብሾፍቱ ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ያደረግን ይመስለኛል፡፡ የሥራችን አንዱ አቅጣጫ ማህበራዊ ተጠያቂነት ነው፡፡ 2008-2009 ይሄንኑ ሂደት በብሾፍቱ ዙሪያም አካሂደናል፡፡ ባካሄድነው ሂደት በአገልግሎት ሰጪው (መንግሥት) እና በአገልግሎት ተቀባዩ (ህዝብ) መካከል ፍፁም ቀናነትና መልካምነት የተመላ ስብሰባ አካሂደናል፡፡ ችግሮችን አንጥሮ በማውጣት ለጋራ መፍትሔ መሄዳችን ይታወሳል፡፡ ለአብነት ብሾፍቱን መጥቀስ ተገቢ ነው። በ2002 ብሾፍቱ ተጨማሪ ገቢ ነበረውና ይሄን ገቢ የከተማው አገልግሎት ለትምህርት እንዲውል ወስኖ ብሾፍቱ ላይ 70 ተጨማሪ መምህራን ተቀጠሩ፡፡
ከመንግሥት ሐላፊዎች ተቀባይነት አግኝቶ እንዲያውም ይሄንን ሂደት ወደሌሎች ሴክተሮች ብንወስደው ሸጋ ነው አልን - አገልግሎት ለመስጠት።
ወደሌሎች ከተሞች የሄድነው ብሾፍቱ ላይ በተነሳ ሀሳብ ነበር፡፡ ተሞክሮውን መነሻ በማድረግ እኤአ 2013 እና 14 ድርጅታችን የማህበረሰቡ በውሃ፣ ትምህርት እና አካባቢ ንፅህና ላይ አተኮረ። በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቀስን፡፡ ስለሆነም በዛሬው ዕለት በምናካሂደው ስብሰባ፤ አገልግሎት ተቀባይና ሰጪው በየበኩላቸው ችግር ብለው የለዩዋቸውን ጉዳዮች በጋራ የሚወያዩበት መድረክ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ገፅ ለገፅ ማለት ይሄው ነው! Interface meeting፡፡ ሃሳባችንን ኃላፊነት በተሞላበትና ቅንነት ባለው መልኩ በመግለፅ ውጤታማ እንድናደርገው በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡
የሀገራችን የዲሞክራቲክ ሂደትና የመልካም አስተዳደር አንዱ ገጽታ ነው። ይሄ ዓይነት ውይይት ሠለጠን የሚሉትም ሀገሮች  የሚያካሂዱት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ልዩ ያደርገዋል።
ቅን መንፈስና የጋራ መግባባት ውጤታማ እንደሚያደርገን ተስፋ አደርጋለሁኝ፡፡” ብለው ደምድመዋል፡፡
ቀጥሎ፤ ህዙቡስ ምን አለ? (ይቀጥላል)

Read 2321 times