Saturday, 03 May 2014 13:25

በአገራቸው ውስጥ “ስደተኛ” የሆኑ 260 ሚሊዮን ቻይናዊያን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በ5 አመት 30 ሺ ስደተኛ ቻይናዊያንን በነዋሪነት የተቀበለች ከተማ ተሸላሚ ሆናለች - 1.6 ሚ. ስደተኞች በከተማዋ ይኖራሉ
          ከተሞች ውስጥ በቋሚነት የሚኖሩ ቻይናዊያን ቢቆጠሩ ወደ 700 ሚሊዮን ገደማ ናቸው። የቻይና መንግስትና ገዢ ፓርቲ እንዲሁም ገለልተኛና ዓለማቀፍ ተቋማት በዚህ ያምናሉ። ነገር ግን፤ እዚያው በዚያው ሌላ ነገር ትሰማላችሁ። የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ወደ 440 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ በይፋ ይነገራል፤ ሪፖርት ይቀርባል። “በአንድ አፍ ሁለት ምላስ” አትሉም? የተሳሳተ ነገር የፃፍኩ እንዳይመስላችሁ። ነገሩ እውነት ነው። “በከተማ የሚኖሩ” እና “የከተማ ነዋሪዎች” ቁጥር እንዴት ይለያያል? የእንቆቅልሹ ፍቺ ይሄውላችሁ። 260 ሚሊዮኖቹ ስደተኞች ናቸው። ከሌላ አገር የመጡ አይደሉም። እዚያው አገራቸው ውስጥ ከገጠር ወደ ከተማ የገቡና በስደተኛነት የተመዘገቡ ቻይናዊያን ናቸው። ከተማ ውስጥ 20 አመት ቢያሳልፉ፣ ቤተሰብ ቢመሰርቱና እዚያው ከተማ ልጅ ቢወልዱ ለውጥ የለውም። “የከተማ ነዋሪ” የሚል እውቅና አያገኙም። ከነልጃቸው “ስደተኛ” በሚል መጠሪያ ነው የሚታወቁት። “ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች” የሚል ስያሜም የተለመደ ነው - እዚያው በቻይና የሚዲያ ዘገባዎች ውስጥ ሳይቀር።
“የከተማ ነዋሪ” መሆንና “ስደተኛ” ተብሎ መኖር፣ ልዩነቱ የስያሜ ጉዳይ ብቻ አይደለም። በአንድ ከተማ ውስጥ እየኖሩ፣ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ በተመሳሳይ ሙያና ብቃት የሚሰሩ ሁለት ቻይናዊያን እኩል ደሞዝ እንዳያገኙ የሚያደርግ ስርዓት ነው። ጡረታ ሲወጡ የሚያገኙት ክፍያም በ10 እጥፍ ይለያያል። በአጠቃላይ፤ በርካታ አመታትን ያስቆጠረው አድልዎ ከአፓርታይድ ጋር ይመሳሰላል - ባለፈው ሳምንት የወጣው ዘ ኢኮኖሚስት መፅሔት እንደገለፀው።
ነገርዬው፤ የ21ኛው ክፍለዘመን ታሪክ ስለማይመስል ግር ያሰኛል። ምናልባት፤ቻይናን እንደ ሁለት አገር ብንቆጥራት ሳይሻል አይቀርም። ታሪኩ የሚጀምረው፤ የዛሬ 55 ዓመት ነው። በብዙዎቹ ኮሙኒስት ፓርቲዎች ላይ እንደተለመደው፣ የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ መሪ ማኦ ዜዱንግ ለከተሜነት ጥሩ ስሜት አልነበራቸውም። “ሰዎች በገፍ ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሱ ቀውስ ይፈጥራሉ” የሚለው ሰበብ ተጨመረበትና ቻይናዊያን የመኖሪያ አካባቢያቸውን እንዳይለውጡ የሚከለክል የቁጥጥር ስርዓት ተፈጠረ። በደርግ ዘመን ተጀምሮ ከነበረው ቁጥጥር ጋር ይመሳሰላል። ከቀበሌ “የይለፍ ወረቀት” እና “የመልቀቂያ ፈቃድ” ያላገኘ ሰው ከመኖሪያ አካባቢው መልቀቅ አይችልም ነበር። ያው፤ ኮሙኒስቶች፣ የሁሉንም ሰው ኑሮና ንብረት የመቆጣጠር ረሃብ አለባቸው - የስልጣን ጥም ልትሉት ትችላላችሁ። የቻይናው ቁጥጥር ፈፅሞ የማያፈናፍን መሆኑ ነው ልዩ የሚያደርገው።
የሆነ ሆኖ፤ማኦ ባወጡት ሕግ መሰረት የአገሬው ሰዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው ተመዘገቡ - የከተማ እና የገጠር ነዋሪ (hukou) በሚል። “የከተማ ዜጋ እና የገጠር ዜጋ” ልንለውም እንችላለን። ለምን ብትሉ? በጣም አስቸጋሪ ነው። ከገጠር ነዋሪነት ወደ ከተማ ነዋሪነት መሸጋገር፤ ከአንድ የአፍሪካ አገር ተሟሙቶ የአሜሪካ ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ እንደማግኘትና ከዚያም ዜግነት እንደመለወጥ ነው። የገጠር ነዋሪ (ዜጋ) የነበረ፣ እድሜ ልኩን የገጠር ዜጋ እንደሆነ ይቀጥላል - ከነልጆቹ፣ ከነልጅ ልጆቹ።
አዋጁና ቁጥጥሩ ቀስ በቀስ እየላላ የመጣው፣ ከማኦ ህልፈት በኋላ በዴንግ ዚያዎፒንግ መሪነት ኮሙኒስት ፓርቲው የኢኮኖሚ ስርዓት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ነው። በማኦ ዘመን፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር መግባቱ፣ ድህነት መባባሱና ረሃብ መከሰቱ አይገርምም። ሌሎች ኮሙኒስት አገራትም የሚጋሩት ታሪክ ነውና። አስገራሚው ነገር፤ የቻይና ኮሙኒስቶች ከድህነት ለመውጣት፣ መጠነኛ የካፒታሊዝም ወይም የነፃ ገበያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰናቸው ነው - የዛሬ 35 ዓመት ገደማ። “የጋራ መሬትና የጋራ ምርት” በሚል በግዴታ በማህበር ተደራጅተው በጋራ ሲደኸዩ የነበሩ ገበሬዎች፤ ማሳ ተከፋፍለው በግል እንዲያመርቱ ተፈቀደ። በከተማም፣ ንብረት ማፍራት፣ የንግድ ወይም የማምረቻ ቢዝነስ መክፈት ይቻላል ተባለ። ሃብት ማፍራትን እንደ ትልቅ ክህደትና ወንጀል ይቆጥር የነበረ ኮሙኒስት ፓርቲ፤ “ሃብታም መሆን ጀግንነት (ቅዱስነት) ነው - To be rich is Glorious” እያለ በባነርና በፖስተር፣ በሬድዮና በቲቪ ያስተምር ጀመር።
በተከፈተችው የነፃ ገበያ ጭላንጭል አማካኝነት፣ የሚታይ የሚጨበጥ ፍሬ ለማግኘት ጊዜ አልፈጀባቸውም። የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል ጀመረ። የነፃ ገበያ ማሻሻያውም ቀስ በቀስ እየሰፋ፣ በአምስት አመታት ውስጥ ኢኮኖሚያቸው ወደ ፈጣን እድገት ተሸጋገረ። ከዚሁ ጋር አብሮ ነው፤ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት የስራ እድል መስፋፋት የጀመረው - በከተሞች በተለይም በማምረቻ የኢንዱስትሪ ቢዝነሶች። ነገር ግን፤ ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይፈልሱ የሚያግድ ሕግ ይዘው፣ በኢኮኖሚ እድገት መቀጠል አይችሉም። የግድ መለወጥ አለበት። ደግሞም ለውጠውታል።
በእርግጥ ህጉ አልተሻረም። ነገር ግን፤ ሕጉን የሚያላላ ዘዴ ተፈጠረ። ወደ ከተማ ሄደው ለመስራት የሚፈልጉ የገጠር ነዋሪዎች፣ በጊዜያዊነት የይለፍና የመኖሪያ ፈቃድ የሚያገኙበት ሰፊ እድል እንዲያገኙ ነው የተወሰነው። “የአገር ውስጥ የዲቪ ሎተሪ” በሉት። በስደት ጊዜያዊ ቪዛና ጊዜያዊ ግሪን ካርድ እንደማግኘት ነው። ጊዜያዊ ተብሎ የተጀመረው ስደት እየሰፋ ቀጠለ እንጂ አልቆመም - ከተማ የገቡት ስደተኞች ወደ አገር ቤት አልተመለሱም። ግን ደግሞ፣ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ወደ ሙሉ ዜግነት አልተለወጠም። 10 እና 20 ዓመት ቢያልፋቸውም፤ ቤተሰብ መስርተው ልጆችን ቢያፈሩም፤ የአገሪቱ ህግ “የከተማ ነዋሪ” በሚል ስያሜ አያውቃቸውም።
ሕይወታቸው ሲታይ፣ በከተማ ከ20 አመት በላይ የኖሩ ናቸው። በህጉ ሲታይ ደግሞ፣ ከነልጆቻቸው ስደተኛ “የገጠር ነዋሪ (ዜጋ)” ናቸው። ከጥቂቶች በስተቀር፣ የብዙዎቹ ስደተኞች እጣ ፋንታ ከዚህ የተለየ ባለመሆኑ፣ ዛሬ ቁጥራቸው 260 ሚሊዮን ደርሷል። በሌላ አነጋገር፣ በከተማ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል፣ 37 በመቶ ያህሉ ስደተኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች ናቸው። ልጆቻቸው በመንግስት ትምህርት ቤት ወይም ዩኒቨርስቲ ውስጥ ማስመዝገብ አይፈቀድላቸውም። በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት ማግኘት አይችሉም። መኖሪያ ቤት ሽያጭና ኪራይ ላይ በመንግስት የሚመደቡ ድጎማዎችንም አያገኙም። በዚያ ላይ ከፍተኛ የጡረታ ክፍያ አድልዎ ይጠብቃቸዋል።ይህንን አድልዎ ለማስወገድ እየጣረ እንደሆነ፣ የቻይና መንግስት መግለፁ አልቀረም። ለበርካታ አመታት በከተማ የኖሩ “ስደተኞች”፣ ሙሉ“የከተማ ነዋሪነት”ን የሚቀዳጁበት ሂደት እንደተጀመረም ይገልፃል። ነገር ግን፤ ሂደቱ ገና ፈቅ አላለም። በአርአያነት የተሸለመችውን ከተማ መጥቀስ ይቻላል። ዞንግሹን ትባላለች። በከተማዋ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ግማሾቹ “ስደተኞች” ናቸው - 1.6 ሚሊዮን ያህል። ባለፉት አምስት አመታት ከእነዚህ ውስጥ “የከተማ ነዋሪነት”ን የተቀዳጁት 30ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው። በከተማዋ ውስጥ ካሉት 200ሺ የስደተኛ ልጆች መካከልም በመንግስት ትምህርት ቤት እንዲመዘገቡ የተፈቀደላቸው ለ25ሺ ያህሉ ነው። የማኦ ቅርስ የኮሙኒዝም ውርስ የሆነው አድልዎ ገና አልተነካም ቢባል ይሻላል።

Read 2419 times