Saturday, 26 April 2014 12:55

‹ሳላ› በፕሮፌሽናል ደረጃ አዳዲስ ክብረወሰኖች ማስመዝገቡን ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(8 votes)

      የ25 ዓመቱ ሳላሀዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃዎችን በአዳዲስ ክብረወሰኖች እያሻሸለ  እድገቱን በመቀጠል ላይ ነው፡፡ ከ3 አመት በፊት ለግብፁ ፕሪሚዬር ሊግ  ክለብ ዋዲ ዳግላ ለመጫወት በተከፈለበት 275ሺ ዶላር የዝውውር ሂሳብ አዲስ ታሪክ  ያስመዘገበው  ሳላሀዲን ሰኢድ ሰሞኑን  ደግሞ  ወደ ሌላው የግብፅ ክለብ አልአሃሊ  በመዛወር በወር 30 ሺ ዶላር እየተከፈለው ለመጫወት ተስማምቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አዲስ ክብረወሰን አስፅፏል ፡፡ ሳላሃዲን በአልአሃሊ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ሲጫወት ከ500ሺ ዶላር በላይ ያገኛል በሚል የዘገበው ሱፕር ስፖርት ነው፡፡
 በግብፁ ክለብ ዋዲ ደጋላ ዘንድሮ 11 የሊግ ግጥሚያዎችን ያደረገው እና በ9 ጨዋታዎች ቋሚ ተሰላፊ የነበረው ሳላሃዲን 6 አስደናቂ ጎሎችን ከመረብ ማዋሃዱ ትኩረት ውስጥ ከቶታል፡፡ ከሳምንት በፊት ሳላሃዲን በዋዲ ደጋላ  የሚቆይበት የኮንትራት ውሉ ዘንድሮ ማብቃቱን የሚያወሱ ዘገባዎች  መውጣት የጀመሩ ሲሆን በክለቡ ቆይታውን እንዲያራዝም ግፊት ቢደረግበትም የዝውውር ህገ ደንብን ጠብቆ መልቀቁ እንደማይቀርና ወደ ሃያላኖቹ የግብፅ ክለቦች ዛማሌክ ወይም አልአሃሊ ሊዛወር እየተደራደረ  ነው የሚሉ መረጃዎች ተናፍሰው  ነበር፡፡ ከወራት  በፊት ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ክለብ ካይዘር ቺፍ ተጨዋቹን ለማስፈረም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉ ተወስቷል፡፡
ቀይ ሰይጣኖች የሚባለው  የግብፁ ክለብ አልአሃሊ  ባለፈው የውድድር ዘመን የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን  ሳላሃዲን ሰኢድን ዘንድሮ እየተሳተፈበት በሚገኘው  የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ማሰለፍ አይችልም፡፡
ሳላሃዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ ብሄራዊ  ቡድን የአጥቂ መስመር ተጨዋችነት ባለፉት 2 ዓመት ከሰባት ወራት 20 ጨዋታዎችን አድርጎ 12 ጎሎችን  በስሙ እንዳስመዘገበ ይታወቃል፡፡ በካፍ ዓመታዊ ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ምርጫ በመላው ዓለም ከሚጫወቱ አፍሪካዊ ፕሮፌሽናሎች በእጩነት ከቀረቡት  25 ተጨዋቾች አንዱ የነበረው ሳላዲን ሰኢድ በትራንስፈር ማርኬት የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመኑ 300ሺ ዩሮ ነው፡፡

Read 3880 times