Monday, 14 April 2014 10:13

የካህናት ስስት በቅኔ ሲሞገት!

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሽራ
Rate this item
(1 Vote)


         ስስት፣ ቅንዓትና ምቀኝነት በየትኛውም የዓለም ክፍል የተጠላና የሚያስጸይፍ ተግባር ነው። ሆዳምነትም እንደዚሁ የስስት ታላቅ ወንድም በመሆኑ የትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። ከዚህም የተነሣ አባቶቻችን (እናቶቻችን) ተረት ሲተርቱ “አልጠግብይ ሲተፋ ያድራል”፣ “ከስስታም አንድ ያንቀው አንድ ይወድቀው”፣ “ሆዳም ከአልሞተ አያርፍም”፣ “ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም”፣ “ሆድ አምላኩ”፣ “ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝዝለታል”። “አህያ ሆድ”፣ “ዘተር ሆድ”፣ “ቅርጫት ሆድ” … እያሉ በመተረት ስስታምነትን ይኮንናሉ፡፡ ብዙ ሰው በተለይ ምግብ ተዘጋጅቶ በቀረበ ጊዜ የዓይን ስስት አለበት፡፡ እጠግብ ስለማይመስለው ሁሉ ነገር ለእርሱ እንዲሆን ይመኛል፡፡ ሌላ ተጋሪ ሰው ሲመጣበት ዓይኑ ደም ይለብሳል፡፡ በተጻራሪው ደግሞ አንዳንድ ሰው፤ ሰው በልቶ የሚጠግብ ስለማይመስለው ያለውን ሁሉ ያለ ስስት ያቀርባል። ብቻውን የሚበላ ሰው በማኅበረሰባችን በእጅጉ የተጠላ በመሆኑ “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል።” ተብሎ ይተረትበታል፡፡
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ስስትና ሆዳምነት ጎልቶ የሚታየው በቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ አንዳንድ ካህናት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት በስስት ልጓም የታሠሩ ስለሆኑ በዕለት መክፈልት፣ መሀራና ተዝካር ጭምር ሲጣሉና ሲደባደቡ ይውላሉ፡፡
መሪ ጌታ ዋለና መሪጌታ ተገኘ የተባሉ ሁለት መሪጌቶች በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም እርስበርሳቸው ስለሚናናቁ ሁልጊዜ በነገር ይጎሻሸማሉ፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ቅዳሴ ተቀድሶ ከደጀሰላም ውስጥ መሀራ ሲበሉ መሪጌታ ተገኘ ሆዳም ኖሮ እየጠቀለለ ቶሎ ቶሎ እንጀራውን ሲጎርስ መሪጌታ ዋለ ይመለከታል፤ ዋለም ተገኘን አይቶ ለመወዳደር ቶሎ ቶሎ ይጎርሳል።
በዚህ ጊዜ መሪጌታ ተገኘ የመሶቡን እንጀራ ሲያገባድደው ተመልክቶ “ብሉ ወንድሞቼ መብል እንደተገኘ ነው” ይላል፡፡ መሪጌታ ተገኘም “አዎ ያውም በዋለ ሆድ” ብሎ የመልስ አጠፌታ ሰጠ፡፡”
የለጋስነት፣ የቁጥብነትና የርኅራኄ መንፈስ ያላቸው ሌሎች ካህናትና ዲያቆናትም የስስታሞችን ድርጊት በምክርና በተግሳጽ ጭምር ለማርገብ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ ቅኔ ጭምር በመቀኘት ስስትንና ሆዳምነትን ይታገላሉ፡፡
በአንድ ወቅት አንድ የቅኔ መምህር፣ ላሊበላን ሊሳለም ወደሮሃ ይሄዳል፡፡ በላሊበላ አካባቢ ደግሞ ሐዋ ሚካኤልና ድቡኮ ማርያም የተባሉ ቦታዎች አሉ። እንግዳው የቅኔ መምህር በእነዚህ ቦታዎች በሚገኙ ቤተክርስቲያኖች በየጊዜው አገልግሎት ቢሰጥም መሀራ (ድግስ) ቤተክርስቲያን ውስጥ በቀረበ ጊዜ ካህናቱ ደጀ ሰላሙን እየዘጉ ይበላሉ። ከሌላ ቦታ የመጣን ካህን በምንም መንገድ ስለማይጋብዙ፣ እንግዳው የቅኔ መምህር ሙሉ ቤት መወድስ ተቀኝቶባቸው ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡
ከቅኔው ውስጥ የማስታውሰው ዋዌውን (ከግማሽ በኋላ ያለውን) ነውና እነሆ፡-
“ስስትኒ ዘወልደ ነዌ ዘሐዋ ሚካኤል አስመኮ፡፡
ተወልደ ላሊበላ ወልኀቀ በድቡኮ፡፡”
ትርጉሙ በሐዋ ሚካኤል የተንሰራፋው የነዌ ልጅ ስስት የተወለደው ላሊበላ፣ ያደገው በድብኮ ነው ማለት ነው፡፡  
እንደዚሁም በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በምትገኘው በደብረ መድኃኒት ጨጎዴ ሐና፣ አንድ ስስታም ቄስና አንድ ሆዳም ዲያቆን በአንድ ቀን ይሞታሉ። ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሺፈራውም ከዚሁ ሁኔታ በመነሣት የሚከተለውን መወድስ ቅኔ ዘርፈዋል፡፡
አንተ ቄስ የመክፈልቱ አለቃ፣
ወ አንተ ዴማስ የቤተልሔም ጎናዴ፡፡
እርሻችሁ ቀፈት ታርሶ የደቀቀው ለስንዴ፡፡
በብዛት ከናንተ ተነሥቶ ተሰጠ ለዳንዴ፡፡
ተጠንቀቅሂ አያ ተማሪ እንዳታሳስትህ በዘዴ
ብዙዎችን ቄሶች አስታለችና መክፈልት ወረገዴ።
ዝኒ ስስት የመጋዣዎች ነጋዴ፤
አጋሰስ አጋሰሱን አነሣው በጨጎዴ፡፡
ወረገዴ አግብታ የፈታች ጋለሞታ ስትሆን አጋሰስ ለጭነት ፈረስ የሚሰጥ ስያሜ ነው፡፡ ብዙ የሚበላና የሚያጋፍር ሰውም አጋሰስ ተብሎ ይሰደባል፡፡
በአንዳንድ ስስታም ቄሶችና ሆዳም ዲያቆናት ተርታ፣ ሆዳም መነኩሴዎችንም በየደብሩ ማግኘት አይገድም፡፡ መሪጌታ ልሣነ ወርቅ የተባሉ ሊቅ የአንዲት ሆዳም መበለት ድርጊት አስገርሟቸው የሚከተለውን ዋዜማ ተቀኝተውባታል፡፡
(ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ 1997 ገጽ 20)
ሖረት እሙሐይ
ለዘዚአሃ ኅብስት ወለዘዚአሃ እንጎቻ፡፡
እሙሐይ ከርሠ እንቲአሃ አኮኑ ስልቻ፡፡
ወአዕጋሪሃ ኀነብር በላዕለ ሠለስቱ ጉልቻ፡፡
ወለመደት ካዕበ ብቻ ለብቻ፡፡
እስመ ዛቲ የሰይጣን ኮርቻ፡፡
በእርግጥም ሊቁ እንዳሉት፣ ሆዳምና ስስታም ሰው የሰይጣን መፈናጠጫና መቀመጫ (ኮርቻ) ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡ በሊቁ በልሳነወርቅ ትዝብት መሠረት መነኩሴይቱ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት አታውቅም፡፡ በመሸ በነጋ እግሮቿን በሦስት ጉልቻዎች ላይ አነባብራ ማስቀመጥ፣ በየዕለቱ እንጎቻና ቂጣ እየጋገረች ለብቻዋ ስለምትበላ ሆድዋ እንደ ስልቻ የተቆዘረ፣ ዐመለ ቢስ ጠባየ ልክስክስ፣ የሰይጣን ፈረስ እንደሆነች እንረዳለን፡፡
በከተሞች አካባቢ ብዙ ጊዜ የተለመደው የብፌ ግብዣ ነው፡፡ ታዲያ አንዳንድ ስስታም ሰው የማይበላውን ሁሉ ቆልሎና የራስ ዳሽን ተራራን አስመስሎ ከወሰደ በኋላ አንገዋልሎና ነካክቶ ይተወዋል፡፡ የሰውን ድግስም ያበላሻል፡፡ አንድ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ስብሰባ ከተደረገ በኋላ፣ በቤተ መንግሥት የራት ግብዣ ተደርጎ እንደነበር አንድ ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡ በግብዣው ላይም ጋዜጠኞች ተጋብዘው ነበርና በወቅቱ የብፌው ድግስ ሁሉ አይቅረኝ የሚል ጋዜጠኛ፤ በሚያስፈራ ሁኔታ ምግብ በሳህኑ ላይ ቆልሎ ወደ መቀመጫው ሲራመድ ሰው ሁሉ እንደ ጉድ ይመለከተዋል፡፡ ከመኻል አንድ የኤሌክትሪክ ገመድ በድንት ሲጠልፈው የያዘው ምግብ በአማረው የቤተ መንግሥት ሥጋጃ ላይ ይበታተናል፡፡ እርሱም ለመውደቅ ይፍገመገማል፡፡ ወዲያው ሁኔታውን ሲከታተልና ሲታዘበው የነበረ አንድ ሰው “የት አባክ! ይበልህ! አንተም አብዝተኸው ነበር” ብሎ ገላመጠው አሉ፡፡
አድማሱ ጀንበሬ (1991 ገጽ 179) በአሳተሙት መጽሐፈ ቅኔ ዝክረ ሊቃውንት መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ አንድ ባለቅኔ “ሰዴ በተሰኘ ቦታ የሚኖሩ ካህናት በስስት ተጠምደው ተማሪን ቁራሽ እንጀራ ሲነፍጉት ተመልክቶ፣ እንዲህ ብሎ ፍርንዱስ መወድስ ተቀኝቶባቸዋል፡፡
“ዕሩቃነ መስጠት ልብስ ካህናተ ሰዴ፣
ወበምድረ ሰዴ ባቢሎን ሀገረ መከራ ክፋት፡፡
አልቦ ዘይዜከሮ፣
ለኤርምያስ ተሜ ዘአልቦ እራት፡፡
እስመ ይብሉ በአንድነት፡፡
ነፍስነ ትፃእ ምስለ ኢሎፍሊ መክፈልት፡፡
እጽሕፍሂ ዜና ግብሮሙ በብርዐ ልሳን ፅርፈት፡፡
እንዘ እብል እምኔሆሙ ይኄይሱ ከለባት፡፡
ካነሱብኝ ዘንድ ከፊቴ ግማሽ እንጀራ ካህናት፡፡
አምጣነ ከለባት ያተርፉ ሥጋ መዋቲ ለአራዊት”
ይህ ቅኔ ስለሰዴ ካህናት ስስት ያስረዳናል። ካህናቱ መስጠት የማያውቁ፣ በስስት ሸማ ተሸፋፍነው የሚኖሩ፣ ሀገራቸው የመከራና የክፋት እንደሆነ፣ ተማሪን የማያስታውሱና ለተማሪም የማይዘከሩ፣ ለአንዲት ቁራሽ መክፈልት ነፍሳቸው የምትወጣ እንደሆነች ያስገነዝበናል፡፡ ከእነዚያ ካህናትም ውሾት የተሻሉ እንደሆኑ፣ እንዲያውም ውሾች ለአራዊት ከሚበሉት ሥጋ እንደሚያተርፉ ትዝብቱን መነሻ አድርጎ ተቀኝቶባቸዋል፡፡
ካህናት ቀድዶ ማልበስ፣ ቆርሶ ማጉረስ ጥሩ እንደሆነ ቢሰብኩም ራሳቸው ግን አያደርጉትም። አንድ ካህን ዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ስብከታቸውን ሲዘሩ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ይለብሰው ላጣ ይስጥ፣ አንድ እንጀራ ያለው ግማሹን ይጎርሰው ለተሳነው ያካፍለው” ሲሉ ያረፍዳሉ፡፡ ባለቤታቸው ለካ ስብከታቸውን ሲሰሙ ቆይተው ወደ ቤት እንደተመለሱ የባለቤታቸውን (የቄሱን ልብስ ከሁለቱ አንዱን) ለእኔ ቢጤ ይሰጣሉ፡፡ ሰባኪው ቄስ ድግሳቸውን ሲኮመኩሙ አረፋፍደው ወደ ቤት ሲመለሱ “አንቱየ ጧት በተስኪያን በተናገሩት መሠረት,ኧ ከእርስዎ ሁለት ልብስ አንዱን ለእኔ ቢጤ ሰጠሁት ቢሏቸው “በስመአብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ! እኔ የሌሎችን አልኩ እንጂ የእኔንማ ለምን” ብለው ባለቤታቸውን ተቆጡ፡፡ ባለቤታቸውም በዚህ ተናድደው “ያንቱን ያንቱን ይተረጉሙ፣ የሌላውን ይደረግሙ” ብለው አሳፈሩዋቸው፡፡
ስስትና ሆዳምነት፣ እንደማይጠቅም ዓለምም ከንቱ መሆንዋን መሪጌታ አስካል (አድማሱ 1991 ገጽ 142) እንደዚህ በማለት በመወድስ ቅኔያቸው ይመክሩናል
ወዴት ያድር ይሆን ልብየ ያለም መንገደኛ፣
እደርሳለሁ ብሎ ተቤት መንገድ ሲጀምር በማታ፡፡
ይሆነው ይመስል ጥቅሞ የእነዓለሚቱ ጨዋታ፡፡
ጊዜው መሽቶበታልና ሳይሰፍር ከቦታ፡፡
ምንም ባትሰድ ሰው አሰናብታ፡፡
ጨዋታ ወዳድ ዓለም እያጫወተች ሁሉን በተርታ፡፡
እኛንም ሲያታልለን የዓለሚቱ ልጅ ደስታ፡፡
ገነት እናታችን ትቆየናለች ደጃፍዋን ዘግታ፡፡
ወይም አልያዝነ ጥቂት ከወንጌሉ ቃል ሸመታ፡፡
አዳም ያቆየው ተከራክሮ ገበያ ንስሐ ሳይፈታ፡፡
ይህንኑ የካህናትን ስስታምነትና ይሉኝታቢስነት የሚያመለክት ሌላ መወድስ ልጨምር፡፡
ቅኔው ፍርንዱስ (ግእዝና አማርኛ ነው፡፡ (አድማሱ 1991 ገጽ 36)
በአልባሰ አይሁድ ቅንዐት ወምቀኝነት፣
ዑፅፍታ ታንሶሱ ወታስተርኢ ኁብርታ፡፡
ልበ ካህናት ወለት እንተ ይእቲ አውታታ፡፡
ወሞተ በቅንዐት፣
ቀኛዝማች አማኑ አማኑኤል ምታ፡፡
ልበ ካህናት ጋለሞታ፣
እስመ ታቀንዖ ፈድፋደ ግራዝማች ደብዮን አግብታ፡፡  
ሞተሂ ያለ ጊዜው በጸሊዐ ቢጽ በሽታ፡፡
መርዓዊ ሀብተ ክህነት ዘተፍኀረ ለደስታ፡፡
ወእምላ ኩሉ ነገር ታሳዝነኛለች ይሉኝታ፡፡
አምጠነ ካህናት ቀተልዋ ወተቀብረት ሳትፈታ፡፡
ካህናት የአይሁድ ልብሳቸው በሆነው በቅንዐትና በምቀኝነት እንደተሸፈኑ፣ ልባቸው ይህንኑ የክፋት መጎናጸፊያ ተከናንባ እንደምትኖር ቀኛዝማች አማኑ የተባለው የምቀኝነትና የቅንዐት ባልዋም ከዚሁ ድርጊቱ የተነሣ እንደሞተ ቅኔው ይነግረናል፡፡
የካህናትን ልብም ሁሉን ከምታሰስት ጋለሞታ ጋር ያመሳስላታል፡፡ ግራዝማች ዳብዩ የዚህች የምታስቀናው የጋለሞታዋ ቅንዓት ባል እንደሆነ፤ ለደስታ የታጨው ሙሽራው የክህነት ሀብትም ጓደኛን በመጥላት በሽታ ተይዞ ያለጊዜው ሞተ ይለናል ባለቅኔው፡፡
ከሁሉም ይልቅ ይሉኝታ ታሳዝነኛለች፣ ምክንያቱም ካህናት ገድለዋት፣ ሳትፈታም ተቀብራለችና ይሉናል ሊቁ፡፡ ካህን እግዚአብሔርን ያገለገለ እየመሰለ፣ በሌላ ልቡ ገንዘብ ስለሚማርከው ይህንኑ አስመልክቶ አንድ ባለቅኔ እንዲህ ይለናል:-
ሥላሴ
ኢትክሉ ተቀንዮተ
ለእግዚአብሔር ወለንዋይ
ለዘይብል አምላክ ሰማዒ መቅድመ ኩሉ ታፍቅሮ፡፡
ለገብርከ አፍቅሮ ነዋይ ይእዜ ሠዓሮ፡፡
እመሰ ለወርቅ አፍቀርከ ወአስተባዛኅከ ክብሮ፡፡
እንዘ በጥንቁቅ ታነብሮ፡፡
አእምር አእምር አእምሮ፡፡
እመ ኮንከ ለንዋይ ገብሮ፡፡
ትርጉም (ካህናት ሆይ) ለእግዚአብሔር እና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡ ያለህን አምላክ ሰሚ ከሁሉ በፊት ታፈቅረው ዘንድ አገልጋይህ ገንዘብ መውደድን ዛሬ አሰናብተው፡፡ ወርቅን ብትወድ ክብሩንም ብታበዛ በጥንቃቄ እያኖርኸው የገንዘብ አገልጋይ እንደሆንህ ማወቅን እወቅ፡፡ “አንድ አገልጋይ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻለውም፡፡` እንደተባለ እግዚአብሔርን እወድዳለሁ አከብራለሁ የሚል ሰው ገንዘብን በጣም የሚያፈቅር ከሆነ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ በማለት ለገንዘቡ ሲንሰፈሰፍ የፈጣሪውን ትእዛዝ መፈጸም የሚያዳግተው መሆኑን ባለቅኔው ያስገነዝባሉ፡፡
በስስታም ካህናት ላይ በርካታ ቅኔዎች ተዘርፈዋል፡ ታላቁ ሊቅ ክፍለ ዮሐንስ በበኩሉ “እምከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ” የሚል መወድስ ሲቀኝ፣ አንድ ሌላ ባለቅኔ ደግሞ “ካህነ ቀላዋጭ ኢትናቅ ምድጥ ዋዕ ነጋዴ” ብሎ ተቀኝቷል። ክፍለ ዮሐንስ ካህን ከመሆን የከብት እረኛ መሆን እንደሚሻል ሲገልጥ ሌላው “ቀላዋጩ ስስታሙ ካህን የምጥዋን ነጋዴና አራሽ ገበሬን አትናቅ ያለእነርሱ መኖር አትችልምና” ብሎ በካህናት ላይ መወድስ ተቀኝቷል፡፡ እስቲ የክፍለ ዮሐንስን ቅኔ እንመልከት:-
እምከዊነ ካህን ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ፣
ወጎለ እንስሳ ትትበደር እምቤተ መቅደስ ዐባይ፡፡
እስመ ቤተ መቅደስ ኮነት ቤተ ፊያታይ፡፡  
ወበላዕለ ኖሎት ኢሀለወ፣
በላዕለ ካህናት ዘሀሎ ዕከይ፡፡
ትእምርተዝኒ ከመንርአይ፡፡
በጎለ እንስሳ ሠረቀ ዘኢየዐርብ ፀሐይ፡፡
ወኖሎት ተዛውዑ ምስለ ሐራ ልዑል ሰማይ፡፡
ዓዲ እምቅድመዝንቱ እምከዊነ ኖሎት ወመራዕይ
ከመ ተጻውዑ ደምፀ እግረ ቃለ ዜና ሠናይ፡፡
ወልደ አንበረም ለምስፍና ወለቅብዐ መንግሥት ወልደ ዕሤይ፡፡
ከላይ የቀረበው ቅኔ ወደ አማርኛ ሲመለስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ካህን ከመሆን እረኛ መሆን ይሻላል፡፡ የእንስሶች በረትም ከታላቅ ቤተመቅደስ ትመረጣለች፡፡ ቤተመቅደስ የሽፍታ ቤት ሆናለችና፡፡ የዚህንም ምልክት እናይ ዘንድ የማይጠልቅና የማይጨልም/ፀሐይ በእንስሳት በረት ወጣ፡፡  እረኞችም ከመላእክት ጋር አብረው ተጫወቱ። ዳግመኛም ከዚህ በፊት ከእረኞችና ከመንጐች ቦታ የአንበረም ልጅ (ሙሴ) ለመስፍንነት=@ የዕሴይም ልጅ (ዳዊት) ለመንግሥት ቅብዓት እንደተጠሩ የመልካም ወሬ ኮቴ ተሰማ፡፡
እረኞች ከብቶቻቸውን አሠማርተው እርስበርስ ከመጨዋወት በቀር ሌላ ተንኮል አያስቡም፡፡ ለጊዜው በጨዋታም ቢጣሉ ወዲያውኑ ይስማማሉ። መስማማታቸው ከቅንነት የተነሣ ሲሆን ክርስቶስ በእንስሳት በረት ሲወለድ እነርሱ (እረኞች) ከመላእክት ጋር አመስግነውታል፡፡
ከዚህም የተነሣ ባለቅኔው ከካህንነት እረኝነት፣ ከቤተመቅደስ በረት ይሻላል ይላሉ፡፡ ደግሞም ክርስቶስ ስለቤተመቅደስ ሲናገር፤ ቤቴ የጸሎት ቤት ነበር፤ እናንተ ግን የቀማኞችና የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” ብሎዋል፡፡
ይህም እውነት ሊነገርባትና ሊሠራባት የተመሠረተችው ቤተመቅደስ፣ ማታለያና መሸቀጫ ስትሆን የከብቶች በረት ግን የክርስቶስ መወለጃና የመላእክት ማመስገኛ መሆኗን ባለቅኔው ገልጠዋል። (ካህሣይ ገ/እግዚአብሔር ብፁዓን እነማናቸው፡፡ 2004 ገጽ 53)  

Read 4612 times