Monday, 31 March 2014 11:22

“በርናባስ” አተታ የበዛበት መጽሐፍ

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

የመጽሐፉ ርዕስ - በርናባስ
ደራሲ - ትግዕሥቱ ተክለማርያም
የታተመበት ዘመን - 2005 ዓ.ም (ግንቦት)
አሳታሚ የኢትዮጵያ ደራስያን ነበር እና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ተዟዟሪ ሂሳብ (ፈንድ)
የታተመበት ቦታ - አዲስ አበባ ብርሃንና ሰላም ማ/ድርጅት
የገፅ ብዛት - 353
የሽፋን ዋጋ - 50.00
ዘውግ - በአንድ ታሪካዊ ክስተት ላይ የተመሠረተ ረጅም ልብ ወለድ፤
ወኪል ባለ ታሪኮች፤
በርናባስ፣ ዶ/ር ሃንፍሬይ እና እሌኒ፣
ሌሎች ሠርዌ ባለታሪኮችም አሉ፤
ታሪኩ በአጭሩ
የ1966 ዓ.ም አብዮት ባመሰቃቀለው ቤተሰብ ውስጥ ትኩረት ሰጥቶ (መነሻ አድርጐ) የተጻፈ ነው፤ ዶ/ር ሃንፍሬይ የ1967 ወይም የአብዮተኛው ትውልድ አባል ናቸው፤ የተቃዋሚ (ህቡዕ) ድርጅት አባል በመሆናቸው ምክንያት በደርግ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ውለው በአንድ ለጊዜው ባላወቁት ሰው ምክንያት ለርሸና እንደወጡ ተደርጐ ከሞት እንዲያመልጡ ዕድል ይመቻችላቸዋል፡፡
ሌላው ሁሉ ቦታ እንደልብ የሚያፈናፍን ስላልነበረ በአፋር በኩል እንዲወጡ ከሞት ያተረፋቸው መኮንን ይመክራቸዋል፤ አፋር ሄደው ወ/ሮ ሐዋ የሚባሉ ደግ የአፋር ባልቴት አግኝተው ተገቢውን እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል፤ “ሐንፍሬይ” የሚለው ስም የወጣላቸውም በአፋሮች ነው፡፡
ሐንፍሬይ በመኮንኑ አማካይነት ከሞት ተርፈው ከአገር የመውጣት ዕድል ቢያገኙም ብቸና አካባቢ ታስተምር ለነበረች አንዲት እህታቸው የተነገራት ግን ሞቷል ተብሎ ነው፡፡ ሆኖም ሐንፍሬይ በአፋሮች ድጋፍ ወደ አሜሪካ የመግባት እና የመማር ዕድል ይገጥማቸውና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቅቃሉ፤ ኢህአዴግ ስልጣን እስከሚጨብጥ ድረስ ያሉበት አይታወቁም ነበር፡፡ ግን ምስኪኗን እህታቸውን (ወለላ ትባላለች) የማየት ጉጉታቸው እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ራሳቸውን ቀይረው ወደ አገር ውስጥ በመግባት እህታቸውን ለመፈለግ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ፤ ግን አይሳካላቸውም፡፡ በእረፍት የመጡት ለአንድ ወር ቢሆንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ራሳቸውን ለመደበቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ከተማሪዎቻቸው መሃል “በርናባስ” የተባለ የደብረዘይት ልጅ ይገኝበታል፤ በርናባስ ወደ ደ/ዘይት የመጣው ከ10 ዓመት በፊት ቢሆንም ተወልዶ ያደገው ደ/ማርቆስ ነው፤ ማርቆስ ገና የ5ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ጀምሮ እሌኒ የምትባል የኮሎኔል ታደለን ልጅ ይወዳል፤ ላይለያዩ (ትልቅ ሰው ሲሆኑ) በትዳር ተሳስረው ሊኖሩ ቃልኪዳን ይይዛሉ፡፡ ግን ደግሞ ቦታ ለያያቸውና ለድፍን 10 ዓመታት ሳይገናኙ ቆዩ፡፡
በአጋጣሚ ግን ለዳታ ስብሰባ በርናባስ ወደ የቦቅላ (ጐጃም) የመሄድ ዕድል ያጋጥመዋል፤ ያኔ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው፤ ዕሌኒን ለማየት እጅግ ጓጉቶ  ቢሄድም ሊያገኛት አልቻለም፡፡
ከዚህ ጐን ለጐን ዶ/ር ሃንፍሬይ እህታቸውን አንዴ ብቻና፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሐረርና “አለች” በተባለበት ቦታ ሁሉ ፈልገው ስላጧት ተስፋ ወደመቁረጥ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ አንድ ምሽት ፒያሳ አካባቢ አንዲት ወጣት መኪናቸውን ተከትላ ስትከንፍ ያዩና ያቆሙላታል፤ ወጣቷ ሴትኛ አዳሪ ብትሆንም ዶ/ሩ አዝነውላት ብር ይከፍሏትና ራት ጋብዘው ወደቤታቸው እየወሰዷት እያለ መንገድ ላይ ትታመማለች፡፡
ወደጓደኛቸው ክሊኒክ ወስደው አሳከሟት፤ ታሪኳን ሲያውቁም ከቤታቸው ወስደው ያስቀምጧታል፤ ከወሬ ወሬም ለምን ሴተኛ አዳሪ መሆን እንደፈለገች ታዋያቸዋለች፤ አባቷን (በዚያ ጊዜ ታስረዋል) ለማየት እስር ቤት አብረው ይሄዱና የሚተዋወቁ ሰዎች ይሆናሉ፤ እንዲያውም ኮሎኔሉ አባቷ የታሰሩት ዶ/ር ሃንፍሬይን በመግደል ወንጀል ተከሰው ስለተፈረደባቸው ነው፡፡
ኮሎኔል ታደለ ሃንፍሬይን ገደልሁት ብለው የውሸት ሪፖርት ለመንግሥት ካቀረቡ በኋላ እንዲያመልጥ መንገዱን አመቻችተዋል፤ ከዚያም አልፈው እህቱን ወለላን አግብተው ወልደው ከብደው ይኖሩ ነበር፡፡ ከልጆቻቸው አንዷም በሴተኛ አዳሪነት የተዋወቋት ዕሌኒ ናት፡፡
ዕሌኒ አዲስ አበባ የመጣችው “አባቴን እጠይቃለሁ” በሚል ምክንያት የልጅነት ፍቅረኛዋን (ዕጮኛዋን) በርናባስን ለመጠየቅ ነው፡፡ ዕሌኒ ኑሮ መርሯት፣ ዕድል ፊቱን አዙሮባት የምታደርገው ስታጣ ነው ሴተኛ አዳሪ መሆን የወሰነችውና በአጋጣሚ ሐንፍሬይን ያገኘቻቸው፤ ሃንፍሬይን አግብታ ለመኖር ወስና በተቀመጠችበት ወቅት ድንገት በርናባስን ታገኘውና የሆነችውን ሁሉ ትነግረዋለች፤ ተላቅሰው ከተለያዩ በኋላ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሃንፍሬይ አባቷን ከእስር አስፈትተው የዕሌኒ እውነተኛው ባል እሳቸው ሳይሆኑ በርናባስ መሆኑን ያስረዷታል፡፡
ወዲያው ዶ/ር ሃንፍሬይ ለዘመናት ሲፈልጓት ኖረው ያጧትን እህታቸውን ወለላን (የዕሌኒን እናት) ያገኛሉ፤ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ በርናባስና ዕሌኒም ተጋብተው ሴት ልጅ ይወልዳሉ፤ በርናባስ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን በማዕረግ ያጠናቅቃል፤ በመጨረሻም “ገናሌ” የሚባል ግዙፍ የእርሻ ኮርፖሬሽን ከበርካታ ባለሃብቶችና የዕውቀት ሰዎች ጋር ያቋቁማሉ፤ ታሪኩ በዚሁ ይደመደማል፡፡
መጽሐፉን (በርናባስን) ለመገምገም ዘጠኝ መመዘኛዎችን ተጠቅሜያለሁ፡፡ እነሱም:-
አወቃቀር (ንድፈ ታሪክ)
ቋንቋ
የወኪል ባለ ታሪኮች አመዳደብ፤
ሴራ
ተአማኒነት
ታሪኩ የተፈፀመበት ጊዜና ቦታ፣ (መቼት)
የተነባቢነት ጉልበት (ልብሰቀላ)
የታሪኩ ጥድፊያ (ጡዘት) እና
መፍትሔ ናቸው፡፡
1.አወቃቀር
በርናባስ የተዋቀረው አብዮቱ ባስከተለው ጦስ ምክንያት ለአደጋ በተጋለጠ አንድ ቤተሰብ ውስጥ የደረሰውን ወይም ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊ ምስቅልቅልና ውጣውረድ ለማሳየት ነው። በዚህ የመዋቅር ችግር የለበትም፡፡ ንድፈ ታሪኩ የተዋቀረበት መንገድ መልካም ነው፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ 53 ገፅ መውሰዱ ግን ተገቢ አይደለም፤ ፈጥኖ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ቢገባ ተገቢ ነበር፡፡
2. ቋንቋ
በርናባስ ላይ የሚታይ ጉልህና መሰረታዊ የቋንቋ ግድፈት ባይኖርም ሊታረሙ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ግን መዘንጋት የለበትም። አብዛኛው የመጽሐፉ ታሪክ የሚያልቀው ደራሲው ስለ ወኪል ባለታሪኮች እየነገረን እንጂ እነሱ (ባለታሪኮቹ አያዳክሙንም  (አይወያዩም) እርስበርሳቸው ቢዳክሙ(ቢወያዩ) መልካም ነበር፡፡ ከአንድ አንቀጽ ወደ ሌላው ሲሸጋገሩ ምክንያታዊነት የሚጎላቸው (ተያያዥነት) የሌላቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ (ገፅ50፣51፣49፣52፣71)
“በጎች ልጆቻቸውን” “ከእንደገና” (117) “በዛሬው ጊዜያት (74)” አንተና አንቱ (ገፅ 85)፣ አንቺ እና አንቱ (92፣94)፣ የመግቢያ ኢንትሮዎችን (115) ወዘተ አይነት አጠቃቀም አልፎ አልፎ ስለሚያጋጥም በታሪኩ ፍሰት ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል፡፡
አላስፈላጊ አታታ (አሰስ ገሰስ ማውራት) ያበዛል፤ አንድ ነገር ይጀምርና ምንም አይነት መቋጫ ሳያበጅለት ወደ ሌላ አታታ ይዘላል፡፡ ይህ በእኔ ግምት የጽሑፉ ጉልህ ችግር ነው፡፡
3. የወኪል ባለ ታሪኮች አመዳደብ፤
ወኪል፤ ባለታሪክ ገፀ ባሕርይ ለሚለው ቃል በአቻነት የተጠቀምሁበት ነው፡፡ ምክንያቱም “ገፅ” ማለት “ፊት” ሲሆን “ባህርይ” የሚለውም ሊታይ የማይችል ረቂቅ ነገር ማለት ነው፡፡ ባህርይ ውስብስብ ነው፤ መለኪያውም ከባድ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም “ገፀ ባህርይ” የሚለው ቃል አይመጥነውም፡፡
የምንነጋገረው ስለ አንድ ታሪክ ነው፤ በልብወለድ መልክ ቀርቦ የምናነበው፤ ታሪኩን የሚከውኑልን ደግሞ ደራሲው ወዶና ፈቅዶ ውክልና የሚሰጣቸው ምናባዊ ሰዎች ናቸው፤ ወኪሎቹ ልክ የምናውቃቸው ያህል ሊቀርቡን፣ “አጀብ” ባያሰኙን እንኳ “ልክ ነው፤ እንዲህ ሊሆን ይችላል ወዘተ” የምንላቸው አይነት መሆን አለባቸው፤ ሰው ከሌለ ባህርይ የለም፤ ባህርይ የሚገለጠውም በተግባር እንጂ በምናብ አይደለም፡፡
ስለዚህ ገሃዱን የምናውቀውን ዓለም ተግባር ወይም አንድ ድርጊት ይከውኑ ዘንድ ታሪክ ሰሪዎቹን በጽሑፎቻችን ውስጥ እንመድባለን፡፡ ይህ ምደባ ውክልና ነው፤ አንድ ባለንብረት በንብረቱ ላይ ወኪል አስቀመጦ ይቆይና ወካዩ ሲሞት የተወካዩ ውክልና ወዲያውኑ ቀሪ ይሆናል፡፡ በልብወለድ ውስጥ የምንወክላቸውም ልብወለዱ ሲያልቅ ውክልናቸው ቀሪ ይሆናል፤ በሌላ ልብወለድ ሌላ ወኪል ያስፈልጋላ!
በዚህ ረገድ የትዕግሥቱ ወኪል ባለታሪኮች በጋብቻና በፖለቲካ የተሳሰሩ በመሆናቸው በታሪኩ ላይ የሚያሳድሩት (አላስፈላጊ ጫና) የለም፡፡ ሆኖም ቢቀሩም ቢኖሩም የማይጐዱና የማይጠቅሙ ሰርዌ ባለታሪኮች አሉ፡፡ ሰርዌ ባለታሪክ የሚያስፈልገው ዋናው ባለ ታሪክ ወደ ዘመቻ ሲጓዝ (ታሪክን ሲያከናውን) የጠጠር ያህልም ቢሆን ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
 4. ሴራ (ፕሎት)
ሴራ በመሠረቱ አንዱን ወኪል ባለ ታሪክ ለመጣል፤ ወይም ሥልጣኑን፣ ገንዘቡን፣ ፍቅረኛውን ወይም ሌላ መሠረታዊ ጥቅሙን ለማሳጣት በተወከለ በሌላ ተቃራኒ ባለ ታሪክ መካከል የሚደረግ ሸር፣ ትብተባ፣ ወይም አጥፍቶ የመኖር ትንቅንቅ ነው፡፡
በበርናባስ ውስጥ የምናገኘው የዚህ አይነት የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ወይም ከተቃራኒ ወገን የተጠነሰሰን አደገኛ ሴራ በጣጥሶ ለማለፍ የሚደረግ ግብግብ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ በተስፋና በቀቢፀ ተሥፋ፣ በአገኛት አጣት ህቅታ ላይ የተመሰረተ፤ በእምነትና ክህደት መሃል የሚወዛወዝ የገደል ዛፍ አይነት በመሆኑ ሴራው ልል ነው፤ ይህ የታሪኩ ግዴታ እንጂ የደራሲው ድክመት አይደለም፡፡
በበርናባስ ውስጥ ያሉት ዋና ዋናዎቹ ባለታሪኮች ተመሳሳይ ባህርይ ይታይባቸዋል፤ ለምሳሌ ሃንፍሬይ የጠፋች እህታቸውን ለመፈለግ የሚዋትቱ፤ ለሴተኛ አዳሪዎችም ሆነ ለተማሪዎቻቸው ደግ ማድረግ የሚቀናቸው ዶ/ር ናቸው፡፡ የዕሌኒ እናት ወለላም “በቀይ ሽብር ተገድሏል” ተብሎ የተነገራት ወንድሟ ሞት ቅስሟን ሰብሮት፤ በወንድሟ ሞት ምክንያትም ባሏ ኮሎኔል ታደለ ለከርቸሌ መዳረጋቸው በሃዘን ላይ ሃዘን ተደርቦባትና ችጋር ከሃዘን ጋር እየቆነደዳት የምትኖር ምስኪን መምህርት ናት፡፡ ዕሌኒና በርናባስም አንዱ ሌላውን ፍለጋ ሲባዝኑ የኖሩ ምስኪን ፍቅረኛሞች እንጂ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የተፋለሙ ባላንጣዎች አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ በበርናባስ መጽሐፍ ውስጥ ደጋግና አፍቃሪ፣ ለፍቅረኛቸውም ታማኝ ባለታሪኮች እንጂ የአንዱን ሰናይ ግብር ለማጥፋት የሚወራጭ መሰሪ የለም፡፡ ይህ ማለት ግን የመጽሐፉን ተነባቢነት ዝቅ ያደርገዋል ማለት አይደለም፡፡
5. ተአማኒነት
ልብ ወለድ ምንም እንኳ ቃሉ “ሃሳብ ወለድ፣ ምናባዊ ፈጠራ” ማለት ቢሆንም የምንኖረውን ህይወት ነው ደራሲው ሚገልጥልን፤ የምንኖረውን ስል ግን ኖረን ልብ የማንለውን፤ እያደረግነው የማናውቀውን፣ ወይም አውቀንና “ይሁነኝ” ብለን የምንተገብረውን እንደ መስተዋት ፊትለፊታችን ቁጭ አድርጎ ራሳችንን የሚያሳየን ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ልብወለድ ህይወታችን ነው፤ ህይወት ደግሞ እውነት ነው፡፡ በዚህ አግባብ በርናባስን ስናየው የአንዲት አገር ልጆች ጎራ ለይተው እንደ ክፍልፋይ ቁጥር ራስ በራሳቸው በተጠፋፉበት በዚያ ወቅት (የቀይና ነጭ ሽብር ወቅት ማለቴ ነው) አንዱ ለሌላው ነፍስ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ተአምር በሚመስል ነገር መዳንም ምክንያት መሆኑ እውነት ነበርና የበርናባስ ታሪክ ተአማኒ ነው፡፡
ሆኖም በቴክኒክ ድክመት የሚከሰቱ አንዳንድ ልል ገጠመኞች መኖራቸው ደግሞ አይካድም። ለምሳሌ፡- ሃንፍሬይ የታሰሩት ብቸና መሆኑን ይነግረንና መቼ እንደሄዱ ሳናውቅ ደ/ማርቆስ ላይ በኮሌኔሉ ድጋፍ ሲያመልጡ እናያለን (ገፅ 80+87)፡፡
የኮሎኔሉ ድንገት ከእስር መፈታትም ሌላው የተአማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፤ ኮሎኔሉ ሃንፍሬይን ገድለሃል ተብለው ተፈርዶባቸው ነው ከርቸሌ የገቡት ግን በይግባኝ ወይም በምህረት፣ አለዚያም የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው፤ ምክንያቱ ሳይታወቅ በሃንፍሬይ አማካይነት ተፈትተዋል ይለናል፡፡ የዚህ ጉዳይ ተአማኒነቱ ልል ነው፡፡ ያን ያህል የተንሰፈሰፉላትን እህታቸውን ሲተዋወቁ ዶ/ር ሃንፍሬይና ኮሎኔል ታደለ ያሳዩት ሁኔታም እውነት አይመስልም፡፡
ኮሎኔሉ ለዚያን ያህል ዘመን አብረው ሲኖሩ የሃንፍሬይን ማምለጥ ለሚስታቸው (ወለላ) ሳይነግሩ መኖራቸው የተገለጠበት መንገድም አሳማኝ አይደለም፤ ቢያንስ በደርግ እንዳልተገደሉ፤ ይህንንም ራሳቸው ኮሉኔሉ እንደተወኑት ለሚስታቸው፣ (ለዶ/ሩ ደግሞ እህት) ቢነግሯት ኖሮ የወለላ ሃዘን ዕጥፍድርብ አይሆንም ነበር፡፡
6. ቦታና ጊዜ (መቼት)
ቦታ አንድ ታሪክ የሚፈጸምበት ሲሆን፣ ጊዜ ደግሞ ታሪኩ የሚፈፀመው (የተፈፀመው) መቼ እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡ የበርናባስ ታሪክ ሰኔ 1991 ዓ.ም ተጀምሮ ሰኔ 1997 ባለው ጊዜ ይጠናቀቃል፤ ታሪኩ በዐበይትነት የተከወነባቸው ቦታዎች፤ ብቻና፣ ደ/ማርቆስና አዲስ አበባ ይሁኑ እንጂ እንደገናሌ፣ የቦቅላ፣ አፋር እና አሜሪካ ያሉ ቦታዎችም ተጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በታሪክ መከወኛነት የተመረጡት ቦታዎች፣ ቤቶችና እስር ቤቶች እንድናያቸው ሆነው አልተገለጡልንም፤ በመሆኑም እዚህ ላይ ጥበብ አላየንም፡፡
7. የተነባቢነት ጉልበት (ልብ ሰቀላ)
ልብ ሰቀላ የሚባለው ደራሲው ታሪኩን ሳይሰለቸን በፍጥነትና በጉጉት እንድናነብለት የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመዋቅር፣ በቋንቋና በመሰል ጥበባት ሊገለጥ የሚችል ነው፡፡ በዚህ ረገድ በርናባስ ምንም እንኳ ታሪኩ ለልብ ሰቀላ፣ በጥድፊያ ለማንበብ የሚመች ቢሆንም በአጓጉል አታታ ብዛት ይህንን ታላቅ አቅም እንዲያጣ ሆኗል፡፡
8. ክረት (ጡዘት)
ይህኛው ደረጃ በአንድ ልብወለድ፣ ወይም በፊልም ወይም በቴአትር ውስጥ ደጋፊና አደናቃፊ፣ ጣይና ተጣይ የሚካተቱበት የታሪኩ ከፍተኛ አካል ነው፡፡ በርናባስ ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች ነበሩት፡፡ ለምሳሌ “ሞቶ ተቀብሯል” የተባሉት ዶ/ር ሃንፍሬይ የቁም ሙቷን እህታቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት፣ ዕሌኒ ፍቅረኛዋን በርናባስን ለማግኘት የምታደርገው መዋተት ቀልባችንን ቀጥ አድርጎ መያዝ ሲችል አሁንም በአጓጉል አታታ ውጥረቱ እንዲረግብ ሆኗል፡፡
9. መፍትሔ (ሪዞሉሽን)
በልብወለድም ሆነ በሌሎች መሰል ጥበባት የተጀመረ ፍልሚያ ፍፃሜ ማግኘት አለበት፤ ልክ እንደ ብረት ምጣድ እንደጋመ፣ የአንባቢውን ቀልብም ቀጥ አድርጎ እንደያዘ፡፡ በርናባስ ውስጥ የታሪኩ መፍትሄ (ፍፃሜ) የዶ/ር ሃንፍሬይ እህት ወለላ መገኘትና የዕሌኒና የበርናባስ ፍቅር መቀጠል፤ በአጃቢነትም የገናሌ እርሻ ኮርፖሬሽን ህልም ዕውን መሆን ነው፡፡ ሁሉም የተጠናቀቁት ፍዝ በሆነ መንገድ ስለሆነ ልብ ወለዱ ላይ ተፅዕኖ ሳያደርጉ አልቀሩም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ማጠቃለያ
በርናባስ ሊያነሳ የፈለገውና ትኩረቱን ያሳረፈበት መንገድ (በአንድ ቤተሰብ ላይ ስለደረሰው መመሰቃቀል) በጠንካራ ጎን ሊፈረጅ የሚችል ነው፡፡ የሆሊውድና የቦሊውድ የፊልም ባለሙያዎች በአገራቸውም ሆነ በሌላው ዓለም አንድ ጉዳይ ሲከሰት ወዲያውኑ ፊልም ይሰሩበታል፤ ትዕግስቱ ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ ቀይ ሽብር በቤተሰባችንና በአገራችን ላይ ትቶ የሄደውን ጦስ በልብወለድ መልክ አቅርቦልናል፤ በዚህ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
በመዋቅር፣ በቋንቋ፣ ወዘተ በተለይ ወኪል ባለታሪኮች ራሳቸው ጉዳያቸውን ራሳቸው እንዲያዳክሙን ባለመደረጉ የቋንቋም ሆነ የሃሳብ ከፍታና ዝቅታቸውን፣ ማህበራዊ ደረጃቸውን፣ ፖለቲካዊ አመለካከታቸውንና የህይወት ፍልስፍናቸውን መረዳት አልቻልንም፡፡ ያለፈን ጉዳይ በምልሰት ማሳየት አንዱ የልብወለድ ጥበብ ቢሆንም፤ በርናባስ ላይ ግን እስከሚሰለች ድረስ ስለምናገኝ ለታሪኩ ወደፊት መግፋት ደንቃራ የሆነ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ድጋሚ መታተሙ ስለማይቀር ከላይ የጠቀስኋቸው ፍሬ ሃሳቦች ትኩረት ቢሰጣቸው መልካም ነው እላለሁ፤ ደራሲውንም በርታ ማለት እወዳለሁ፡፡    

Read 1841 times