Saturday, 22 March 2014 13:04

አነጋጋሪው የተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ-ታሪክ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(5 votes)

        “ሀገሬ የህይወቴ ጥሪ” በሚል ርዕስ በ1948 ዓ.ም የተፃፈው የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን የቀረበው ዘንድሮ ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ መጽሐፉ በተመረቀበት ወቅት ስለ ባለታሪኩና መጽሐፉ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አህመድ ሀሰን፤ “አንድ ሰው ታሪክ ለመፃፍ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ ከተነሳ ያልተፃፈውን ታሪክ ማሳየት መቻል አለበት” በሚል ኃይለቃል የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእን መጽሐፍ በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
ባለታሪኩ ከቦታ ቦታ፣ ከአገር አገር ተንቀሳቃሽ ስለነበሩ በመጽሐፋቸው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ማየት አስችለውናል ያሉት ዶ/ር አህመድ ሃሰን፤ “ለተለያየ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ መልክአ ምድርን፣ ሕዝብን፣ ባህልን፣ ሥርዓትን…በትኩረት ለመመልከት ጥረዋል፡፡ የብዕር፣ የወረቀትና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ችግር በነበረበት ዘመን የዕለት ውሎ ማስታወሻ የመፃፍ ልምዳቸው ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ ለማዘጋጀት አብቅቷቸዋል” ብለዋል፡፡
“ማንም ታሪክ ፀሐፊ ሁሉንም ሰው ሊያስማማ የሚችል የታሪክ መጽሐፍ ሊጽፍ አይችልም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ታሪክ ፀሐፊዎች ወገንተኛ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በ1933 ዓ.ም እንግሊዝ ኢትዮጵያን ባትረዳ ነፃነታችን ሊመለስ አይችልም ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ያለ እንግሊዝ እርዳታ ኢትዮጵያዊያን ነፃነታቸውን ማስመለስ ይችሉ እንደነበር ከሚያምኑት አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ፣ በማስረጃነትም እንግሊዞች በከተሞች እንጂ በገጠር የነበራቸው ድርሻ አናሳ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ደራሲው እውነት ተንገዳግዳ ከወደቀችበት ብቻ ሳይሆን ሞታ ከተቀበረችበት ፈንቅላ መውጣት እንደምትችል   በመጽሐፋቸው አሳይተውናል” ብለዋል - ዶ/ር አህመድ ፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ቤተሰባዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ትስስራቸው ከማክተሙ ትንሽ ቀደም ብሎ የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ ታትሞ ቢሆን ኖሮ፣ የልዩነት አቀንቃኞቹን በብርቱ የሚሞግት መፅሃፍ  ይሆን ነበር ሲሉ አድናቆታቸውን የገለፁት የሥነ ጽሑፍ መምህሩ መሰረት አበጀ፤ መጽሐፉ ለህትመት ከተዘጋጀ በኋላ በማማከርና በሌሎች ጉዳዮች ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን በሥራው አጋጣሚ ያዩትን ችግር ሲገልፁም “የአገራችን ትራንስፎርሜሽን የህትመት ኢንዱስትሪው ወዴትና እንዴት ማደግ እንዳለበት አቅጣጫ አለማስቀመጡ ያስገርማል” ሲሉ ተችተዋል፡፡
የመጽሐፉ አርታኢ መምህር ደረጀ ገብሬ በመጽሐፉ ውስጥ “የአርታኢው ማስታወሻ” በሚል ካቀረቡት ጽሑፍ አሳጥረው አንብበዋል። የደራሲውን ሃሳብ፣ የፃፈበትን ዘመን መንፈስና የመጽሐፉን ወጥነት ለመጠበቅ 660 የግርጌ ማስታወሻዎችን የተጠቀሙት አርታኢው፤መጽሐፉ መገረም እንደፈጠረባቸውና ጥያቄ እንዳጫረባቸው በግርጌ ማስታወሻዎቹ ገልፀዋል፡፡
አፄ ዮሐንስ ኢትዮጵያን ትልቅ አገር ለማድረግና ለማስፋፋት ልጅ ምኒልክንና ልጅ አዳልን እንዳነገሡ፣ ራስ ጐበናንም በኬንያ የማንገሥ አሳብ እንደነበራቸው፤ይህንን እቅዳቸውን የሚያውቁ ሰዎች “ለምን ልጆችዎን አያነግሱም?” ቢሏቸው “እኔን ያነገሠኝ እግዚአብሔር ነው፤ለልጆቼም እግዚአብሔር ያሰበላቸውን ይሰጣቸዋል” ማለታቸውን ደራሲው የፃፉ ሲሆን አርታኢው በበኩላቸው፤ “ይህ ሃሳብ በሌሎች መረጃዎች ይደገፍ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል - በግርጌ ማስታወሻ ላይ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ አባት የሐማሴን ሰው መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን አርታኢው አሁንም ይጠይቃሉ፤ “የታሪክ ምርምርና የዘር ቆጠራን እንደገና መመራመር ያስፈልግ ይሆን?” በማለት፡፡
የአቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ ግለ ታሪክ መረጃ የሚሰጡ፣ መገረምን የሚፈጥሩ፣ ክርክርና ሙግት የሚያስነሱ ብዙ ታሪኮችን የያዘ መፅሃፍ ነው። መደመምን ከሚፈጥሩ ታሪኮች መካከል ከአፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ጋር ተያይዞ የተጠቀሰው አንዱ ነው፡፡
“እኔ እዘምታለሁ፤ ሱሪዎን ለእኔ ይስጡኝ ብለው እቴጌ ጣይቱ አፄ ምኒልክን ባያስጨንቋቸው ኖሮ የአድዋን ጦርነት በጣሊያን ላይ ለማንሳት ምንጊዜም ፈቃደኛ አልነበሩም” ይላል - መፅሃፉ፡፡ የዚህ ምክንያቱም አፄ ምኒልክ የትግሬን መሳፍንትና መኳንንት ይፈሩ ስለነበር ነው ብለዋል - ፀሃፊው፡፡ ከንጉሡ ፍርሃትና ከእቴጌይቱ ድፍረት ጋር በተያያዘ የተነገረ ሌላ ታሪክም አለ፡፡ “አዲስ አበባ በጭቃ የተሞላች “ፊንፊኔ” የተባለች ዱርና ገደል ነበረች፡፡ አፄ ምኒልክ በሌሉበት ከእንጦጦ ፍልውሃ ለመታጠብ ወርደው ኮረብታይቱን ለከተማነት የመረጥዋት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው፡፡ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ግን ውራጌዎችንንና ኦሮሞዎችን ስለፈሩ ቆጥ በመሰለው የእንጦጦ ገደል ሠፈሩ”
ሊቢያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን ለኢጣሊያን በቅጥር ወታደርነት ማገልገላቸው፤ በገጠር ኢትዮጵያ ይተገበር የነበረውና ወላጆች ልጆቻቸውን ለማጋባት የሚስማሙበት ባህል ከእስራኤሎች የተወረሰ መሆኑን፤ ልጅ ኢያሱ ሃይማኖቱን ቀይሯል ብለው የሃሰት ወሬ በመንዛት በአገሪቱ ቀውስ እንዲፈጠር ጥረት አድርገው የተሳካላቸው የኢትዮጵያን ዕድገትና መስፋፋት የፈሩ ሦስት የውጭ አገር መንግሥታት መሆናቸውን፤ ኤርትራዊያንን የሚያሳዝን ተግባር ይፈጽሙ ስለነበሩ የአፄ ኃይለሥላሴ ባለስልጣናትና መጥፎ ሥራዎቻቸው፤ ፋሽስት ጣሊያን በተባረረ ማግስት ጠላት ትቶት የወጣውን ንብረት በሽሚያ ለመካፈልና በሃሰት አንዱ ለሌላው መስክሮ የመሿሿሙ ሂደት፤ እንግሊዝኛ ቋንቋ ማወቅ የአዋቂነት መጨረሻ ተደርጐ መወሰድ የተጀመረው ከመቼ አንስቶ እንደሆነ፤ዝሙት አዳሪነት በኢትዮጵያ የተጀመረውና የተስፋፋው እንዴትና ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ…የሚያመለክቱ ብዙ ታሪኮች በመፅሃፉ ውስጥ ተካተውበታል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው እየለፉና እየደከሙ ለስደት የሚዳረጉበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ አደገች ተመነደገች ተብሎ ሲጨበጨብላት ተመልሳ ቁልቁል የመውረድ ተደጋጋሚ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ የዚህ ችግሯ ምንጭ ምን እንደሆነ፤ አድርባይነት፣ ጉቦኝነት፣ ሌላውን ጠልፎ በመጣል እራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ መጣጣር…መነሻቸውን ሊያመለክቱ የሚችሉና ብዙ የሚያስተምሩ በርካታ መረጃዎችን የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡
 በ272 ገፆች የቀረበው “ሀገሬ የህይወቴ ጥሪ” የተሰኘው መጽሐፍ በ250 ብር ነው ለገበያ የቀረበው፡፡ አምስት ቋንቋዎችን ይናገሩ የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲ፤ 17 መፃሕፍትን እንዳዘጋጁ የተጠቀሰ ሲሆን አስራ አንዱ በቤተሰባቸው ዘንድ እንደሚገኝና ከደራሲው ሥራዎች መካከል ታትሞ ለአንባቢያን በመሰራጨት ግለ ታሪኩ የመጀመሪያው እንደሆነ ቤተሰቦች በምረቃ ሥነስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ መፅሃፉ ለህትመት እንዲበቃ በተለያየ መልኩ እገዛና ትብብር ያደረጉላቸውን አካላትም አመስግነዋል፡፡

Read 3864 times