Saturday, 22 March 2014 12:23

ሰይጣናዊ ተልዕኮ ያለበት የፈረንጅ ሥራ ለባህል ወረራ

Written by  ጵርስፎራ ዘዋሽራ
Rate this item
(3 votes)

         በመሠረቱ የሰው ልጅ አእምሮ ሁልጊዜ በሥራ መወጠርና መጨነቅ እንደሌለበት ይልቁንም ከሥራ በኋላ የደከመ አእምሮን በተለያየ የመዝናኛ ስልት ማዝናናት፣ እረፍት ማድረግ፣ መጫወትና መደሰት ተገቢ መሆኑን የሥነልቡና ሊቃውንት ሳይናገሩን በተፈጥሮ ሕግ የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ሲባል ይመስላል እነ ዳንኪራና እነ ጭፈራ የተፈጠሩት፡፡
አእምሮን ለማዝናናት፣ ለማሳረፍ ለሰው ልጅ የሚመከረው እንዲዘምርና ፈጣሪውን እንዲያመሰግን ቢሆንም ሥጋዊ ስሜቱ ስለሚያይልበት አብዛኛው ሰው ከመዘመር ይልቅ መዝፈንን፣ መደነስን፣ ዳንኪራ መምታትን፣ መጨፈርን ይመርጣል፡፡ ይህ መጥፎ ባይባልም አሁን በአገራችን በአለው ተጨባጭ ሁኔታ የዳንኪራ መምቻ ቦታዎችና የምሽት ክበባት የሚባሉት ለወጣቱ ትውልድ የጥፋት ድማሚቶች ሆነው ከፊቱ ላይ ተደቅነውበታል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ጠላቶች የተወረረች ሆናለች፡፡ ረሀብና ችግር ቀንደኛ ጠላቶቿ ሲሆኑ የአልሻባብ አሸባሪ ቡድንም ከክፉ ዓይን አስገብቶ በጥንቃቄ እየተመለከታት ያለ ሌላው ጠላቷ ነው፡፡ በታሪካዊ ጠላትነት የምትታወቀው ግብፅም እንደዋዛ የምትታይ ጠላት አይደለችም። ከምንም በላይ ደግሞ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ቀንደኛ ጠላት የባህል ወረራ ሲሆን ወደር የማይገኝለት፣ ያለ ጥይት ኮሽታ ትውልድ አጥፊና ተተኪ የሚያሳጣ የጠላቶች ሁሉ ጠላት ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ባህል (culture) ሰውን ከእንስሳት የሚለየው አካባቢውን በፍጥነት በመቆጣጠር ሰብእናውንና ህልውናውን ባህላዊ በሆነ መንገድ ስለሚያሳድግ ነው፡፡ ለዛሬው ሰውነቱ ያበቃውም ትልቁ መሣሪያ ባህል ነው፡፡
በአሜሪካዊው “አንትሮፖሊጂስት” ኤድዋርድ ታይለር አገላለጽ መሠረት፣ ባህል በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡
1ኛ/ በቁስ የሚገለጹ (material culture) ወይም (artifacts) ለምሳሌ ጦር፣ ጋሻ፣ የሙዚቃና ሙዚቃ ነክ ባህል መሣሪያዎች ማሲንቆ፣ ክራር  በገና፣ እምቢልታ፣ ወዘተ ናቸው፡፡
2ኛ/ በቁስ የማይገለጹ (non-material culture) ሃይማኖት፣ ሥነ-ምግባር፣ እምነት፣ ሞራል፣ ሕግ፣ ልማድ፣ የሠርግ ዘፈን፣ ፉከራ፣ ቀረርቶ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡  
አንድ ሕፃን ከተወለደ ቀን ጀምሮ የቋንቋ ልሳነ ዕድገቱን በማዳበር እየተኮላተፈ በሚያየው፣ በሚሰማውና በሚዳስሰው ነገር ሁሉ ሐሳቡን ለመግለጽ/ለማናገር ይሞክራል፡፡ ያየውን ለመተግበር ይጥራል፡፡ በጥቅሉ የመማርን ሂደት ይጀምራል፡፡
የሕፃኑ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ቤተሰብ ሲሆን፣ በአካባቢው አብረው የሚያድጉ ልጆች (peers)፣ ትምህርት ቤትና ሚዲያ ሌሎች የሚማርባቸው የትምህርት መስኮች (socializing agents) ናቸው፡፡
አንድ ሕፃን የማኅበረሰቡን ወይም ኅብረተሰቡን ሕግና ደንብ ጠብቆ እንዲያድግና ከአካባቢው ጋር ራሱን አጣጥሞ፣ በዲሲፕሊን ታንፆና መልካም ሰብእና ተላብሶ እንዲያድግ የቤተሰብ ሚናና ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የማይቀበለውን ሥራ የፈጸመ ወይም ደንብ የጣሰ ልጅ ሲያጋጥም “አሳዳጊ የበደለው” የሚል ክፉ ስም ይለጠፍበታል፡፡ ይህ እንዳይሆን የወላጆች ሚና ታላቅ ነው፡፡
ከጎረቤት አብሮ አደግ (peers) እና ከትምህርት ቤት የክፍል ጓደኞች፣ ከመምህራን፣ ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አባላት የሚቀስመው በጎም ይሁን መጥፎ ትምህርት በልጁ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖ የዋዛ አይደለም፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ሌሎቹ የዕውቀት መቅሰሚያ መድረኮች ሲሆኑ መጻሕፍት፣ ጋዜጦች፣ ቴሌቭዥን፣  ራዲዮ፣ ፊልሞች፣ ኢንተርኔት ወዘተ…በእዚሁ ሥር የሚካተቱ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ በተለይም ሠለጠኑ በተባሉ ከተሞች ለሚገኙ ሕፃናት እና ወጣቶች ቅርብ በመሆናቸው ተጠቃሚው ወይም ተጎጂው የከተማው ወጣት ይሆናል፡፡ ኢንተርኔት እና ፊልሞች ግን በተለየ ሁኔታ በባህላችን ላይ የተጣሉ ጋሬጣዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በባህላችን ላይ ወረራ በማካሄድ የመገናኛ ዘዴዎች ወደር የሌላቸው የጥፋት መንገዶች ሆነዋል፡፡
በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በሌሎች የሠለጠኑ አገሮች ውስጥ የሚኖሩት ወላጆች፤ ልጆቻቸው የረቀቀውን የዓለም የዕድገት ቴክኖሎጂ እንዲያውቁላቸው  የማይጠቀሙት ስልት የለም፡፡ የአውሮፕላን አሻንጉሊት ፈታትቶ እስከመገጣጠም ድረስ እንዲያውቁ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለፈጠራ ያዘጋጇቸዋል፡፡ ጎጂና ጠቃሚ ነገሮችን ከወዲሁ እንዲያውቁ ተደርጎ በጥንቃቄ ያድጋሉ፡፡ መንግሥታቸውም ከምንም በላይና ከወላጆች በበለጠ ለሕፃናት እንክብካቤ ያደርጋል። ሌላው ቀርቶ ለሕጻናት መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ ምግቦችና መጠጦች፣ ለሕክምና ወጭዎች ልዩ ቅናሽ ያደርግላቸዋል፡፡ የሰለጠኑ ሀገራት መሪዎች “እኔ ከሞትኩ… ” የሚለውን “የሀገሬን” ብሂል አይከተሉም፡፡ ይልቅስ አገር ተተኪ ትውልድ እንዳታጣ ይታትራሉ፡፡ ይጥራሉ፡፡
ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ግን ለአዳጊ ልጆችና ወጣቶች ጉዳይ ልዩ ትኩረት አይደረግም፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች (Pornography) ወደ አገር ውስጥ በገፍ ሲገቡና በየቪዲዮ ቤቱ ታጭቀው፣ ድምፅ በሌለው መሣሪያ አዳጊዎች ሲጠፉ ሐይ የሚል ጠንካራ የመንግሥት አካል ባለመኖሩ፣ በትውልዱ ላይ የሞት ጥላ እያንዣበበ ይገኛል፡፡
ፈረንጆች ልጆቻቸውን ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች ለማድረግ ሲጥሩ፣ የእኛ የአፍሪካውያን ልጆች ግን ከዝንጀሮ ተርታ ቢሰለፉ የሚደሰቱ ወገኖች በመበራከት ላይ ያሉ ይመስላል። ቁጥሩንና ቀኑ ትዝ ባይለኝም የፈረንጆችን ተንኮል አስመልክቶ ድሮ በደርግ ዘመን “ሉሲ” በምትባል መጽሔት ሪቻርድ ፓንክረስት የፃፉት መጣጥፍ ትዝ ይለኛል፡፡
ይኸውም “Even if they donate, do not believe the Ferenjs” የሚል ነው፡፡ ፈረንጆች ለሚያደርጉት የልግስና ተግባር ሁሉ ከጀርባቸው አንድ ነገር እንዳለ መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡ የነጣው ሁሉ ወተት መስሎን ከመጎንጨታችን በፊት የሰጡንን ነገር ለይቶ የመጠቀም ኃላፊነት የእኛው ነው፡፡
ከዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የሕዝቡን አኗኗር፣ ወግ፣ ባህል፣ ዕሴትና ሥነ-ምግባር አስመልክቶ በጥቂቱ ብንዳስስ አሁን ለቆምንበት ዘመን ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
በዚያ ዘውዳዊ ሥርዓት ወግና ባህል የሚከበርበት፣ የማኅበረሰቡን ዕሴቶችና የአኗኗር ዘይቤዎችን ያልጠበቀ ሰው ይወገዝ ነበር፡፡ ዳንስ ቤቶች ቢኖሩም ውሱንና ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች፣ ባህሉን ሳይጥሱ የሚዝናኑ ወጣቶች ያለ ሰዓት እላፊ ገደብ የሚዝናኑባቸው ክለቦች ነበሩ፡፡
ሲጋራ ማጨስ የአራዳነት ምልክት በመሆኑ እነ “ቫይስሮይ” እነ “ኬንት” በየዳንስ ቤቱ እንደጉድ ይጨሱ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዲት ሴት እርቃኗን ስትደንስ በዚያ ዘመን ታይታ አታውቅም፡፡ ይህን ተግባር ፈጽማ የት ልትገባ? ከማን ጋርና የት ልትኖር?
በጣም አጭር ቀሚስ በዘመኑ አጠራር “ሱፐር ሚኒ” ለብሳ በከተማ ስትዘዋወር የታየች ሴት በፖሊስ ታድና የእሥር ቅጣቷን ቀምሳ ትወጣ ነበር። ሚዲያዎችም ይህንን ተቀባይነት የሌለውን ተግባር ይዋጋሉ፡፡ ኅብረተሰቡም “ውጉዝ ከመአርዮስ” በማለት ይረግማል፡፡ መንግሥትና ሕግ አስከባሪው አካልም የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡
በደርግ ዘመነ መንግሥትም ለየት ያለ ነገር አይተናል፡፡ መጤና ጎጂ ባህልን ለመዋጋት ሥር ነቀል እርምጃ መውሰድ ተጀመረ፡፡ ደርጉ የምሽት ክበቦችንና ጭፈራ ቤቶችን ጥርቅም አድርጐ ዘጋ፡፡ በቀን የመጠጣትን ልምድ ለማስወገድ በቀን ሲጠጣ የተገኘ ሰው፣ ጠጅ የተሞላበት ብርሌ በአናቱ ተሸክሞ በጠራራ ፀሐይ “እኔን ያየህ ተቀጣ…” እየተባለ በአደባባይ  እንዲዞር ተደረገ፡፡ ወጣት የሆነ ሁሉ ከ12 ሰዓት በፊት ቡና ቤት አልኮል ሲጎነጭ ቢገኝ፣ የቡና ቤቱ ባለቤት ጭምር አበሳውን ያይ ነበር፡፡ ጠጭውም እንደዚያው፡፡
ገደብ የለሽ ወሲብን ለመግታት የጋብቻ ውል የሌላቸው ጥንዶች፣ ለቀን ወይም ለአዳር አልጋ እንዳይከራዩ ታግዶ ነበር፡፡ ሴተኛ አዳሪነትን ላለማበረታታት በተለያዩ ፋብሪካዎች እንዲቀጠሩና ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ጉለሌ ጋርመንትና ሳሙና ፋብሪካዎች በምሳሌነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወጣት ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው በሥራ ሰዓትና በግልጥ ሁኔታ በረንዳ ላይ ተኮልኩሎ ጫት መቃም ተወግዞ ነበር፡፡ ወጣ ያለ መጤ አለባበስና እስታይል የሚያሳይ ወጣት “ጆሊ ጃኪዝም” የሚባል ስም ተሰጥቶት በልዩ ዓይን ስለሚታይ ከማኅበረሰቡ ቅጣት (social sanction) ለመዳን፣ ራሱን ከአገሩ ባህል ጋር ወዲያው ያመሳስላል፡፡ የወንድ ወይዛዝርትነትና የአሜሪካን “ሂፒዎች” አለባበስ፣ አጋጌጥ በአገራችን አይታለምም ነበር፡፡
በኃይለሥላሴና በደርግ ዘመን የተፈጸመው ሁሉ ትክክል ነበር ወይም ስሕተት ነው የሚል አቋም የለኝም፣ ለንጽጽር የቀረበ በመሆኑ ዳኝነቱን ለእናንተ እተዋለሁ፡፡
ኢህአዴግ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም አገሪቱን በቁጥጥር ሥር ሲያውል የደርግን ሥርዓት ከመመንገል ውጭ ለምን ሥልጣን ላይ እንደወጣ ዓላማ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ በወቅቱ ጨዋ ሠራዊት ለመሆኑ አዲስ አበባን በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ የበርሐ ልብሱን በመስኮትና በየሕንፃው አንጠልጥሎ፣ አላፊ አግዳሚውን በዓይነአፋር አመለካከት እያየ፣ ሕዝቡም እያየው የታለፈው ዘመን የሚዘነጋ አይደለም፡፡
በዘመነ ኢሕአዴግ በደርግ ጥረት በልማት መርሐ-ግብር በሕዝብ ተተክሎ ዝሆን የማይጥለው ደን እንደ ጠላት ሀብት ስለታየ፣ በራሱ በተካዩ ሕዝብ ድምጥማጡ ሲጠፋ ሐይ የሚለው ጠፋ፡፡ በገጠር ምርታማ የነበሩ የገበሬዎች ማኅበራት ተደመሰሱ፡፡ ልማቱም ከሥርዓቱ ጋር አብሮ እንዲወድም ተደረገ። በከተማ ደብዛቸው ጠፍቶ የነበሩት የምሽት ክበቦች ቀስ በቀስ መከፈት ጀመሩ፡፡ ጫት ቤቶች ቁጥራቸው በእጥፍ ጨመረ፡፡ የቃሚው ወጣት ቁጥርም እንደዚሁ፡፡
ድሮ ባገር ቤት በአዋቂ (ጠንቋይ) ቤቶች የትልቅ ብርሌ ቅርፅ ያለው ቅል የትምባሆ ቅጠል ተጨቅጭቆና (ተወቅጦ) በቀሰም ትምባሆ የሚማግበትና የሚንበቀበቅበት “ጋያ” ነበር፡፡ ያ በዘመናዊ መልክ በዐረብ አገራት “ሺሻ” በሚል ስያሜ “በኮባልት” ዓይነት ብረት ተሠርቶ ወደ አገራችን በገፍ ገባ፡፡ በሺሻም ስም ኮኬይን፣ ማሪዋና፣ ሄሮይን፣ የመሳሰሉት ጠንካራ የሀሺሽ ዓይነቶች (Hard drugs) በኮንትሮባንድ መልክ ገብተው መቸብቸብ ጀመሩ፡፡ እድሜ ለጃማይካውያን “ካናቪስም” ረከስ ባለ ዋጋ በተጠቃሚው እጅ ገባ፡፡ ወጣቱ በእነዚህ ሐይቆች እየሰጠመ የተለያየ የወንጀል ድርጊት ተዋናይ ሆነ፡፡
ከባለ ሥልጣናት ጀምሮ እስከ ባለጸጋዎች ደረስ ዳንኪራ የሚመታባቸው ቤቶች፣ ሴቶች እርቃነ ሥጋቸውን ሆነው የሚደንሱባቸው፣ ሐሺሽ የሚጨሱባቸው ጭፈራ ቤቶች በዋና ከተማይቱ አብበው የወጣቱን ልብ በመሰብሰብ ሰለባ አደረጉት።
በችግርና በተለያየ ምክንያት ሥራዬ ብለው በሴተኛ አዳሪነት ከተሰማሩት እህቶቻችን በተጨማሪ፣ ኑሮን ለማሸነፍና በአለባበስም አንሶ ላለመታየት አንዳንድ ሴት የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በደላላዎች አማካኝነት ሥጋቸውን በገንዘብ መለወጥ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህም በታላላቅ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲዎች ዘንድ በገሐድ የሚታይ እውነታ ነው፡፡
ምን ዓይነት ፊልም መርጠው ማየት እንደሚገባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያልተሰጣቸው አዳጊዎችና ወጣቶች… በወሲብ ፊልምና በ “በፌስ ቡክ” ላይ ተለጥፈው በመዋል የደባል ሱስ ቁራኛ፣ የልጅ ጡረተኛ ሆነዋል፡፡ ይህም ወጣቱ ስለ ሀገር ዕድገትና ብልፅግና እንዳያስብ  ማደንዘዢያ (anesthesia) የተሰጠው ይመስላል፡፡
አደንዛዥ ዕፅን ጨምሮ በሌሎች ማኅበራዊ ጠንቆች ላይ ወጣቱንና ማኅበረሰቡን በሚዲያ በማስተማር ፈንታ፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ከማንም ከምንም በላይ የላቀ ትኩረት ተደርጐበት ሰሚ እስኪሰለች ደረሰ ሰፊ የስርጭት ጊዜ መሰጠቱ ልብ ላለው ያስደምማል፡፡ የሚተላለፉት ጉዳዮች የሚያስገርሙ ከመሆናቸው በላይ የተጫዋቾች የቤተሰብ ጉዳይና የግል ታሪክ ሆነው አርቲቡርቲ ነገር የሚታጨቅባቸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለአገሪቱ ዕድገት የአንድ ሣንቲም ያህል ዋጋ የሌላቸው ለመሆናቸው ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡
እገሌ የተባለው ተጫዋች ሚስቱ ባረገዘችበት ወቅት የተለየ ፒጃማ ወይም ፓንት እጅግ ውድ በሆነ ፓውንድ ገዛላት፣ የሕፃኑ ልደት ሲከበር በአልማዝ የተሠራ ስጦታ ለሕፃኑ ተገዛለት፣ እንቶኔ የተባለው ተጫዋች በዚህን ያህል ፓውንድ/ዶላር/ ለዚህ ክለብ ተሸጠ፡፡ ሌላው ታዋቂ ተጫዋች ከሠርጉ በኋላ ለጫጉላ ሽርሽር ውድ በሆኑ የዓለም መዝናኛዎችና ሆቴሎች ተዝናና ወዘተ የሚለው ዜና፣ የዳቦ ሽታ ለናፈቀው ደሀ ሕዝብ ይኸ ምኑ ነው?
እንዲህ ከተትረፈረፈው የአየር ሰዓት፣ ትውልድ የሚያድን ትምህርት ለመስጠት ለምን እንዳልተፈለገ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል፡፡
የሥነ-ልቦና እና የሶሺዮሎጂ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ስለ ሕፃናት አስተዳደግ፣ ስለ መልካም ሥነ ምግባር፣ ስለ ባህል፣ ስለ ወጣት አጥፊነት፣ ስለ ትምህርት ክትትልና ውጤታማ የአጠናን ዘዴ፣ ስለ መጤ (ዲቃላ) ባህል፣ ስለ ሥነ-ተዋልዶ ጤና ትምህርት (ዕድሜያቸውን ባገናዘበ መልኩ) በዚህ ሥርም ስለቅድመ ጋብቻ ወሲብ፣ ስለ አባላዘር በሽታዎችና ኤች አይቪ ኤድስ ስለሚያስከትለው ጠንቅ ወዘተ… ወጣቱ እንዲማር ቢደረግ ትውልድን ለማዳን ሌላኛው ስልት ይሆን ነበር፡፡
የታሪክ ምሁራንን በመጋበዝ ውድ ስለሆነው ታሪካችን፣ ስለቅድመ አያቶች ጀግንነት፣ ስለአገር ፍቅር፣ ስለ ቅርሶቻችን እንዲማሩ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በሳይንስ በኩልም የሌሎች ዓለማትን ተመክሮ በመውሰድ የዘመኑን ድንቃድንቅ የሳይንስ ግኝቶች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሕፃናት እንዲያውቁ ብንተጋና ከልጅነታቸው ጀምሮ የፈጠራ ችሎታቸውን ቢያዳብሩ ብዙ ሳይንቲስቶች አናወጣም ነበር?
በተለይ በአሁኑ ጊዜ በከፋ መልኩ እየታዩ ከአሉት ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የግብረ ሰዶማውያን ጉዳይ ነው። በተለይም በአንደኛ ደረጃ  ት/ቤቶች በሚማሩ ሕፃናት ልጆች ላይ የሚፈጸመው የግብረ ሰዶማውያን ሰይጣናዊ ድርጊት ለጆሮ የሚቀፍ ነው፡፡ ዘግናኝ ወንጀል እየተሠራባቸው ጉዳቱ የደረሰባቸው ልጆችና ወላጆች ገመና ተዳፍኖ እንዳልፈነዳ “ቮልካኖ”ሕዝቡን በማሳዘን ላይ ይገኛል፡፡
አገሪቱ ተስፋ የሚጣልባቸውን የነገ ዶክተሮች፣ መሐንዲሶችን፣ ተመራማሪዎች፣ ሐኪሞች፣ ሳይንቲስቶች፣ ወዘተ… ትፈልጋለች፡፡ እነዚህ ወጣቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ የሳጥናኤል ኮሌጅ ተመዝጋቢዎችና ተመራቂዎች ሆነው ማየት በተለይም ለወላጆች ዘግናኝ ነው፡፡ ሰቆቃ ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ ሁሉ ተጠቂ የሆኑ ሕፃናትን እንደራሱ ልጆች አድርጎ በዓይነ ሕሊናው መመልከት አለበት፡፡
በመሆኑም አዳጊ ሕፃናትና የነገው አገር ተረካቢ ወጣት የሥነ-ልቡና ሞት እየሞተ ስለፖለቲካ፣ ስለአገር ዕድገት፣ ብልጽግና፣ ስለዲሞክራሲ፣ ስለግብርና መር ኢኮኖሚ፣ ስለ 1 ለ 5 አደረጃጀት፣ ስለዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር መጨመር፣ ስለ ካይዘን፣ ስለ ፓርቲ፣ ስለ “Top ten” አደረጃጀት፣ ስለፎረም፣ ስለካቢኔ፣ ስለፓርላማ፣ ስለአነስተኛና ጥቃቅን ወዘተ.. በሚዲያ ብንለፈልፍ ዋጋ የለውም፡፡ በአገር ሞት ላይ እንደመዝፈን ስለሚቆጠር መንግሥትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎችና ኅብረተሰቡ ሰይጣናዊ ተልዕኮ ከአነገበው የፈረንጅ ሥራና የባህል ወረራ ወጣቱን ለማዳን ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው እላለሁ፡፡

Read 3782 times