Saturday, 22 February 2014 12:42

የሚለማውን አገር የሚረከብ ትውልድ አላዘጋጀንም!

Written by  ከሀብታሙ ወርቅነህ
Rate this item
(0 votes)

      ተምሮ ላገሩ የማይጠቅም ወይም ዕውቀቱ የጋን መብራት የሆነ ምሑር ለጦቢያ አይበጃትም! የሕዝቡን ሰቆቃ የሚያዳምጥ፣በወገን ላብና ደም ሆዱን አሳብጦ፣ ንብረት አካብቶ የሚናጥጥ ባለስልጣን ለጦቢያ አይበጃትም! የሕዝብን አንደበት ለጉሞ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብትን ገፍፎ፣ ያገርን ስም አጥፍቶ፣ ውበቷን ጥላሸት ቀብቶ፣ ትውልድ ሲመክን የዳር ተመልካች ሆኖ ሐይ! የማይል፣ ያገር ሉዓላዊነትና የወገን ቁስል ሰቆቃ የማይሰማው፣ በወተት ፋንታ መርዝ እየተጋቱ ለሚገኙ አዳጊና አገር ተኪ ሕፃናት የማይቆም ሥርዓት ለጦቢያ አይበጃትም!!
እንዳለመታደል ሆኖ  ጦቢያችን በብዙ ጠላቶች የተወረረች አገር ሆናለች፡፡ ረሐብና ድህነት ቀንደኛ ጠላቶቿ ናቸው፡፡ ኋላ ቀር ፖለቲካዊ ባህልና ሥርዓትም እንደዚሁ፡፡ የአልሸባብ አሸባሪ ቡድንም ክፉ ዓይኑን የጣለባት ሌላው ጠላቷ ነው፡፡ በታሪካዊ ጠላትነት የምትታወቀው ግብፅም የዋዛ የምትታይ ጠላት አይደለችም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ቀንደኛ ጠላት የባህል ወረራ ሲሆን ያለ ጥይት ኮሽታ ወደርየለሽ ትውልድ አጥፊና ተተኪ የሚያሳጣ የጠላቶች ሁሉ ጠላት ነው፡፡
ባህል (Culture) ለሰው ልጅ ከሚቀርቡ እንስሳት (the primates) ሰውን ልዩ በማድረግ አካባቢውን በፍጥነት በመቆጣጠር ለዛሬው ሰውነቱ ያበቃው ትልቁ መሣሪያ ነው፡፡ በአሜሪካዊው ‘አንትሮፖሎጂስት’ ኤድዋርድ ታይለር አገላለጽ መሠረት፣ ባህል በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል፡፡
በቁስ የሚገለጹ (material culture) ወይም (artifacts) ለምሳሌ፣ ያገራችንን ባህል የሚያሳዩ ቁሳቁሶች ሆነው ለጦር ሜዳ የሚያገለግሉ ጦር፣ ጋሻ፣ የሙዚቃና ሙዚቃ ነክ ባህል መሣሪያዎች-- ማሲንቆ፣ ክራር፣ በገና፣ እምቢልታ፣ ወዘተ ናቸው፡፡
በቁስ የማይገለጹ (non-material culture) ኃይማኖቶች፣ እምነቶች፣ ሞራል፣ ህግ፣ ልማዶች፣ የሠርግ ዘፈን፣ ፉከራው፣ ቀረርቶው ወዘተ … ናቸው፡፡ አንድ ሕፃን ከተወለደ ቀን ጀምሮ የቋንቋ ልሳነ ዕድገቱን በማዳበር እየተኮላተፈ በሚያየው፣ በሚሰማውና በሚዳስሰው ነገር ሁሉ ሐሳቡን ለመግለፅ ወይም ለመናገር ይሞክራል፡፡ ያየውን ለመተግበር ይጥራል፡፡ በጥቅሉ የመማርን ሂደት ይጀምራል፡፡ የሕፃኑ የመጀመሪያ ት/ቤት ቤተሰብ ሲሆን፣ በአካባቢ አብረው የሚያድጉ ልጆች (peers)፣ ት/ቤትና ሚዲያ ሌሎች የሚማርባቸው ወኪሎች (socializing agents) ናቸው፡፡
አንድ ሕፃን የማኅበረሰቡን ወይም ኅብረተሰቡን ሕግና ደንብ ጠብቆ እንዲያድግና ከአካባቢው ጋር ራሱን አጣጣሞ በዲሲፕሊን ታንፆና መልካም ሰብዕና ተላብሶ እንዲያድግ የቤተሰቡ ሚናና ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የማይቀበለውን ሥራ የፈፀመ ወይም ደንብ የጣሰ ልጅ ሲያጋጥም “አሳዳጊ የበደለው” የሚል ክፉ ስም ይለጠፍበታል፡፡ ይህ እንዳይሆን የወላጆች ሚና ታላቅ ነው፡፡
ከጎረቤት አብሮ አደግ (peers) እና ከት/ቤት የክፍል ጓደኞች፣ ከመምህራን፣ ከት/ቤቱ ማኅበረሰብ የሚቀስመው በጎም ይሁን መጥፎ ትምህርት በልጁ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ወይም አወንታዊ ተፅዕኖ የዋዛ አይደለም፡፡
ሚዲያ አራተኛው “ሶሻላይዚንግ ኤጀንት” ሲሆን መጻሕፍት፣ ጋዜጦች፣ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ፊልሞች፣ ኢንተርኔት ወዘተ … በዚሁ ሥር የሚካተቱ ሆነው በተለይም ሠለጠኑ በተባሉ ከተሞች ላይ ላሉ ሕፃናት እና ወጣቶች ቅርብ በመሆናቸው ተጠቃሚው ወይም ተጎጂው የከተማው ወጣት ይሆናል፡፡ በተለይ ኢንተርኔትና ፊልሞች በባህላችን ላይ የተጣሉ ጋሬጣዎች ናቸው፡፡
የአውሮፓ፣ የአሜሪካና ሌሎች የሠለጠኑ አህጉራት፣ ሕፃናቶቻቸው ከረቀቀው የዓለም ቴክኖሎጂ ጋር በለጋ እድሜያቸው እንዲተዋወቁላቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ የአውሮፕላን አሻንጉሊት ፈታተው እስከመገጣጠም ድረስ እንዲካኑ ይደረጋል፡፡ ለፈጠራ ይዘጋጃሉ። ጎጂና ጠቃሚ ነገሮችን ከወዲሁ እንዲያውቁ ተደርጎ በጥንቃቄ ያድጋሉ፡፡ መንግስታቸው ከወላጆች ባልተናነሰ ለሕፃናት እንክብካቤ ያደርጋል። “እኔ ከሞትኩ …” የሚለውን የሐገሬን ብሒል አይከተልም። ይልቅስ አገር ተተኪ እንዳታጣ ይታትራል፡፡ ይተጋል፡፡
ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ግን የአዳጊ ልጆችና የወጣቶች ጉዳይ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ወሲብ ቀስቃሽ ፊልሞች (Pornography) ወደ አገር በገፍ ሲገቡና በየቪዲዮ ቤቱ ታጭቀው፣ ድምፅ በሌለው መሣሪያ አዳጊዎችን ሲያጠፉ ሐይ የሚል በመጥፋቱ  በአገሪቱ አዲስ ትውልድ ላይ የሞት ጥላ እያንዣበበ ይገኛል፡፡
ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ የሕዝቡን አኗኗር፣ ወግ፣ ባህል፣ እሴትና ዲሲፕሊን በወፍ በረር መቃኘት አሁን ለቆምንበት ዘመን ማሳያ ስለሚሆን እነሆ!
በዚያ የዘውድ ሥርዓት ወግና ባህል የሚከበርበት፣ የማኅበረሰቡን እሴቶችና የአኗኗር ዲሲፕሊኖች ያልጠበቀ ሰው የሚወገዝበት ዘመን ነበር፡፡ ዳንስ ቤቶች ቢኖሩም ውሱንና ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች፣ ባህሉን ሳይጥሉ የሚዝናኑ ወጣቶች ያለ ሰዓት እላፊ ገደብ የሚዝናኑበት ክለቦች ነበሩ፡፡ ሲጋራ ማጨስ የአራዳነት ምልክት በመሆኑ እነ “ቫይስሮይ” እነ “ኬንት” በየዳንስ ቤቱ እንደጉድ ይጨሱ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዲት ሴት እርቃኗን እንድትደንስ መረን አትለቀቅም ነበር፡፡ ይህን ተግባር ፈፅማ የት ልትገባ? የት ልትኖር? በማን አገር?
በአደባባይ በጣም አጭር ቀሚስ በዘመኑ አጠራር “ሱፐር ሚኒ” ለብሳ በከተማ ስትዘዋወር የታየች ሴት፣ በፖሊስ ታድና የገንዘብና የእስር ቅጣቷን ቀምሳ ትወጣ ነበር፡፡ ሚዲያዎችም ይህንን ተቀባይነት የሌለው ተግባር ይዋጋሉ፡፡ ኅብረተሰቡም “ውጉዝ ወከመ አርዮስ” በማለት ይረግማል፡፡ መንግስትና ህግ አስከባሪው አካልም የራሱን ሚና ይጫወታል፡፡
ወደ ደርግ ዘመነ መንግስት ስንመጣ ለየት ያለ ነገር እናስተውለናል፡፡ መጤና ጎጂ ባህልን ለመዋጋት ሥር-ነቀል እርምጃ ወሰደ፡፡ የምሽት ክበቦችንና ጭፈራ ቤቶችን ጥርቅም አድርጎ ዘጋ፡፡ በቀን የመጠጣትን ልማድ ለማስወገድ በቀን ሲጠጣ የተገኘ፣ ጠጅ የተሞላበት ብርሌ በአናቱ ይዞ በጠራራ ፀሐይ “እኔን ያየህ ተቀጣ…” እያለ በአደባባይ እንዲዞር ተደረገ፡፡ ወጣት የሆነ ሁሉ ከ12 ሰዓት በፊት ቡና ቤት አልኮሆል ሲጎነጭ ቢገኝ፣ የቡና ቤቱ ባለቤት አበሳውን ያይ ነበር፡፡ ጠጪውም እንደዚያው፡፡
ገደብ የለሽ ወሲብን ለመግታት የጋብቻ ውል የሌላቸው ጥንዶች ለቀን ወይም ለአዳር አልጋ እንዳይከራዩ አገደ፡፡ ሴተኛ አዳሪነትን ላለማበረታታት በተለያዩ ፋብሪካዎች እንዲቀጠሩና ሴተኛ አዳሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ብዙ ሙከራዎች ተደረጉ፡፡ ጉለሌ ጋርመንትና ሳሙና ፋብሪካዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ ወጣት ብቻ ሳይሆን ማንም ሰው በሥራ ሰዓትና በግልፅ ሁኔታ በረንዳ ላይ ተኮልኩሎ ጫት መቃም ተወገዘ፡፡ ወጣ ያለ መጤ አለባበስና ስታይል የሚያሳይ ወጣት “ጆሊ ጃኪዝም” የሚል ስም ተሰጥቶት፣ በልዩ ዓይን ስለሚታይ ከማኅበረሰቡ ቅጣት (Social sanction) ለመዳን ራሱን ከአገሩ ባህል ጋር ወዲያው ያመሳስላል፡፡ የወንድ ወይዛዝርትነትና የአሜሪካን “ሂፒዎች” አለባበስ፣ አጋጌጥ በአገራችን አይታለምም ነበር፡፡
ውድ አንባቢያን! በደርግ ዘመን የተፈፀመው ሁሉ ትክክል ነው ወይም ስህተት ነው የሚል አቋም ይዤ እንዳልተነሳሁ እንድትገነዘቡልኝ አደራ እያልኩ፣ ለንፅፅር የቀረበ በመሆኑ ዳኝነቱን ለእናንተ ትቼዋለሁ፡፡
ኢሕአዴግ በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም አገሪቱን በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡ ደብዛቸው ጠፍቶ የነበሩት የምሽት ክበቦች ቀስ በቀስ መከፈት ጀመሩ፡፡ ጫት ቤቶች ቁጥራቸው በእጥፍ ጨመረ፡፡ የቃሚው ወጣት ቁጥርም እንደዚሁ፡፡ ድሮ ባገር ቤት በአዋቂ (ጠንቋይ) ቤቶች ከቅል ተሠርቶ የትልቅ ብርሌ ቅርፅ ያለው፣ የትምባሆ ቅጠል ተጨቅጭቆ (ተወቅጦ) በቀሰም ትምባሆ የሚማግበትና የሚንበቀበቅ “ጋያ” ነበር፡፡ ያ በዘመናዊ መልክ ከአረብ አገራት “ሺሻ” በሚል ስያሜ ‘በኮባልት’ ዓይነት ብረት ተሠርቶ ወደ አገራችን በገፍ ገባ፡፡ በሺሻ ስም ኮኬይን፣ ማሪዋና፣ ሄሮይን፣ የመሳሰሉት ጠንካራ የሀሺሽ ዓይነቶች (Hard drugs) በኮንትሮባንድ መልክ ገብተው መቸብቸብ ጀመሩ፡፡ እድሜ ለጃማይካዊያን! “ካናቪስም” ረከስ ባለ ዋጋ በተጠቃሚው እጅ ገባ። ወጣቱ በእነዚህ ሐይቆች እየሰጠመ የተለያየ የወንጀል ድርጊት ተዋናይ ሆነ፡፡
ከባለስልጣናት ጀምሮ እስከ ባለፀጋዎች ድረስ ዳንኪራ የሚመታባቸው፣ ሴቶች እርቃናቸውን  ሆነው የሚደንሱባቸው፣ ሐሺሽ የሚጨሱባቸው ጭፈራ ቤቶች በዋና ከተማይቱ አብበው የወጣቱን ልብ በመሰብሰብ ወቃጣ አደረጉት፡፡ ለአገር የማያስብ ስልብ ሆነ፡፡
በችግርና በተለያየ ምክንያት ሥራዬ ብለው በሴተኛ አዳሪነት ከተሠማሩት እህቶቻችን በተጨማሪ፣ ኑሮን ለማሸነፍና በአለባበስም አንሶ ላለመታየት አንዳንድ ሴት የመንግስትና የግል ድርጅት ሠራተኞች እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በደላሎች አማካኝነት ሥጋቸውን በገንዘብ መለወጥ ጀመሩ፡፡
ስለ ኢንተርኔት አጠቃቀም፣ ምን ዓይነት ፊልም መርጠው ማየት እንደሚገባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያልተሰጣቸው አዳጊዎችና ወጣቶች … በወሲብ ፊልምና በ “ፌስ ቡክ” ላይ ተጥደው በመዋል የደባል ሱስ ቁራኛ፣ የልጅ ጡረተኛ ሆኑ፡፡ ወጣቱ ስለ ዕድገትና ብልፅግና እንዳያስብ የተሰጠው ማደንዘዢያ (anesthesia) እንዳስተኛው ቀረ፡፡  
ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ አደንዛዥ ዕፅን ጨምሮ በሌሎች ማህበራዊ ጠንቆች ዙርያ ወጣቱንና ማኅበረሰቡን በማስተማር ፈንታ፣ ለአውሮፓ እግር ኳስ የላቀ ትኩረት ሰጡ፡፡ እገሌ የተባለው ተጫዋች ሚስቱ ባረገዘችበት ወቅት የተለየ ፒጃማ ወይም ፓንት እጅግ ውድ በሆነ ፓውንድ ገዛላት፣ የሕፃኑ ልደት ሲከበር በአልማዝ የተሠራ ስጦታ ተገዛለት፣ እንቶኔ የተባለው ተጫዋች በዚህን ያህል ፓውንድ /ዶላር/ ለዚህ ክለብ ተሸጠ፡፡ ሌላው ታዋቂ ተጫዋች ከሠርጉ በኋላ ለጫጉላ ሽርሽር ውድ በሆኑ የዓለም መዝናኛዎችና ሆቴሎች ተዝናና ወዘተ፡፡ የፈጀው ዘግናኝ ገንዘብ ይጠቀሳል፡፡ ወገኖቼ፤ ድህነትና የኑሮ ውድነት ለሚጨፍርበት መከረኛ ሕዝብ ይሄ ምኑ ነው? እኔ ሁሌም እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ ከተትረፈረፈው የሚዲያ የአየር ሰዓት ጥቂቱ እንኳን  ለምን ትውልድ ለሚያድን ትምህርት እንደማይውል ነው፡፡
የሥነ-ልቦና እና የሶስዮሎጂ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ስለ ሕፃናት አስተዳደግ፣ ስለ ዲሲፕሊን፣ ስለ ባህል፣ ስለ ወጣት አጥፊነት፣ ስለ ትምህርት ክትትልና ስለ ውጤታማ የአጠናን ዘዴ፣ ስለ መጤ (ዲቃላ) ጎጅ ባህል፣ ስለ ሥነ-ተዋልዶ ጤና ትምህርት (ዕድሜያቸውን ባገናዘበ መልኩ)፣ ስለ ቅድመ ጋብቻ ወሲብ፣ ስለ አባላዘር በሽታዎችና ኤች አይቪ ኤድስ ወዘተ … ወጣቱ እንዲማር ቢደረግ አንዱ የትውልድ ማዳን ሥልት አይሆንም ነበር? የታሪክ ምሁራንን በመጋበዝ ውድ ስለሆነው ታሪካችን፣ ስለ ቅድመ አያቶች ጀግንነት፣ ስለ አገር ፍቅር፣ ስለ ቅርሶቻችን እንዲማሩ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ አይሆንም?
የሌሎች ዓለማትን ተሞክሮ በመውሰድ የዘመኑን ድንቃድንቅ የሣይንስ ግኝቶችና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሕፃናት እንዲያውቁ ቢደረግ---ከልጅነታቸው ጀምሮ የፈጠራ ችሎታቸውን ቢያዳብሩ ብዙ ሳይንቲስቶች አናወጣም ነበር? መልሱን ለአንባቢያን ትቼዋለሁ፡፡
እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የግብረ ሰዶማዊያን ጉዳይ ሌላው ትኩረት የሚሻ ማህበራዊ ቀውስ ነው፡፡ በተለይም በ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በሚማሩ ሕፃናት ወንድ ልጆች ላይ የሚፈፀመው የግብረሰዶማዊያን ሠይጣናዊ ድርጊት ለጆሮ የሚቀፍ ነው፡፡ ዘግናኝ ወንጀል እየተሠራባቸው ጉዳቱ በደረሰባቸው ልጆችና ወላጆች ገመና ተዳፍኖ እንዳልፈነዳ “ቮልኬኖ” ከተማይቱን እያንቀጠቀጠ ይገኛል፡፡
አገሪቱ ተስፋ የጣለችባቸው የነገው ዶክተሮች፣ መሀንዲሶች፣ ተመራማሪዎች፣ ሣንቲስቶች ወዘተ … ባልተጠበቀ ሁኔታ የሳጥናኤል ኮሌጅ ተመዝጋቢና ተመራቂ ሆነው ማየት በተለይም ለወላጆች ዘግናኝ ነው፡፡ ሰቆቃ ነው፡፡ የወለደ ፍርዱን ይስጥ። ኢትዮጵያዊ  ነኝ የሚል ዜጋ ሁሉ ተጠቂ የሆኑ ሕፃናትን እንደራሱ ልጆች አድርጎ በዓይነ ሕሊናው ይመልከት፡፡
የአዳጊ ሕፃናትን ጉዳይ ችላ ብሎ ወይም ስለነገው አገር ተረካቢ ወጣት እጣ ፈንታ ምንም ሳይጨነቁ ስለ ፖለቲካ፣ስለ አገር ዕድገትና ብልፅግና፣ ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ግብርና መር ኢኮኖሚ፣ ስለ 1ለ5 አደረጃጀት፣ስለ ዩኒቨርስቲዎች ቁጥር መጨመር፣ ስለ ካይዘን፣ ስለ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ስለ  ፎረም፣ ስለ ካቢኔ፣ ስለ ፓርላማ፣ ስለ አነስተኛና ጥቃቅን ወዘተ … መለፈፍ በአገር ሞት ላይ እንደመዝፈን የሚቆጠር ነው፡፡ የህፃናትን ህይወት ሳንታደግ የቱንም ያህል ለልማት ብንታትር ትርፉ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ልማት ልማት ብለን የለማችውን አገር የሚረከበን እንዳናጣ እሰጋለሁ። እናም መንግስትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ክፍሎችና ሕብረተሰቡ ለአዳጊዎቻችን ልዩ ትኩረት ይስጥ፡፡


Read 3094 times