Monday, 03 February 2014 13:56

“ሰው አብሮኝ እንዲዘፍን እፈልጋለሁ”

Written by 
Rate this item
(12 votes)

አንበሳ የኢትዮጵያዊነታችን ትልቅ መገለጫ ነው
በሽያጭ የኦሮምኛ ዘፈኖችን የሚወዳደራቸው የለም

ዝነኛው ድምጻዊ ታደለ ሮባ በቅርቡ “ምስጋና” የተሰኘ አዲስ አልበም አውጥቷል፡፡ ከሙያ ባልደረባው ብርሃኑ ተዘራ ጋር
4 አልበሞችን ቢያወጣም ሙሉ አልበም ለብቻው ሲያወጣ ግን የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አበባየሁ ገበያው በሙያውና በህይወቱ ዙርያ አነጋግራዋለች፡፡

በቀበሌ ኪነት በኩል ነው ወደ ሙዚቃ የገባኸው ወይስ በሌላ?
አዎ፤ የ12 ቀበሌ የታዳጊ ኪነት ቡድን ውስጥ እጫወት ነበር፡፡ አሊ ቢራ የሰፈራችን ልጅ ነው፡፡ ያኔ ትንሽ ስለነበርኩ

በደንብ አላስታውስም እንጂ የጊታሯን አምፕሊፋየር የሰጠን እሱ ነበር፡፡  እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የአሊ ቢራ ዘፈኖች

“እንጀራዬ” ሆኑ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ የእሱ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡
ተወልደህ ያደግህበት ሰባተኛ የአርቲስቶች መፍለቂያ ነው፡፡ ከሰፈሩ ብዙ አርቲስቶች የወጡበትምክንያት ምን

ይመስልሃል? ከውሃው ይሆን እንዴ?
አዎ…እነጐሳዬ፣ አለማየሁ ሂርጳ፣ አብዱ ኪያር፣ ቴዲ አፍሮ፣ አብነት አጐናፍር፣ ወንድሙ ጅራ፣ መውደድ ክብሩ… የእዛ

አካባቢ ልጆች ናቸው፡፡ በተወዛዋዥነትም ብዙ አሉ - ከዚያ ሰፈር የወጡ። እንደሚመስለኝ የመርካቶ ጐረቤት በሆኑ

ሰፈሮች ያደጉ ልጆች ድፍረት አላቸው፡፡ ድፍረትም ታለንትም፡፡ የቦሌ ልጅ ሆነው ከግቢ የማይወጡ፣ ታለንቱ

ቢናራቸውም ላይጠቀሙበት ይችላሉ። ደግሞ የእኛ ሰፈር አርቲስቶች ብቻ ሳይሆኑ ትላልቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾችም

የወጡበት ነው። የቡናና የጊዮርጊስ ተጫዋቾች የማን መሰሉሽ? ዛሬ ግን ሰፈራችን ሜዳ የለም፤  ኳስ ሜዳው ፎቅ

ተሰርቶበታል፤ አስራ ሰባት ሜዳም ትምህርት ቤት ሆኗል፡፡ ለእዚህ እኮ ነው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የክፍለ ሀገር

ልጆች ብቻ የሆኑት፡፡ የሜዳው ነገር ሊታሰብበት ይገባል፡፡  
እስቲ ስለ “ላፎንቴ”… አመሰራረት ንገረኝ…
ነፍሱን ይማርና የላፎንቴን አንደኛው አባል የነበረው ፀጋቸው የሚባል ጓደኛችንና አለማየሁ ኢርጳ አሮሠ ሆቴል ይሠሩ

ነበር፡፡ “ጐበዝ ልጅ አለ” ብለው  ለአሮሠ ሆቴል ባለቤት ለአቶ ሮባ ነገሩትናእኔም እዛ መጫወት ጀመርኩ፡፡ አሮሠ ሳለሁ

የማልጫወተው ዘፈን አልነበረም፡፡ ኪሱዋሂሊ፣ ጉራጊኛ፣ ሱዳንኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኦሮምኛና ትግርኛ ሁሉ እሠራ

ነበር፡፡ ከተፋ ስትሰሪ  ይሄ የሚጠበቅ ነው፡፡ እዛ እየሠራን ሳለ “ያየህራድ አላምረው ሮያል ፓላስ” የሚባል ቤት

ተከፈተ። እዚያ ቤት ከተማው ውስጥ አሉ የተባሉ ዘፋኞች ይሰሩ ነበር፡፡ እኛም ለጥቂት ወራት እዛ ከሰራን በኋላ እኔ፣

አበበ ተካ፣ ብርሃኑ ተዘራና ፀጋቸው ሆነን “ላፎንቴን” በሚል ስራ ጀመርን፡፡ አበበ ወዲያው ወጣ፡፡
አንድ ጊዜ የኦሮምኛ ዘፋኞች ተሰባስባችሁ ማህበር ለማቋቋም ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ምን ደረሰ? ዓላማውስ ምን ነበር?
አዎ አንድ ማህበር በኦሮምኛ ዘፋኞች ተቋቁሞ ነበር፡፡ ስብስባው ጨፌ ላይ ነበር የተደረገው። እንቅስቃሴው አሁን ምን

ደረጃ ላይ እንደደረሰ አላውቅም፡፡ የኮፒ ራይት ጥሰትን ለማስቀረት ጠበቅ ብሎና በደንብ ታስቦበት ቢሰራ ጥሩ ነበር፡፡

በነገራችን ላይ በሽያጭ በኩል የኦሮምኛ ዘፈኖችን የሚወዳደራቸው የለም፡፡ እኛ የማናውቃቸው ዘፋኞች አሉ - ሃረር፣

አርሲ፣ ባሌ… የእነሱ አልበም እስከ 100 ሺ ቅጂዎች ይሸጣል፡፡ የእኛ እኮ እንደነሱ አይሸጥም፡፡ የእነሱ እንደገና “በርን”

ባይደረግ …. ሶስት መቶ ሺና ከዛም በላይ ይሸጥ ነበር፡፡  
በሙዚቃ ሥራ ምን ያህል አድጌያለሁ ትላለህ?
የትምህርት መጨረሻ የለውም፡፡ ግን በሙዚቃ ሥራ በስያለሁ፡፡ በፊት እየዘፈንኩኝ ሳላውቀው፤ ከቅኝት (ሪትም) ሁሉ

እወጣ ነበር፡፡ አሁን በደንብ በስየበታለሁ፤ ግን ገና ይቀረኛል፡፡ በሙዚቃ መሳሪያ በኩል ጊታርና ኪቦርድ ለራሴ መጫወት

እችላለሁ። መማሩና መብሰሉ ነገም የሚቀጥል ሂደት ነው፡፡
የአዲሱ አልበምህ ሽፋን ላይ በአንበሶች ተከበህ ትታያለህ፡፡ አንበሶች ትወዳለህ ወይስ ሌላ ትርጉም አለው?
ከልጅነቴ ጀምሮ አንበሳ እወዳለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ (በአባቶቻችን ዘመን) በአንበሶች ታጅበን ነበር

የምንዋጋው፡፡ ከትውልድ እስከ ትውልድ ብዙ ነገሮቻችን የአንበሳ ነበረ፡፡ አንበሳ አውቶብስ፣ የአየር መንገድና የቴሌ

አርማ …ብቻ የተለያዩ ነገሮቻችን የአንበሳ አርማ ነበራቸው፡፡ አንበሳ የኢትዮጵያዊነታችን ትልቅ መገለጫ ነው ብዬ

አምናለሁ፡፡ ከአንቺና ከእኔ ጀምሮ አንበሶች ነን…አንቺ አሁን የሴት አንበሳ ነሽ፡፡
እርግጠኛ ነህ?
አዎ! የሴት አንበሳ ነሽ…/ሳቅ/ እኔ ደግሞ በእምነቴ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ፡፡ ግን ኮኮቤ ሊዮ ነው - ባላምንበትም፡፡

ሊዮ ደግሞ ምልክቱ አንበሳ ነው። በዚህ የአንበሳ ፍቅሬ ነው በአንበሶች ታጅቤ የምታይኝ፡፡ እንደ ንጉስ ለመሆን ወይንም

ፖለቲከኛ ሆኜ አይደለም፡፡ ከህፃንነቴ ጀምሮ አንበሳ እወዳለሁ። አንድ ሰው የሚፈልገው ነገር ማድረግ አለበት የሚል

እምነት ስላለኝ የምፈልገውን አድርጌያለሁ፡፡ በአልበሙ ላይ የሚታዩት ሁለቱ የእውነት አንበሶች ሲሆኑ እኔ ደግሞ የሰው

አንበሳ ነኝ፡፡
በምትሰራቸው ነጠላ ዜማም ይሁን ሙሉ አልበም ላይ አዳዲስ ወጣቶችን በፊቸሪንግ ታስገባለህ? ወጣቶቹን ለማገዝ

አስበህ ነው?
እንደ አቅሜ ሙዚቃ የማዳመጥ ችሎታ አለኝ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ የማሰራቸው ልጆች ችሎታውና ተሰጥኦው

ቢኖራቸውም ምቹ ዕድልና መድረክ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ እኛ ደግሞ በህዝብ ውስጥ አለን..እናም አዳዲስ ልጆች ከእኛ ጋር

በመሆን ከህዝብ ጋር መተዋወቅ  አለባቸው ብዬ አምናለሁ። በዚህ እነሱም እኛም እንጠቀማለን፡፡ ችሎታቸውን

ስለምናደንቅ ነው የምናሰራቸው፡፡ በፊት ከላፎንቴን ጋር ፊቸሪንግ የሰሩ ልጆች በሙሉ አሁን ትላልቅ ቦታ ደርሰዋል፡፡

ሁሉም ራሳቸውን ችለው ቆመዋል፡፡
ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው እየመጣህ ነው አይደል?
አዎ፡፡ ወደ ፊልም ገብቻለሁ፤ በቅርቡ የሚወጣ ፊልም አለኝ፡፡ እግዚአብሄር ካስተካከለው የተመልካችን አስተያየት አይቼ

ወደፊት የምቀጥልበት ይሆናል፡፡
የአልበም ስራ በሌለ ጊዜ ምንድነው የምትሰራው? ናይት ክለብ…
እኔ ብዙ ጊዜ እዚህ አልሰራም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ነው፡፡ አሁን ግን አልበሜን ከሰራሁ በኋላ ማናጀሬና ማርኬቲንጉ

አንዳንድ ነገሮችን እያጠኑ ነው፡፡ ባለፈው ጎንደር ሄጄ፤ ከስፖንሰሬ ከዳሸን ቢራ ጋር አንዳንድ ነገሮችን አስተካክለናል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ ደሴና ኮምቦልቻ ሄጄ ነበር፤ አንድ የአፋር ባለሃብት ሆቴል ከፍተው ለምርቃቱ  እንድገኝ ስለፈለጉ ነው፡፡

ቀጥለን ደሞ ወደ ደቡብና ምስራቁ ክፍል እንሄዳለን፡፡
ከአዲስ አልበም በኋላ ኮንሰርት የተለመደ ነው፡፡ ጥያቄ አልቀረበልህም?
ከአሁኑ ለንደን ፕሮግራም እንድይዝላቸው ጠይቀውኛል፡፡ ግን አልሄድም፤ ምክንያቱም አልበሙ በደንብ መሰማትና

መደመጥ አለበት። ሰው ከእኔ ጋር እንዲዘፍን እንጂ እኔ ብቻዬን እንድዘፍን አልፈልግም፡፡ የለንደን ያልኩሽ  ከፋሲካ

በኋላ ስለሆነ ለእኔ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡
እስከ አሁን ስንት አልበም ሰራህ?
ከብርሃኑ ተዘራ ጋር አራት አልበሞች ሰርተናል….‹‹ተው አምላኬ››፣ ‹‹እንዲች እንዲች››፣ ‹‹እጅ አንሰጥም›› እና ‹‹ባቡሬ››፡፡

ከዛ በኋላ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ሰርቼአለሁ፡፡ ለብቻዬ አልበም ሳወጣ ይህ አዲሱ ‹‹ምስጋና›› የመጀመሪያዬ ነው፡፡  
አርቲስቶች ችግር ሲደርስባቸው ቀድመህ ትደርሳለህ ይባላል?…
የተወሰንን አርቲስቶች በክፉም በደጉም የምንገናኝ ነን፡፡ አርቲስቶች ችግር ሲደርስባቸው የሰው እጅ ከሚያዩ፣ ለዚሁ

ዓላማ የሚሆን አንድ ነገር መከፈት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ እድር የለንም፡፡
አሁን እያሰብን ነው፡፡ ለቅሶ ላይ ወይም የሆነ ቦታ ስንገናኝ ለምን አንመሰርትም እንባባላለን። በጓደኞች መካከል ችግር

ሲፈጠር ለመፍታት እንጥራለን፡፡ እኔ ብቻዬን ምስጋናውን (ክሬይቱን) መውሰድ አልፈልግም፡፡ በተረፈ ሜሪ ጆይ ውስጥ

ሁለት የማሳድጋቸው ልጆች አሉኝ፡፡ መናገር የማልፈልጋቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎችም አሉ፡፡ በአጠቃለይ ግን ጥሩ ነው፡፡
የሞባይል ስልክህን መጥሪያ (ሪንግቶን)እንደሰማሁብ  ከአዲሱ አልበምህ ሳይሆን አይቀርም …ተሳሳትኩ?
14ኛው ዘፈን ነው - ‹‹እስዋን ተዋት›› የሚለው። የግጥሙ መነሻ ሃሳብ የማሚላ ነው፡፡ ሙሉውን ግጥም የሰራው ሳሚ

ሎሬት ነው፡፡ በጣም ጎበዝ የሰፈሬ ልጅ ነው፤ ሳሚ፡፡ ዘፈኑ ቀዝቀዝ ብሎ መልዕክቱም ደስ ይላል፡፡
“እስዋን ተዋት” ነው የሚለው፡፡ አንዳንዴ ጓደኞችሽ  ያንቺ ባህሪ ያልሆነውን ነገር ያወራሉ አይደል…”ተዋት በቃ! ተዋት

አትሟት.እኔ እስዋነቷ ነው የምፈልገው… በቃ እንደዚህ አትበሏት..ተዋት” ..ነው የሚለው፡፡ ልጅቷ ሳቅ፣ ጨዋታና ጭፈራ

ትወዳለች፤ ሌላ ምንም ጥፋት የለባትም፡፡ ግን አለ አይደል ሁልጊዜ ነጌቲቩን የሚያወሩ አሉ፡፡ እነሱን ነው … “ተዋት”

የሚለው፡፡

Read 6748 times