Sunday, 19 January 2014 00:00

“ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

              እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሠላም አደረሳችሁ፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በቃ የአበሻ ልጆች በየሄድንበት ‘ትክሻውን የሚያሳየን’ ይብዛ! ግራ ገባን እኮ… ገሚሶቹ “በህገ ወጥ መንገድ ገብታችሁ…” አሉና አስወጡን፣ ገሚሶቹ ደግሞ…“በህገ ወጥ መንገድ ስለገባችሁ አሽቀንጥረን ልንወረወራችሁ ነው …” እያሉን ነው፡ (ዚምባብዌ አለችበት ነው የተባለው!) ይሄን ሁሉ “የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል” ብለን ዝም አልን… (“ይሁን ብለን ዝም አልን…” የምትለው የመጽሐፉ ቃል ‘ትመቸኛለች’፡፡) አሁን ደግሞ ያ ሁሉ አልበቃ ብሎ ጭራሽ በህጋዊ ሰነዶች ያውም ‘ዓለም ላወቀው ፀሀይ ለሞቀው ሥራ’ የሚሄዱ ጋዜጠኞችን መከልከል… “ልብ ያለው ልብ ያድርግ” የሚያሰኝ ነው፡፡

ምን ገረመህ አትሉኝም… የስፖርት ጋዜጠኞቹ እንደዛ ሲጉላሉ “ህጋዊ በሆኑ ዜጎቼ ላይማ እንዲህ ማድረግ አትችሉም!” ምናምን የሚል… “የእኔ ጋሻ፣ የእኔ መከታ!” የሚባለው አይነት ኦፊሴላዊ ድምጽ መጥፋቱ፡፡ አሀ…ሳንወድ በግድ “የአህያ ባል…” ምናምን የሚሉት ተረት ትዝ ሊለን ምንም አልቀረማ! እኔ የምለው…እኛ ሰውዬ… “ንቀውናል፣ ደፍረውናል፣ ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ሞተናል!” ምናምን አልነበር ያሉት! ይኸው ከስንት ዘመን በኋላ ንቀቱም፣ ድፍረቱም ቅጥ እያጣ አይመስላችሁም! ነገራችን እኮ…አለ አይደል… “ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል” ሆኗል፡፡ ምንም ‘የምንሸጠው ዳዊት’ ባይኖረንም ለመከራ ያለን እየሆንን ነው፡፡ ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” የሚሏት ተረት ትዝ ትላችኋለች? እንዴት አሪፍ አባባል መሰለቻችሁ፡፡

‘ጎመን እየቀነጠስን” ምች የሚመታን በዛና! ይቺን ስሙኝማ…በዛ ሰሞን አንድ ስፍራ ላይ ሁለት ሰዎች በሆነ ነገር ይጋጫሉ፡፡ ገላጋይ ሀይ፣ ሀይ ብሎ እንደምንም ለያይቷቸው እያስማማቸው እያለ፣ የአንደኛው ጓደኛ የተባለ ሰውዬ ይመጣል፡ እናላችሁ… ጉዳዩን ሳያውቅ፣ “በምን ተጋጩ…” እንኳን ብሎ ሳይጠይቅ፣ ዋናው አጥፊ የእሱ ጓደኛ ይሁን፣ አይሁን እንኳን ሳያውቅ ነገሩን እንደ አዲስ ጀመረው፡፡ ዋናው ባለጉዳይ እኮ “ይቅር ለእግዜር እየተባባለ ነው! እናላችሁ…በየቦታው ‘ጎመን ቀንጥሰን ምች የሚመታን’ በ‘ማይኮነስረን’ አቧራ የምናስነሳ መአት ነን፡፡ “ነገር የሚከረው ጎንጓኙን ሲያገኝ ነው” የሚሏት ተረት አለች፡፡ ፈረንጆቹ ሰው በማያገባው ነገር ጥልቅ ሲል…‘ኢትስ ነን ኦፍ ዩር ቢዝነስ’ የሚሏት ኩም ማድረጊያ አባባል አለቻቸው፡፡ እኛ ዘንድ ያለጉዳያችን ‘የምንለጠፍ’፣ ‘አብራችሁ ካልሰፋችሁኝ’ የምንል እየበዛን ነው፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንዴት ነው ባህሪያችን መሽቶ ሲነጋ መቶ ሰማንያ ዲግሪ ተሽከርክሮ ወዲያኛው ጫፍ የሚሄደው! ምን መሰላችሁ…ትናንትና “ኑሮ ከበደን እያልን እየጮህን እርምጃ የማይወስዱት እነኚህ ሰዎች ጭራሽ በምድር ላይ ያለን አይመስላቸውም እንዴ!” ምናምን ስትባባሉ የነበረው ሰውዬ፤ በሦስተኛው ቀን መቶ ሰማንያ ዲግሪ ይሽከረከርና… “ምን አለ በለኝ በጥቂት ዓመት ውስጥ ሦስት ዲጂት ዕድገት ባንገባ…” ምናምን አይነት ነገር ይላችኋል፡፡ ወይ ደግሞ ትናንት ይሄ የባቡር፣ የመንገድ፣ የህንጻ ሥራ ምናምን አሪፍ ነገሮች አይደሉ! አዲስ እኮ ሲንጋፖርን ልትመስል ምንም አልቀራት…” ምናምን ስትባባሉ የቆያችሁት ሰው በሦስተኛው ቀን… “እኔ የምለው እነኚህ ሰዎች መንገዱን ሁሉ ቆፍረው፣ ቆፍረው… ጣልያን የደበቀው ማርትሬዛ አለ ተብለዋል እንዴ!” ምናምን ይልላችኋል፡፡ ግራ ገባን …አይደለም ለወራት ወይም ለዓመት የተለያየው ሰው፣ ሳምንት ቆይተን የምናገኘው ሰውም ‘ሪሳይክልድ’ ምናምን ሆኖ እየመጣ ግራ ገባን! (በዛ በመተሳሰቡ ዘመን ቢሆን… “እኔን ግራ ግብት ይበለኝ! ምነው እንዲህ ሆድ ባሰህ!” የሚል አዛኝ አይጠፋም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን “ታዲያ አካሄዱን አላውቅበት ብለህ ስትደናበር ግራ ቢገባህ እኛ ምን እናድርግህ! ባወጣ ያውጣህ! አይነት ነገር ሆኗል!) እናላችሁ ‘ጎመን እየቀነጠስን ምች የሚመታን’ ስንበዛ ሁሉም ነገር ‘አርቲፊሻል’ ይሆናል፡፡ የራስ እምነት፣ የራስ ሀሳብ ብሎ ነገር የለም፤ ሀሳብና እምነት አንጻራዊ ናቸው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…) ዋናው ‘ጨዋታ’ ጎመን ቀንጥሰን በምች ለመመታት አዋጪውን መንገድ ማወቁ ሆኗል፡፡

ነገርዬውማ እንግዲህ እንዲህ የሚያደርገን እስከምን ድረስ መሰላችሁ…የሚያዋጣ ገበያ እስኪደርስ! በሥራ አካባቢ በሉት፣ በመኖሪያ አካባቢ በሉት፣ በሌሎች ማህበራዊ …በሉት ጎመን ቀንጥሰን ምች የሚመታን የሌለንበት ቦታ የለም፡፡ ስሙኝማ…ታዋቂ ሰዎች አካባቢ፣ ፈረንካ ያላቸው ሰዎች አካባቢ፣ ወፍራም ላይ የሚቀመጡ ሰዎች አካባቢ የማይጠፉ ‘ባለሟሎችን’ ተመልከቱ…ምን አለፋችሁ “ሰው ይሄን ያህል ይወርዳል!” ያሠኛችኋል፡፡ ሬስቱራንት ውስጥ አሳላፊ ካልመጣ የሚቆጡት ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፣ ባለ ወፍራም ወንበሩ ሊፍት ውስጥ ቀድሞ እንዲገባ መንገድ ካልተለቀቀ ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፣ ለታዋቂዎቹ ሰዎች ጠብ እርግፍ ካላላችሁ ‘ምች የሚመታቸው’ ባለሟሎቹ ናቸው፡፡ የ‘ቦተሊካ’ ነገሩንማ ተዉት፡፡ “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” ተረት በትክክል የምትሠራው እዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ወገን ወይ በዚያ ወገን በመሆናችሁ፣ ወይንም ናችሁ ተብሎ በመታሰቡ ‘የሚወርዱባችሁ’… አለ አይደል… ‘ጎመን ቀንጣሾቹ’ የምች ሰለባዎች ናቸው፣፣ (ቂ…ቂ…ቂ….) እግረ መንገዴን ሀሳብ አለን…እነኚህ የበዙት ‘የፍረጃ’ ስሞች በአንድ ይጠቃለሉልንማ! አሀ…በዛብና! የበፊቱ አሪፍ ነበር፡፡ በቃ ነገራችን ‘አላምር ካለ’…ፀረ አብዮተኛ ይባላል አለቀ፣ ደቀቀ፡፡ እንደ ዘንድሮ… ‘ናፋቂ’ የለ…‘ምናምኒስት’ የለ…‘ኒኦ ምናምን’ የለ… ‘አፍቃሪ ምናምን’ የለ… እና የምንጠራባቸው ‘የፍረጃ ስሞች’ ተጠቃለው አንድ ይሁኑልንማ፡፡ አሀ… ጎመን ቀንጥሰው ምች የሚመታቸው ቃላት መለማመጃ አያድርጉና! እኔ የምለው… “በቀደም ሁሉን አንድዬ ፊት ወስደህ ስታስለፈልፍ ምነው የአንተ ቢጤ ጋዜጠኞችን አልጠቀስክ…” ምናምን ያልከኝ ወዳጄ…ምን መሰለህ የእኛ ነገር ለአንድዬ ለራሱ እንኳን ግራ የሚያጋባ ሆኗል! አሀ…ልክ ነዋ… እንደ ጋዜጠኛ ‘ማህበራት መፍላት’ ከሆነ ብዛታችን እኮ… አለ አይደል… እናላችሁ ጋዜጠኛ አንድዬ ፊት ይቀርባል… “አንተ ደግሞ ምን ነበርክ?” “ጋዜጠኛ…” “ይቅርታ ምን አልከኝ?” “ጋዜጠኛ፡፡

” (አንድዬ ከት ብሎ ይስቃል) “አንድዬ…ምነው ጋዜጠኛ መሆን ይህን ያህል ያስቃል?” “አይ ምን….” (እንደገና ሳቅ ያቋርጠዋል) “ኧረ አንድዬ ስሜቴን እየጎዳህብኝ ነው?” “ይቅርታ የእኔ ልጅ…የእኔ ልጅ ልበልህ እንጂ! ወይ ጋዜጠኛ! አንተን ለብቻህ ነው የማናግርህ?” “ምን አጠፋሁ…” “መጀመሪያ ምን ጋዜጣ ወይም ምን ጣቢያ ላይ ነው የምትሠራው?” “ጌታዬ ጋዜጠኛ ለመባል የግድ ወረቀት ላይ መለቅለቅ ወይም መለፍለፍ አያስፈልገኝም፡፡ ጌታዬ ከፈለግህ የጋዜጠኛ ማህበር አባልነት መታወቂያዬን አሳይሀለሁ፡፡” “እሱ አይደል እኔንስ ግራ የገባኝ… ነው ወይስ ማህበር የምታቋቁሙት እንደ እግር ኳሱ አሥራ አንድ፣ አሥራ አንድ እየሆናችሁ ነው!” ወዳጄ..ይኸው ስለ እኛ አወራሁ፡፡ “ተልባ በጥባጯ እያለች ጎመን ቀንጣሿ ምች መታት…” የሚለው ተረት “ዘንድሮ አይሠራም…” የሚባልበትን ዘመን ያምጣልንማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4573 times