Saturday, 11 January 2014 12:01

አፍሪካዊ ፍልስፍና? ቀልድ ነው!

Written by  ዳንኤል ተሾመ ተክሉ
Rate this item
(1 Vote)

“አፍሪካዊ ማንነት ሳይፈጠር አፍሪካዊ ፍልስፍና የለም”

አቶ ደረጀ ሕብስቱ፤ ታህሣሥ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “የአውሮጳ ፈላስፋዎችን የሚተቸው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ!” በሚል ርእስ ባቀረቡት ፅሑፍ፤ ፕሮፌሠር ፀናይ ሠረቀብርሀን በአፍሪካዊ ፍልስፍና አስፈላጊነት ላይ የሚያራምዱትን አቋም አስነብበውናል፡፡ የጽሑፌ ዓላማ ለፕሮፌሠሩ ተጨማሪ እይታ ማከል ነው። የአቶ ደረጀ ጽሑፍ ጭብጥ፤ አፍሪካውያን የነገሰባቸውን የአውሮፓ ፍልስፍና አሽቀንጥረው በመጣል በራሳቸው ፍልስፍና ሊተኩት እንደሚገባ ይጠቁማል። አውሮፓውያን ዓለምን በፍልስፍና እንዴት ለመቆጣጠር በቁ? አውሮፓውያኑ የተለዩ ሰዎች በመሆናቸው አይደለም፡፡ አውሮፓውያን የደረሱበት የማህበረሰብ እድገት ደረጃ እውቀትን በተሻለ መልኩ በዓለም ዙሪያ ለማሰራጨት ያስቻላቸው በመሆኑ እንጂ። ፕሮፌሠር ፀናይ፤ የዘረዘሩት የአውሮፓውያኑ ዘረኝነት የማንከራከርበት ተጨባጭ እውነት ነው። ዘመኑ ዘረኝነት የነገሰበት ነበርና አውሮፓውያኑን የዘመናቸው ዘረኝነት ሣይዳብሳቸው አላለፈም። ሠበር ዜና አይደለም ለማለት ነው። የአውሮፓንም ይሁን የትኛውንም ማህበረሰብ ፍልስፍናው አይፈጥረውም፡፡

ባንጻሩ ሁሉም ማህበረሰብ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ ፍልስፍናው ይገልፀዋል፡፡ ይህንንም በምሳሌ ለማስቀመጥ ያህል ኢትዮጵያ ሠፊ የኢንዱስትሪ መሠረት ሳይኖራት ስለ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ንቅናቄ መቀስቀስ አገር ለማስተዳደር የሚበቃና የሠፊውን ህዝብ ተቀባይነት የሚያገኝ ፍልስፍና አይሆንም፡፡ የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ፋብሪካ፣ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ መሠረት ሲጣል ግን ስለፋብሪካ ሠራተኞች መብትና ተያያዥ ጉዳዮች ማውራት ይጀመራል፡፡ በጊዜ ሂደትም ሠፊ ተቀባይነትን የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ይደርሣል። ይህ የሚያሳየው ማንም ማህበረሰብ በውስጡ የሌለውን ነገር ፍልስፍናው እንደማይገልፀው ነው። ይህ እንግዲህ ከሌሎች ማህበረሰቦች በውሰት የሚመጡ ፍልስፍናዎች ሳይጤኑ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጣ ፍልስፍና በአገር ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ይፈልጋል፡፡

ይህ ምቹ ሁኔታ በውድ ወይንም በግድ የሚፈጠር ነው። ፍልስፍናዎች ይጋጫሉ። የኃይል ሚዛኑ ያደላለት ያሸንፋል። የእንግሊዙ ፍልስፍና፤ የህንዱን የጨፈለቀው በትክክለኝነቱ ልቆት ሣይሆን የእንግሊዙ መትረየስ ከህንዱ ጎራዴ በልጦ ስለተገኘ ብቻ ነው። የተወሰኑ ሰዎች የውጭውን ፍልስፍና ተቀብለው ወደ አገራቸው ቢመለሱና ከውጭ ሰው የተማሩትን ላገራቸው ሰው ለማስተማር ቢሞክሩ፣ አገራቸው ውስጥ ከውጭ ላመጡት ፍልስፍና አመቺ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር የሚያስተምሩት ነገር ተቀባይነት አያገኝላቸውም፡፡ ሰፊው ህዝብ አመለካከታቸውን የሚቀበልበት ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ምሳሌ እንውሰድ። በስልሳዎቹ እስከ አብዮቱ መባቻ የተማሪዎች ንቅናቄ ከሞላ ጎደል በማርክሲዝም ዙርያ የሚሽከረከር ነበር። ፕሮፌሠር ፀናይ ቃል በቃል ባይሉትም ካርል ማርክስ ፍልስፍናውን ያስቀመጠው፤ በኢንዱስትሪ ከተራመደው ምእራብ አውሮፓ በተለይም ከድህረ-ኢንዱስትሪ አብዮት እንግሊዝ እይታ አንጻር ነው፡፡ ጥሩ፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማርክሲያዊ አብዮት ለማካሄድ ሲነሱ፣ ኢትዮጵያ ያኔ ቀርቶ አሁን እንኳን ድህረ-ኢንዱስትሪ-አብዮት እንግሊዝ የነበራትን ያህል የኢንዱስትሪ መሠረት የላትም፡፡ ማርክሲዝም እንዴት በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ተቀባይነትን አገኘ? ኢትዮጵያ የተስፋፋና በወጉ የደረጀ የኢንዱስትሪ ተቋማት ባይኖሩዋትም ለዳበረ ኢንዱስትሪ እርሾ የሚሆኑ መለስተኛ ድርጅቶች ነበሯት፡፡

እንግዲህ ሁሉም አውቃለሁ ባይ እንደሚያጣቅሰው፤ በ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴተኛ አዳሪዎች ከኢንዱስትሪ ሠራተኞቹ የበለጠ ቁጥር ነበራቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የሠራተኛውን መደብ አብዮታዊ አመራር የሚያራምደው ማርክሲዝም እንዴት በኢትዮጵያ ሊሰርፅ ቻለ? አንድ አብይ ምክንያት ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ማርክሲዝም ከኢንዱስትሪ ማህበረሰብ አንጻር ቢነደፍም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ግብርናና ገጠራዊነት ያመዘነባቸው ማህበረሰቦችም ቢሆኑ ሊመስጣቸው የሚችል እኩልነት፣ ፍትህ፣ ነጻነት ወዘተ… አስተምህሮቶች የነበሩት በመሆኑ ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ለዘመናት ገኖ የነበረው የገዢው መደብ ፍልስፍና ባገር ውስጥ ተቀባይነት ባገኘ የውጭ ተፅእኖ ተደረመሰ። ፕሮፌሠሩ የሚያቀርቡት አማራጭ፣ በተስፋፋው የአውሮፓ ፍልስፍና ምትክ አፍሪካዊ ፍልስፍና መፈለግ አለብን የሚል ነው፡፡ መሠረታዊ ግጭት ሊፈጠር ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከሆነ አፍሪካዊ ፍልስፍና የሚገልፀው አፍሪካዊ ማንነትና አውሮፓዊ ፍልስፍና የሚገልፀው አውሮፓዊ ማንነት ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ አፍሪካዊነት ከጂኦግራፊአዊ መገለጫነት ወይንም አህጉርነት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡

በአንጻሩ አውሮፓዊ ማንነት በዳበረ የግንኙነትና የመጓጓዣ መንገዶች ምክንያትነት የተቀየጠ ማንነት ፈጥሯል፡፡ የአብዛኛው አፍሪካዊ ማህበረሰብ ማንነት በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎቹ ከመደምሰሱ በፊትም ቢሆን አፍሪካ የተዋሀደ ማንነት አልነበራትም፡፡ ሁሉም ሠፈርና መንደር ራሱን ችሎ የሌሎችን ትብብር ሳይሻ ግዛት ነበር፡፡ ረጅም የመንግሥት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ እንኳን ሙሉ በሙሉ የተዋሀደች አገር አልነበረችም፡፡ ቅኝ አገዛዝ በአፍሪካ ሲነግስ ቀድሞ የነበረው የአፍሪካውያን የሠፈርና መንደር ማንነት ተጨፈለቀ። በኋላ ላይ በመላው አህጉር የተቀጣጠለው የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል በአፍሪካውያን ማንነት ላይ ከመመሥረት ይልቅ አውሮፓውያንን በመቃወም ላይ ብቻ የተመሠረተ ነበር፡፡ ማንነታቸውን በቅኝ አገዛዝ የተቀሙ ህዝቦች፣ ነጻ ከወጡ በኋላ የተጎናጸፉት ቀድሞ አውሮፓውያኑ ከመምጣታቸው በፊት የነበራቸውን የሠፈር ማንነት አይደለም። የተጎናጸፉት በነጻነት የትግል ሂደት የፈለሰፉትን አዲስ ማንነት ወይንም ብሄራዊ ስሜት ነው። ከዚህ አንጻር የአውሮፓን ፍልስፍና እንዲተካ በፕሮፌሠሩ የታለመው አፍሪካዊ ፍልስፍና፣ ከፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉ የተጣባ ከመሆን ውጭ መንገድ ስለማይኖረው የታሰበለትን ከአውሮፓ ተፅእኖ ነጻ የመሆን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም። ይህም ማለት አፍሪካዊ ማህበረሰብ የአውሮፓ ፍልስፍናን ደግፎ ሲንቀሳቀስ በአውሮፓ ተፅእኖ ሥር የመውደቁን ያህል የአውሮፓን ፍልስፍና ነቅፎ ቢንቀሳቀስ በአውሮፓ ተቃራኒ ተፅእኖ ስር ይሆናል፡፡ አፍሪካዊ ማንነት የሃምሳ ሁለት አገራት በአንድ የአህጉር ካርታ ከመታጨቅ በመለስ ተቀይጦ አንድ ወጥ የሆነ መልክ ሳይኖረው፣ አፍሪካዊ ፍልስፍና አንድ ወጥ ማንነትን ሊገልፅ አይችልም።

አፍሪካዊ ማንነት ሳይፈጠር አፍሪካዊ ፍልስፍና የለም ለማለት ነው፡፡ ፍልስፍና በማህበረሰቡ የአስተዳደር ዘይቤ የሚወሰን በመሆኑ ከፖለቲካ ጥያቄነት አያልፍም። ፖለቲካዊ ጥያቄው አፍሪካ ከአውሮፓ ተፅእኖ ነጻ የሆነ የራስዋን ፍልስፍና ማራመድ አለባት ወይ የሚለው አይደለም። አፍሪካ ማንነትዋን የምትገልፅበት ፍልስፍና ለመመስረት አስፈላጊ የሆኑት ሁኔታዎች አሏት ወይ የሚለውም አይደለም። ፖለቲካዊ ጥያቄው አፍሪካዊ የሚባል ወጥ የሆነ ማንነት አለ ወይ የሚለው ነው። ምናልባት የክብርም የኩራትም ጥያቄ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኛ ከፈረንጅ አናንስም፤ የራሳችንን ነገር እንፍጠር የሚል ስሜት እንደሚኖር መረዳት ይቻላል፡፡ የሆነው ሆኖ የምንፈጥረውን ፍልስፍና ልናዘልቀው የምንችለው የምንኖርበት ማህበረሰብ በበቂ ሊገነዘበው የሚችል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፕሮፌሠር ኃሳብዎት ይገባናል፡፡ ዳሩ ግን አፍሪካዊ ፍልስፍናን ለመፍጠር ስንነሣ አፍሪካዊ ማንነትን ገና እንዳልፈጠርን አንርሣ ለማለት ነው። ሰናይ ጊዜ!! > 

Read 2870 times