Saturday, 28 December 2013 12:21

“ሐቅ ሐቁን ለህፃናት”

Written by  ካሌብ ንጉሴ
Rate this item
(0 votes)

በጥላቻና በእርግማን የተሞላ “መጽሐፍ”

ደራሲ - “አታኸልቲ ሓጐስ
ርዕስ -ሖቅ ሖቁን ለህፃናት
የገፅ ብዛት - 175
የታተመበት ዘመን - 1998 ዓ.ም
የሽፋን ዋጋ - ብር 15.00
መፅሃፉ፤ በአጤ ቴዎድሮስ፣ አጤ ዮሐንስና አጤ ምኒልክ ዘመነ ግዛት ላይ ተመስርቶ የሶስቱንም ነገሥታት ጥንካሬ ሳይሆን ድክመት ለማሳየት የሚሞክር ነው። በተለይ አጤ ኃይለሥላሴን ጨምሮ በዋናነት የሸዋንና የአጤ ምኒልክን “ከሃዲነት” ለማሳየት ያለ የሌለውን የስድብና የእርግማን ናዳውን ለማውረድ ይሞክራል፡፡ አጤ ዮሐንስን ለመናጆነት ቢጨምርም ጭካኔያዎቻቸውን ሌላው ቢቀር የእህታቸው ባል በነበሩት አጤ ተክለጊዮርጊስ ላይ የፈጸሙትን ዘግናኝ ጭካኔ እንኳ አይጠቅሰውም፡፡
ጥያቄ የሚያስነሳው ገና ከርዕሱ ነው፤ “ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” ይላል፡፡ በርዕሱ መሠረት መጽሐፉ የታለመው ለህፃናት ነው ማለት ነው፡፡ ግን ለህፃናት በሚመጥን መልኩ አልተዘጋጀም፡፡ ቋንቋው የተቃና አይደለም፤ ታሪኮቹ እዚያና እዚህ ይወራጫሉ፤ ከሐቅ ይልቅ ተራ ዘለፋና ስሜት ይበዛበታል፡፡ ቀድሞ ነገር ሐቅ የሚያስፈልገው ለህፃናት ብቻ ነው? ሐቅ ሐቁ ለህፃናት ከሆነ፣ ውሸት ውሸቱን ለማን እንዳሰቡለት ፀሐፊው አልገለጹም፡፡
በሶስቱ ነገሥታት ላይ ተመሥርቶ የተጻፈው “መጽሐፍ”፤ ከታሪክ ዘውግ ሊመደብ ቢችልም አንድም የታሪክ አጻጻፍ ባህርይ አይታይበትም፤ ፀሐፊው ራሳቸው እንደነገሩን የታሪክ ዕውቀት የላቸውም፡፡ ከታሪክ አዋቂነት ይልቅ ጨቋኞችን ለመጣል ወደ ትግል መግባታቸውን ነግረውናል (ገፅ 4)፡፡
“ንፁህ ህሊና ያለው ሰው ከእንግዲህ ታሪክ እየሠራን ወደፊት እንገሰግሳለን እንጂ ተመልሰን ቁስል እየነካካን እንኖራለን የሚል አልነበረም” የሚሉን ፀሐፊው፤ እዚሁ ገጽ ላይ (ገጽ 5) መልሰው የስድብ ናዳቸውን ያወርዱታል፡፡ ለጽሑፉ መነሻ የሆነው የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው ድንጋጤ መሆኑን ከመጀመሪያዎቹ የ“መጽሐፉ” ገጾች መገንዘበ ይቻላል፡፡
አንድ ታሪክ ጸሐፊ ከሁሉ አስቀድሞ ሊጽፍ በፈለገው ጉዳይ ላይ የተሟላ ዕውቀት፣ ትዕግስት፣ ሚዛናዊ አስተሳሰብና ክህሎት ሊኖሩት ይገባል፡፡ ታሪክ ልብወለድ አይደለም፤ ልብወለድ ስላልሆነም እንዳሻን እየፈጠርን ምናባዊ ታሪክ ልንተርክ አንችልም፡፡ በዚህ ስሌት ሲታሰብ “ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” በብዙ እንከኖች የተሞላ ነው፡፡
“መጽሐፉ” እጅግ ብዙ ገፅ የሰጠው ሸዋንና አጤ ምኒልክን በመዝለፍና በከሃዲነት በመወንጀል ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያን ታሪክ በመቶ ዓመት ብቻ ለመወሰን ይዳዳዋል፤ የዚህ ሰበቡም በአጤ ምኒልክ ላይ ያለውን መሪር ጥላቻ ለማሳየት ይመስላል፡፡
በመሠረቱ ይህ ታላቅ ስህተት ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው’ኮ ከሉሲ ነው፡፡ እሱም ቢሆን የስነሰብእ እና የከርሰምድር ተመራማሪዎች አዲስ ግኝት እስከሚያወጡ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪክ ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እንደዚህ “መጽሐፍ” ጸሐፊ፤ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የመጣ ሰው መቸም ይህን ይክደዋል ብዬ አላምንም፡፡ ትግራይ’ኮ የረጅም ጊዜ ታሪካችን መነሻ፣ የሥልጣኔዎቻችን እና የሃይማኖቶች ሁሉ በር፣ የኪነጥበባት ምንጭ ናት። የየሃን ምኩራብ፣ የአክሱምን ሀውልቶች፣ የኢዛናን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ በቅርቡ የተገኘው የዓድአካውህ መካነ ቅርስና ሌሎችንም ለአፍሪካና ለዓለም ካበረከተ ታላቅ ህዝብ ውስጥ የወጣ ሰው፤ ታሪካችንን በመቶ ዓመት መጉመድ እጅግ አሳዛኝ ድፍረት ነው፤ ወይም አለአዋቂነት ይመስለኛል፡፡
እንደሚመስለኝ የመቶ ዓመቱ ተረት ሊፈጠር የቻለው አጤ ዮሐንስ በጐጃም ላይ በፈፀሙት ቅጣት ተበሳጭተው ታላቁን የትግራይን ህዝብ ጨምረው በአወገዙት ወይም በዘለፉት አፈወርቅ ገብረየሱስ ምክንያት ነው፡፡ አፈወርቅ አጤ ቴዎድሮስንና አጤ ዮሐንስን አውሬ አድርገው፣ አጤ ምኒልክን የመልአክነት ማዕረግ አቀዳጅተዋል፡፡ ለዚያ ደፋር ጽሑፋቸውም ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ በጊዜው ተመጣጣኝ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ በዚያ ጽሑፍም ነጋድራስ ገብረ ህይወት የአገራችን የመጀመሪያው ሃያሲ መሆናቸውን የመስኩ ምሁራን አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረየሱስ “አጤ ምኒሊክ” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ ከታተመ 105 ዓመት ሆኖታል፡፡ ዛሬም ያንኑ ስድብ እያነሱ መቃቃርንና ጥላቻን ለትውልዱ ማስተላለፍ ፋይዳው አይገባኝም። “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ባሰ” እንደሚባለው፣ እያንዳንዱ መሪ በምስኪኑ ህዝብ ላይ የፈፀመውን የግፍ ዓይነት ብንዘረዝር፣ ሌላው ቀርቶ በሃይማኖት መጻሕፍት (በተለይ በገድሎች) ሰበብ ህዝብ ምን ያህል ሲንቋሸሽ እንደኖረ መግለጽ ይቻላል፡፡ ግን ፋይዳ የለውም፡፡
“በታሪክ የሚኮሩ ኋላ ቀሮች በአገራችን ብዙ ናቸው (ገጽ 8)” የሚሉን ጸሐፊው፤ ከታሪካችን ሌላ በምን እንደምንኮራ ሊነግሩን አልሞከሩም፡፡ “የዝንጀሮ ሰነፍ የአባቱን ዋሻ ይፀየፍ” እንዲሉ ካልሆነ በቀር ለምን በታሪካችን አንኮራበትም? ሰውን እንደ እንቁላል ቀቅለው የበሉት የሂትለርና ሙሶሎኒ ታሪክ እንኳ ከእነ እድፉ ከእነ ጉድፉ ተመዝግቦ እየተጠበቀ ነው፡፡ እንዲያውም በጀርመንማ “አዲሶቹ ናዚዎች ነን” የሚሉ ወጣቶች ፀጉራቸውን እየተላጩ በዋና ዋና ጐዳናዎች ሳይቀር መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
“ጥቃቅን ነገሮችን ትተን በተግባር ላይ ህገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ብቸኛና ሁነኛ መፍቻ ነው። ይህንን የሚቃወም ትግሬዎችን በመጥላት ብቻ በስሜት የሚነጉዱ ሸዋዊ የሚኒልክ አስተሳሰብ ጠፍቶባቸውና ጨልሞባቸው የሚባዝኑ ናቸው” (ገጽ 12) የሚለው አገላለጽ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ታሪክንና ደፋር ዘለፋን ምን አገናኛቸው ያሰኛል፡፡ በአጤ ምኒልክ ዘመን አፈወርቅ ስለተሳደበ፣ በእኛም ዘመን የፈለግነውን ህዝብና ወገን ብንሰድብ ሃይ ባይ የለንም” ከሚል የጉራ መንፈስ በመነሳት ከሆነ ፍፁም የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡
በመሠረቱ ህገመንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ወዶና ፈቅዶ ያረቀቀውና ያፀደቀው እንጂ የትግራይ ክልል ብቻ የግል ሃብት አይደለም፡፡ በ1987 ዓ.ም በፀደቀ ህገመንግሥት ሰበብ ወደ ኋላ 100 ዓመት ተጉዞ ምኒልክንና ሸዋን መዝለፍ ከየት የመጣ ታሪክ ፀሐፊነት ነው? ህገመንግስት የእግዚአብሔር የእጅ ሥራ ውጤት አይደለም፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ እንዳፀደቀው ሁሉ እንኳን መቃወም ከነአካቴው ሊሰርዘውም ይችላል፡፡ ህገመንግስቱን መቃወም ማለት በምንም መንገድ የትግራይን ህዝብ መጥላት ሊሆን አይችልም፡፡
ሌላውና ያለ ቦታው የደነጐሩት ጉዳይ የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች ሲመጡ በጦርነት መሆኑን የገለጹበት መንገድ ነው (ገጽ 16) ይህ ትልቅ ስህተት ነው፤ ክርስትናም ሆነ እስልምና ወደ አገራችን የገቡት ያለምንም ሁከት ነበር፡፡ ለዚህ ማስረጃ ፍለጋ ጸሐፊው ሩቅ መሄድ የለባቸውም፤ ውቅሮ የሚገኘውን የነጃሽ መስጅድ እና አክሱም ጽዮንን ጐብኝተው ሃይማኖቶቹ ያለ አንዳች እንከን ወደ አገራችን እንደገቡ መረዳት ይችላሉ፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴንና አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያንም ፀሐፊው “ደቂቀ ምኒልክ” በማለት “ስሁል ሚካኤል” ለዘመነ መሳፍንት መከሰት አስተዋጽኦ አላቸው” በማለታቸው ወርፈዋቸዋል። ይህ አይነቱ ዞናዊ አስተሳሰብ በመሠረቱ ከአንድ “ታሪክ እጽፋለሁ” ብሎ ከተነሳ “ምሁር” የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ስሁል ሚካኤል አጤ ኢዮአስን ገድለው ወይም አስገድለው ከሆነ ታሪኩ መጻፍ ያለበት እንዳለ እንደነበረ ነው፡፡ ጸሐፊው “አላስገደሉም፤ አልገደሉም” ብለው የሚከራከሩ ከሆነ የቀደምት ጸሐፊያኑን ሃሳብ በማስረጃ ነው ውድቅ ማድረግ ያለባቸው እንጂ ተራ ዘለፋ የአዋቂነት መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡
“አጤ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ አደረጉ” የሚለው ሃሳብም ጸሐፊውን በእጅጉ አንገብግቧቸዋል፡፡ (ገፅ 20-21)፡፡ “እንደ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ እንኳን የጐንደር ንጉስ ወይም የሌላ አካባቢ ንጉስ የሚባል ንጉስ ታይቶ አይታወቅም” ማን ነው ታዲያ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ያለና በአፄ ቴዎድሮስ ወደ አንድነት የመጣ?” ሲሉም ይጠይቃሉ፤ በስማቸው አደባባይና መንገድ መሰየሙንም ይቃወማሉ፡፡ (ገ. 26)  
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የጸሐፊው የታሪክ ሊቅነት ፈጥጦ የሚወጣው፡፡ ቀድሞ ነገር “ኢትዮጵያ” ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ብቻ የምታጠቃልል አገር አልነበረችም፤ ሰፊ ግዛት የነበራት ገናና አገር ነበረች፡፡ በየአካባቢውና በየቋንቋው የተሰየሙ በርካታ ነገሥታትም ነበሩ፡፡ በርካታ የአካባቢ ነገስታት ስለነበሩም ነው ማዕከላዊውን ሥልጣን የሚይዘው ሰው “ንጉሠ ነገሥት” የሚል የማዕረግ መጠሪያ የሚሰጠው፡፡
ለምሳሌም በአፋር “ሱልጣን”፣ በሐረር “አሚር”፣ በወላይታ “ንጉሥ”፣ በከፋም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም መሰል የሥልጣን ማዕረጋት ነበሩ፡፡ ሆኖም በአጤ ቴዎድሮስ ተጀምሮ በአጤ ምኒልክ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተማከለ መንግሥት አልነበረም፤ ከአጤ ቴዎድሮስ በፊት የነበሩት ነገሥታት በርካታ የመሆናቸውን ያህል የሚያስተሳስራቸው ፖለቲካዊም ሆነ ማህበረ ኢኮኖሚ ሥርዓት አልነበረም፡፡
“ንጉስ ሚካኤል በወሎ፣ ንጉስ ምኒልክ በሸዋና ከዛ በታች ያሉት ግዛቶች፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት በጐጃም አድርገው ራሳቸው ንጉሰ ነገስት ተብለው በማዕከላዊነት እየመሩ ሥልጣን በየደረጃው ለማከፋፈል መሞከራቸው ያሳያል” (ገፅ 22) ይሉናል ጸሐፊው ሲያስተምሩን። ይህ “ታሪክም” ነው “ሐቅ” ሆኖ ለህፃናት ሊተላለፍ የተፈለገው። በመሠረቱ ይህ ታላቅ ውሸት ነው፡፡ ምኒልክ ከአጤ ቴዎድሮስ ጠፍተው ሸዋ እንደገቡ “ንጉሠ ሸዋ” የሚል ማዕረግ የሰጡት ለራሳቸው ነው፡፡ ራስ ሚካኤልም “ንጉስ” የሆኑት በልጃቸው በኢያሱ አባ ጤና ሲሆን የራስነት ማዕረግ የሰጧቸው ግን አጤ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ የማይካደው ለጐጃሙ ራስ አዳል “ተክለ ሃይማኖት” የሚል ስምና የንጉሥነት ማዕረግ የሰጡ አጤ ዮሐንስ መሆናቸው ነው፡፡
ጸሐፊው የአጤ ቴዎድሮስንና የአጤ ዮሐንስን ጭካኔ ሲያነጻጽሩም በተንሻፈፈ ሚዛን ለማስቀመጥ ሞክረዋል፤ አጤ ቴዎድሮስን በተቻለ መጠን አውሬ ለማድረግ ይሞክሩና አጤ ዮሃንስ ላይ ሲደርሱ ብዕራቸው ይዶለዱምባቸዋል። “አፄ ዮሃንስ እንደ አፄ ቴዎድሮስ በሃይልና በማንጓጠጥ አያምኑም ነበር፡፡ ለሁሉም ተቀናቃኝ መሪዎች በሃይል ደምስሰው ስልጣን ብቻቸው እንዲይዙት አይፈልጉም ነበር። … ሳይቀበሏቸው ሲቀሩ ወደ ጦርነት ገብተው ከማረኳቸው በኋላም ወደ ማሰርና መግደል አይቻኮሉም ነበር፡፡ በጦርነቱ ካሸነፉ በኋላ ጦርነቱ የማያስፈልግ እንደነበረና ለተፈጠረው እልቂት አዝነው ሁለተኛ እንዳይደገም በመጽሐፍ ቅዱስ አስምለው መተማመኛ እንዲፈጠር ያደርጉ ነበር፡፡ እምብዛ መላላታቸው ግን ስህተት መሆኑ አይቀርም (ገፅ 31)” ሲሉም የዮሐንስ ጭካኔ መላላት እንዳስቆጫቸው ጽፈውልናል፡፡
ኧረ ለመሆኑ አድዋ ላይ ተዋግተው የማረኳቸውን የእህታቸውን ባል አጤ ተክለ ጊዮርጊስን እንደ አባ ገሪማ ላይ በምን አይነት መንገድ ነበር የገደሏቸው? እንኳንስ በጦር ሜዳ ተሰልፎ የወጋቸውን አንድም የመከላከል አቅም ያልነበረውን የወሎን ሙስሊም ሀይማኖቱን  በግድ ለማስለወጥ ምን አይነት እርምጃ ነበር የወሰዱት? በ1881 ዓ.ም በጐጃም ሰላማዊ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በከብቱ፣ በቤቱና በደኑ ላይ ሳይቀር ምን ዓይነት የጭካኔ እርምጃ ነበር የወሰዱት? በዚህ ድርጊታቸው የተማረረው ጐጃሜስ ምን ብሎ ገጠመ? እያንዳንዱን የጭካኔ እርምጃ በማስረጃ በማስደገፍ መዘርዘር ይቻላል፤ ግን ዮሐንስም ሆኑ ምኒልክና ቴዎድሮስ መመዘን ያለባቸው በነበሩበት ዘመን በመሆኑ፤ በሌላም በኩል ጐጠኝነትንና ዘረኝነትን ለማራገብ ሌት ከቀን ለሚዋትቱ የዋሆች ደንጋይ ማቀበል ይሆናልና አልፈዋለሁ፡፡
“ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” መጽሐፍ ላይ የወሎ ሙስሊሞችን አስመልክቶ የተገለፀው ሃሳብ ለብቻዬ እንድስቅ አድርጐኛል፡፡
“በወሎ የነበሩ አክራሪ ሸኾች ‘እስላም ሃይማኖትና ሃገር ነው፡፡ በቱርክ ሃይማኖትን የሚያስፋፋ እየመጣልን ነውና ግብፅን ለማገዝ ተነስ’ እያሉ ለግብፅ ወራሪ ሃይል በማገዛቸውና በሃገራቸው ነፃነት ላይ ስለተንቀሳቀሱ ነው ለውጡ የመጣው (ገፅ 32)” ሲሉ ጸሐፊው በወሎ ሙስሊሞች ላይ ዮሐንስ ለምን እንደ ጨከኑ ሊያስተምሩን ሞክረዋል፡፡ ለካ አክራሪነት የተጀመረው ያኔ ነው? ትልቅ “ግኝት” ነው፡፡
ደግነቱ ዮሐንስ ሞተዋል እንጂ ይህን ቢሰሙ “ለምን ትዋሻለህ? ሙስሊሞችን በጭካኔ የቀጣኋቸው ሃይማኖቴን ባለመቀበላቸው ነው” ሲሉ ጸሐፊውን ይወቅሷቸው ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አጤ ዮሐንስ “ሀቀኛ ክርስቲያን” ነበሯ!  
ገፅ 26 ላይ “የተበተነች ኢትዮጵያ አልነበረችም፤ ስለሆነም ቴዎድሮስ አንድ ያደረጉት ህዝብ የለም” ሲሉ ቆይተው፣ በገፅ 35 ላይ ደግሞ የመጀመሪያ ሃሳባቸውን በማፍረስ “አፄ ዮሐንስ ከሳቸው በፊት ተበታትኖ የነበረ የኢትዮጵያ ግዛት ወደ ነበረበት ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አውሮፓ አገር ድረስ ታዋቂነት ያገኘ ነበር” ይሉናል፡፡
ለቴዎድሮስ ሲሆን አገር “አልተበተነም”፤ ለዮሐንስ ሲሆን ግን ይበተናል፡፡ ቀድሞ ነገር አጤ ዮሐንስ በግዛታቸው ላይ የጨመሩት እንኳንስ ጠቅላይ ግዛት አንድ ወረዳ መጥቀስ አይቻልም፡፡ እናም ወዳጄ! “የቄሳርን ለቄሳር!” እንዲሉ፤ የቴዎድሮስን ታሪክ ለቴዎድሮስ፤ የዮሐንስንም ለዮሐንስ መስጠት ይልመድብን፡፡ ሳምንት እቀጥላለሁ፡፡

Read 3290 times