Monday, 25 November 2013 11:28

እግዜርን የሚሞግቱ ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ለሕይወቱ ጣዕም ጭመራ፣ ለነፍሱ ፍካት ግጥም ተምጦ ከተወለደባቸው አንድም ሀገር ጀምሮ የሰው ልጅ ግጥምን ለፌሽታ ብቻ ሣይሆን ለወቀሣና ለሙግት ይጠቀሙበት ዘንድ ወድደው ነበር፡፡
ለምሣሌ ከዕብራዊያኑ ገጣሚ አንዱ የሆነውና የመዝሙር አገልጋይ ነበር የሚባለው ዕንባቆም፣ ወገቡን ታጥቆ ከእሥራኤል አምላክ ጋር ሙግት ገጥሟል፡፡ ጥያቄዎችን ጠይቋል፡፡
ዕንባቆም ጥያቄው መረር ያለ፣ ግራ መጋባቱን ያፈረጠመ ነው፡፡ እንዲህ ይላል- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፡፡
እግዚአብሔር ሆይ፣ ለርዳታ እየተጣራሁ፣
አንተ የማትሰማው እስከመቼ ነው?
“ግፍ በዛ” ብዬ እየጮእሁ፤
አንተ የማታድነው እስከመቼ ነው?
ስለምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ
እንዴትስ ግፍ ሲፈፀም ትታገሳለህ?
እግዚአብሔር ላይ ጥያቄ ያነሱ፤ ለምን እንዲህ ይሆናል? ብለው የጠየቁ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው። በቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ እንኳ የግጥም መጽሐፍ ተብለው የሚጠሩት መዝሙራትና የኢዮብ መጽሐፍ ሣይቀር ቅሬታቸውን አልደበቁም፡፡ ገጣሚያን ለመጀመሪያ ጊዜ ተወልደውበታል፣ ወይም ግጥም ተወልዶበታል በተባለችው ምድር የበቀሉት የብሉይ ኪዳን ፀሐፍት እግዚአብሔርን ሞግተውት ሲያልፉ፣ አንዳንዶቹ መልስ ተሰጥቷቸው ጥያቄያቸውን ወደ ዝምታና ምሥጋና መልሰው ነበር፡፡ ታዲያ እግዚአብሔርን የሚጠይቁ፤ በሽሙጥ እግዚብሔርን የሚወቅሱ፣ በስንኞቻቸው እምባቸውን የሚረጩ፤ በጥርጣሬ እምነትን የሚገረድፉ ብዙ ናቸው። አንዳንዴ ነገሮች ግራ ሲያጋቡኝ ድንገት ብልጭ እያሉብኝ የምፈግግባቸው የሜሮን ጌትነት ጥቂት ስንኞች ዛሬም ትዝ ብለውኛል፡፡
“ጨዋታ” ነው የሚለው ርዕሱ
ንጉሥ ያደርጉሃል
ካሻቸው ወታደር
እግዜርና ሰይጣን
ዳማ ሲጫወቱ
አንተን አርገው ጠጠር፡፡
የዚህ አይነት ስንኞች የሕይወት ውል ፍተሻ ውስጥ ገብተን ሥንዳክር፣ ልባችን ውስጥ የሚከሰቱ ድንገተኛ ምላሾች ይመሥሉኛል፡፡ ልክ አንዳንድ ፈላስፎች በጥያቄ ተቀፍድደው፣ ሕይወት እንቆቆልሽ ሥትሆንባቸው፣ ሀሣባቸውን በወረቀት እንደጠረዙት ሁሉ፣ ገጣሚውም በዜማ ጠቅልሎ ያፈርጠዋል፡፡
ወጣቷ ገጣሚት ሜሮን፤ ሰዎች በዕጣ ፈንታ ይሁን በሕይወት ግብግብ በመንፈሳዊያን ሀይሎች ሥር ናቸው፤ ብላ ሥትገምት፣ ሰዎች የዳማ ጠጠር የሆኑ መሠላት፡፡ እናም ሕይወት የሁለት ሃያላን ጨዋታ ሆኖ ታያት፡፡ ገጣሚ ናትና በብስጭት ነፍስዋን አመናቀረቻት፤ ያኔ ስንኞች ወረቀት ላይ ዘለሉ፡፡ ያላወቅን አይምሠላችሁ የሚሉ ስንኞች፡፡
ሌላው የሀገራችን ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬም ረዘም ያለ ግጥም ፅፎ ፈጣሪን “እውነት ከመንበርህ የለህማ” ብሎታል፡፡
… ምነው እርሾው ተሟጠጠ … ጎታ ጐተራው ታጠጠ
ረሀብ ላንቃው ፈጠጠ … ያዳም ልጅ አፅሙ ገጠጠ
ምነው ጭር አለ ቀየው! ሀሩር ንዳዱ በረታ
ኮርማው ጭማዱ ተረታ
ምነው ነበልባሉ አየለ! ማሳው ተንቀለቀለ
ነቀለ ሞፈር ሰቀለ! ተገድራ ደቀለ
ምነው ምድር ጨነገፈች … ዝላ ተርገፈገፈች
ካስማ እንደተደገፈች ምነው ሳታብብ ረገፈች፡፡
*   *   *
እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት ከመንበርህ የለህማ!
ገጣሚው በሕዝብ ላይ የደረሰው ረሀብና እልቂት፣ የተስፋ ጭርታ፣ የሕይወት መክሠም፣ የሣቅ ስደት አንገብግቦታል፡፡ እናም ይህንን ግፍ እያየህ ምላሽ ካልሰጠህ፣ ጭራሽ የለህም ማለት ነው እያለ ፈጣሪን ይሞግታል፡፡ ገጣሚው በተፈጠረው ችግር ስሜቱ ተነክቷል፣ ነፍሱ አስላለች፡፡ ግን አቅም ስለሌለው ተጠያቂ ነው ያለውን ጠይቋል፡፡ ግና ፈጣሪ የሚመልሰው መልስ ግን የለም! … ምናልባት የሚያዳምጥ ልብ፣ የሚያስተውል አእምሮም ይፈለግ ይሆናል፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው፤ መንገዴ ከመንገዳችሁ ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ እንዲሁ የራቀ ሆኖ ይሆን? ብቻ የፈጣሪና የገጣሚ ሙግት ሺህ ዓመታት ዘልቋል፡፡ ወደፊትም የሰው ልጅና መኖሪያው ዓለም እስካለች ጭቅጭቁና ሙግቱ ይቀጥላል፡፡
በቅርብ ዓመታት (ባለፉት አሥርት) ከታተሙ ግጥሞች ውስጥ ገብረክርስቶስ ደስታ የፃፈው መረር ይላል፡፡ ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬና ሌሎች ደግሞ አብዝተው ይጠይቃሉ፡፡
እግዚአብሔር ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከተነሱት ቅሬታዎች መካከል “የዕድሜ መንገድ ላይ” ያለውን ግጥም አስታወስኩ፡፡
አዳም መከረኛው እልፍ ዛፍ ታድሎ
አንድ ቢያጣ ሣተ
አንድ ቢያጣ ሞተ፣
ለእኔ ለዕድለኛው
አንድ ተፈቅዶልኝ   
እልፍ ተከልክሎ፤
እንዴት ብዬ ልሣት
ዙሪያዬ በሙሉ በለስ ተንጠልጥሎ፡፡
ይህ ግጥም በአዳም ዘመን ከነበረው የሀጢአት ፈተናና ትግል ይልቅ የዛሬው እልፍ ነው ባይ ነው። በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያለውን “ፀጋ” የሚል ብርታት የረሣ፣ ወይም በቂ አይደለም ብሎ እግዜርን በጓሮ በር የሚሞግት ነገር አለው፡፡
በብዙ ነገሮቹ እግዜርን መሞገት የሚያዘወትረው ዳዊት ፀጋዬ፤ “ሕዝብ፣ እግዜር፣ መንግስት” በሚል ርዕስ በፃፈው ግጥሙ እንዲህ ይላል:-
እግዚአብሔር፣
ምን ብሎ ይመልስ የሕዝብን እሮሮ
መንግስትን
እንዲናገር እንጂ እንዳይሰማ ፈጥሮ!
ዳዊት፤ መንግስት የሕዝቡን እሮሮ የማይመልሰው እግዚአብሔር ሲፈጥረው፣ ጆሮ ከልክሎት ነው ይላል፡፡ ልቡ ደንድኖዋል ለማለትም ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ተጠያቂው እግዜር ነው ባይ ነው! ለሕዝቡ እሮሮ ሁሉ መልስ ማምጣት የሚችል ነው እያለ መልሶ ደግሞ አግድም የሕዝቡን ሮሮ መመለስ አይችልም ብሎ ስንኝ ቋጥሯል፡፡
አሁንም ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ እንደ ሙሉጌታ ተስፋዬ ፊት ለፊት ሣይሆን በጓሮ በር የፍትህ ጥያቄ ለመጠየቅ ያንኳኳል፡፡ “ለአንተ ስል” ይላል ርዕሱ፡፡
ሰዎች በረሀብ ሲያልቁ
አፋቸውን በአንተ እንዳያላቅቁ፣
ፍትሕ በምድር ሲጠፋ
ብስጭታቸው እንዳይከፋ
እምነታቸው እንዳይላላ
ነፍሳቸው አንተን እንዳትጠላ፣
“እግዚአብሔር የለም እንዴ?” ሲሉ፣
“አዎ የለም” የምለው
ስለ አንተ ብዬ ነው፡፡
ግጥሙ ረሀብ በዝቶ፣ ጉሥቁልና ነግሦ፣ ፍትሕ ጠፍቶ ሳለ ለዚህ መልስ አልሰጠህም፤ ዝም ብለሃል። ይህንን ያየ ሕዝብ ደግሞ የዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂ “አንተ ነህ” እንዳይል ሰዎች “እግዚአብሔር የለም እንዴ?” ብለው ሲጠይቁኝ አንተን ከወንጀል ነፃ ለማድረግ ብዬ “የለም፤” ብያለሁ ነው የሚለው። በአንድ በኩል የችግሮቹን ከፍታ ያንረዋል፣ በሌላ በኩል ገፋ ያለ ምሬቱን “ኖረህ አላዳንከንም!” በሚል ቀለም ያደምቀዋል፡፡
ተንፍስ ብሎ ለሰው ልጅ ሁሉ መተንፈሻ ያደረገው? ማን ያውቃል? በተከረከሙ ስንኞች፣ በቀበጡ ዜማዎች ውበት የሰው ልጅ ጥያቄውንና የፍትህ ረሃቡን ጋብ ያደርግ እንደሆነ? በርግጥም ግጥም አስተማሪና ሰባኪ አይደለም፡፡ አዝናኝና ስሜት አሥፈንጣሪ ነው፡፡
እግረ መንገዱን ግን ከሥጋ ቆርሶ፣ ከደም ለውሶ የሚሠራው ውበት የነገን ሠማይ በተስፋ ይደግፋል። እኔም ስለ እግዜር በተፃፈች አንዲት ግጥም ሀሣቤን ብቋጭስ…
ባለ ዶሮው ጨካኙ ሰው
በዶሮው ላይ ቅርጫት ደፋ፡፡
እግዜር ደጉ
ለርሱ ዶሮች ስለ ራራ
ሰማይ ብሎ ሰፋ ያለ
ቅርጫት ሠራ፡፡
አንዳንዴ ተስፋ ስናጣ፣ ጥያቄ ሲከብበን፣ እንቅፋቱ ሲገጨን ማምለጫ የሌለን ይመሥለኛል። ያኔ ይህች ፀሐይን ያህል ውበትና ሕይወት ያቀፈ ሰማይ፣ በኛ ላይ የተደፋ ቅርጫት ያህል ይከብደናል። እግዜርስ ሰማይ ላይ ሆኖ ስንነተርከው ዝም ማለቱ  አይገርምም? እግዜር ራሱ ገጣሚ ይመሥለኛል፡፡ ምናልባት እኛ የስንኞቹ መገጣጠሚያ ቃላት!!

Read 3988 times