Saturday, 26 October 2013 13:42

በገዳይነቱ የሚታወቀው የወባ በሽታ!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(4 votes)

ከመስከረም እስከ ህዳር የወባ ወቅት ስለሆነ ጥንቃቄ አድርጉ!
በወባ በሽታ ከሚሞቱት ውስጥ 90 በመቶው አፍሪካውያን ናቸው!
በአገራችን 52 ሚ. ህዝብ የሚኖረው በወባማ አካባቢዎች ነው!

ዮናስ አብይ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የስራው ባህርይው መስክ የሚያስወጣ ስለሆነ፣ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ነው፡፡ ለስራ የሚንቀሳቀስባቸው የአገሪቱ ድንበር አካባቢዎች ቆላማ በመሆናቸው በወባ የመያዝ ዕድል ገጥሞታል፡፡ በአንድ ወቅት ለሞት አድርሳው የነበረችው የወባ በሽታው፣ በጊዜው እየተቀሰቀሰች ታሰቃየዋለች፡፡ ከአርተም በተባለው የወባ በሽታ መድሃኒት ከበሽታው እፎይታን ቢያገኝም ከበሽታው ጨርሶ ሊፈወስ ባለመቻሉ በየጊዜው መሰቃየቱ አልቀረም፡፡ “በሽታው ሊነሳብኝ ሲል ይታወቀኛል፤ ራስ ምታቱ፣ ብርድ ብርድ የማለት ስሜቱ ከፍተኛ ነው፡፡ የምግብ ፍላጐቴም ጨርሶ ይዘጋል፡፡ ከአዲስ አበባ ክልል ሳልወጣ ወባዬ ተነስታብኝ በጣም ታምሜ አውቃለሁ፡፡ በሽታው አንዴ ውስጥሽ ከገባ በየምክንያቱ እየተነሳ ያሰቃይሻል፡፡ ለስራ በምዘዋወርባቸው አካባቢዎች በበሽታው ተይዘው የሚሰቃዩትን ህፃናት ስመለከት በጣም አዝናለሁ፡፡ እኔ በዚህ አቅሜና ጥንካሬዬ ያልቻልኩትን ስቃይ እነሱ እንዴት እንደቻሉት ለማሰብ ከባድ ነው፡፡” ይላል - በሽታው ምን ያህል እንደሚያሰቃይ ሲገልጽ፡፡
ዮናስ፤ በወባ በሽታ ሳቢያ ለዓመታት መሰቃየቱንና መቸገሩንም ይናገራል፡፡ ሁልጊዜም የስጋትና የጭንቀት ህይወትን እንደሚያሳልፍ፣ በሽታው ያሳደረበት ተጽእኖም ቀላል እንዳልሆነ ይገልፃል፡፡ በአገራችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ቁጥር አንድ የሰው ልጆች ገዳይ በሽታ እንደሆነ የሚታወቀው የወባ በሽታ፤ በወረርሽኝ መልክ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ለብዙሃን ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡
በሽታው በአገር ኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ኑሮና በፖለቲካው ላይ የሚያስከትለው ቀውስ በቀላሉ የሚገመት ባለመሆኑም አገሮች ሁሉ ወባን ከአገራቸው ለማጥፋት ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዘውታል፡፡ በአገራችንም በጤናው ዘርፍ ትኩረት ከተሰጠባቸው አምስቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ቀዳሚው ወባን መከላከልና መቆጣጠር መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግስት በወባ መከላከል ላይ ፖሊሲ ነድፎ እያከናወነ ባለው ተግባር ውጤታማ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ የወባ በሽታ ስርጭቱ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማድረግ መቻሉን የጤና ጥበቃ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዓለማችን በየዓመቱ ከ250 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን ከእነዚህ የበሽታው ተጠቂዎች መካከል 10 በመቶ ያህሉ በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጣሉ። በበሽታው ህይወታቸውን ከሚያጡት ሰዎች መካከልም 90 በመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ከአፍሪካ አገራት መካከል በወባ ስርጭት የሚታወቁት አገራት ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ታንዛንያና ኬንያ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በሽታው በአብዛኛው በህፃናት፣ በአረጋዊያንና በነፍሰጡር እናቶች ላይ በይበልጥ ይታያል፡፡ ቀደም ሲል ንዳድ በሚል መጠሪያ ስም ይታወቅ የነበረው የወባ በሽታ፤ በአገራችን ከባህር ወለል በታች በ2000 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይከሰታል፡፡ ለወባ ትንኝ መራቢያነት ምቹ ከሆኑ ነገሮች መካከል የታቆረ ውሃ፣ ሙቀትና አየር ዋነኞቹ ሲሆኑ በአገራችን ያሉ 75 በመቶ ያህሉ አካባቢዎች ለወባ ትንኝ መራቢያነት ምቹ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ አስደንጋጩ እውነታ በእነዚህ ወባማ አካባቢዎች ከ52 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡
በሽታው በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ህዳር ወራት ባሉት ጊዜያት የሚሰራጭ ሲሆን በአንዳንድ የበልግ ዝናብ በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች፣ ከሚያዝያ እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያትም ይሰራጫል። በሽታው በሴቷ የወባ ትንኝ ንክሻ አማካኝነት እንደሚተላለፍ የሚታወቅ ሲሆን የበሽታው ምልክት የሚታየው ይህችው የወባ አማጭ ተህዋሲያንን የተሸከመችው ትንኝ ከተናከሰች ከ7ኛው ቀን እስከ አስራ አራተኛው ቀን ድረስ ነው፡፡ የበሽታው ምልክቶችም ከፍተኛ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ የማለት ስሜትና ማስመለስ እንዲሁም የምግብ ፍላጐት ማጣት ናቸው፡፡ የበሽታው አምጪ ተህዋሲያን በተለያዩ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች ሊሸፈኑና ህመምተኛው በሽታው ሳይታወቅለት ለቀናት ሊያሰቃይ ይችላል፡፡
በአገራችን የወጣ በሽታን ከሚያሰራጩት ተህዋሲያን መካከል ፕላስሞዲየም ፋልስፋርሞና ፓላስቲሞዲየም ቫይቫክስ የተባሉ ዋነኞቹ ሲሆኑ ለተዋህሲያኑ መራባት እጅግ አመቺ የሆኑት ወቅቶች የክረምቱ ወራት ተጠናቆ የበጋው ወራት የሚጀምርባቸው ከመስከረም እስከ ህዳር ያሉት ጊዜያት ናቸው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዲዲቲ የወባ በሽታን ለመከላከል በመላው አገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ ይውል ነበር፡፡ የዚህ መድሃኒት ፍቱንነት እየተዳከመ በመምጣቱ ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዚህ መድሃኒት በተሻለ የወባ ትንኞች ለመግደል ይረዳል የተባለውና ዴላሜትሪን በሚል መጠሪያ የሚታወቀው መድሃኒት በጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በወባማ የአገሪቱ አካባቢዎች በፀረ ወባ ትንኝ መድሃኒት ርጭት ባለሙያዎች አማካኝነት በተለይ በወባማ ጊዜያት የመድሃኒት ስርጭቱ የሚከናወን ሲሆን ህብረተሰቡም ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮችን እንዲጠቀም የማስተማሩና አቅርቦቱን የማስፋፋቱ እንዲሁም ውሃ ያቆሩ አካባቢዎች የማደራረቁና የማጥፋቱ ተግባር በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡
መንግስት በጤናው ዘርፍ በምዕተ ዓመቱ አሳካቸዋለሁ ብሎ ከተነሳባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር ውጤታማ እየሆነ መምጣቱንና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የወባ ስርጭት እየቀነሰ መሆኑን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይሁን እንጂ የአለም ጤና ድርጅት በበኩሉ፤ አገሪቱ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቂ ጥረት አለማድረጓንና አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በወባ በሽታ እየተያዙ እንደሚሞቱ ጠቁሟል፡፡
የዓለም ሙቀት መጨመርና አካባቢያዊ ለውጡ የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉን የገለፀው የዓለም ጤና ድርጅት፤ ቀደም ሲል በሽታው ታይቶባቸው በማያውቁ አካባቢዎች ሳይቀር በሽታው መታየቱንና በአንዳንድ ወባ የጠፋባቸው ቦታዎችም ተመልሶ እየተከሰተ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በቅርቡ ባወጣው መረጃ፤ በአገሪቱ በየዓመቱ በወባ የተያዙ 3ሚ.149ሺ 741 በሽተኞች እንደሚመዘገቡ አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ወባማ ባልሆኑ አካባቢዎችም የወባ ስርጭቱ እየተስፋፋ መሆኑን የጠቆመው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤት የተደረገ ጥናት፤ ለዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መስፋፋት፣ ሰፈራ፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ፍልሰትና የአካባቢ መራቆት ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሷል። በቆቃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ በተካሄደ ጥናትም፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በግድቡ ዙሪያ የሚኖሩ ከ19 ሺህ 350 በላይ አርሶ አደሮች የወባ ተጠቂ እንደሆኑ መገለፁን ጠቁሟል-የጤና አጠባበቅ ትምህርት ቤቱ ጥናት፡፡

Read 7321 times